ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)
ዓርብ ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የ2011 ዓ.ም. በጀት ፀድቋል፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት ሥራ ላይ የሚውለው 346.9 ቢሊዮን ብር በጀት ከመፅደቁ በፊት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከገጠመው ፈተና እንዲላቀቅ፣ የበጀት ፖሊሲ የትኩረት ነጥቦችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከመስጠታቸውም በላይ የመፍትሔ አቅጣጫም ጠቁመዋል፡፡ ከዘንድሮ አጠቃላይ በጀት 64 በመቶ ያህሉ ለድህነት ቅነሳ ዘርፎች መሆኑን ገልጸው፣ ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ብልጫ ያለው የበጀት ድልድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ይዞታ፣ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግና በማዕድን፣ በግዙፍ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከፋይዳቸው ይልቅ ጉዳታቸው እያመዘነ በመሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይጀመሩ መታገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ከውጭ የተበደሩት ይቅርና ከአገር ውስጥ ተበድረው ያልመሰሉት 400 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ከፋይናንስ ጀምሮ እስከ ኮርፖሬት አስተዳደራቸው ድረስ ጥልቅ ምርመራ ተካሂዶ እስኪጣራ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አይጀመሩም ብለዋል፡፡ ከፍተኛ የሀብት ማሸሽና መሸሸግ ተግባር በባለሀብቶች የሚፈጸም ስለመሆኑ መንግሥት መረጃ እንዳለው፣ ይህ ሀብት ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ገብቶ ቢሆን ኖሮ የአገሪቱን ካፒታል እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ ባለሀብቶች እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ በመኖርያ ቤቶቻቸው መለስተኛ ባንክ በመገንባት መሸሸጋቸውን መንግሥት መረጃ አለው ብለዋል፡፡ ‹‹በባለሀብቶች ቤት ውስጥ ተከማችቶ የሚገኝ ሀብት ችግር ቢኖርበትም በሕግ አግባብ ምሕረት እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ወደ ባንክ ሥርዓት እንዲገባም ጠይቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጠንካራ ዕርምጃ ይወሰዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የበጀት ጫና ውስጥ የወደቀው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመፍትሔ መንገድ
በሰኔ ወር መጀመርያ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የ2011 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር ሆኖ እንዲፀድቅ ይጠይቃል፡፡
ይህ ረቂቅ በጀት በ2010 ዓ.ም. ከፌዴራል መንግሥት አጠቃላይ ወጪ ጋር ሲነፃፀር፣ በ12.1 ቢሊዮን ብር ወይም በ3.6 በመቶ ብልጫ ያሳያል፡፡ የ2011 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የዛሬ ሦስት ወር ገደማ የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ከሰጡበት በኋላ ዓርብ ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ፀድቋል፡፡
ከፀደቀው በጀት ውስጥ ትልቁ ድርሻ ማለትም 135.7 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ተጨማሪ ስድስት ቢሊዮን ብር ለክልሎች ለበጀት ድጎማና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበ ነው፡፡
ለክልሎች ከሚከፋፈለው የአጠቃላይ በጀቱ ቀጥሎ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው 113.6 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች መሸፈኛ የሚውል ሲሆን፣ ቀሪው 91.7 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመደበኛ ወጪዎች እንደሚውል የበጀት አዋጁ ያመለክታል፡፡
የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል እንደማሳያ የሚሆነው የካፒታል በጀት ድርሻ ሲሆን፣ ለ2011 ዓ.ም. የተመደበው የካፒታል በጀት 113.6 ቢሊዮን ብር ከ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ የካፒታል በጀት ድርሻ ብልጫ ማሳየት የሚገባው ቢሆንም፣ ከዚህ በተቃራኒ ከ2010 ዓ.ም. ድርሻ በመጠኑ ቅናሽ ያሳያል ወይም በበጀት አዋጁ ማብራሪያ መሠረት ተመጣጣኝ ነው፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ሐሙስ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የዚህም ምክንያቱ በቀጣዩ በጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶ እንዳይጀመሩ መንግሥት ውሳኔ በማሳለፉ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ይህም ቢሆን የካፒታል በጀቱ በቀደሙት ዓመታት የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል፡፡ ትኩረት የተሰጣቸው እነዚሁ ፕሮጀክቶችም ትምህርት፣ መንገድ፣ ግብርና፣ የመጠጥ ውኃ፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪ፣ ከተማ ልማት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ቀጣዩ የበጀት ዓመትም ለድህነት ተኮር ዓላማዎች ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
የፀደቀውን አጠቃላይ የ2011 ዓ.ም. በጀት ለመሸፈን የገቢ ምንጭ ሆነው የተቀመጡት የአገር ውስጥ ታክስና ሌሎች የአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፣ የውጭ ብድርና ዕርዳታ ሲሆኑ ቀሪው ምንጩ ያልታወቀ በመሆኑ የበጀት ጉድለት በመሆን ተለይቷል፡፡ ጉድለቱ የሚሸፈነው ከዚህ ቀደም የአገር ውስጥና በውጭ ብድር የነበረ ቢሆንም፣ በ2011 ዓ.ም. ግን ይኼንን ጉድለት በአገር ውስጥ ብድር ብቻ ለመሸፈን ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ ይሆናል የተባለው የአገር ውስጥ ብድር ማለት የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ (ትሬዥሪ ቢል) እና ከብሔራዊ ባንክ የሚገኝ ብድር የሚል መጠሪያ በመንግሥት የሚሰጠው ብር የማተም ድርጊት ነው፡፡
በዚሁ መሠረት የ2011 ዓ.ም. በጀትን ለማሟላት ከአገር ውስጥ ታክስና ሌሎች የገቢ ምንጮች፣ እንዲሁም ከውጭ በድርና ዕርዳታ 287.6 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡
የገቢ ምንጭ ተብሎ ከተለየው 287.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ የውጭ ብድርና ዕርዳታ 20 ቢሊዮን ብር ገደማ፣ የአገር ውስጥ ታክስ ደግሞ 211.1 ቢሊዮን ብር ድርሻ እንደሚኖራቸው ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ከአጠቃላይ የቀጣዩ ዓመት 346.9 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ የበጀት ጉድለት ሆኖ የተመዘገበው 59.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የበጀት ጉድለት የሚሸፈነው ከአገር ውስጥ ብድር (ብር ማተም) ስለሆነ የዋጋ ንረት እንደሚያስከትል ቢታመንም፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት በሚኖረው ድርሻ 2.3 በመቶ መሆኑን፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛ ከሆነው ሦስት በመቶ በታች እንዲሆን በመደረጉ የዋጋ ንረት እያስከትልም ባይባልም የጎላ ተፅዕኖ እንደማይኖረው ግን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
ይህ ቢሆንም የበጀት ጉድለቱ ከታቀደው በላይ ሊሰፋ የሚችልባቸውን የሚያመላክቱ ሥጋቶች ይታያሉ፡፡ የዚህም ዋነኛ መንስዔው ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሰበሰበው የአገር ውስጥ ገቢ ከዕቅድ በታች እየሆነ መምጣቱ፣ በተለይም በ2010 ዓ.ም. ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 201 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ እንደማይሰበሰብ ከወዲሁ መረጋገጡ፣ በ2011 ዓ.ም. በጀት የገቢ ምንጭ ላይ ግን ከዚሁ ከአገር ውስጥ ታክስ ገቢ 211 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ መደረጉ፣ ከእውነታው የተቃረነ ወይም ልዩ የታክስ አሰባሰብ ሥርዓት ማሻሻያ ተግባራዊ ተደርጎ ዕቅዱን ማሳካት ካልተቻለ የበጀት ጉድለቱን በእጅጉ የሚያሰፋው በመሆኑ ነው፡፡
ከተያዘው 346.9 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት 59.3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መኖሩ፣ የታክስ ገቢ ዘንድሮ ከታያበት 50 ቢሊዮን ብር ጉድለትና የዘንድሮ በጀት የገቢ ምንጭ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ የሚገኝ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ቢቻል እንኳን፣ የሚገኝበት የጊዜ ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ ሥጋትን የሚያጭር መሆኑ አጠያያቂ አለመሆኑ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በ2010 ዓ.ም. መታየቱን ከሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ማብራሪያ መረዳት ይቻላል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በ2009 ዓ.ም. እንደሚሰበሰብ ከታቀደው የታክስ ገቢ ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ያልቻለ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ 50 ቢሊዮን ብር አይሰበሰብም፡፡ ‹‹የዚህ አንድምታ በመንግሥት ወጪ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ወጪዎች ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት እንዲተላለፉ መንግሥት ይገደዳል፡፡ ይህም የበጀት ጫና ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሚኖረው ትልቁ ጉዳት ለኅብረተሰቡ መድረስ ያለባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እንዲጓደሉ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከበጀት ጫና ወጪ የመንግሥት ራስ ምታት የሆነው የውጭ ምንዛሪ ግኝት መሆኑም ይታወቃል፡፡ የአንድ አገር ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እንቅስቃሴ መገኘት ካልቻለ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ችግር ስለመኖሩ አመላካች እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡
በ2010 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር መሆኑን፣ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ እንኳን መድረስ አለመቻሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ በዓመት 13 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ግዥ እንደምትፈጽም ገልጸው፣ ‹‹በኤክስፖርት ዘርፍ የሚታየውን የገቢ ማሽቆልቆል መፍታትና መሠረታዊ ለውጥ መፍጠር ካልተቻለ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ዘላቂነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚከተው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ችግር መፍታት የሚያስችሉት የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2011 ዓ.ም. በጀትን ለማፀደቅ ዓርብ ሰኔ 29 ቀን በምክር ቤቱ በመገኘት ኢኮኖሚውን ከገጠመው ፈተና ለማላቀቅ፣ የበጀት ፖሊሲ የትኩረት ነጥቦችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመፍትሔ መንገድ
‹‹ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት ለውጥ ከሆነ ገና ሦስት ወር በመሆኑ፣ በሚቀጥለው ዓመት ዝርዝር ጥናት አድርገን እስከምንዘጋጀ ድረስ የተሟላ ዕውቀትና ችግሮችን በሚቀርፍ አግባብ የተዘጋጀ በጀት ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፤›› በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ይህ ቢሆንም ከመሠረታዊ የአገሪቱ ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ የቀረበ በጀት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዚህ ማሳያ የሚሆነው እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ለ2011 ዓ.ም. የቀረበው አጠቃላይ የአገሪቱ በጀት ድህነት ቅነሳ ላይ ትልቅ ትኩረት ተደርጎ ድልድል መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከአጠቃላይ የቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 64 በመቶ የሚሆነው ለድህነት ቅነሳ ዘርፎች የሚውል መሆኑን፣ ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ብልጫ ያለው የበጀት ድልድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣዩ የበጀት ዓመት ዝርዝር ጥናት ላይ በመመሥረትና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያቶች በማጥናት የበጀት ፖሊሲ እንደሚነደፍ ገልጸው፣ ለዚህም ሲባል የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር እንዲደራጅ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካተታቸውን፣ የማማከር ሥራውንም ለአገራቸው በነፃ ለማበርከት ፈቃደኛ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡
የቀጣዩ ዓመት በጀት ለድህነት ቅነሳ ትኩረት የሰጠ ቢሆንም፣ ኢኮኖሚውን ለማስቀጠል የሚረዱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለጊዜው ገታ በማድረግ የተጀመሩትን ማጠናቀቅ ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
ኢኮኖሚው የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ በዋነኛነት ትኩረት እንደሚሰጥ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከነዚህም መካከል የኤክስፖርት ዘርፍና ከዘርፉ የሚገኘውን እጅግ ዝቅተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ለመቀየር መዋቅራዊ መፍትሔ እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡
‹‹ኤክስፖርት መር ኢኮኖሚ እንደምንከተል በተደጋጋሚ ብንናገርም በምንናገረው ልክ አልሠራንም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዋናነት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለኤክስፖርት ዘርፉ ጥንካሬ ተቀዳሚ ምርጫ ተደርጎ መንግሥትም በዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት ቢያደርግም፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የተንጠለጠለው ግን በአነስተኛ የግብርና ዘርፍ ምርቶች ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢኮኖሚው አሁን በደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ያለበት ስለሆነ፣ ይኼንን በውጭ ብድርና ዕርዳታ ሳይሆን በአገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መመለስ ካልተቻለ ኢኮኖሚው እንደሚጎዳ በዝርዝር ማየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ አመራር በተለየ ሁኔታ ከሚደራጁት አንስቶ ለዘርፉ የሚደረገውን ሀብት ማሻሻል፣ ዘርፉን ከላይ እስከ ታች ማዘመን እንደሚገባና ለዚህም መንግሥት ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የሆርቲካልቸር ዘርፉ ዕምቅ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው አስረድተዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በጥሩ መሠረት ላይ ተመሥርቷል የሚባለው ግብዓቱ በአገር ውስጥ ሲመነጭ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ያለው ሁኔታ ይኼንን አይገልጽም ብለዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኤክስፖርትን ይመራል የሚል የፖሊሲ አቅጣጫ ቢቀመጥም፣ ለዚህ ዘርፍ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉ ምርቶች በአብዛኛው በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባ በመሆኑ፣ እንዲሁም ከዚህ ዘርፍ መገኘት የሚገባውን ሀብት የማሸሽ አሻጥር በመስፋፋቱ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ይወጣበታል እንጂ እያስገባ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው ሀብት ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች እንኳን ያነሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ከላይ እስከ ታች ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኤክስፖርት ግኝትን ለማስፋት ትኩረት የሚደረግበት ሌላው ዘርፍ የማዕድን ሀብት እንደሚሆን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ዕምቅ ሀብት አገሪቱ እስካሁን እየተጠቀመች እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለይ አገሪቱ ካላት የወርቅ ሀብት የሚገባትን እያገኘች አለመሆኑን በመጥቀስ ትልልቅ ኩባንያዎች በወርቅ ምርት እንዲሰማሩ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት ትኩረት የሚደረግበት የቱሪዝም ዘርፍ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ስድስት ሚሊዮን መንገደኞችን ወደ ተለያዩ አገሮች ለማጓጓዝ አዲስ አበባን እንደ መሸጋገሪያ (ትራንዚት) የሚጠቀም ቢሆንም፣ መንገደኞች በአዲስ አበባ አንድ ቀን አድረው ወጪ እንዲያወጡ የሚያስችሉ የቱሪዝም አገልግሎቶችን ለማቅረብ እየተቻለ ትኩረት አለመሰጠቱን አስረድተዋል፡፡ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እያመለጣት እንደሆነ ብቻ ተገንዝቦ መሥራት በራሱ ትልቅ የገቢ ምንጭ እንደሚሆንና በዘርፉ ላይ ምን ያህል እንዳልተሠራ አብራርተዋል፡፡
የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቀጣይነት ማረጋገጥ ከተፈለገ ትኩረት ተሰጥቶ መፈታት ያለበት ሌላው ችግር፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት የሚገኘው የታክስ ገቢ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ መሠረታዊው ጉዳይ የታክስ አስተዳደሩን ማዘመን ዋነኛ መሆኑን የጠቀሱት ጠቀላይ ሚኒስትሩ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡ ታክስ ላለመክፈል ባለሀብቶች ሀብታቸውን እየደበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ያሉ መቶ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በሕግ መሠረት ታክስ ቢከፍሉ እንኳን ትልቅ ገቢ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል፡፡
ሌላው ጉዳይ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ግንባታ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ የሆነ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም፣ እነዚህ ድርጅቶች ከፋይዳቸው ይልቅ ጉዳታቸው እያመዘነ በመሆኑ አዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር የታገደ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ምክንያቱን ሲያስረዱም እነዚህ የልማት ድርጀቶች በግል ባለሀብቱ የማይደፈሩ ዘርፎች ውስጥ ገብተው ኢኮኖሚውን እንዲያንቀሳቅሱ ታልሞ የተመሠረቱ ቢሆንም፣ ተቋማቱን ግዙፍ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ሳይጨነቁ ለመጀመር ደፋር ሆነው ለማጠናቀቅ ቁርጠኝነት የማይታይባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እነዚህ ድርጅቶች ከውጭ የተበደሩት ይቅርና ከአገር ውስጥ ተበድረው ያልመለሱት 400 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከፋይናንስ አስተዳደራቸው ጀምሮ እስከ ኮርፖሬት አስተዳደር ድረስ ጥልቅ ምርመራ ተካሂዶ እስኪጣራ ድረስ አዲስ ፕሮጀክት እንደማይጀመር ተናግረዋል፡፡
‹‹የቀረበው በጀት ለታለመለት ዓላማ ካልዋለ ዋጋ የለውም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁሉም የመንግሥት አመራር ኃላፊነት እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡