Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበታራሚዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው በሕግ ሊጠየቁ ነው

በታራሚዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው በሕግ ሊጠየቁ ነው

ቀን:

ሰሞኑን ከኃላፊነታቸው የተነሱ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው በፍርደኞችና የክስ ሒደታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ እስረኞች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸማቸው በቀጣይ በሚደረግ ምርመራ ከተረጋገጠባቸው፣ በሕግ እንደሚጠየቁ ተገለጸ፡፡

ታራሚዎችና እስረኞች ከፍተኛ የሆነ በደልና ስቃይ እንደደረሰባቸው በቅርቡ ከእስር የተፈቱ ዜጎች እየገለጹ በመሆኑ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎችን በማንሳት አዳዲስ ኃላፊዎችን ሾሟል፡፡

የቀድሞ ኃላፊዎችን በማንሳት ተተኪ ኃላፊዎች መሾማቸውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ እንደተናገሩት፣ የማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደር የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበት ነው፡፡

‹‹ተቋሙ ግዴታውን ባለመወጣቱ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበበት ነው፡፡ በማንም ይሁን በማን የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ መጣስ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ደግሞ ወንጀል ነው፡፡ በማረሚያ ቤት ውስጥ ታራሚ በሆነ ዜጋ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጥሰዋል ተብለው በተከሰሱ ወገኖች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም ወንጀል በመሆኑ፣ በወንጀሉ ውስጥ ገብተው የተገኙ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ማጣራት ተደርጎ ለሕግ እንደሚቀርቡ ዓቃቤ ሕጉ አስታውቀዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ አገር እየገነባን በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ሊከበር ይገባል ያሉት ዓቃቤ ሕጉ፣ በሕግ ቁጥጥር ሥር ያለን ዜጋ አርሞና አንፆ ማውጣትና ሕግ አክብሮ አምራች ኃይል እንዲሆን ማድረግ ሲገባ፣ አካልን አጉድሎና ሰብዓዊ ክብሩን ገፎ የሚያወጣ ተቋም መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

‹‹በማረሚያ ቤቶቹ የሚገኙ ታራሚዎች ወንጀል ፈጽመው የታሰሩ ቢሆንም ወንድሞቻችን ናቸው፤›› ያሉት አቶ ብርሃኑ ታርመው፣ ታድሰውና ሕግ አውቀው እንዲወጡ ማድረግ ካልተቻለ ሕገወጥነት እየተስፋፋ እንደሚሄድም ጠቁመዋል፡፡ ነባር አመራሮች በሥራቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው ባለመሥራታቸው፣ ችግሮች መፈጠራቸውን አስምረው፣ የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያስከብሩ አመራሮች መሾማቸውን ተናግረዋል፡፡ ይኼም የተደረገው ማረሚያ ቤቱን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 365/95 አንቀጽ(7) መሠረት መሆኑንም አክለዋል፡፡

በመሆኑም በቀድሞ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ረጋሳ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የሰው ሀብትና መሠረታዊ ፍላጎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌትዬ ደጀኔና የጥበቃና ተሃድሶ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፀጋ ወልደ ሩፋኤል ምትክ አምስት ኃላፊዎች ተሾመዋል፡፡

በዋና ዳይሬክተርነት አቶ ጀማል አባስ፣ ረዳት ኮሚሽነር ያረጋል አደመ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ፋይናንስና የሰው ሀብት ዘርፍ ኃላፊ፣ ኮማንደር ደስታ አስመላሽ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የተሃድሶ ዘርፍ ኃላፊ፣ ኮማንደር ሙላት ዓለሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የጥበቃ ደኅንነት ዘርፍ ኃላፊ፣ እንዲሁም ኮማንደር ወንድሙ ጫማ ምክትል ዳይሬክተርና የመሠረታዊ ፍላጎት ዘርፍ ኃላፊ ተደርገው ተሾመዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...