አምና (መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም.) በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ደርሶ የነበረውን የሰደድ እሳት ለማጥፋትና የዱር እንስሳትና ዕፀዋትን ለመታደግ ሲንቀሳቀስ ሕይወቱን ላጣው ለአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው አቶ ቢንያም አድማሱ በፓርኩ ቅጥር ግቢ ሐውልት ቆመለት፡፡ ከብሔራዊ ፓርኩ በተገኘው መረጃ፣ አንደኛ ሙት ዓመቱን አስመልክቶ መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገው የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት፣ በዲንሾ የፓርኩ ዋና መግቢያ ላይ የታነፀው የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ ሐውልቱ የወጣቱን የደን ሕይወት የሚያሳይ ሲሆን ታሪኩን የያዘ ማስታወሻም ተጽፎበታል፡፡ በቢኒያም አድማሱ ስም የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎችን የሚሸልም የመታሰቢያ ሽልማት ድርጅት ለማቋቋም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ መቀጠሉን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ በ33 ዓመቱ በእሳት አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም አማካሪ የነበረው አቶ ቢንያም፣ ከአካባቢ ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ጋር የተያያዘ ሥራ በሚሠራው ፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ ባልደረባና የቱሪዝም ልማት አማካሪ የነበረ ሲሆን፣ ከተቋሙ ጋር በመሆን በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአቡነ ዮሴፍ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ፣ በመንዝ ጓሳ ጥብቅ ስፍራ፣ በአርሲ አካባቢዎችና በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አያሌ ሥራዎችን ማከናወኑ ይነገርለታል፡፡ ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘውና በ1962 ዓ.ም. የተቋቋመው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ጠቅላላ ስፋቱ ከ2,200 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል ከ1,500 ጫማ እስከ 4,377 ጫማ የሚለካ ከፍታ አለው፡፡ የደጋ፣ የወይና ደጋና የቆላ ሥነ ምኅዳሮችና ትልልቅ የዕፀዋት (ቨጂቴሺን) ዞኖች አሉት፡፡