በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ለተያዙ፣ ለተፈረደባቸውና ሳይያዙ በውጭ አገር በስደት ለሚኖሩ ግለሰቦችና የሕግ ሰውነት ላላቸው አካላት ምሕረት ለመስጠት መንግሥት ያቀረበው የምሕረት መስጫ አዋጅ ሳይፀድቅ፣ ፓርላማው የዓመቱን የሥራ ጊዜውን አጠናቆ ለእረፍት ተበተነ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በተለያዩ ወንጀሎች ለሚፈለጉ ሰዎች ምሕረት ለመስጠት በመወሰን ፓርላማው እንዲያፀድቀው ከላከ በኋላ፣ ፓርላማው ምሕረት ለመስጠት በተላከለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ሐሙስ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በመወያየት ረቂቁን በዝርዝር ዓይቶ፣ ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ፓርላማው ለእረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ይህንን የምሕረት መስጫ አዋጅ ያፀደቀዋል የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም፣ ቅዳሜ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የዓመቱን የመጨረሻ ስብሰባውን በልዩ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት በማካሄድ ለእረፍት ተበትኗል፡፡
በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች ምሕረት ለመስጠት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መግቢያ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግና አጋጥሞ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተሳተፉ ሰዎችን ድርጊት ለመሰረዝ ምሕረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በዚህ መሠረት ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በፊት የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን፣ ማለትም በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚደረግ ወንጀል፣ የሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንን ተግባራዊነት ማሰናከል፣ የጦር መሣሪያ ይዞ ማመፅ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ማስነሳት፣ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት መንካት፣ የአገር መከላከያ ኃይልን መጉዳትና የአገር ክህደት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም ከጠላት ጋር በመተባበር የሐሰት ወሬዎች ማውራትና ማነሳሳት፣ ለፀረ ሽብርተኝነት የወጣ አዋጅን መተላለፍ ይገኙበታል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመተላለፍ የሰው ሕይወት ያጠፋ ግን የምሕረቱ ተጠቃሚ መሆን አይችልም፡፡ ይህንን አዋጅ ፓርላማው ሳያፀድቀው ለእረፍት ቢበተንም፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ያፀድቀዋል ብለዋል፡፡