Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አዲስ ኃላፊ ሾሙ

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አዲስ ኃላፊ ሾሙ

  ቀን:

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነርነት አቶ ኢዮብ ተካልኝን ሾሙ፡፡ አቶ ኢዮብ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡  

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው በተሾሙት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ምትክ አቶ ኢዮብ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸው ተረጋግጧል፡፡ የሹመታቸውን ዜና በማስመልከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ ኢዮብ መሾማቸውን ከማረጋገጣቸው ውጪ፣ ወደፊት ስለሚያከናውኗቸው ሥራዎችና ስላሏቸው ዕቅዶች አሁን ምንም ዓይነት ዝርዝር ሐሳብ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

  አቶ ኢዮብን በቅርበት ከሚያውቋቸው መካከል አንዱ የሆኑትና የ251 ኮሙዪኒኬሽን ኩባንያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲስ ዓለማየሁ ስለአቶ ኢዮብ ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ ስትራቴጂስትና ከሌሎች በተለየ ነገሮችን የሚመለከቱ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን ክፈተት በማጥበብ በኩል ትልቅ ሚና የተጫወቱ፣ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ማገልገል የቻሉ ፈርጀ ብዙ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው፡፡ 

  የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ ለመቀበል ጥቂት ወራት የቀሯቸው አቶ ኢዮብ፣ የማስትሬት ዲግሪያቸው ከጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውንም ደግሞ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ መስክ እንዳገኙ ግለ ታሪካቸው ያትታል፡፡ በፖለቲካ ኢኮኖሚ መስክ ካላቸው የአካዴሚ ዝግጅት በተጨማሪ በበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል፡፡

  እስከ ሹመታቸው ድረስ ኤስጂአይ ፍሮንቲየር ካፒታል ኢትዮጵያ በተሰኘው አማካሪ ተቋም ውስጥ በዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኢዮብ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥም በዲፕሎማትነት ማገልገላቸው ይነገርላዋቸዋል፡፡

  ከአምስት ዓመታት በፊትም በኢትዮጵያ መንግሥትና በግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር ፎረም ኃላፊ በመሆን ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ማገልገላቸውን ከግለ ታሪካቸው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዓለም ባንክና በዓለም ገንዘብ ድርጅት በኩል የኢትዮጵያ መንግሥትን በማማከር ሲሳተፉ እንደቆዩ፣ በዓለም ባንክ ሥር በሚተዳደረው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ለግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አገልግሎት አቅራቢ ተቋም)፣ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ተቋም ውስጥ፣ እንዲሁም በምሥራቅና በደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ውስጥ ማገልገላቸው ስለአቶ ኢዮብ ልምድና ተሞክሮ ከሚገልጹ ማሳያዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 

  አዲሱ ተሿሚ ከአቶ መኮንን ማንያዘዋልና ከብሔራዊ ባንክ ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በመከተል ሦስተኛው የኮሚሽኑ ኃላፊ ናቸው፡፡ አቶ መኮንን አንጋፋና በጡረታ የተገለሉ ቢሆኑም፣ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አመራር ዘመን የተመሠረተውን ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን በመሥራች ኃላፊነት የመሩ ናቸው፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በንግድ ሚኒስቴር በኋላም በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርነት ካገለገሉ በኋላ በጡረታ የተሰናበቱት አቶ መኮንን፣ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ሒደት ውስጥ ዋና ተደራዳሪ እንደነበሩም ይታወሳል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img