በውብሸት ሙላት
ሰሞኑን የሕዝብ አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል በማረፊያና በማረሚያ ቤቶች ሲፈጸም የነበረው ዘግናኝና ሰቅጣጭ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አንድኛው ነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን)፣ በአማራ ቴሌቪዥንና በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የቀረበውን ወይም የተላለፈውን መጥቀስ ይችላል፡፡
‹‹የሒውማን ራይትስ ወች› ዘገባ ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳይቷል፡፡ እነዚህ ያው በሰፋት ለሕዝብ በመድረሳቸውና በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በመቅረባቸው እንጂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን በሚመለከት በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ የተወሰኑ መጻሕፍትም ታትመው ለሕዝብ ቀርበዋል፡፡ መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በተለይ በሸዋሮቢትና በቂሊንጦ ታስረው ስለነበሩ ሰዎች በተወሰነ መልኩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመ ሪፖርት ማድረጉ ይታወቃል፡፡
መንግሥትም ማዕከላዊ የተባለውን ማረፊያም ማሰቃያም የነበረውን ቤት ዘግቷል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ጊዜያት የተሰወሩና አድራሻቸው የማይታወቅ ሰዎች መኖራቸውን ስማቸውን፣ ከየትና መቼ እንደተሰወሩ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተዘገበ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ በተወሰነ መልኩ የጥላቻ ወንጀሎች አንድምታ እንዳላቸውም የጉዳቱ ሰለባዎች ሲናገሩ ተስተውሏል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤት ኃላፊዎችንም ከኃላፊነት ቦታቸው በማንሳት የወንጀል ምርመራ ሊያደርግ እንደሚችል የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ቃል ገብተዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እንዲሁም የሰብዓዊ ክብር ውርደቱ በእስረኞች ላይ ብቻ ሳይገደብ ብሔርን መሠረት አድርጎ ከተለያዩ ክልሎች በማፈናቀል በመፈጸም ላይ ነው፡፡ በተለይ የማፈናቀል ድርጊቱ አሁንም ቢሆን እንዳልቆመ ይታወቃል፡፡ ምናልባት ልዩነቱ የሚፈናቀሉበት አካባቢ፣ የተፈናቃዩ ብዛትና የሚፈናቀለው ብሔር መለያየታቸው ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት የሰብዓዊ ክብረ ነክና አዋራጅ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ለመከላከል እንዲሁም ፈጽመው ሲገኙም በፈጻሚዎቹ ላይ የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ያስችል ዘንድ እስካሁን ያለውን የወንጀል ፍትሕ ተቋም አወቃቀሩን ማሻሻል፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከርና ሚዲያዎችንም ወደ ኋላ እንዳይመለሱ የሚደግፍ አሠራር መዘርጋትና ተጨማሪ ሕግጋትን ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው፣ መሻሻል ካለባቸው የፍትሕ ተቋማት መካከል አወቃቀራቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ነው፡፡ የተቋማቱ መሻሻል የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን የመከላከል ሒደቱ ቋሚነትና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ስለሚያግዝ ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ታራሚዎች፣ ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች የሚሉትን አጠራር መጠቀም ያልተመረጠው ከተያዙበት ጊዜ ጀምረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው ከሆነ ሕገ መንግሥታዊ በሆነው አሠራር ስላልተያዙ፣ ይልቁንም ኢሕገ መንግሥታዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸውን ከሌሎች እንዲህ ዓይነት ጥሰት ከማይፈጸምባቸው ለመለየት ነው፡፡
ስለ ፖለስ አወቃቀር
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተገለጸውና ከፖሊሳዊ ተግባር አንፃር ብቻ ስናየው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው በምርመራ ወቅት ነው፡፡ በእርግጥ እስረኞች በሚያዙበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈጸምም የከፋው ጥሰት የሚፈጸመው ግን በምርመራ ወቅት ነው፡፡ የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ የሚከናወነው በአንድ ተቋም ነው፡፡ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ተግባርን ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች በተለያዩ ተቋማት ሥር መተዳደር የተሻለ ነው፡፡
የመጀመርያው ምክንያት ውጤታማና ፍትሐዊ የሆነ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ለማስፈን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ለወንጀል መከላከልና ምርመራ የሚያስፈልገው ዕውቀትም ሥልጠናም የተለያየ ነው፡፡ ትምህርቱም ሆነ ቴክኖሎጂው እንዲሁ ይለያያል፡፡ በተለይ ለወንጀል ምርመራ የሚሠለጥኑ ሰዎች የወንጀል አደራረጉንና ረቂቅነቱን ከፈጻሚዎቹ በበለጠ ሊረዱ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ለመርማሪ ፖሊስነት የሚመለመሉ ዕጩዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በመሆኑም ለመርማሪነት የሚመለመሉ ፖሊሶች/ባለሙያዎች በተለያየ የትምህርት መስኮች የሠለጠኑ ወይም ደግሞ ዕውቀት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወንጀል መርማሪ ከወንጀል አድራጊ የበለጠ ዕውቀት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ይህን ለማድረግ ለወንጀል ተከላካይነትና መርማሪነት ለመመልመል መሥፈርቱ የተለያየ ነው የሚሆነው፡፡
በኢትዮጵያ፣ በፌዴራልም ይሁን በክልሎች የወንጀል መከላከልም ሆነ ምርመራ ተቋማት የሚመሩት በአንድ መሥሪያ ቤት ሥር ነው፡፡ የክልሎቹም በክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራሉም እንዲሁ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፡፡ መርማሪ የሚሆኑት ፖሊሶችን በተለያዩ ጊዜያት የምርመራ ሳይንስና ጥበብ ቢማሩም፣ የሚመረመረውን ጉዳይ (ለምሳሌ ፋይናንስ፣ ኮምፒውተር፣ ቴሌኮም፣ ሕክምና. . . ወዘተ.) ዕውቀት ሳይኖራቸው ብቁና የተዋጣላቸው መርማሪዎች የመሆናቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ በተለያዩ ተቋማት ሥር ይመሩ ዘንድ አንድኛው ምክንያት ይህ ሁኔታ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የወንጀል መከላከልና ምርመራውን በአንድ መሥሪያ ቤት ሥር ማዋቀር ከዚህም የከፋ ችግር ያለው መሆኑ ነው፡፡ በወንጀል መከላከል ጊዜም ሆነ ተጠርጣሪን ለመያዝ በሚደረግ ጥረት ፖሊስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊፈጽም ይችላል፡፡ በአንድ የፖሊስ ጣቢያ የወሰን ክልል ውስጥ ፖሊስ ለሚፈጽመው የወንጀል መተላለፍ ድርጊት ምርመራውን እንዲያከናውን የሚጠበቀው የዚያው ጣቢያ የፖሊስ ባልደረባ ነው፡፡
አንድ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችን አንዱን አንዱ እንዲመረምር የሚያደርግ ተቋማዊ አወቃቀር ውጤታማቱም ፍትሐዊነቱም አጠያያቂ ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ እስካሁን ሲፈጸሙ የነበሩት የእስረኞች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዋቢ ነው፡፡ አንድ በወንጀል መከላከል ላይ የተሰማራ ፖሊስ ለምርመራ የሚያስረክበውን ተጠርጣሪ የጤንነትና የአካላዊ ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመያዝና መቼ ማን ምን እንዳደረገ ለማስረዳትም እንዲያግዝ ሆኖ የተዋቀረ ነው፡፡ ሁለቱ ተቋማት ቢለያዩ ብሎም ተቋማዊ የሆነ ርክክብ የሚደረግበት ሥርዓት ቢኖር የተጠርጣዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለማሻሻል ይረዳል፡፡ የወንጀል ምርመራን በበላይነት የሚመራው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት በመሆኑ የወንጀል ምርመራ ተቋምንም እንደ አዲስ በማደራጀት በጠቅላይ ዓቃቤ መሥሪያ ቤት ሥር እንዲዋቀር ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡
የወንጀል መከላከልን ደግሞ ምናልባት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን ከእንደገና በማዋቀር (ምናልባትም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በማድረግ) ወይም ደግሞ በክልሎች እንደሚደረገው የአስተዳደርና ፀጥታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በማቋቋም ተጠሪነቱን ለእዚህ መሥሪያ ቤት ማድረግ ነው፡፡ በወንጀል መከላከል ጊዜ በፖሊስ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ለማጣራት አንድ ተቋም በራሱ ሠራተኞች ላይ በሌላ የራሱ ሠራተኛ አማካይነት ገለልተኛ የምርመራ ሥራ ላለማድረግ እንቅፋት ይሆናል፡፡ የምርመራ ተቋሙም ሕዝባዊ ተዓማኒነትም እንዳይኖረው መሰናክል ይሆናል፡፡ ስለሆነም በእነዚህና ሌሎች ተደራቢ ምክንያች እነዚህ ሁለት የፖሊስ ተግባራት በተለያዩ ተቋማት ሥር ቢደራጁ የተሻለ ነው፡፡
የፖሊስ ምልመላን በሚመለከት
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሲነሱ የክልሉ የፖሊስ ኃይል ቀድሞ ሲያደርጉት ከነበረው ፖሊስ ድርጊት በተሻለ ሁኔታ ሕዝባዊና ሰብዓዊ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ የፖሊስ አባላት የአካባቢው/የየክልሉ ተወላጆች መሆናቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የአካባቢውን ተወላጅ ለፖሊስነት መመልመል ተጠያቂነትም ለማስፈን የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ ማን ማንን ምን እንዳደረገ ለማወቅ ይቀላል፡፡ ውጤታማ የወንጀል መከለካል ሥራም የሚፈጸመው አካባቢውን ሁኔታ በጥልቀት የሚያውቅ ሰው ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚደረገው የፖሊስ ምልመላ ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡
እንደሚታወቀው ለአዲስ አበባ የፖሊስ አባል ለመሆን የቅጥር ማስታወቂያ የሚወጣውና ምልመላውም የሚከናወነው ከየክልሎቹ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ለመቅጠር የመዝገባ ቦታው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች ይከናወናል፡፡ በአንድ በኩል የከተማው ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን እያለው፣ በጀቱንም ከተማ መስተዳድሩ የመሸፈን ግዴታ እንዳለበት እየታወቀ፣ ራሱን ለሚጠብቀው ፖሊስ ከሌላ ክልል መቅጠሩ ሕገ መንግሥታዊነት ይጎለዋል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥታዊውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጥስ ስለሆነ፡፡ ከዚህ ባለፈ በሌሎች ክልሎች እየተለወጠ እንደመጣው ፖሊሳዊ አሠራር ኢሰብዓዊነትን በመቀነስ ሕዝባዊ ተዓማኒነትን ያሳድጋል፡፡
የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ ተቋም እንደ ወንጀል መርማሪ
የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም የሚደራጀው በፌዴራል መንግሥት ብቻ ነው፡፡ በተቋቋመበት አዋጅ ላይ እንደተገለጸው አንድ እንጂ ከዚያ ውጭ ሌላ የደኅንነት ተቋም እንደማይኖር ተደንግጓል፡፡ ይህ ተቋም በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃም አደረጃጀት አለው፡፡ ከእነዚህ አደረጃጀቶች በተጨማሪ ግን በዚሁ መሥሪያ ቤት ሥር የሚገኙ የዜግነትና ኢሚግሬሽን ጉዳዮችን የሚያከናውኑ ቅርንጫፎች በተለያዩ ቦታዎች አሉ፡፡
ሰሞኑን ከሰማናቸው ስለ ስብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተለይ በአማራ ክልል የቴሌቪዥን ጣባያ እንደተላለፈው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ሠራተኞችም ሰዎችን በመያዝ በአንዳንድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤታቸውና በአዲስ አበባም ጭምር በሚገኙ ለሕዝብ ይፋ ባልሆኑ ቤቶች በመውሰድ የተለያዩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ ሠራተኞች አገሪቱን ከተለያዩ የፀጥታ ሥጋቶች ለመከላከል የደኅንነትና መረጃ የማሰባሰብ ብሎም የመተንተን ተግባር ማከናወን አለባቸው፡፡ በሚያገኙት መረጃ ተመርኩዘው በወንጀል የሚጠረጠርን ሰው በፖሊስ ማስያዝ ተቀዳሚው ምርጫ ነው፡፡ የመያዝ ሥልጣን የሚሰጣቸውን ሕግ በመጠቀም ተጠርጣሪን ሲይዙ የሚጠረጠረው ሰው ማረፍ ያለበት በታወቁ የማረፊያ ቤቶች መሆን ሲገባው ከሕዝብ በተደበቁ ሥውር ቤቶች ሰውሮ ምርመራ ማድረግ፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን (ለምሳሌ በአማራ ቲቪ እንደተሠራጨው ባህር ዳር የሚገኘው የዜግነትና ኢሚግሬሽን ጽሕፈት ቤት) የምርመራና የማረፊያ ቦታ ማድረግን የሚከለክል አሠራር መስፈን አለበት፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ምርመራ ተቋምንና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነትን መሥሪያ ቤትን ወንጀል ምርመራን በሚመለከት ሁለተኛው ተቋም ማድረግ የሌለበትንና ያላቸውን ግንኙነት ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡
አፈናቃዮችን ለመዳኘትና ለፍትሕ ተቋም ለማቅረብ
የመፈናቀል ጉዳይ አሁንም ቢሆን ሊቆም አልቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የጌደዮ ተወላጅ ተፈናቃዮችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ከዚያ በፊት የነበረውን የማፈናቀል ድርጊቶች ተፈጽመው ነገር ግን አፈናቃዮች ወደ ፍትሕ አደባባይ ሲቀርቡ አይስተዋልም፡፡ ቀረቡም ከተባለ የተወሰኑ ብቻ ናቸው፡፡ ማፈናቀልን ለመቀነስ አንድኛው መፍትሔ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ውስጥ በማድረግም ይሁን በዝምታ የተሳተፉ ሰዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ ከሕጋዊ ዕርምጃዎቹ አንዱ ደግሞ በወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው የፍትሕ ተቋማት አደረጃጀት ይህንን ሁኔታ በገለልተኝነት ውጤታማ የሆነ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድ የተቋማቶቹን አወቃቀር ዳግም መጤን ያስፈልጋል፡፡ የዳግም ፍተሸውን አስፈላጊነት በሚመለከት ጉዳዩን በምሳሌ እንመለከተው፡፡
እንደግዲህ የማፈናቀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ክልል (ወረዳና ዞንን ጨምሮ) ያለው ፖሲስ እነዚህን የማፈናቀል ወንጀሎች ያለአድልኦ የመመርመር፣ ዓቃቤ ሕግም በገለልተኝነት ክሱን የመምራት ፍርድ ቤቶችም እንዲሁ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ በራሱ ፈተናው ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሀ›› የተባለው ብሔር አባላት በኢትዮጵያዊነታቸው ሌላ ቦታ በመሄድ ‹‹ለ›› የተባለ ብሔር በሚያስተዳድረው ወረዳ ወይም ዞን ወይንም ክልል ውስጥ ሲኖሩ ከማፈናቀል ጋር ወንጀል ቢፈጸም፤ ከሳሽ የ‹‹ሀ›› ብሔር አባላት ተከሳሽ ደግሞ የ‹‹ለ›› ብሔር አባላት የሆኑ በዋናነት ሹመኞች ሊሆኑ ነው፡፡ በዚህ የክስ ሒደት ውስጥ የሚሳተፉት ፖሊሱም፣ ዓቃቤ ሕጉም፣ ዳኛውም የተከሳሹ፣ የ‹‹ለ›› ብሔር አባላት፣ በመሆናቸው ዕድል ከፍተኛ ስለሆነገለልተኝነታቸው አጠያያቂ ነው የሚሆነው፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹን ወንጀሎችም ይሁን የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ከክልል የዳኝነት ሥልጣን ወጥተው ለፌዴራል ቢሰጡና ምርመራውንም የፌዴራል ፖሊስ፣ ከሳሽም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቱም እንዲሁ የፌዴራሉ ቢሆን ለገለልተኝነቱ የተሻለ ይሆናል፡፡ የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና የሚያዩ ክልሎች እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሲጋጥሟቸው ራሱ የፌዴራሉ ፍርድ ቤት በራሱ ዳኞች ነገር ግን የአቤቱታ አቅራቢም ሆነ ክሱ በቀረበበት ብሔር (ክልል) አባላት ውጭ ያሉ ዳኞች ሊያዩት ይገባል፡፡ መርማሪ ፖሊሶችና ዓቃቤ ሕጎችም እንዲሁ፡፡ ይኼን ዓይነቱን አሠራር የሚያፀና ሕግ በማውጣት በማፈናቀል የሚፈጸምን የሰብዓዊ መብት መጣስን እንዲቀንስ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
በብዙ መገናኛ ብዙኃን እንደተላለፈው አንደኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው በአዲስ አበባ መስተዳድር ሥር የሚገኙ የተወሰኑ እስር ቤቶች/ፖሊስ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡