Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርሳይቃጠል በቅጠል

ሳይቃጠል በቅጠል

ቀን:

በተለያየ ጊዜ በውጭ አገር ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ የአሠራር ፍልስፍናዎችን ወይም ዘዴዎችን መንግሥት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞክር መቆየቱ ታወቃል፡፡

በዚህም መሠረት በርካቶቹ ከፈጣሪዎቹ አገሮች ቀጥታ እየተገለበጡ፣ ነገር ግን ከሙያው ጋር ግንኙነት በሌላቸው ግለሰቦች በምደባና በሹመት ሠራተኛው ላይ እንደ መርግ በሚጫኑበት አመራሮች በኩል ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከርና ያልተሠራው ተሠራ፣ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው፣ ወዘተ እየተባለ የውሸት ሪፖርት ከበላይ አካላት ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ይኼም ሄዶ ሄዶ አገሪቱንና ሕዝቡን አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት ስንት ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ የባከነበት ጉዳይ እንደ ዘበት ተድበስብሶ ይቀራል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጃፓን፣ እንዲሁም በተለያዩ የእስያ አገሮች ታላቅ አገራዊ ለውጥ (በተለይ በማምረቻው ኢንዱትሪ ዘርፍ) ያስገኘውን የካይዘን ፍልስፍና ነው፡፡ ፍልስፍናውን ወደ አገራችን አምጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፣ ይህ በመንግሥትም ይሁን በጃፓን መንግሥት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የአሠራር ፍልስፍና የታለመለትን ግብ ሳይመታ መና ሆኖ እንዳይቀር የሚመለከተው አካል ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ነጥቦች ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ፍልስፍናውን በዋናነት እንዲያስተገብር ኃላፊነት በወሰደው የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት በአመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች በሹመት፣ እንዲሁም በምደባ (የሥራ ዘመናቸውን በጨረሱ የሕዝብ ተወካዮች አባላትን በመመደብ) ምንም ዓይነት ከፍልስፍናው ጋር ተዛማጅነት የሌለው ትምህርት የተማሩ ግለሰቦችን ኃላፊነት ላይ ማስቀመጡ ያላዋቂ ሳሚ እንደሚባለው እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ፡፡

የኢንስቲትዩቱ የአደረጃጀት መዋቅር ሲቀረፅ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በዘፈቀደና እርስ በርስ ለመጠቃቀም ተብሎ 160 ሠራተኛ ላሉት ተቋም አምስት ምክትል ሥራ አስኪያጅና 28 ዳይሬክተሮች እንዲኖሩት በማድረግ በአገር ልጅና በድርጅት አባልነት በመፈላለግ ያለምንም ይሉኝታ የእርስ በርስ መጠቃቀሚያ ተቋም መሆኑ ይታረም፡፡

እስካሁን ፍልስፍናውን እንዲተገብሩ ታግዘዋል የተባሉት የማምረቻ፣ የአገልግሎት ሰጪና የትምህርት ተቋማት ውስጥ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩትን ለሚዲያ ፍጆታ ከማዋል በዘለለ ስንት ተቋማት በክትትልና ድጋፍ ማጣት ወደነበሩበት እንደተመለሱ በውስጡ ያለን ባለሙያዎች የምናውቀው ሀቅ በመሆኑ ይህም ይፈተሽ፡፡

በኢንስቲትዩቱ ውስጥ እየታየ ያለውና ከዘመኑ ጋር የማይሄደው የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት፣ ገንቢ አስተያየቶችን በግልጽነት የሚሰጡ ሠራተኞችን በቂም በቀል ጠብቆ የማጥቃትና የማሸማቀቅ አሠራር ለማንም የማይበጅ መሆኑ ታውቆ ቢታረም፡፡

በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ከዚህ በፊት የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ያሉ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢፈተሹ፡፡ ለምሳሌ ያህል መመርያን ያልተከተሉ ግዥዎች በተለይም በሕንፃ ኪራይ፣ በተሽከርካሪዎች ጥገናና በመሳሰሉት ላይ እየተሠራ ያለውን ነገር የሚመለከተው አካል ቢያየው ለአገርም ለሕዝብም ጠቃሚ ነው፡፡  

የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴዎችን በአዋጁ መሠረት የሥራ ዘመናቸውን ሳያጠናቅቁ እስከማፍረስና በሌላ እስከመተካት የተደረሰበት አሠራር ለምን ሲባል እንደተፈጸመ ቢታይ፣ ብዙውን ጊዜ በኮሚቴ የሚሠሩ ሥራዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ ሳይወጡ መስክ የወጡ በማስመሰል ውሎ አበል መክፈል፣ ለምሳሌ የJEG ኮሚቴ እዚሁ አዲስ አበባ ኢትዮ ቻይና ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሥራውን ከሠራ በኋላ ቢሾፍቱ እንደሄደ ተደርጎ ለኮሚቴው አባላት የውሎ አበል መክፈሉ፣ ምንም እንኳ አንድ የኮሚቴው አባል አበል ለመውሰድ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀርም እንዲሁ ያሉትን አሠራሮች መንግሥት ይመርምራቸው፡፡

በካይዘን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርትን በአገር ውስጥ ለማስተማር ለአንድ ተማሪ ከ110 ሺሕ ብር በላይ ከፍሎ ለማሠልጠን ውል መዋዋሉ ተገቢነቱ ቢፈተሽ እሰየሁ ነው፡፡ በቅርቡ በኢንስቲትዩቱ ፖለቲካዊ አመለካከትንና የወንዜ ልጅነት ባማከለ መልኩ ተግባራዊ የተደረገው የሠራተኞች ድልድል ለተቋሙ ሕልውና ስለማይበጅ ፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስትር ጣልቃ ገብቶ ቢፈትሸው ለለውጥ የሚበጅ ዕርምጃ ይሆናል፡፡

ከላይ የተገለጹትን ዋና ዋና ችግሮች፣ እንዲሁም ያልተገለጹትን ሌሎች አሳሳቢ ችግሮች ግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴርና የሕዝብ ተወካዩቹ ምክር ቤት የተጋነነ ሪፖርት ተቀብለው እዚህ ግባ የማይባል ግብረ መልስ በመስጠት ከመሸነጋገል ይልቅ ይህን ለብዙ የታለመ ኢንስቲትዩት ከውድቀት በማዳን በአገር ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ለማስቀረት ጥረት ለሁሉም ይበጃል እንላለን፡፡

(ከኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች መካከል)

* * *

ለሰነድ አልባ ቤቶች ጉዳይ የመጨረሻው መፍትሔ ይተግበር

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል የሰነድ አልባ ፕሮጀክት ዴስክ በማቋቋም ዕልባት እንዲሰጥበት የተደረገውን ጥረት አደንቃለሁ፡፡

ሆኖም ግን እንደተፈለገው በተባለለት ጊዜ ሥራው እንዳላላቀ የሚታወቅ ነው፡፡ በሚዲያ እንደተገለጸውም፣ ካርታ ተሠርቶ እንዲወስዱ ከተደረጉት ውስጥ አብዛኞቹ እንዳልወሰዱ ታውቋል፡፡ በእኔ ግንዛቤ ዋና ዋና የምላቸው ሦስት ችግሮች በአስተዳደራዊ ውሳኔ ባለመፈታታቸው የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡

  1. የሰነድ አልባ ይዞታ ያለው ብዙኃኑ ሕዝብ መሬቱን ሲገዛ መሀል ከተማ ለመኖር ባለመቻሉና ሕጋዊ ቦታንም ለመግዛት አቅሙ ስለማይፈቅድ በተመጣጣኝ ዋጋ ሰነድ አልባ ቦታዎችን እንዲገዛ ተገዷል፡፡ ስለሆነም አሁን ወደ ሕጋዊ ለማምጣት መስተዳድሩ በፈቀደው ለመስተናገድ ቢፈልግም ለቦታው የሚሰጠው የሊዝ ዋጋ አቅሙን ያላገናዘበ በመሆኑ ሊከፍል ስላልቻለ ካርታውን መውሰድ አቅቶታል፡፡
  2. የሰነድ አልባውን ቦታ ሲገዛ የነበረው የመሬት ልኬትና አሁን በተሻሻለው የመንገድ ጥናት አንዳንድ ቦታዎችን ስለሚያጠብ ባለንብረቱ ለክቶ የያዘው ቦታና መስተዳድሩ ይገባሃል የሚለው ቦታ ባለመመጣጠኑ የተሻሻለውን የመንገድ ጥናት ግንዛቤ ባለመውሰዱ የተፈጠረ ክፍተት ስላለ የተሠራውን ካርታ ላለመውሰድ ተገዷል፡፡
  3. ይህን መልዕክት እንድጽፍና የመንግሥት ያለህ እንድል ያደረገኝ ዋናው ጉዳይ በተመሳሳይ ጊዜና ቀን ተመሳሳይ ቤት ከጓደኛዬ ጋር ስፋቱ 480 ሜትር ካሬ የሆነ ቦታ ገዝተን በተሰጠን ዕድል ለመጠቀም የሰነድ አልባ ፕሮጀክት ዴስክ መረጃችንን አስገብተን፣ ረዥም ጊዜ ጠብቀን፣ ልንስተናገድ ስንቀርብ የእሱ ሙሉው 480 ሜትር ካሬው ካርታ ተሠርቶለት ውሰድ ሲባል፣ የእኔ ግን ለሁለት ተቆርጦ ከሁለት አንዱን የመረጥከውን ውሰድ የሚል ጥያቄ ቀርቦልኛል፡፡

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ከጓደኛዬ ጋር በተመሳሳይ ቀንና ዓመተ ምሕረት ገዝተን እሱ ሙሉ ካርታ ተሠርቶለት እኔ እንዴት ቦታው ለሁለት ተከፍሎ የመረጥከውን አንዱን ውሰድ እባላለሁ የሚል ጥያቄ ሳነሳ የተሰጠኝ መልስ አንተ የተወሰነው ቦታ ላይ ቤት ስላልሠራህ መልማት የሚችል ቦታ ስለሆነ ለሌላ ሰው ይተላለፋል የሚል መልስ ተሰጠኝ፡፡

እኔ ቦታው ላይ ከነበረኝ ቤት ተጨማሪ መሥራት ያልቻልኩት ጭቃ ቤት መሥራት አቅቶኝ ሳይሆን ሕጉን በማክበርና ምንም ዓይነት ግንባታ ያለ ግንባታ ፈቃድ እንደማይሠራ ጠንቅቄ ስለማውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕግን ማክበር እንደ ስንፍና ተቆጥሮ በአንድ መመርያ የተፈቀደልንን መሬት ለጓደኛዬ ተፈቅዶ ለእኔ መከልከሉ ሥጋ ሰጥቶ ቢላዋ እንደመከልከል ነውና፡፡

የተከበራችሁ የመስተዳድራችን ኃላፊዎች ይህ ችግር የእኔ ብቻ ሳይሆን በከተማችን ያሉ ሰነድ አልባ ይዞታ ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ችግር ስለሆነ፣ የያዝነው ቦታ በመመርያው መሠረት ካርታ የሚያሰጠን ነውና የክፍለ ከተማ አመራሮችን በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡን እንድታደርጉልንና ለመንግሥትም መክፈል ያለብንን የሊዝ ክፍያ እንድንከፍል በድጋሚ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንድትሰጡን ከአደራ ጭምር እንጠይቃለን፡፡

(ከእስከዛው ቻላቸው፣ ከላፍቶ ክፍለ ከተማ)

* * *

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...