Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅሠርጓ ቢሰረዝም የሠርጓን ዕለት በተለየ ሁኔታ ያሳለፈችው ሙሽራ

ሠርጓ ቢሰረዝም የሠርጓን ዕለት በተለየ ሁኔታ ያሳለፈችው ሙሽራ

ቀን:

ለሠርጋቸው ዕለት ሁሉ ነገር ተሰነዳድቶና ተዘገጃጅቶ ባለቀበት ሁኔታ እጮኛዋ ለ23 ዓመቷ ሼልቢ ስዊንክ ጋብቻውን እንደሰረዘው የገለጸላት ከሠርጋቸው ዕለት አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ነበር፡፡ የ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ እንደሚያመለክተው ይህን ተከትሎ ሙሽሪት ሁሉን ነገር መሰረዝ ነበረባት፡፡ የእንግዶችን ጥሪ ጨምሮ ሁሉንም በጋብቻው ዕለት ሊካሔዱ ታቅደው የነበሩ ፕሮግራሞችን ሰረዘች፡፡ አንድ ነገር ግን አልሰረዘችም ነበር፡፡ የፎቶግራፍ ፕሮግራሟን፡፡

የፎቶግራፍ ፕሮግራሟን የታደሙት ግን እሷ፣ ሚዜዎቿና ወላጆቿ ብቻ ነበሩ፡፡ የፎቶግራፍ ፕሮግራሙም እንደዚሁ የተለመደ ዓይነት አልነበረም፡፡ ሁሉም የፎቶግራፍ ፕሮግራሙ ታዳሚዎች ስፕሬይ ቀለም ይዘው በመሰላቸው መንገድ የሙሽሪትን ቬሎ በተለያዩ ቀለማት ማቅለም ጀመሩ፡፡ የሚዜዎቹ ቀሚስም በተመሳሳይ መልኩ በቀለም ማሸብረቁን ያዘ፡፡ ‹‹ቀሚሴ እንደዚያ ቀለም ሰያርፍበት ነፃነት ተሰማኝ፡፡ የነበረብኝ የብስጭትና የሀዘን ስሜት ለቆኝ የሔደ ያህል ተሰማኝ፡፡ የተሰማኝን ነገር በትክክል በቃላት መግለጽ አልችልም፡፡ ብቻ ሁሉንም ነገር ትቼ እንደገና ራሴን መሆን የጀመርኩበት አጋጣሚ ነው›› ብላለች ሙሽራዋ ስዊንክ፡፡

********************

ተሰሚን ፍለጋ!!

‹‹የራበኝ ፍቅር›› – እንዳለችው እሷ – በዜማ በቅኔ
ዕድሜየን በሙሉ – ሲርበኝ ይኖራል – እየሻትኩት እኔ፤

ፍቅር ብቻ መስሎኝ – የእስከዛሬ እመሜ – የእስከዛሬ ራቤ
ሰላምን፣ ፍትህን፣ እኩል መታየትን – እየተራብኩ አለሁ – ደርቤ ደርቤ
ተ-ር-ቤ ተርቤ – ተርቤ ተ-ር-ቤ

የሚሞረሙረኝ – ሆዴን የሚፍቀው – የሚሸረክተው
ራቤ በዛና – አስታዋሽ አጥቼ – ‹‹ራብ››ን የሚል ተው፤
በዛበት መሰለኝ – ዛለ ሰውነቴ
ራብም ራበኝ – ግልብጥብጤ ወጣ – ተዛነፈ እውነቴ፤

‹‹ራብ ግን ምንድን ነው?›› – አልክ አሉ አንት ጓዴ
‹‹ራብተኛስ የታል?›› – አልክ አሉ አንት ጓዴ
ከዚህ ሁሉ መሀል – ከሚተራመሰው
ሽቅብና ቁልቁል – ከሚንከላወሰው
መንገድ ላይ የተኛ – ባታይ የወደቀ
አካሉ የከሳ – ጎኑ የደቀቀ
የሌለ እንዳይመስልህ ……
ሆዱ የተራበ፣
ልቡ የተራበ፣
አዕምሮው የተራበ፣
ዓይኑ የተራበ
ሁ-ሉ-ን የተራበ…..
ስለከለለህ ነው – ቦርጩ የተነፋ – በልቶ የጠገበ!!

ምናልባት ቢሰሙህ – አንተን ከኛ አብልጠው
(ያው የኛን አንደበት – የመደመጥ እጦት – ስለገሸለጠው)
አንተ እንዲህ በልልን…
‹‹ጠግባችሁ እናንተ – በበርሜል ስትደፉ
ኑሮን ከዓለም በላይ – ባያሌው ስትገፉ
ህይወት ለመቀጠል
ትራፊ ልመና – ቆመናል ከደፉ፡፡››

  • በደመቀ ከበደ

*****

ባዶ ክብር

የገረመኝ መዋሸቱ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ላምነው አለመቻሌ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንዲት እውነት ማውራት የማይሆንላት ወጣት፣ እጮኛዋና እርሷ ስላሳላፉት ጥሩ ጊዜ ለጓደኛዋ ስታወራላት እንዲህ አለች፡- ‹‹እጮኛዬ ፓይለት እንደሆነ ታውቂያለሽ አይደል?›› (ልብ በሉ! ጓደኛዋ ፓይለት አይደለም)፡፡

‹‹አንድ ቀን በግሉ አይሮፕላን ሊያንሸራሽረኝ ፈልጎ ጠዋት ከቦሌ ተነሥተን እየበረርን ሰበታ አረፍን›› አለቻት፡፡ የምታዳምጣት ጓደኛዋም ‹‹እንዴ!… አንቺ? ሰበታ አይሮፕላን ማረፊያ አለ እንዴ?›› ስትላት ልጅቷም ‹‹ውይ! ሰበታ አልኩ እንዴ ወልቂጤ እኮ ማለቴ ነው›› በማለት ሸመጠጠች፤ አሁንም ጓደኛዋ ‹‹አንቺ! አሁንስ አበዛሽው! ወልቂጤ እኮ አይሮፕላን ማረፊያ የለም!›› ብትላትም ‹‹አይ አይደለም ተሳስቼ ነው ሱሉልታ ማለቴ እኮ ነው›› ብላ የውሸት ድፍረቷን ቀጠለች፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ከተሞችን ስትጠራ ከቆየች በኋላ በመጨረሻም አላፈናፍን ያለቻት ጓደኛዋ ‹‹… ዛሬ በሰማይ ላይ ስትበሪ ትቆያለሽ እንጂ አታርፊያትም…›› ብላ ቀለደችባት፡፡

አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች የመዋሸት ምክንያት ሳይኖራቸው ዝም ብለው የሚቀጥፉበት አጋጣሚ አለ፡፡ መዋሸት ግን ከመከበር ይልቅ ያዋርዳል፡፡ በሰዎች ዘንድ ከፍ ከመደረግ ይልቅ በተቃራኒው ሐፍረትን ያከናንባል፡፡

የሰው ክብሩና መመዘኛው ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ!›› ‹‹እንዲህና እንደዚህ ዓይነት ሀብት አለኝ›› የሚለው ባዶ ክብር አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት የውሸት ተግባራት ከመከበር ይልቅ ውርደትን ያመጣሉ፡፡

በውሸት ራሳችንን ከፍ ስናደርግ ባዶነታችንን ማሳየታችን እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ አበው ‹‹ባዶ ዕቃ ብዙ ድምጽ ያሰማል!›› ይላሉ፡፡ ባዶ የሆነ ሰው ስለራሱ ብዙ ጉራዎችን መንዛቱ መታወቂያው ነው፡፡ ስለራሳችን ጉራ ስንነዛ ግን ባዶነታችንን ትልቅ ማድረጋችን እንደሆነ እናስተውል፡፡ ፊኛ ትልቅ ቢመስልም በመርፌ ነካ ሲደረግ ግን ውስጡ ባዶ ነው፡፡ ሀሰተኛ ሰውም እንደፊኛ ራሱን ከፍ ቢያደርግም አንድ ቀን በእውነት መርፌ ሲነካ ባዶ መሆኑ ይገለጥበታል፡፡

  • ዳንኤል ዓለሙ (የምሕረት ልጅ) ‹‹ራስን የመለወጥ ምሥጢር›› (2005)

**********************

ስኳር እንዴት ጤናን ይጐዳል?

የዜጐችን ከፍተኛ ስኳር ተጠቃሚ መሆን ለመከላከል አገሮች እንደ ለስላሳ መጠጦች ባሉ ጣፋጭ ነገሮች ከፍተኛ ታክስ እስከመጣል እየደረሱ ነው፡፡ አምራቾች ላይ የሚጣለውም ታክስ በሚያመርቷቸው ጣፋጭ ነገሮች ላይ በሚያኖሩት ስኳር መጠን እንዲሆን ያደረጉ አገሮችም አሉ፡፡ የስኳር ንጥረ ነገር በፍራፍሬ ውስጥ እንደሚገኘው በተፈጥሮ፤ በምርት ሒደት ውስጥም የተለያዩ ነገሮች ላይ ሊጨመር ይችላል፡፡

አጥኚዎች እንደሚሉት ስኳር እንደ ጨው በራሱ ጐጂ አይደለም፡፡ በቀጥታ ጐጂ የሚሆነው ለጥርስ ብቻ ነው እንጂ፡፡ ስኳርን በመጠነኛ ሁኔታ መጠቀም ለጤና ጐጂ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ከስኳር የተገኘ ኃይል በሰውነት ጥቅም ላይ ካልዋለ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ሊያስከትል ለስኳር በሽታም ሊዳርግ ይችላል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ከመጠን ያለፈ ስኳር ለከፍተኛ ውፍረት፣ ለልብ ሕመምና ለስኳር ያጋልጣል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...