በከባድ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረዋል
በቅርቡ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙትና የቀድሞ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ በከባድ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡ ሐሙስ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ቢንያም ተወልደ ወልደ ማርያም በዋናነት የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት የተፈጸመው፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ የተሳጣቸውን ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው፣ በመኖሪያ ቤታቸው የተለያዩ የውጭ አገሮች ገንዘቦች መደበቃቸው ጥቆማ እንደደረሰው፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪው ከኤጀንሲው ያወጧቸው ሚስጥራዊ ሰነዶች፣ የጦር መሣሪያ፣ የአይቲ መሣሪዎችና የባንክ ሰነዶችም ቤታቸው ውስጥ መደበቃቸውን ጥቆማ እንደደረሰው አክሏል፡፡
በተጨማሪም ለኤጀንሲው ሠራተኞች ከሚሰጥ የውጭ አገር ሥልጠና ጋር በተያያዘ ከደንብና መመርያ ውጪ 3.2 ሚሊዮን ዶላር ለአንድ የውጭ አገር ኩባንያ፣ በአንድ ጊዜ ያላግባብ ክፍያ መፈጸማቸውንና በዚህም ምክንያት መንግሥትና ሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ጥቆማ እንደረሰው መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ሌላው የደረሰው ጥቆማ ተጠርጣሪው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አካብተዋል የሚል መሆኑን ጠቁሞ፣ አቶ ቢኒያምን ከሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ካደረገ በኋላ ቤታቸውን ሲፈትሽ አሥር ሺሕ ዶላር፣ ስድስት ላፕቶፖች፣ አንድ ሽጉጥ ከመሰል ጥይቶች ጋር፣ ሰባት የሞባይል ቀፎዎችና የኤጀንሲው የተለያዩ ሰነዶች፣ የቤት ግንባታ ብሉ ፕሪንትና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ሰነዶችን ማግኘቱን አስረድቷል፡፡
የተጠርጣሪውን ቃል በመቀበል የስልክ መረጃዎችን ከኢትዮ ቴሌኮም ለማስወጣት፣ የደመወዝ መጠን ከኢንሳና አሁን ከሚሠሩበት ተቋም ለመሰብሰብ፣ የሀብት ምዝገባ ማስረጃ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ለመሰብሰብ፣ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ለኤጀንሲው ለመላክና ውጤቱን ለመሰብሰብና ሌሎች ምርመራዎችን ለማድረግ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ቢንያም ለፍርድ ቤት እንደተናገሩት፣ መርማሪው ቀረኝ የሚላቸው ማስረጃዎች በመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው እሳቸውን በእስር እንዲቆዩ የሚያደርግ አይደለም፡፡ በመሆኑም ቋሚ አድራሻ ያላቸው በመሆኑና ቅረቡ ሲባሉ መቅረብ የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ የዋስትና ጥያቄያቸውን በማለፍ፣ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡