Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትናንትን የረሳ ዛሬ እንደሌለ ይቆጠራል!

ሰላም! ሰላም! ‘ከማይረባ ሰነፍ ይሻላል ዱባ፣ አጥር ላይ ሆኖ ያደምቃል አምባ’ ያለው ማን ነበር? ብዬ ብጠይቅ በአገራችን ተጨባጭ የኑሮና የፖለቲካ ፍቺ መሠረት ሰነፉ በሥራ ፈት፣ ዱባው በሙሰኛ፣ አምባው በመዲናችን ተተረጎመና አረፈው። ቆይ እኔ ምለው፣ ይኼን ያህል ዓመት አገራችን ተርጓሚ ብቻ ነው እንዴ ወልዳ የምትቀብረው? እውነቴን እኮ ነው። “ከጉድ ጉድ መርጠው ክፍለ ከተማ ተከፋፍለው፣ እንደወረደ ሲጽፉልን እያነበብን፣ እንደወረደ አፅድቀው እንደወረደ ሲያውጁልን ተግባራዊ እያደረግን፤ እንደወረደ ስንናገር ግን ለምድነው የማንተላለፈው?” ብዬ የባሻዬን ልጅ ብጠይቀው “ማንም እንደወረደ ለወረደብህና ለተረጎመብህ ምን ያስጨንቅሃል?” ብሎ ወረደብኝ። “ውረድ እንውረድ ተባባሉና ‘አስለፈለፉት’ አፋፍ ቆሙና” አለ የአገሬ ሰው? ታዲያ እኔም የባሻዬን ልጅ ሰምቼ ሰነፉ ሙሰኛ፣ ዱባው ሥራ ፈት፣ አምባው ባለማና ባልታረሰ መሬት ለምን አልተተረጎመም? የሚለውን ጥያቄዬን አጠፍኩት። ከሠፈር እስከ አገር የልማት ፕላን በሚታጠፍበት አገር አሁን የእኔ ጥያቄ መታጠፍ ያናድዳል? ማን ይናደዳል ያው የባሻዬ ልጅ ነዋ።

“እኔ ለወሬኛና ለሐሜተኛ አትጨነቅ አልኩህ እንጂ ለዴሞክራሲያዊ መብትህ ዘብ አትቁም አልኩህ?” ብሎ ተበሳጨብኝ። እውነቴን ነው የምላችሁ ብስጭቱ ደስ የሚል ነገር በውስጤ ፈጠረ። ይኼ ምሁር ወጣት ምንም ዓይነት የአስተዳደርና የመሪነት ሥልጣን ሳይኖረው፣ ሰው ለመብቱ ዘብ እንዲቆም ያሳየው ወኔ ነገ የሚያፈራውን ፍሬ አሳየኝ። በሩቅ ያየሁትን ፍሬ ከሆነ በእኔ ዕድሜ ለመብላት ካልሆነ በልጆቼ ዕድሜ ለማስለቀም (እኛ ባንጠግብ ልጆቻችን ጠግበው ከደፉ ምን እንፈልጋለን?) ጓጓሁ። ጓጓሁና የሥራ ወኔዬን ለኩሼ የበኩሌን ለመወጣት ወደ ደንበኞቼ ከነፍኩ። የአዲስ አበባን መንገዶች ‘ክራውድድነት’ ያየ በክንፌ ሊያላግጥ ከቃጣው መቼም ባቡር አምልጦት መሆን አለበት። ቆይ ግን ክንፍ የለኝም እያልን ጫማ መወርወር መቼ ነው የምናቆመው? ነው የተገኘውን መጠቀም መቃወምን አይገልጽልንም? ወይ ክንፍና እግር አያ!

“መተካካት ተግባራዊ እየሆነ ያለው ባቡር ውስጥ ነው፤” የሚል ወዳጅ አለኝ። ‘ምንድነው የሚያውራው?’ ብዬ አንድ ‘ሲኖትራክ’ የማሻሽለጥለትን ደንበኛ ለማግኘት በባቡር ተሳፈርኩ። ከመሳፈሬ በፊት ግን የባቡሩን በር ጥርቅም አድርገው የያዙ ሁለት መለዮ ለባሾች አይቼ ደነገጥኩ። “እኔ ምለው ሌላም አገር ፖሊስ ነው አስወጪ አስገቢ? ወይስ እዚህ ብቻ ነው?” ብዬ አንዱን ስጠይቀው፣ “እንዲህም አልተቻልን እባክህ። ቆይ አሁን ባቡሩ ሲመጣ ታያለህ፤” አለኝ። እንዲያ ሲለኝ ባቡሩ በቆመ በሄደ ቁጥር በየፌርማታው ስለሚደረግ የቡድን ፀብ እንጂ ስለወጪና ወራጅ ግፊያና እርግጫ የሚያወራ አልመሰለኝም። ኋላ ሳይማ እንዳለው ነው። ፖሊሶቹ የሚታዩት የባቡሩ መግቢያና መውጫ በሮች ከመከፈታቸው በፊትና ከተዘጉ በኋላ ነው። መሀል ላይ ወገኔ እርስ በእርሱ በሊዝ ሳይሆን በሐሳብ በገዛው መሬት እያደር የሚያገረሽ ፀብ ያለበት ቆስቁሶ መራኮት ነው። እንጂ ሰላማዊ የሕዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሆኖ አልታየኝም። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይኼ ይሆን እንዴ? ቆይ እስኪ ባሻዬን ጠይቄ እነግራችኋለሁ!

 አንድ ዳያስፖራ ይኼን የድሮ ከተማ በደቦ ገፍቶ ለማፍረስ የሚደረግ መሰል ግፊያ አስተውሎ “ኢሮፕ እኮ ወራጅ እስኪወርድ ተሳፋሪ በትዕግሥት ፈንጠር ብሎ ጠብቆ ነው የሚሳፈረው። መቼ እንደምንሠለጥን እኮ እኛ?” እያለ አላስቀምጥ አለ። ከአሁን አሁን ‘ቀስ በቀስ እንማራለን’ ልበለው ‘ኢሮፕ በአንድ ቀን አልነቃችም’ ልበለው? ‘በአንድ ቀን የሚነቃ ብርሌ ብቻ ነው እሱም ከአገልግሎት ውጪ ለመሆን ነው’ ልበለው እያልኩ ሳመነታ አንዱ፣ “ወንድም ይኼ ከአያት ከቅም አያቶቻችን ሲወር ሲዋረድ የመጣ ባህላችን ነው። እስኪ መቼ ነው ሳንጋፋ ሥልጣን የተጋራነው? ርስት ያሰፋነው? ጎታ የሞላነው? ወንበር ያገኘነው? የታክሲ እጥረት፣ የምግብ የቤት እጥረት የፈጠርነው?” ብሎ ዝም አስባለልኝ። ሰው እንኳን በአገሩ፣ ያለቦታው ያለአገሩ የሰው ሰው ይጋፋ የለም እንዴ? ታዲያ ከዚያ ይኼ የውስጥ ለውስጡ ግፊያ አይሻልም ትላላችሁ? ጉልበት ላለው ማለቴ ነው!

መቼም ባቡር ተሳፈርኩ ብያችሁ ዝም ብዬ አልወርድም። አንዱ በስልክ፣ “እኔ እኮ አጥቼ እንጂ መቼ አርፌ ተቀመጥኩ?” ሲል ሰማሁትና ጠጋ አልኩኝ። ያው ሳትጋፉ መጠጋጋት አይሠራም በሚለው ስለምንስማማ አጠጋጌን፣ ማነው አገፋፌን አላብራራም። “በዚህ ጊዜ ፈላጊና ተፈላጊ አልገናኝ ይላል እንዴ?” አልኩት። “ታናሽ ወንድሜ ሳልመረቅ በስሜ አንድ ቋሚ ንብረት ከሌለኝ ትምህርቴን አልጨርስም’ እያለ ይዝታል፤” ብሎ ቁጭ። ከነገ ዛሬ ወጣቱ ‘ኑ ሥራን በልካችን እንፍጠር’ ብሎ ወላጅና መንግሥት ያሳርፋል ብለን እንጠብቃለን ለካ ይኼም አለ’ እያልኩ በልቤ አራት መቶ ካሬ የሚሸጥ መሬት እጄ ላይ እንዳለ ነገርኩት። ኋላ ሲነግረኝ ለካ ወጣቱ ተማሪ በስሙ የተቀመጠ የውርስ ገንዝብ ኖሮታል። ውርስ ሲለኝ ደግሞ ስለባሻዬ ማሰብ ጀመርኩ። ባሻዬ እንደዛሬው ሳይሆን ትናንት አጥንትና ሐረግ በሚመዘዝበት ዘመን የከበርቴ ልጅ ነበሩ። ኋላ ለገበሬው ምሎ ገበሬውን ጭምር ያፈናቀለው ሥርዓት ወርሶባቸው በበቃኝ ያስቀረላቸው ረጃት ለማንም ሳይሆን ከእህት ከወንድሞቻቸው አቀያይሞ አኖራቸው።

በዚህኛው ሁዳዴ ባሻዬ፣ “ይቅር ብያለሁ ይቅር በላቸው…” እያሉ ለዘመናት የት ይድረሱ የት ስለማያውቁላቸው ቤተሰቦቻቸው ይጸልያሉ። ከወረስነው እስካፈራነው ንብረት ትውልድ መርገም እንጂ በረከት የማይወርስበት ምክንያት ምን ይሆን ብዬ በማያገባኝ መግባት ስጀምር ይሸጣል፣ ያልኩት ቦታ የሚከራይ መሆኑ ትዝ አይለኝም? እንደምንም ብዬ፣ “ባለይዞታው አሜሪካ እንጂ እዚህ ቆርበው አንቱ ተብለው ማለፍ አያስቡም። ምናልባት ትራምፕ ከተመረጠ ግን ቤት ሠርቼ እቀመጥበታለሁ ስለሚሉ አይሸጡትም፤” ስለው፣ “እመነኝ ትራምፕማ አይመረጥም፤” አለ። ወዲያው ይመረጣል አይመረጥም የቀለጠ ክርክር። ደንበኛዬም አማራጭ ፈልግ ሳይለኝ፣ እንዲያ ነው እንዲህ ነው ሳይለኝ መውረጃዬ ደርሶ ተለያየን። እኚህ ትራምፕ የሚባሉ ሰውዬ ደግሞ ብለው ብለው በእንጀራዬ መጡ? ለነገሩ የዘመኑ መሪዎች እንጀራ ከመጋገር የተጋገረውን ማሳረር ላይ የሚያተኩሩ ሆነዋል። ለማን አቤት ይባል ይሆን?

“እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም እያልኩ ታዲያ ይኸው ፆሜን አላድርም። እኔም አለግም እሱም አያሳፍረኝም፤” ስላቸው መቼ ዕለት ከዘጠኝ በኋላ ባሻዬ አፋቸውን አሟሽተው ቡና ስንጠጣ፣ “እሱ የከፈተውንማ ሳይዘጋው አያድርም፣ እውነት ነው። እኛን እኮ የቸገረን እኛው ራሳችን እየከፈትን አልከድን ያልነው ነው፤” ብለው ተመስጠው አዩኝ። በፆም የዛለ ሰውነታቸውን አላደቅም ብዬ ዝም ብልም ባሻዬ ቀጠሉ። “አንበርብር ስማ እንጂ ይህቺ ዓለም ግን ወዴት እየሄደች ያለች ይመስልሃል? የኑክሌሩንና የአቶሚክ ቦምቡን ፍጥጫና የሽብሩን ወሬ ትተህ እንደው ፀሐይና ጨረቃ የተማከሩብን ምክር እውነት ዕድሜ የሚሰጠኝ ይመስልሃል?” አሉኝ። ፀሐይስ ያው እንደ ዘመኑ ፋሽን ተከታይ ክንብንቧን ጥላ እርቃኗን ስለምትወጣ እንደሆነ የተናገሩት ግልጽ ነው።

“ጨረቃ ደግሞ ምን አድርጋ ነው?” ብዬ መልሼ ጠየቅኳቸው። “ከዚህ በላይ? ዝም ከማለት ሌላ ምን ደባ አለ። ቀን ሲበላሽ ማታስ ይኖራል እንዴ? ሰውስ ቢሆን የሰማይ አካላት ጥፋቱን እያዩ ዝም ባሉበት ዘመን ምድርን ከዚህ ወዲያ ላለመበደል ተነጋግሮ እንዴት ይግባባል?” ሲሉኝ ባሻዬ በመንፈሳዊ ቋንቋ እያወሩ እንደሆነ ገባኝ። ደጋግሜ እንዳጫወትኳችሁ ባሻዬ ጥብቅ ሃይማኖተኛ ናቸው። ለጥፋት የተቀጠረ ቀን ስላለ እንኳን በሰው በሰማይ በተፈጠሩ መላዕክት ኃይልም ቢሆን ማምለጥ አይቻልም ብለው ያምናሉ። ግን እንዲህ እያሉ ነዋሪውን ለንሰሐ ማዘጋጀት ያቆሙት አንዱን እንዲህ እንዳሁኑ እኔን በጥበብ ቃል ‘የምድሩን ቀዝቀዝ የሰማዩን ጠበቅ’ እንዳደርግ እንደነገሩኝ፣ “ምፅዓት ደርሷል ዓለም መጥፊያዋ ቀርቧል፤” ቢሉት ሄዶ አሉ ለዓባይ ያዋጣው ገንዘብ እንዲመለስለት ማመልከቻ አጻፈ አሉ። በምፅዓትና በህዳሴ መሀል የተጣበቀ ትውልድ!

በሉ እንሰነባበት። ያልኳችሁን ሲኖትራክ ጆሮውን ብዬ ሸጥኩት። የምሬን አንድ ሚስጥር ላውራችሁ? ቢፈቀድ፣ ይኼ ሲኖትራክ የተባለ የየብስ ሻርክ ለአገናነዝ እንዳንመች እያደረገ ሳይጨርሰን በፊት ከአገር ውጭ እያሸጥኩ የምጨርሰው እኔ ነበርኩ። ያው የሚስጥርን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ አንድ ወዳጄ ይኼን ራዕዬን ሰምቶ ሲያሾፍብኝ፣ “ምዕራባውያን የአፍሪካን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ በሽታ እየፈለሰፉ ጨረሱን። ቻይና ግን አዝናልን ቢያንስ በራሳችን እጅ በገዛ ገንዘባችን ገዝተን እንድንጫረስ ሲኖትራክ ሠራችልን። ቢያንስ ከማናየውና ከማንጨብጠው ቫይረስ እያየነው እየሰማነው የሚወጣብን አይሻለንም? ተው በሞታችን አትምጣ ተው፤” ይለኛል። በነገራችን ላይ፣ “ሙታንን ሙታን ይቅበሯቸው’ የተባለው ያኔ ሲኖትራክ ስላልነበረ ነው፤” ያለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። እንኳንም ያኔ ማኦ ተወልዶ ቻይናን ዛሬ እንደምናውቃት ቻይና አላደረጋት እንጂ፣ በባሻዬ ልጅ ዘመንና ጥቅስ አቀለባበስ ከሄድን እስካሁን በግንባር ቀደምነት ከዚህ ዓለም በሞት አሰናባች የነበረውን ጦርነት ሲኖትራክ ይተካው ነበር ማለት ነው። “እግዜርም አውቆ ቻይናና ፈጠራዎቿን ፍፃሜ ዘመን ላይ ፈጥሮ ነው፤” ብሎ አንዱ ይተርታል። እኔና የባሻዬ ልጅ ግሮሰሪ ገብተናል።

“መኪናው ላይ ከመፍረድ ሾፌሮቹን ማስመርመር ዋና መፍትሔ ይመስለኛል፤” ይላል ሌላው። “መንጃ ፈቃድ አሰጣጡን ልትል ከሆነ ተቀድመሃል፤” ሲባል፣ “የለም ምናልባት ዛሬ እንደምንሰማው ማበረታቻ መድኃኒት ተጠቅመው ድል ሲያፍሱ እንደኖሩት አትሌቶች ዓይነት ‘ኬዝ’ ሊኖር ይችላል፤” አለ፡፡ “ግፍ፣ ሱስ፣ ወሬ፣ ቸልተኝነት አልያም ደንታ ቢስነት ቢባል ነው። መቼም ከእነዚህ ነገሮች በላይ ለጥፋት የሚያቻኩል አገር የሚበድል አጥፊ ነገር የለም። ሁሉም ነገር መጠኑን ሲያልፍ ይሰለቻል፤›› ይላል የግሮሰሪው ባለቤት። አንዳንዴ ዓለምን ባለችኝ የማትረባ ዕውቀት ስታዘባት ታሳዝነኛለች፡፡ ዛሬ የሸለለባት፣ ነገ ሲያዝንባት፣ ትናንት የፈነጨባት፣ ዛሬ አንገቱን ሲደፋባት አርተፊሻል ትመስለኛለች፡፡ እነ ትሬንታ ኳትሮ ባጓሩበት አገር ሲኖትራክ ሲደነፋ ግርም ይለኛል፡፡ የሰው ነገርም እንዲህ ይመስለኛል፡፡ ትናንትን ረስቶ ዛሬ ሲደነፋ፣ የነገን ዘንግቶ የሚዋልል ከንቱ ፍጡር ይሆናል፡፡ ይኼኔ ነው እንግዲህ ትናንትን የረሳ ዛሬ እንደሌለ ይቆጠራል የሚባለው፡፡ መልካም ሰንበት!           

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት