Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበለውጥ ዋዜማና ማግሥት ለምን አመፅ ይከሰታል?

በለውጥ ዋዜማና ማግሥት ለምን አመፅ ይከሰታል?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በሦስተኛው ዓለም ወይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ተብለው በሚጠሩ ግዛቶች አንድ ጨቋኝ ሥርዓትን በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ መሸከም ሲያቅታቸው፣ በየፊናቸው አሽቀንጥረው ለመጣል ይፈልጋሉ፡፡ በአስተዳደር ሥርዓታቸው ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ስለማይኖር ሰብዓዊ መብታቸውንና ፍላጎታቸው በልዩ ልዩ የአመፅና የነውጥ መንገዶች ለማስከበር ይፈልጋሉ፡፡ አመፁ ወይም ግጭቱ የተከሰተበትን ምክንያትና ያስከተለው ጥፋት ማወቅና ማሳወቅ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ግጭት ለመቀነስ ምን ያህል ይረዳል? አንዱ ግጭት ከሌላው ጋር የሚገጣጠመውና የሚያያዘው እንዴት ነው? የትኛው ነው ትልቁና የሁከት ነቀርሳ ሆኖ የነበረው? አሁንስ በክልል አጎራባቾች ውስጥ ተዳፍኖ የሚኖር የጠብ ምክንያት አለ ወይ? ከኖረ ቅደምከተል ተሰጥቶ መጠናት ያለበት ጉዳይ ምንድነው? ችግሩስ በክልልና በፌዴሬሽን ደረጃ እንደምን ይታያል? ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ፋይዳ አለው? ሌሎችስ ከዚህ ምን ሊማሩ ይችላሉ? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ሰፋ አድርጎ መተንተን ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው በዚህ ጽሑፍ ስለሁከት መንስዔ፣ ውጤትና መፍትሔ ከቀረበ በኋላ የሁኔታውን መጥፎነት በምሳሌ ለማየት እንዲረዳም ከ1983 እስከ 1984 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ የተከሰተውን ችግር በአብነት ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ምን ማድረግ እንደሚገባው አስተያየት ለመሰንዘር ይሞከራል፡፡

የግጭት መንስዔውና ውጤቱ በአጭሩ

ጸሐፊው ይኼንን ጽሑፍ ዛሬ ለንባብ ከማቅረቡ ስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት ስለግጭትና መንስዔው መጠነኛ የዳሰሳ ጥናት አድርጎ ነበር፡፡ ስለሆነም በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌና በትግራይ ክልሎች አንዳንድ ሽማግሌዎችን አነጋግሯል፡፡ ያነጋገራቸው  የአገር ሽማግሌዎች በቀላሉ እንደሚገልጹት የፖለቲካ ግጭት ሁሉም ባለሥልጣን ለመሆን ከመፈለግ፣ ማ ከማን ያንሳል የሚል፣ ወይም ባለሥልጣኑ የማይረባ፣ ጨቋኝ፣ ዝሙተኛ፣ አድሏዊ፣ ደካማ ወይም እኔ ልሰማ ባይ መሆን ከምክንያቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሥልጣን ኮርቻ ከወጡ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሰላምና መረጋጋትን ይፈጥሩና ከጥቂት ጊዜ በኋላ አስተዳደራቸው ደካማ  ሲሆን ዓለማቸውን እየቀጩ መኖር እንጂ ለሕዝብ ደንታ ቢስ ይሆኑና  በአንድ ወይም በሌላ አመፅ ይነሳል፡፡ አመፁም ግጭትን ያስከትላል፡፡ የግጭት ዋነኛ መገለጫ ባህርይ መገዳደልና መዘራረፍ ስለሆነ፣ በግጭቱ መፈጠር ወይም ለግጭቱ መቀጠል አስተዋፅኦ የሌለው ሕዝብ በማይመለከተው ጉዳይ ሀብቱና ንብረቱ ብሎም ሕይወቱ የሚጠፋበት ስለሆነ ፍርኃት ይነግሣል፡፡ ፍርኃት ሲነግሥም ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሄዱ ይገደዳሉ፡፡ ፍርኃቱም በብሔረሰቡ ተወስኖ የሚቀር ወይም ድንበር ተሻግሮ የሚሄድ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መሬት ተመሳሳይ የሆነ አቀማመጥና ተመሳሳይ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት በአንድ ቦታ የላትም፡፡ ስለሆነም የአንዱ አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ከሌላው አካባቢ  የተፈጥሮ ሀብት ልቆ በሚገኝበት ጊዜ ያንን የተፈጥሮ ሀብት አስገድዶ ለመንጠቅ፣ የረዥም ጊዜ ጦርነት ሰፍኖ እንደቆየ የአገር ሽማግሌዎቹ ያስታውሳሉ፡፡ ሁሉም የመሬት ባለቤት ወይም የሰፊ መሬት ባለቤት መሆን ስለሚሻ የእኔ ነው ብሎ በሚያስበው የግጦሽ መሬት ሌሎች ከብቶቻቸውን ስላስገቡ ብቻ ሳይሆን፣ ለምን በዚያ መንገድ አሳለፉ ብሎ የሚያስነሳው ጠብ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ይጀመርና አንዱ ሌላውን ቢገድል ደም ለመመለስ ሲባል ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል፡፡ በዝርፊያ ወይም በሌብነት የተጀመረ ጦርነት የጎሳና የብሔር ጦርነት ሊሆን ይችላል፡፡ በዘራፊና በተዘራፊ የሚደረገው ጦርነት አንድም ለአጭር ጊዜ ወይም እንደ ሁኔታው ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሊሆን ይችላል፡፡ የዘራፊዎቹና የተዘራፊዎቹ አቅም ይወስነዋል፡፡ ወይም ታፍኖ ለነበረው ቂም መፈንዳት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ተቀራራቢነት ያላቸው ጎሳዎች በጋብቻ፣ ወይም በአንድ የጋራ ዓላማ ላይ በመመሥረት መቀራረብ ብሎም መዋሀድ ይችላሉ፡፡ ጎሳዎች የቤተሰብ ስብስቦች በመሆናቸው በድምር ጎሳውንና በተናጠልም እያንዳንዱን የቤተሰብ ማንነት ለማወቅ ታሪኩን፣ ጥንካሬውን፣ ድክመቱንና ችግሩን ለማወቅ ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡ ታዲያ ይህ በአገራችን ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የተከሰተ ነው፡፡ ለአውሮፓ አኅጉር መበጣጠስ አስተዋፅኦ ያደረገው የብሔር ብሔረሰብ ግጭት ጭምር ነበር፡፡ የአዶልፍ ሒትለር አመለካከት በአርያን ዘሮች የበላይነት ላይ የሚያጠነጥን ነበር፡፡ እስያውያንም ህንድ ከመንጎሉ፣ መንጎሉ ከቻይናው፣ ቻይናው ከጃፓኑ ጋር የሚያጋጨው የበላይነት ፍለጋን የሚያንፀባርቅ ማኅበራዊ ግጭት አለበት፡፡ ከተወለዱበት ሥፍራ ለተገኙት ሰዎች ሥልጣን የሚሰጡት፣ በሚታመኑ ሥፍራዎች የሚያስቀምጡት፣ የቅርብ አማካሪዎቻቸው የሚያደርጉት የመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡

በማንኛውም ምክንያት አመፅ ይነሳ በጦርነት ጊዜ ዕምነት የለምየትውልድም ሆነ የጋብቻ ዝምድና የለምባህል የለም፡፡ ስለትምህርት፣ ስለጤና አይታሰብም፡፡ የሞተ መቅበር፣ የተጎዳን መዳኘት የለም፡፡ ጥፋት እንጂ ልማት አይታይም፡፡ የሚገድል ምንጊዜም የሚታየው አለመሞት ነው፡፡ ስለሆነም የሽማግሌ ድምፅ፣ የጎሳ መሪ ድምፅ፣ የሕዝብ ድምፅ አይሰማም፡፡ ለድርድር ከቀረቡ በኋላ ወደ ጫካ መመለስ ይኖራል፡፡

ወደ አሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ እንግባ፡፡ ከምን እንጀምር? በጸሐፊው እምነት በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁከትን በሚመለከት መጻፍ የሚቻል ቢሆንም ከዛሬው ይልቅ ከትናንቱ የተሻለ መማር ስለሚቻል፣ የሽግግር መንግሥት ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመመሥረት ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ (በመተከል)፣ በስምጥ ሸለቆዎች፣ በበደኖ፣ በወተር፣ በአረካ፣ በኢሉባቦር፣ በኢሳና ጉርጉራ በመተሐራ ያጋጠሙትን በአስተማሪነታቸው እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

በቤንሻንጉልና ጉምዝና በኦሮሞ አጎራባች መካከል የተከሰተው ግጭት

በሁለቱ ክልሎች ችግር መፈጠሩ ተጠቀሰ እንጂ፣ የችግሩ ምንጭ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ሳይሆን በኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) እና በቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) መካከል የተከሰተ አለመግባባት ነበር፡፡ ኦነግ በወቅቱ ለሽግግር መንግሥቱ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት የሕዝብ ግጭት የተፈጠረው ቤህነን የኦነግ ሠራዊት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በመከልከሉ ነው፡፡ ኦነግ ጨምሮ እንደገለጸው በርካታ የቤንሻንጉል ተወላጆች ከኦነግ ጎን በመሠለፍ ሕዝባዊ ትግል ሲያደርጉ መኖራቸውን ጠቅሶ ቤህነን ይህን ዕድል ሊከለክላቸው አይገባም ነው፡፡ ነገሩ ከአባልነት ጋር የተያያዘ ቢመስልም፣ የዛሬይቱ አሶሳ የወለጋ አካል እንደነበረችና ወለጋን ከሱዳን ጋር የምታገናኝ ድልድይ መሆኗን ማስተዋል ይገባል፡፡ በቤንሻንጉልና በወለጋ ወሰኖች መካከልም አጨቃጫቂ ቦታዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ የተከሰተውን የመጋደል፣ መንገድ የመዝጋት፣ የሰፈራ መንደሮችን ማቃጠል፣ ሰዎችን የማፈናቀል ዕርምጃ ለታሪክ የምንተወው ይሆናል፡፡ በዚህ አካባቢ የተከሰተው ችግር ከደርግ መንግሥት መውደቅ ዋዜማ እስከ ሽግግር ዘመኑ እንደነበር ሰነዶች የሚያረጋግጡት ነው፡፡

በስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ የተከሰተው ችግር

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 18 ቀን 1984 ዓ.ም. ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባው ከተመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ፣ በስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ የተከሰተውን ችግር ይመለከታል፡፡ ለምክር ቤቱ በቀረበው ሰነድ መሠረት በስምጥ ሸለቆው ማለትም በከንባታና በአርሲ፣ በአርሲና በአላባ፣ በጉጂና በቦረና፣ በሲዳማና በአርሲ መካከል ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ የግጭቱ መንስዔም የወሰን ጉዳይ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በዚያ ግጭትም የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ሰዎችም ከነበሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፡፡ ለምሳሌ 4,000 የሚሆኑ ከንባታዎች ከኑሯቸው ተፈናቅለው ሻሸመኔ በተሠራ መጠለያ እንዲኖሩ ተደርጎ ነበር፡፡ የመንግሥት እርሻ ልማት ወድሟል፡፡ አበርኖሳ ከተባለው ምርጥ ከብት እርባታ ብዙ ከብቶች እየተዘረፉ ታርደዋል፡፡ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ በአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የአካባቢው ሽማግሌዎች  ስለተከሰተው ችግር ሲናገሩ፣ ‹‹በዕድሜ ዘመናችን ብዙ ግጭት ዓይተናል፣ እንደ ዛሬ ግን አላየንም፤›› ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በግጭቱ ማግሥት የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ቢሞከርም ጥፋቱን የሚያካክስ እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡

በሽግግር ዘመኑ ሠራዊት የነበራቸው ኃይሎችና በሕዝቡ ላይ ያስከተሉት ችግር

በሽግግሩ ዘመን ሠራዊት የነበራቸው ኃይሎች (የሽግግር መንግሥቱ አባላት) ከኢሕአዴግ ሌላ የአፋር ነፃነት ግንባር (አነግ)፣ የቤኒሻንጉል ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዴሕ)፣ የጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ጋሕዴግ)፣ ሆሪያል (የኢትዮጵያ ሶማሌ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ኢስላማዊ ግምባር (ኦነኢግ)፣  የኢሳና ጉርጉራ ነፃነት ግንባር (ኢጉነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የተባበረው የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ኦሕነግ)፣ የምዕራብ ሶማሌ ነፃነት ግንባር (ምሶነግ) ነበሩ፡፡ ከእነዚህም አሥራ አንድ ድርጅቶች ውስጥ የሶማሌዎቹ አራት 36 በመቶ፣ የኦሮሞ ሦስት 27 በመቶ በመሆኑ ሁለቱ ድርጅቶች ከ50 በመቶ በላይ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች የደርግን መንግሥት ለመጣል በየአቅጣጫው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆኑም የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በአካባቢያቸው የበላይነታቸውን ለማስከበር፣ በተለይም የኢሕአዴግ ሠራዊትን የበላይነት በመቃወም ግጭት መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ የሚፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ይቻል ዘንድ የሽግግር መንግሥቱ የመከላከያና የደኅንነት ፖሊሲ ኮሚቴ የካቲት 1984 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት የመፍትሔ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ ከመፍትሔዎቹ አንዱም አለን የሚሉትን የሠራዊት ብዛት እንዲያስመዘግቡ ያቀረበው ሐሳብ ነበር፡፡ በዘህም መሠረት አራቱ ማለትም አነግ፣ ቤህነን፣ ጋሕዴግነ ኦነግ ሠራዊት እንዳላቸው ሲያሳውቁ ሌሎቹ ግን ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ ሐሳቡም በየጊዜው የሚከሰተውን ግጭት ለማስቆም ነበር፡፡ ነገር ግን የሚፈለገው ውጤት ባለመገኘቱ የበደኖንና የወተርን አሰቃቂ ግጭት ፈጠረ፡፡ ውድ አንባቢያን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚገለጸው ውጤቱ እንጂ ሒደቱ አለመሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

የበደኖ፣ የወተርና የሌሎች አካባቢዎች ግጭቶች

የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 13 ቀን 1984 .. 40 መደበኛ ስብሰባው ከተወያየባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ በበደኖ ተፈጸመ በተባለው ዕልቂት በተዘጋጀው አጀንዳ ላይ ነበር፡፡ ይኼንንም በሚመለከት የተለያዩ የምክር ቤት አባላት በደርግ መንግሥት የተጨፈጨፈው ሕዝብ አስከሬን ከየቦታው ገና ተለቅሞ ሳያልቅ፣ በደኖ ላይ ይህን የመሰለ አስከፊ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱም እንዳይደገም መወገዝ እንዳለበትና ጉዳዩ በሚገባ ተጠንቶ አጥፊው ሲረጋገጥ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና የኦነግ ተወካይ በመገናኛ ብዙኃን በተላለፈው ዜና ተመሥርቶ ድርጊቱን ማውገዝ እንደማይገባ፣ ድርጊቱ መወገዝ ያለበት መፈጸሙ ሲረጋገጥና አጥፊው ድርጅትም ሲታወቅ መሆን እንዳለበት ካብራሩ በኋላ የበደኖ ጉዳይ ይጠና ከተባለ በሐረር፣ወተር፣ በአርሲ፣ በሻሸመኔ፣ቁልቢ፣ ወዘተየተፈጸሙትም ኢሰብዓዊ ድርጊቶች አብረው መታየት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በመገናኛ ብዙኃን ሳይገለጹ ቆይተው፣ የበደኖ ጉዳይ እንዴት በተለየ ትኩረት ሊተላለፍ እንደቻለ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ የበደኖ ዕልቂት ሰላማዊ በሆነ (ምንም ጦርነት በሌለበት) ቦታ የዚህ ብሔረሰብ አባል፣ የዚህ ድርጅት ደጋፊ ነህ በሚል ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች በግፍ የተገደሉ ስለሆነ ድርጊቱ በሌላው አካባቢ ከተፈጸመው ጋር ሊነፃፀር እንደማይችል፣ አንድ የኢሕአዴግ ተወካይ ከቻርተሩ አኳያ ሲታይ ድርጊቱ መወገዝ ያለበት ስለሆነ እንዲወገዝና ድርጊቱን የፈጸመው ድርጅት ከተጣራ በኋላ ደግሞ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድበት አሳስበዋል፡፡

ከበደኖ ድርጊት በተጨማሪ በሃይማኖትና በብሔሰረብ ልዩነት የተነሳ የሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዲወገዝ፣ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የሚነሱት ግጭቶች አግባብና ሰላማዊ ስላልሆኑ እንዲኮነኑ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሰላም ዋስትና በሚመለከትም ምክር ቤቱ አንድ ጠንከር ያለ ውሳኔ አስተላልፎ መግለጫ እንዲወጣ የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡

የኦሞቲክ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ተወካይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተፈጸሙ አሰብዓዊ ድርጊቶች ሁሉ በተጨባጭ ተጠንተው እንዲቀርቡና በአጥፊው ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስበው፣ በደቡብናሰሜን ኦሞ አካባቢዎች የሞቱት 250 ሰዎች ጉዳይና ጃንጀሮ አካባቢም በተመሳሳይ ሁኔታ 22 ሰዎች እንደ እንስሳ በቢላዋ ታርደውለመገኘታቸውም አብሮ እንዲጠና ጠይቀዋል፡፡ ሆኖም የጎሳ ግጭት ድሮም የነበረ ስለሆነ አሁን በፖለቲካ ምክንያት እንደመጣ ተደርጎ መቅረብ እንደሌለበት ሰብሳቢው አብራርተው፣ የሚቋቋመው ኮሚቴ የበደኖንና የወተርን ጉዳዮች አጥንቶና የሚመለከተውን ድርጅት አነጋግሮ ጉዳዮችን በሚገባ ካጣራ በኋላ፣ ለምክር ቤቱ ውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ አስገንዝበው ለሥራ ውጤታማነትም ከኦነግና ከኢሕአዴግ አባላት ውጪ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

የአረካ ግጭት

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 23 ቀን 1984 ዓ.ም. ባካሄደው 50 መደበኛ ስብሰባ፣ የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በወላይታ አውራጃ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በአረካ ከተማ ገበያተኛ ላይ ኢሰብዓዊና ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ መካሄዱን፣ በዚህም ድርጊት 60 የሚሆኑ ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ 100 ያህሉ ደግሞ ቆስለዋል ተብሎ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በምክክሩ ወቅት በተሰጠው ማብራሪያ  በወቅቱ ሕገወጥ ሠልፍ እንደተካሄደ፣ ይህም ሕገወጥ ሠልፍ400 ያህል የቀድሞ ወታደሮችና በተባባሪዎቻቸው እንደተዘጋጀ፣ ሠልፈኞቹ ችግር ቢኖራቸው በሰላም ማስረዳት ሲገባቸው የመንግሥት ኃላፊዎችን ማስፈራራት እንደጀመሩናስልክ መስመር እንደበጠሱ፣ ሱቆችን፣ ሻይ ቤቶችንና ምግብ ቤቶችን እንደዘጉና ገበያውን እንዲበተን እንዳደረጉ፣ በመጨረሻም ከሠልፈኞቹ ወታደሮች መካከል አንዱ ቦምብ እንደወረወረና ከዚህ በኋላ በተከፈተው ተኩስ ሦስት ሰላማዊ ሰዎችና ሰባት የቀድሞ ወታደሮች እንደ ሞቱ፣ ስድስት ሰላማዊና አራት የቀድሞ ወታደሮች እንደ ቆሰሉ ተጠቅሷል፡፡ በሁለቱም በኩል የቀረበው መረጃ እንዳለ ሆኖ በአረካ የሚገኘውን የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ተጠሪዎችንና የመንግሥት አስተዳደር ተጠሪዎችን የሚያነጋግር፣ ድርጊቱን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ምን እንደነበር የሚገልጽ አጠቃላይ ሪፖርት የሚያቀርብና በሰላማዊ ሕዝብ ላይ አስቀድሞ ተኩስ የከፈተው ማን እንደሆነ፣ በሕዝብና በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት ምን ያህል እንደሆነና በጥፋቱስ ተጠያቂ ማን ሊሆን እንደሚችል የሚመረምር ከኢሕአዴግና ከደቡብ ሕዝቦች ኅብረት ውጪ የሚሆን ኮሚቴ እንዲመረጥ አደረገ፡፡

የመረጃው አሰባሰብ ለጊዜውም ሆነ ወደፊት ጠቃሚ የመነሻ ሐሳቦችን ቀርፆ ሊይዝ በሚችለው መንገድ እንዲገናዘብ በነደፈው ዕቅድ መሠረት ከመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ከቴሌቪዥን መምርያ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ሪፖርት አቅራቢዎችን ከኢትዮጵያ ፕሬስ መምርያ ፎቶ ግራፍ አንሺ አንድ ቃለ ጉባዔ አጠናቃሪ ከምክር ቤቱ በመያዝ ከአዲስ አበባ ተንቀሳቀሰ፡፡ ኮሚቴው ጉዞውን ሐምሌ 27 ቀን 1984 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት ተንቀሳቅሶ በወቅቱ የወላይታ አውራጃ ርዕሰ ከተማ ሶዶ እንደ ደረሰ፣ በመጀመርያ ከመገናኛ ብዙኃን ለመጡ አባሎች መግለጫ በመስጠት ሥራውን በመጀመር ጥናቱንም ለምክር ቤቱ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ውድ አንባቢያን በሽግግሩ ዘመን መጀመርያ፣ በሽግግሩ ዘመን ማብቂያና በአሁኑ ጊዜ ልዩ ልዩ የአመፅ ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ ሁሉም ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ለመሆናቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡

ወደፊት ምን መደረግ አለበት?

  ዛሬ በአገራችን የተለያዩ አመለካከቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምነቶች፣ ርዕዮቶችና ዴሞክራሲያዊ መንገዶች እየታዩ ናቸው፡፡ ይህም ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ልምዶች ጋር ሲደመር አንድነታችንን የበለጠ እንደሚያጠናክረው አያጠያይቅም፡፡ አንድነታች ባለን ልዩነት ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ከደሙ ጋር ተዋህዶ ለኖረው ሕዝብ እንደገና ማስተማር አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ማንኛውም በሥልጣን ላይ ያለ አካልም ሆነ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚሻ የፒራሚድ ቅርፅ ያለውን የፖለቲካ ሕይወት እያለፈ ሲሄድ ማስተዋል የሚኖርበት ይኼንን ሀቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመሠረቱ ፖለቲከኞች ሊይዙት የሚገባው አቋም ‹‹በእኔ ፍልስፍና፣ በእኔ ርዕዮት፣ በእኔ ኢኮኖሚያዊ ትልም ብትጓዙ የተሻለ ማኅበራዊ ሕይወት ይኖራችኋል…›› የሚል እንጂ፣ ‹‹ብትወዱም ባትወዱም ሕይወት ወደ ተሻለ አቅጣጫ ይጓዝም፣ አይጓዝም መከተል የሚኖርባችሁ እኔን ብቻ ነው…›› ወይም ‹‹ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ትክክል አይደሉም፣ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ እንዲሁም ማንም በዚህ አካባቢ እኔን የሚያህል ሀቀኛ የለም…›› እያሉ የሰዎችን መብት በመዳፈር መሆን የለበትም፡፡ ይኼንን አቋም ይዞ እንዳሸው ለመፏለል ቢያስብ እያደር እየተጠላ ከዴሞክራሲያዊ ተግባር እየራቀ በአምባገነናዊ አስተሳሰብ ራሱን እያፋፋ ይሄዳል፡፡ ይህ ደግሞ እብሪተኝነትን ያስከትላል፡፡ ያደርጋልም፡፡ ሕዝብም ነገሩ ይዋል ይደር እንጂ እብሪተኛውን ከጀርባው አሽቀንጥሮ መጣል ስላለበት፣ ያለማቋረጥ ዘዴ እየፈለገና እየታገለ ይኖራል፡፡

‹‹የእኔን አስተሳሰብ በተለያየ መንገድ (በሕገወጥ ጭምር) ካልተቀበላችሁ በስተቀር እጨቁናችኋለሁ፣ አስራችኋለሁ፣ እገድላችኋለሁ…›› እያሉ በማስፈራራት፣ እንዳስፈላጊነቱም ሌላው እንዲሸማቀቅ የሚያደርጉ ዕርምጃዎችን መውሰድ በሥልጣን ለመቆየት ከመፈለግ የተሳሳተ አመለካከት በመነሳት የሚያከናውኑት ተግባር ራስን ከፍተኛ የፖለቲካ ክስረት ውስጥ የሚጥልና ሕዝብን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡ ..አ. 1809 እስከ 1865 የነበሩት አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹ባሪያ ለመሆን እንደማልፈልገው ሁሉ ጌታ ለመሆን አልሻም፡፡ በበኩሌ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ይህ ነው፤›› ያሉትም ዛሬ ለብዙዎቻችን አርአያነት ያለው ይመስለኛል፡፡ እኚህ ሰው እንዳሉትም፣ በፖለቲካው መስክ የተሠማራን ሁሉ ሕዝብን ከጭቆና፣ ከሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ከድህነትና ከበሽታ ለማላቃቅ እንጂ ተቃራኒውን ለመፈጸም እንዳልሆነ በቀና አስተሳሰብ እንደገና እንድናጤነው ወቅቱ ይጠይቀናል፡፡ የሕዝብ ድምፅ  የተሻለ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡

ዛሬ የምንገኝበት የሽግግር ዘመን ከዘመናት የተለያየ አምባገነናዊ አገዛዝ ወደ አዲስ የዴሞክራሲ አቅጣጫ የሚጓዝ እንደመሆኑ መጠን፣ ከአሮጌ አስተሳባብ ወደ አዲስ አስተሳሰብ መቀየር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ይኸው ዴሞክራሲያዊ ጮራ ካለመለመዱ የተነሳ የፀሐይን ጨረር ያህል ዓይነ ህሊናችንን ሊወጋ ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ልናስተውለው የሚገባ ዓብይ ቁም ነገር ግን ከዴሞክራሲው የሚፈነጥቀው ጨረር ብቻ ሳይሆን፣ ጨረሩ በሕዝብ ላይ አርፎ የሚያሳየውን ክስተት መሆን ይኖርበታል፡፡ ወትሮም ሰው የሚመለከተው ፀሐይን ሳይሆን የምታሳየውን ነው፡፡ ይኸው የዴሞክራሲ ጮራ ሁነቶችንአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የመፋቀር እሴታችን የት እንደሚገኝ ሊያሳየን ይገባል፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ ዴሞክራሲ ማለት ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶችና በዙሪያቸው ሊሰባሰቡ የሚችሉ ኃይሎች የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚሽቀዳደሙበት፣ የሐሳብና የአሠራር ልዩነታቸውን በግልጽ ለሕዝብ አቅርበው ማንነታቸውን የሚያሳዩበትና ለሕዝብ ታማኞች፣ ትሁቶች፣ ታዛዦችና ይሁንታውን ከሚሰጣቸው ሕዝብ ቀድመው የሚገኙ መሆናቸውን ተፈትነው የሚያልፉበት፣ የተወዳዳሪዎቻቸው ፉክክር ሳይበግራቸው የሕዝብን ስሜት ለመሳብ ጥረት የሚያደርጉበት፣ በመጨረሻም በሕዝብ ድምፅ ከብዙ ተወዳዳሪዎች መካከል በጣም ጥቂቶች ድል የሚቀዳጁበት መድረክ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች በእርግጠኛነት ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ለመሥራት ቁርጠኛ ዓላማ ካላቸው እንደምንም ብለው በማለፍ የሥልጣን ኮርቻ ላይ መንጠልጥል ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብ ሌሎች አማራጮችም እንዳሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲያውቃቸው ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ በእነሱና በተቀናቃኞቻቸው መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርገው ማሳየት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን ይገባዋል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣኑን የሚመሩት አባሎቻቸው በብልጥነት፣ በቆርጦ ቀጥልነትና በሸፍጠኝነት ሳይሆን በቀናነት፣ በደግነትና በሩህሩህነት በግንባር ቀደም መስዋዕትነት ከፋይነት የሚታወቁ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆንም አያጠያይቅም፡፡

‹‹ጥሩ መጽሐፍ የሚያጠፉ ዕውቀት ራሱን እንደ ገደለ ይቆጠራል›› በማለት ዕውቁ እንግሊዛዊ የሥነ ጽሑፍ ሰው ጆን ሚልተን እንዳለው ሁሉ፣ ዛሬ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ብለን በሀቅ ካልተነሳንና ዓለማችንን ዳር ለማድረስ ካልቆረጥን በስተቀር ሁላችንም የምታናግረን፣ የምታሳስበን፣ የምታጽፈን፣ እንድንደግፍና እንድንቃወም የምታደርገን አገራችንን ልንጎዳት እንችላለን፡፡

ስለዚህም በዚች አገር ፍትሕ፣ ርትዕ፣ ሰላምና አንድነት ተከብረው እንዲቆዩ ማንኛቸውም የፖለቲካ ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ለሕዝብ የሚበጅ አስተዳደር ይዤያለሁ ብለው ከፊታችን ከቆሙ፣ በበጎም ሆነ በመጥፎ ትምህርት ሊገኝበት እንደሚችል አውቀን በትዕግሥት ሁኔታዎችን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያ ለአንዱ እናት ለሌላው እንጀራ እናት ሆና ከቆየችበት ዘመን ልትላቀቅ የምትችለው ሕዝብ በፍቅር ዓይን መተያየት ሲጀመርና ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነቱን ሲያጠናክር ነው፡፡ ሰዎች በፈለጉት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ኑሮ መስክ ሊራመዱ የሚችሉትም አንድ እምነት ሲኖራቸው እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ስለአንድነታችንና ልዩነታችን ለማስንዘብ በየፊናችን ስንሰማራ ደግሞ የብዙ ዘመናት የብሔር ብሔረሰብ ጭቆናን አስወግደን ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ አስተደደር ለመመሥረት ባለን ዓላማ እንጂ በአሜሪካ ያሉት ሞንጎሎይድ፣ ካውካሶይድና ኔግሮይድ እንደ አሜሪካዊ ሁሉ አንድ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን በመዘንጋት አይደለም፡፡ አሜሪካንም በምሳሌነት የጠቀስኩት የዘመናችን ትልቅ አገር በመሆኗ ነው፡፡ኢትዮጵያ ሕዝብም እስከ ደቡብ እየተፈራረቀ በገዛበት ዘመን ከፍተኛ ማኅበራዊ ውህደት እንደተፈጠረ ለመተንተን መሞከር ደግሞ ለቀባሪው አረዱት እንደሚባል ይሆናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አጎራባች አገሮችና የቀይ ባህርን ተሻግረው ወደ አገር ከገቡ ዓረቦችም ተዳቅለን ኖረናል፡፡ እንደሚታወቀው ለረጅም ዘመናት በአንድ ላይ ስለኖርን ልምዳችን፣ ባህላችን፣ ባህሪያችንና ትውልዳችን ስለተዋሀደ በአንድ ላይ ኢትዮጵያዊ ሊያሰኘን ችሏል፡፡

ከዚህም አንፃር ብሔርና ብሔረሰብ እያልን የምናራምደው እንቅስቃሴ ዘመን የወለደው የፖለቲካ ስትራቴጂጭቆና የፈጠረው ጥያቄ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነታቸው ያላቸውን መብት የሚነካ ከቶ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕዝቦች በፈለጉት አቅጣጫ ቢደራጁ አንድነታቸው የተመሠረተው ልዩነታቸው ፍቅርና አንድነት እንጂ ጦር መሣሪያ የሚያማዝዛቸውም አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ሰው ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዋሳት፣ ልዩ ልዩ አካላት አሉ፡፡ ሁሉም ግን አንድ ላይ እንዲኖር አደረጉት እንጂ ሕይወት አላሳጡትም፡፡ አንዱ አካል ያለ ሌላው አካል የተሟላ አይሆንም፡፡  በአጭሩ አንድ ኢትዮጵያዊ የአገሪቱን ሕግና ደንብ እስካከበረ ድረስ በፖለቲካ ፓርቲ በብሔር ብሔረሰቦች ተደራጅቶ ቢንቀሳቀስ መብቱ እንደሆነ ሊታወቅለት ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተደጋጋሚ ለሕዝብ ተስፋ እንደሰጡት ሁሉ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቀናቃኝ ድርጅቶቻቸውን አሸንፈው ሥልጣን ለመያዝ የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዱ የፖለቲካ ድርጅት ከሌላው የተሻለ ዓላማና መርሐ ግብር እንዳለው ለማሳየት ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ፣ የስብሰባ ጥሪዎችን በማሰማት ቅስቀሳውን እንደሚጀምር መገመት ይቻላል፡፡ አንዳንድ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶችም ራሳቸው ወደ ፓርቲ የሚቀይሩበት፣ ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚቀርቧቸው ሳይሆን ከሚርቋቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ልዩነታቸውን አቻችለው ግንባር የሚፈጥሩበት፣ ወይም አንድ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚመጣም ይገመታል፡፡ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም አንድም ባለው ዴሞክራሲያዊ መንገድ በግልጽ ተጠቅመው፣ ያለበለዚያም ከሌሎች ጋር ሆነው የወደፊት ዓላማቸውን እንደሚያራምዱጠበቃል፡፡አንዱ ህልውና በሌላው መጨፍለቅ ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን መጠንቀቅና ዕድገት የሚገኘው በመደጋገፍ እንጂ በመነጣጠል እንዳልሆነ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ነፃ ውድድር አካሂደን ፍላጎታችንን ለማርካት የምንችለው ነፃ አመለካከት ሲኖረንና ነፃ እንቅስቃሴ ስናደርግ ነው፡፡

ይህም ሆኖ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ሕዝቡን የሚያገለግሉ እንጂ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያገለግል አለመሆኑን ካልተገነዘብን፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሚቋቋመው በፖለቲካ ፓርቲዎች ምኞት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ፍላጎት መሆኑን ካልተቀበልን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የሕዝብን ስሜት ተከትሎ የሚራመድ መሆኑን ካላጤንን በእግርጥም የከፋ አደጋ ይጠብቀናል፡፡ ሕዝቡም የበሰለ አመለካከት ያላቸውንና በተግባር ተፈትነው ጠቃሚ ውጤት ያስገኛሉ፣ ጥሩ ዳኝነት ይሰጣሉ፣ ያስተዳድራሉ ብሎ የሚያምንባቸውን ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባቸው የሰፋ ነው የሚላቸውን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ከግለሰቦች መካከል በቁርጠኛ ውሳኔ መምረጥ ካልቻለ፣ አገሪቱ ከማትወጣው ኪሳራ ውስጥ ትወድቃለች፡፡ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶችም ሁሉም መሪ መሆን እንዳማይቻሉ አውቀው ሽንፈትን በፀጋ ሊቀበሉ ይገባል፡፡ ለማንኛውም ቀና አስተሳሰብና ቀና ልቦና እንዲሰጠን በየፊናችን ጥረት ማድረግ አማራጭ የማይገኝለት የወቅቱ ተግባር መሆኑን እያሳሰብኩ የዛሬውን ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...