Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአገር ሽማግሌዎች መድረክ በሰላምና በአንድነት ላይ የሚመክር አገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሊያካሂድ ነው

የአገር ሽማግሌዎች መድረክ በሰላምና በአንድነት ላይ የሚመክር አገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሊያካሂድ ነው

ቀን:

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያደረጉ ያሉትን ንቅናቄ መደገፍ አለብን››

የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ

የኢፌዴሪ ሁለተኛው ፕሬዚዳንት በነበሩት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የበላይ ጠባቂነት የሚመራው የአገር ሽማግሌዎች መድረክ በአገሪቱ የተጀመረውን የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተባበር፣ አንድ የመሆንና የመደመር እንቅስቃሴ ላይ የሚመክር አገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ ለማካሄድ ዝግጅቱን መጨረሱን አስታወቀ፡፡

ተደማጭነትና ተቀባይነት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦችና ወጣቶች የተሰባሰቡበት መሆኑ በተገለጸው የአገር ሽማግሌዎች ኮንፈረንስ የዘጠኙም ክልሎች የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ በተለይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ወገኖችን ጨምሮ፣ ከ1,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡

 የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ ምክክር መድረክ ሰብሳቢ፣ ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር) ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ የመድረኩ የኮሚቴ አባላት ሐሙስ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የኮንፈረንሱ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ኮንፈረንሱ በቅርቡ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል እንደሚካሄድ፣ ኮንፈረንሱ አንድ ጊዜ ብቻ ተደርጎ የሚያበቃ አለመሆኑን፣ በፌዴራል ደረጃ በየሁለት ዓመቱ እየተደረገ በአጠቃላይ ስለአገሪቱ ሰላም፣ ልማት፣ ፍቅርና አብሮ የመኖር የዘመናት እሴት ላይ በመመካከርና በመወያየት ጥሩ ጥሩው ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን፣ በክፍተቶቹ ላይ ዕርማት የሚወሰድበትን ሁኔታዎች እያመቻቸ በቋሚነት የሚቀጥል መሆኑን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡ በክልሎች በየዓመቱ ኮንፈረንሱ እንደሚደረግና በዞን፣ በወረዳና በቀበሌዎችም እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡

መድረኩ 65 አባላትን ይዞ የተቋቋመው ከስምንት ወራት በፊት መሆኑን የጠቆሙት ሰብሳቢው፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ነዋሪዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ‹‹ከአገር ሽማግሌዎች ውጪ ሌላ አካል ሊፈታው አይችልም›› በሚል ሐሳብ መሆኑን፣ ይኼም በሁለቱ ክልሎች ፕሬዚዳንቶችና በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች መካከል ተቀባይነትን ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡ ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ ከ300 በላይ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ውይይት በጅግጅጋ ከተማ አካሂደው፣ 100 ነዋሪዎች ተመርጠው ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ወደ ፌዴራል መንግሥት እንዲመጡ ያደረገው መድረኩ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው የመፍታት ትልቅ እሴት እንዳላቸው የገለጹት ሰብሳቢው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሁሉም ክልሎች ባለሥልጣናት፣ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ ወገኖች፣ የሁሉም ሃይማኖት ተወካዮችና መሪዎች የሚገኙበት ኮንፈረንስ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡ ለኮንፈረንሱ ዝግጅት የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ሚኒስቴር አብሯቸው እየሠራ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ፣ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና ክልሎችም ለዝግጅቱ ወጪ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ቃል እንደገቡላቸውም ተናግረዋል፡፡ የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ ‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያገባናል!›› የሚል ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረግ መሆኑን አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ሕዝቦቿ በቂ የሆነ የተፈለገው ዓይነት ሀብት ያላት ቢሆንም፣ ይኼንን ሀብት መጠቀም የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ሳያውቁ ወዳልተፈለገ ግጭት ውስጥ የገቡ ወይም ሌላ አመለካከት ኖሯቸው ወደ ግጭት የገቡ ወንድሞችና እህቶች፣ ወደ ራሳቸው እንዲመለሱና የሰላም ዘማሪ እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡ ‹‹የተመረጥንና የተከበርን ሕዝቦች ባለንበት መቀጠል አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ አጭር ጊዜ ውስጥ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴና ሥራ የሚያስደስት፣ አገሪቱንም ወደ ፈጣን የልማትና የሰላም ዕርምጃ የሚወስዱ አበረታች፣ አስደሳችና ለአገሪቱም ዕድገት የሚያመጣ መሆኑ ታውቆ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊደግፈው እንደሚገባ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አሳስበዋል፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተገበሯቸው የሚገኙ የሰላምና የልማት እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት በእሳቸው የሚመራው ኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ መድረክ 16 ምክረ ሐሳቦችን ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

በየትኛውም ክልል ለሚቀርቡ ሕዝባዊ ጥያቄዎች መንግሥት በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር ተወያይቶ ምላሽ እንዲሰጥ፣ ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ፣ ለመላ አገሪቱ የሚጠቅም የምሕረትና የይቅርታ አዋጅ ቢታወጅ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን መጥበብ አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መወያያ መድረክ ቢዘጋጅ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና ወገንተኝነት የፀዳ ባለሙያ በሙያው መስክ ቢመደብ፣ ለሙስና አፋጣኝና ሥር ነቀል መፍትሔ ቢሰጥ፣ ለፍትሕና ለርትዕ ጥያቄዎች በአግባቡ ፈጣን ምላሽ ቢሰጥ፣ ሥር ነቀል የሚዲያ ነፃነት እንዲሰፍን ቢደረግ፣ የአገሪቱ ሰላምና ልማት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል በወቅታዊ ችግሮች ላይ ሕዝብና መንግሥት የሚወያዩባቸው የተለያዩ የምክክር መድረኮች እንዲዘጋጁና ሌሎችንም ምክር ሐሳቦች ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን መድረኩ ያቀረባቸው 16 ምክረ ሐሳቦች በወቅቱ ባይተገበሩም፣ በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተገበሩት ስለሆነ፣ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የመድረኩ አባላት ደስተኛ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚገናኙበትን መንገድ ለመፍጠር እየጣሩ እንደነበር የገለጹት አቶ ግርማ፣ ‹‹እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜ ዝምታው ተሰብሮ ሰላም በመውረዱ ተደስቻለሁ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ የምትጠቀምበት ሁኔታ እንደሚኖር ግምታቸውን ገልጸው፣ የሁለቱ አገር ሕዝቦችም በፓስፖርት ሳይሆን በቀበሌ መታወቂያ የሚገናኙበት ሁኔታ በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መነገሩ ትልቅ ጅምር መሆኑን አክለዋል፡፡

የመድረኩ ኮሚቴ አባላት ፕሮፌሰር ዘካርያ አህመድ፣ ታደሰ ብጡል (ኢንጂነር)፣ ወ/ሮ ዓይሻ መሐመድና ሌሎችም አባላት አሁን እየታየው ያለው ሰላም አስደሳች መሆኑን፣ በተለይ ለሴቶች ሰላም እግጅ አስፈላጊ መሆኑንና ምክንያቱ ደግሞ ተደራራቢ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ እንደሆነ በመግለጽ ሰፋ ያለ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡. 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...