Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የሕይወቴ ምስጢር››

‹‹የሕይወቴ ምስጢር››

ቀን:

‹‹ግለ ታሪኩን የሚደርስ አብዛኛው ጸሐፊ፣ መጀመርያ ማነኝና ነው ግለ ታሪኬን የማውጀው?›› የሚል ጥያቄ በውስጡ፣ የሚያብሰለስል ይመስለኛል፡፡

እንደ ማር የጣፈጠና ሰማይ ምድርን ያንቀጠቀጠ ግለ ታሪክ ለንባብ በበቃበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የኔ ግለ ታሪክ መቅረብ የቱን ያኽል ፋይዳ ይኖረዋል? ይህንና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎችን በመልኩና በግልባጩ አስመስክሮ የግለ ታሪክን አከታተብ ዘዴዎችን በአንጻራዊነት መዝኖና አበጥሮ፣ ልዩነታቸውንና አንድነታቸውን መርምሮና በጥሞና አለዝቦ፣ ለ‘ራሱ ጥያቄ የራሱን መልስ ካገኘ በኋላ ነው፣ ይህ ደራሲ ብዕሩን ያነሳው፡፡›› የሚሉት፣ አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ናቸው፡፡ መሰንበቻውን ‹‹የሕይወቴ ምስጢር ግለ ታሪክ›› የተሰኘ መጽሐፋቸውን ለአደባባይ አብቅተዋል፡፡

የሩቁን ትተን በቅርቡ ከዐሠርት ወዲህ በአማርኛ ለንባብ ከበቁ መጻሕፍት መካከል የፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ‹‹የሕይወቴ ታሪክ – ኦቶባዮግራፊ››፣ የተመስገን ገብሬ ‹‹የሕይወቴ ታሪክ›› የልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ካየኹትና ከማስታውሰው››፣ የአቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ ግለ ታሪክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የነዚህን ፈለግ የተከተሉትና ‹‹ተከተል አለቃኽን፣ ተመልከት ዓላማኽን›› የሚለው ብሂል በመጽሐፋቸው መንደርደርያ ላይ የገለጹት አቶ አጥናፍ ሰገድ፣ ‹‹የሕይወቴ ምስጢር›› ካሉት ድርሳናቸው ላይ ‹‹የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ›› የሚል ንኡስ ርእስ አካትተውበታል፡፡

‹‹ነገርን ከሥሩ፣ ውኃን ከጥሩ›› እንዲሉ ደራሲው ዝክረ ልደቱንና ዕድገቱን ዕረኝነቱንና ዐውደ ትምህርቱን፣ የአስተማሪነቱንና የጋዜጠኝነቱን ጉዞ፣ በጠለፋ ካገቧት አጋራቸው ጋር የነበራቸውንና ያላቸውን የትዳር ሕይወታቸውን፣ በመንግሥት መዋቅር በአስተዳደር ውስጥ የነበራቸውን ኃላፊነት ከአገሪቱ ታሪክና ፖለቲካ ምሕዋር ጋር አሰናስለው አቅርበውበታል፡፡

በጋዜጠኝነታቸው ከጀማሪ ዜና ዘጋቢነት፣ የሙያው ቁንጮ እስከ ኾነው፣ ዋና አዘጋጅነት ደረጃ በደረጃ ያደጉት አቶ አጥናፍ ሰገድ፣ ከአገሪቱ ጋዜጠኝነት ታሪክ ጨልፈው ካላዩት ውስጥ ጋዜጠኞች ይፈጽሙት የነበረው ስህተትና የሚሰጣቸው ምላሽ ነበር፡፡ እንዲህም ይላል፡፡

‹‹ጋዜጠኞች፣ በምንጽፈው ስህተት፣ ብዙ ጊዜ በተግሳጽ ነበር የምንታለፈው፡፡ ስህተቱ ከበድ ካለ፣ በገንዘብ ተቀጥተን ወደ ሌላ ክፍል እንዛወር ነበር እንጂ፣ ተከ’ሰንና ተፈርዶብን ወህኒ የተወረወርንበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም፡፡ ይኸንን በማስረጃ ላንጥር፡፡

‹‹1951 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ይመስለኛል፡፡ መነን መጽሔት ዝግጅት ክፍል ሥራ እንደጀመርኩ፡፡ የቀድሞዋ ዩጐዝላቪያ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቲቶ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ ነበሩ፡፡ የጎበኙትን ዜና ባጀበ አንድ ፎቶግራፍ ሥር የተጻፈ መግለጫ፣ ‹‹ክቡር ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቲቶና ባለቤታቸው ክብርት ማዳም ዮባንክ ብሮዝ ቲቶ በተገኙበት ግርማዊ ኃይለ ሥላሴና ግርማዊት እቴጌ መነን ታላቅ የምሳ ግብዣ አደረጉ›› ማለት ሲገባው ‹በተገኙበት ከሚለው ቃል ውስጥ፣›  ‹ገ›  ፊደል ተገድፋ፤ ‹‹ምሳ› ከሚለው ቃል ደግሞ ‹ሳ› ፊደል በ‹ስ› ተተክታ መጽሔቱ ታትሞ ተሰራጨ፡፡ ሥርጭቱ በመገባደድ ላይ እንዳለ፣ ከክቡር አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ቢሮ ሥርጭቱ እንዲቆም፣ የተሰራጨውም መጽሔት ከጋዜጣ አዟሪዎች ላይ እየተገዛ እንዲቀመጥ ጥብቅ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ የመጽሔቱ የአማርኛ አዘጋጅ፤ አቶ መንግሥቱ መኮንና እኔ፣ ተጠርተን ሚኒስትሩ ቢሮ ሄድን፡፡ የተጠራንበትን ምክንያት አውቀነው ስለነበር ደንግጠናል፡፡ እንደ ደረስንም ግቡ ተባልንና ገብተን እጅ ነስተን ቆምን፡፡ ‹መንግሥቱ! ሥራው አቅቶኽ ከኾነ ተወው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ዜና እንደዚህ ተበለሻሽቶ የሚወጣበት መጽሔት … በእጅጉ ያሳፍራል›› በማለት ገስጸው አሰናበቱን፡፡ በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ በኋላም የሳምንታዊው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አቶ አጥናፍ ሰገድ ሌላኛው ገጠመኛቸውንም ገልጸዋል፡፡

‹‹ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ 1956 ዓ.ም. እንደነበር ትዝ ይለኛል፣ ሶማሊያ መንግሥት የ‹‹ታላቋ ሶማሊያን›› ግንባታ ቅዠቱን ለማሳካት፣ የውጋዴንን አውራጃ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል፣ በመደበኛ ጦርነትና በሰርጎ ገብ ግጭት ሲሞክር ነበር፡፡ የሶማሊያ ሰርጎ ገብ ሽፍታ በጋዜጣው መጀመርያ ገጽ ላይ በሚያሳይ አንድ ካርቱን ሥር One of the Somale Expansionist ‹‹ከሶማሊያ ገንጣይ ወንበዴዎች አንዱ›› በማለት የተጻፈው መግለጫ፣ ግርማዊነታቸው በስታዲየም ተገኝተው፣ ለአንድ በስፖርት አሸናፊ ለሆነ ቡድን አምበል ዋንጫ ሲሸልሙ ከሚያሳየው ፎቶግራፍ መግለጫ ጋር በማሳከር ‹‹His Imperial Majesty Haile Sillasse I awarding a trophy to one of the Somale expansionist ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ለአንድ የሶማሊያ ገንጣይ ወንበዴ ዋንጫ ሲሸልሙ›› በመባል ታትሞ ወጣ፡፡

‹‹በዚህ፣ ይሆናል ተብሎ በማይታሰብ ስህተት ምክንያት፣ የቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ከደመወዝ 400 ብር፣ እንደዚሁም ረዳት አዘጋጆች አንዳንድ መቶ ብር ተቀጥተናል፡፡››

ከነተከታዮቹ 312 ገጾች ያሉት መጽሐፉ፣ 24 ምዕራፎችን ከፎቶግራፎችና ከልዩ ልዩ ሰነዶች ጋር ይዟል፡፡ የመጽሐፉን ረቂቅ አንብበው አስተያየት ከሰጡት ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፡፡-

‹‹… የትዳር ሕይወቱን ውጣ ውረድ ያሳየበት መጽሐፍ ባልተኼደበት መንገድ የኼደበት ሥራው ነው፡፡ ሁላችንም የመጣነው ሁሉንም ነገር ‹ምሥጢር› ነው ከሚል ባህልና ሥርዓት ውስጥ በመሆኑ፣ ጀግንነታችንንና ድንቅ የሚባሉ ሥራዎቻችን ካልሆኑ በስተቀር፣ የአደባባይ ምስጢር የሆኑ ገመናዎቻችንን፣ እንኳንስ በመጽሐፍ መልክ፣ በንግግርም ለማውጣት አንደፍርም፡፡ አቶ አጥናፍ ሰገድ፤ የሰበረው ይህንን ልማድና ባህል ነው፡፡ እናም፤ ድክመቱን እንዳንደግመው ነገር ግን፣ እንድንማርበት አድርጎ በግሩም ቋንቋ እነሆ ብሎናል፡፡››

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...