Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተነፍገናል ያሉ የሸኮ ብሔረሰብ ተወካዮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ...

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተነፍገናል ያሉ የሸኮ ብሔረሰብ ተወካዮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

ላለፉት 27 ዓመታት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተነፍገናል ያሉ የሸኮ ብሔረሰብ አባላት በግፍ አጥተነዋል ያሉት መብት እንዲከበርላቸው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቤቱታ አቀረቡ፡፡

      የሸኮ ብሔረሰብ አባላት ሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወካዮቻቸው አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት አቤቱታ እንደሚያመለክተው፣ ኢሕአዴግ አገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፊት በደቡብ ክልል ጉርፋርዳ፣ የኪና መሀል ሸኮ የተሰኙ ሦስት ወረዳዎች ውስጥ በ80 ቀበሌዎች እስከ 500 ሺሕ የሚገመት የሸኮ ሕዝብ ይኖር እንደነበር ገልጸዋል፡፡

      ነገር ግን ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የብሔርና ብሔረሰቦች መብት ሲከበርና ብሔርና ብሔረሰቦች በዞንና በወረዳ ተደራጅተው ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ፣ ባህል፣ ቋንቋና፣ ወጋቸውን ሲያሳድጉ የሸኮ ብሔረሰብ ግን ለዚህ አለመታደሉን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      ‹‹የሾኮ ብሔረሰብ ላይ የደቡብ ክልል መንግሥት ባሳደረው ተፅዕኖ ቤንችና ሸካ በሚባሉ የሁለት ብሔረሰቦች ዞኖች ሥር ለሁለት ተከፍለንና ተሰግስገን እንድንኖር ተደርገናል፤›› ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ ያቀረቡት የሸኮ ብሔረሰብ አባላት፣ ‹‹በቋንቋችን መማር አልቻልንም፡፡ በሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ራሳችንን ችለን ልንቆጥር አልቻልንም፡፡ ራሳችንን እያስተዳደርን ባለመሆኑ ከፍተኛ አስተዳደራዊ በደል እየደረሰብን ነው፤›› ሲሉም አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡

       ‹‹እስከ ደርግ ውድቀት ማግሥት ድረስ የቤንች ብሔረሰብ ጠንመጃጅ የሚባል አንድ ወረዳ ብቻ ነበረው፡፡ የሸካ ብሔረሰብም አደራቻና ማሻ የሚባሉ ሁለት ወረዳዎች ብቻ ነበሩት፡፡ ነገር ግን ከደርግ ውድቀት በኋላ ቤንች ብሔረሰብ ጉፈርዳንና መሀል ሸኮ ወረዳዎችን ወስዶብናል፡፡ ሸካም እንዲሁ የኪ ወረዳን ወስዶብናል፤›› ብለዋል፡፡

      ‹‹ሁለቱም ብሔረሰቦች ያሉንን ወረዳዎች ተከፋፍለው ወስደውብናል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛ (ሸኮ) የምናስተዳድረው ወረዳ የለንም፤›› ሲሉ በደብዳቤያቸው አስረድተዋል፡፡

       ‹‹ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፈንን የማንነት መብት ከመታፈኑ በተጨማሪ፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋችንን (ሸኮኛ) ትተን የእነሱን ቋንቋ እንድንማር ተገደናል፡፡ በሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ወቅት የእነሱ ማሟያ ተደርገናል፤›› ሲሉም አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡

      የሸኮ ብሔረሰብን ወክለው አዲስ አበባ በመምጣት የአቤቱታ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገቡት አቶ አንድሪስ በዲና አቶ ባሳ ባንጨሾ ናቸው፡፡

      አቶ አንድሪስ ለሪፖርተር ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን በመጠየቃችን ብቻ ላለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ በደል ደርሶብናል፡፡ የሄድንባቸው ቦታዎች በሙሉ በደላችንን የሚያበዙ ነበሩ፡፡ አሁን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የለውጥ ሰው በመሆናቸው ችግራችንን ይፈታሉ ብለን ነው የመጣነው፤›› ብለዋል፡፡

      ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን በመጠየቃችን ብቻ ከ1885 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ከ500 በላይ የሸኮ ሕዝብ ተጨፍጭፎ ተገድሏል፡፡ በጅምላ ተቀብሯል፡፡ ይህንን ያደረጉ ባለሥልጣናት ግን ዛሬም ድረስ ከሥልጣን ወደ ሌላ ሥልጣን ዕርከን እየተሸጋገሩ ነው፤›› ሲሉ አቶ አንድሪስ ተናግረዋል፡፡

      አቶ አንድሪስ ጨምረው፣ ‹‹የጎሳ መሪያችን አባ ፈተሸ ሾሻን ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀብር በሚል ምክንያት አዲስ አበባ በመውሰድ ሰውረውብናል፡፡ የጎሳ መሪያችን በሕይወት ካሉ እንዲያመጡ፣ ከተገደሉም ገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

      አቶ ባሳ በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ለ27 ዓመታት ከ500 በላይ የሸኮ ተወላጆችን ያስገደሉና የገደሉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም የት እንደተቀበሩ የማይታወቁ ወገኖች ስላሉ በክብር የሚያርፉበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡

      የሸኮ ብሔረሰብ አባላት ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸው መብት እንዲከበርና የታሰሩ ወገኖቻቸው እንዲፈቱ፣ በአጠቃላይም ለብሔረሰቡ ፍትሕ እንዲሰጥ ተወካዮቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...