Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንገዳቸውን የሳቱ ታዳጊዎች

መንገዳቸውን የሳቱ ታዳጊዎች

ቀን:

ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ ቦሌ ከኤድና ሞል ወደ ፍሬንድሺፕ ሆቴል የሚወስደውን መንገድ ይዘው ቁልቁል የሚሄዱት ጓደኛሞች ብዙ መጠጣታቸውን ከአረማመዳቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ሁለት ሴቶችና ሦስት ወንዶች ናቸው፡፡ አንደኛዋን ሴት ሁለቱ ወንዶች ለመደገፍ ይሞክራሉ፡፡ ስስ ቲሸርቷ ከወገቧ በላይ ተሰብስቧል፡፡ የምትሄድበትን መንገድ ብዙም አትመለከትም፡፡ ያደረገችው ቡትስ ጫማ ከወራጅ ውኃና ከጠጠር የመከላከል ሥራውን በደንብ እየተወጣ ይመስላል፡፡ እግሯን እየጎተተች ነውና የምትሄደው፡፡ ጓደኛሞቹ ከጥቂት ርቀት በላይ መሄድ አልቻሉም፡፡ አዲስ እየተገነባ ያለ ሕንፃ ጋር ቆም አሉ፡፡ ሦስተኛው ባልታወቀ ምክንያት ትተውት እንዲሄዱ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሁለቱ ሴቶች ደግሞ ወደመጡበት አቅጣጫ ለመመለስ የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ እሱ ያለ የሌለ አቅሙን አሰባስቦ እየተኮለታተፈ በእንግሊዝኛ በአማርኛም ትተውት እንዲሄዱ እየተቆጣ መናገር ጀመረ፡፡ እነሱም ትተውት ወደ መጡበት አቅጣጫ ተመለሱ፡፡ በአቅራቢያው ካገኘው ጀብሎ ሲጋራ ገዝቶ፣ ጣቶቹ እየተንቀጠቀጡ ለኮሰ፡፡ እያጤሰና እየተወለጋገደ ከጓደኞቹ በተቃራኒ መንገድ ጉዞውን ቀጠለ፡፡

ብዙም ሳይርቅ እዚያው አካባቢ ሌሎች ታዳጊዎች የመንገድ ጠርዝ ላይ ተቀምጠው ወይም የሚሄዱበት የጠፋባቸው እስኪመስል ሲወዛገቡ አስተውለናል፡፡ በአብዛኛው ዓርብና ቅዳሜ ወደየት አቅጣጫ እንደሚሄድ የማያውቁት ታክሲ ውስጥ ተደጋግፈው የሚገቡና ወንበር ላይ እንኳን ለመቀመጥ አቅም ያጡም ያጋጥማሉ፡፡ ለፀብ የሚጋበዙ ወንዶች፣ የሚያለቅሱ ሴቶችና በመንገድ ጥግ የሚያስመልሱ ታዳጊዎችም የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ገጠመኝ ናቸው፡፡ የአመሻሹ ድባብ እስከ እኩለ ሌሊትና ከዛም በላይ ሊዘልቅ ይችላል፡፡

ፒያሳ አካባቢ ለዓመታት ታዳጊዎች በብዛት የሚዝናኑበት ቤት ነው፡፡ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች አይገቡም ቢባልም ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ አይመስልም፡፡ ቤቱ ውስጥ ሲገቡ የሲጋራ ጭስ ያፍናል፡፡ ወቅታዊ የሚባሉ ሞቅ ያሉ ሙዚቃዎች ተከፍተዋል፡፡ ሲጋራ ያልያዙ ታዳጊዎች ጥቂት ናቸው፡፡ ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚደንሱ፣ በቡድን ክብ ሠርተው የሚጨፍሩም ቤቱን ሞልተውታል፡፡ አካባቢው በታዳጊዎች መካከል በሚፈጠር እሰጣገባም ይታወቃል፡፡ በቤቱ ኮርነር ላይ የሚገኝ ወንበር ላይ የተቀመጡ ታዳጊ ወንድና ሴት ይሳሳማሉ፡፡ ሴቲቷ በሙዚቃዎች መሀል በተቀመጠችበት ትደንሳለች፡፡ ከእነሱ ብዙም ሳይርቅ ጠረጴዛቸው በድራፍት ብርጭቆዎች የተሞላ ታዳጊዎች አሉ፡፡ በቤቱ ከሲጋራ ውጪ ጠረኑ ከየት እንደሚመጣ የማይታወቅ ማሪዋና ይሸታል፡፡ ታዳጊዎቹን ምቾች የነሳቸው አይመስልም፡፡ በላይ በላዩ ይጠጣሉ፤ ያጨሳሉ፤ ይጨፍራሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ትዕይንት ቦሌ ወይም ፒያሳ ላይ የተወሰነ አይደለም፡፡ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ዕለት በዕለት የሚያጋጥም እንጂ፡፡

የ14 ዓመቱ ታዳጊ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ ቤተሰቦቹ ለጥቂት ሳምንታት ከአገር ወጡ፡፡ አክስቱ እየተመላለሰች ልጆቹንም ቤቱንም እንድታይ ወላጆቹ አደራ ብለዋል፡፡ አክስቱም እንደተባለችው ታደርግ ጀመር፡፡ ታዳጊው አክስቱ ባልሄደች ቀን የቤት ሠራተኛዋ ሳሎን ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች እንድታወጣቸው ጠየቀ፡፡ ቤቱንም ግቢውንም የሆነ የሆነ ነገር እንድታደርግም ጠይቋታል፡፡ ሠራተኛዋ ግራ ተጋባች፡፡ ለካስ ታዳጊው በመኖሪያ ቤቱ ፓርቲ ለማድረግ ዝግጅቱን እያደረገ ነው፡፡

ፓርቲውን ለማካሄድ ያሰበው ሳሎን ውስጥ ሲሆን፣ ፓርቲውን ለሚታደሙ የዕድሜ እኩዮቹ ስለሚቀርበው መጠጥም ተዘጋጅቶበታል፡፡ ፓርቲው በሙዚቃ እንዲደምቅም ሞንታርቦ ተከራየ፡፡ ወደ ፓርቲው ያልተጋበዙ ሰዎች እንዳይገቡ የሚከላከል ቦዲ ጋርድ ለመቅጠር በድርድር ላይ ነበር፡፡ የፓርቲው መግቢያ 70 ብር ሲሆን፣ ትኬቶቹም ተሸጠው ነበር፡፡ ታዳጊው ለፓርቲው የሚያወጣውን ወጪና ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ አስልቶ ጨርሷል፡፡ የፓርቲውን መካሄድ በጉጉት ሲጠባበቅ ግን ያልጠረጠረው ነገር ተከሰተ፡፡ የታዳጊው አኳኋን ያላማራት የቤት ሠራተኛ ለአክስቱ ደውላ አሳወቀች፡፡ አክስትየውም የአጐቱን ልጅ ጠርታ መላ እንዲፈልግ ጠየቀችው፡፡

የተጠራው ወጣት ታዳጊውን ማግባባት ጀመረ፡፡ የፓርቲውን መሰናዶ አስቆመው፡፡ ታዳጊው ፓርቲውን ለማካሄድ ብዙ ነገሮችን እንዳደረገ በመዘርዘር አጐቱ እንዲረዳው ለማድረግ ቢሞክርም የአጐቱን አቋም ሲመለከት ፓርቲው የሚሳካ ነገር እንዳልሆነ ተረዳ፡፡ አጐቱም ስለ ጉዳዩ ለቤተሰቦቹ እንዳይነገርበት አጥብቆ ይለምን ጀመር፡፡ ዘመዶቹ ተስማምተው ወላጆቹ ሲመለሱ ምንም ሳይሉ ቀረ፡፡

ይህንን አጋጣሚ ያካፈለችን ከታዳጊው የቅርብ ዘመድ ስትሆን፣ ተመሳሳይ ፓርቲዎች መሄድ ባይለምድ እሱም ለማዘጋጀት እንደማያስብ ትናገራለች፡፡ ታዳጊው ሲጠጣ ያለምንም ፍርኃትና ልምድ እንዳለው ሰው መሆኑን አስተውላለች፡፡ ቤተሰቦቹ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚሻማ ሥራ ስለሚሠሩ ተገቢው ቁጥጥር እንዳልተደረገለት ይሰማታል፡፡ በእሱ ዕድሜ ያሉ ሌሎች ዘመዶቿም ላይ ተመሳሳይ ባህሪ ታያለች፡፡ በተለይ ቅዳሜና እሑድ ለመጠጣት ሲገባበዙ ያስገርማታል፡፡ የገንዘብ ጉዳይ የብዙዎቹ ጥያቄ እንዳልሆነ ያህል አብዛኛውን ጊዜ የሚፈልጉትን የሚያደርጉበት ገንዘብ ይዘው ይታያሉ፡፡

በትምህርት ቀንም ቢሆን መምህራን በትምህርት ገበታቸው መገኘታቸውን ሲያረጋግጡ አይስተዋልም፡፡ ለተማሪዎች ትኩረት ሰጥቶ ያሉበትን ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው የሚያሳውቅ ትምህርት ቤት ቢኖር እንኳን፣ ወላጆች ዕርምጃ ሲወስዱ አይታይም፡፡ ለልጆች ነፃነት መስጠት በሚል ሰበብ ከቤት እንዳሻቸው እንዲወጡ ገንዘብም እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡ ‹‹አሁን ቤተሰብም መምህርም አይፈራም፤ ታዳጊዎች የሚፈልጉትን ነገር በአጠቃላይ በአቅራቢያቸው ያገኛሉ፡፡ ታዳጊዎች ላይ የሚታየው በሱስ የመጠመድ ችግር የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፤›› ትላለች፡፡

ብዙዎች ሐሳቧን ይጋራሉ፡፡ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ያሉ ብዙዎች በአልባሌ ሱስ ተጠምደው ይታያሉ፡፡ በርካታ ወላጆች የሚያደርጉት ግራ ተጋብተው ያለበት ጊዜ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በልጆቹ አስደንጋጭ ባህሪ ግራ የተጋቡ ትምህርት ቤቶችም ከተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በኋላ ልጆችን እያባረሩ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ሦስትና አራት ትምህርት ቤት የቀያየሩ ልጆች ጥቂት አይደሉም፡፡ ቦሌ፣ ፒያሳ እንዲሁም በሌሎችም የመዲናችን አካባቢዎች የሚስተዋለው ነገር አንዳንዴ ለማመን የሚያስቸግር ነው፡፡ ታዳጊዎች በመጠጥ፣ በአደንዛዥ ፅዖች ናላቸው ዞሮ በየመንገዱ መመልከት ተደጋጋሚ አጋጣሚ ሆኗል፡፡ በየሠፈሩ መጠጥና አደንዛዥ ዕፅ በድብቅ የሚያቀርቡም ነጋዴዎችና በአደባባይ የሚንቀሳቀሱም ተበራክተዋል፡፡ ችግሩም በመጠጥና አደንዛዥ ዕፅ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሌሎችም ዓይነት አልባሌ ሱሶች ተገዢ ታዳጊዎች መበራከት አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ለረዳቸው ለቤተሰብና ለአገራቸው ብዙ ነገር ያደርጋሉ የሚባሉ ሕፃናት ለአዕምሯቸውና ለአካላቸው ጤንነት አደገኛ የሆነ ነገር ውስጥ መግባት የማንም ኢትዮጵያዊ ራስ ምታት ነው፡፡ የሚታየው ነገር እንዴት አድርጌ ልጅ አሳድጋለሁ? የሚያስብል እንደሆነ የሚናገሩም ብዙዎች ናቸው፡፡ ቤተሰቦች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንግሥትና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት እየወሰዱ ስላሉት ዕርምጃም ይጠይቃሉ፡፡ ስለችግሩ ሥር መስደድ በተደጋጋሚ ቢነገርም ነገሮች የተባባሱ ይመስላል፡፡

ለምለም በቀለ (ስሟ ተቀይሯል) 22 ዓመቷ ነው፡፡ ዘንድሮ ከአንድ የግል ኮሌጅ ትመረቃለች፡፡ ዛሬ ላይ ሆና በአሥራዎቹ አጋማሽ የነበራትን ሕይወት ስታስበው ትጸጸታለች፡፡ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ዓርብ፣ ቅዳሜና እሑድ መጠጣት ጀመረች፡፡ አባቷ ማድረግ የምትፈልገውን ነገር በሙሉ አይከለክሏትም፡፡ እናቷ የምትሄድበትን ቦታና ከማን ጋር እንደምትሆን እየጠየቁ፣ በዝምታ ያልፉታል፡፡ አንዳንዴ ይቆጧታል፡፡ ለውጥ ግን አላመጣም፡፡ በሚሰጧት ገንዘብ የምትፈልገውን ታደርግለች፡፡

እሷና ጓደኞቿ የሚያዘወትሯቸው ቦታዎች እየተገናኙ እየጠጡ ማምሸትን ተያያዙት፡፡ ‹‹ሐሽሽ፣ ጫት፣ ሲጋራ፣ መጠጥ፣ ሺሻ ያላደረግነው ነገር አልነበረም፤›› ትላለች፡፡ ከመሀከላቸው ቀን እየተኙ ሌሊቱን በምሽት ክለቦች የሚያሳልፉም ነበሩ፡፡ በወንድ ጓደኛዋ ተጽእኖ ሥር እንደነበረች ትናገራለች፡፡ ‹‹የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ የጀመርኩት በጣም ፈጥኜ ነበር፡፡ ያኔ የነበረኝ ሕይወት በዛሬው ማንነቴ ላይ ጫና አሳድሯል፤›› ትላለች፡፡ ከቤተሰቦቿና በአካባቢዋ ካሉ ሰዎች ጋር ያላት ግንኙነት መሻከሩን ትጠቅሳለች፡፡

11ኛ ክፍል ስትደርስ ግን ቤተክርስቲያን መሄድ ጀምራ እንደተለወጠች ትናገራለች፡፡ ‹‹እኔ ቶሎ ነቅቻለሁ፤ ሕይወቴን በምን መንገድ መምራት እንዳለብኝ ወስኜ ተቀይሬያለሁ፤›› ትላለች፡፡ ዛሬ ከበፊት ጓደኞቿ ጋር አትገናኝም፡፡ በቀድሞ አኗኗራቸው የቀጠሉት ጓደኞቿ ሕይወት ያሳስባታል፡፡ ለምለም ከትምህርቷ ጐን ለጐን በማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ ትሠራለች፡፡ በሥራዋ ምክንያት በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ስትገኝ ታዳጊዎች ላይ የምታየው ነገር እንደሚያሳስባት ትናገራለች፡፡

አካሄዳቸው ያሳስበኛል ከምትላቸው ታዳጊዎች የ16 ዓመቱ ታናሽ ወንድሟ አንዱ ነው፡፡ እሷ ባለፈችበት መንገድ እንዳይሄድ ትመክረዋለች፡፡ ቢሆንም በዙሪያው ያለው ነገር ሁሉ ወደዚህ አደገኛ መንገድ የሚያመራ ነው፡፡ ‹‹ዛሬ ያለው ሁኔታ ከኛ የባሰ አስፈሪ ነው፤ ቤተሰብ ከልጆቹ ጋር በግልጽ እየተነጋገረ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት፤›› ትላለች፡፡ በእሷ አመለካከት፣ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው በየዕድሜ ደረጃቸው ስለሚገጥሟቸው ነገሮች ማስተማር አለባቸው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረን ያየነው ለምለም ከገለጸችልን የተለየ አይደለም፡፡ ታዳጊዎች በቡድን ሆነው አንድ መጠጥ ቤት ሲገቡ ምግባራቸው ትክክል የሆነ ያህል በድፍረት ነው፡፡ በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የከተማዋ ጎዳናዎች በሰከሩ ታዳጊዎች ይሞላሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አደንዛዥ ዕፅ የሚሸጥባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙትም እኚሁ ታዳጊዎች ናቸው፡፡

የተለያዩ አካላት ለችግሩ መንስዔ የሚሏቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በዋነኛነት የሚጠቀሰው መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ አለመውሰዱ ነው፡፡ ታዳጊዎችን ለአልባሌ ሱስ የሚያጋልጡ ሥፍራዎች በተደጋጋሚ ሕጋዊ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል ቢባልም ሥርጭቱ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ዘመን ያመጣቸው የተለያዩ ነገሮች ታዳጊዎች ለተለያየ ዓይነት አኗኗር ተጋላጭ እንዳደረጋቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ የሱስ ተገዢነት እንደ ዘመናዊነት መገለጫ የሚታይበት ሁኔታም አለ፡፡ ታዳጊዎች ማንኛውንም ዓይነት ነገር ለማግኘት ብዙ ርቀት መጓዝ አያስፈልጋቸውም፡፡ ባላቸው ገንዘብ ልክ ከሠፈር አረቄ ቤቶች እስከ ትልልቅ ሆቴሎች እየሄዱ ይስተናገዳሉ፡፡ ሺሻው፣ ማሪዋናው፣ ጫቱ እያለ ሁሉም በቅርብ ርቀት የትም ቦታ ይገኛል፡፡ ለታዳጊዎቹ ይህን ሁኔታ እያመቻቸ ከዚህ ቢዝነስ ለማትረፍ የሚሞክረው ማኅበረሰብ ራሱ የችግሩ ተጠቂ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሩ በየቤቱ እያንኳኳ ሁሉንም እየነካ ነውና፡፡

አንዳንድ ቤተሰቦች የችግሩ ክብደት የገባቸው አይመስልም፡፡ የቱን ያህልም ጊዜ ባይኖራቸው፣ በግልፅ የመነጋገር ባህል ያላዳበሩ ቢሆንም ይህ ችግር በየትኛውም መንገድ ሊጋፈጡት የሚገባ እንደሆነ አይረዱም፡፡ በአንድ የግል ትምህርት ቤት መምህር የሆነው አቶ ሰይፉ ወርቁ፣ ትምህርት ቤቶች ስለተማሪዎቻቸው ሕይወት ምን ያህል ይሰማቸዋል? ሲል ይጠይቃል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ገቢያቸውን ከማስፋፋት በዘለለ ለተማሪዎች ሲጨነቁ አይታይም፡፡ ተማሪዎችን በሥነ ምግባርና ዕውቀት ከማነጽ ይልቅ፣ ወላጆች ማየት የሚፈልጉትን በጐ ገጽታ በሌለበት (በማስመሰል) ለመፍጠር ይሞክራሉ፡፡ ‹‹በከፍተኛ ማዕረግ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ተሸጋገሩ ከሚባሉት ውስጥ በሥነ ምግባርና በዕውቀትም ብቁ ያልሆኑ ልጆች ይኖራሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ይህንን እውነታ ለወላጆች አያሳውቁም፤›› ይላል፡፡

አብዛኞቹ መምህራን ለሙያው ክብር ሳይኖራቸው እንደ አንድ የሥራ አማራጭ ስለሚይዙት፣ በሥራቸውና በክፍያውም ደስተኛ ስለማይሆኑ የተማሪዎቻቸው ሕይወት ያሳስባቸዋል ለማለት እንደማያስደፍር ይናገራል፡፡ አንዳንድ መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ሲጠጡ ወይም ጫት ሲቅሙ እንደሚታይም ይገልጻል፡፡ ታዳጊነት አርቆ ባለማሰብ ለሱስ ለመጋለጥ የቀረበ ዕድሜ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎቻቸውን አመለካከት መቅረጽ እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ ተማሪዎች የተለያየ ችሎታ የሚያዳብሩባቸው ክለቦች ቢስፋፉ መልካም ነው ይላል፡፡

የመምህሩን ሐሳብ የሚጋራው ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን ካውንስለር በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር በሥነ ተዋልዶና ጤና ማዕከል ለዓመታት ሠርቷል፡፡ በእሱ እምነት፣ መንግሥት ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ዘግይቷል፡፡ ‹‹ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ሲሰጥ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ ህልውና ግን ቸል ተብሏል፤›› የሚለው ባለሙያው፣ አሁን ያለው አካሄድ ከዓመታት በኋላ አገሪቱን ዋጋ እንደሚያስከፍላት ያስረዳል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ታዳጊዎችን ለመታደግ ቁጥጥር ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ታዳጊዎች ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አመለካከት እንዲኖራቸው መደረግ አለበት፡፡ ብዙ ወላጆች ታዳጊዎች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩባቸው የሚችሉ ነገሮችን እንዴት መጋፈጥ እንደሚችሉ ለልጆቻቸው ሲያስረዷቸው አይታይም፡፡ በተለይም ወጣት ወላጆች ለልጆቻቸው ባልተገባ መጠን የመወሰን ነፃነት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን በመቅጣት ለውጥ የሚመጣ ይመስላቸዋል፡፡ ሌሎች ጊዜ ባመጣው ለውጥና የዘመን መራቀቅ ከልጆቻቸው ጋር የተፈጠረውን ክፍተት ችላ ብለዋል፡፡ የትዳር ችግሮችም ለልጆች ባህሪ መበላሸት ምክንያት ሆኖ እየታየ ነው፡፡ አንድ ወላጅ ከሌላው የትዳር አጋሩ ስለልጆቹ ማንነት ሲደብቅ፣ ገንዘብ ሲሰጥም ይስተዋላል፡፡

ስለልጆቻቸው የሱስ ተገዥነት እያወቁ፣ ልጆቻቸው ገንዘብ ለማግኘት ተቸግረው እንዳይሰርቁ በሚል ከኪሳቸው ገንዘብ እየሰጡ ለልጆቻቸው ጥፋት የሚተባበሩ ወላጆች ገጥመውታል፡፡ ባለሙያው እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጠው፣ ታዳጊዎች የሚወያዩባቸውና መረጃ የሚያገኙባቸው የምክር አገልግሎት ቦታዎች እንዲስፋፉ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋሞች በየጊዜው የተለያየ ሠፈር ላይ ጥናት እየሠሩ ሪፖርት ከማቅረብ ባለፈ ትውልዱን የሚታደግ ዕርምጃ እንዲወስዱ ያሳስባል፡፡ ታዳጊዎች ላይ ከሱስ ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚፈቱባቸውን መንገዶች ማመቻቸትም አስፈላጊ ነው ይላል፡፡

‹‹ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ያልተገባ ባህሪ ከለላ መስጠት የለባቸውም፤ የውኃ፣ የቀለም፣ የአዛውንትና ሌላም ቀን እየተባለ ለተማሪዎች መንገድ ይሰጣል፡፡ በትምህርት ቤት ስም ከከተማ ወጥቶ ማደርም እየተለመደ ነው፤›› ይላል፡፡ በመጠጥና አደንዛዥ ዕፅ ግፊት ከማን ጋር ግንኙነት እንደፈጸመች ሳታውቅ በ14 ዓመቷ አርግዛ ፅንስ ያቋረጠች ታዳጊ ዘወትር አትረሳውም፡፡

የሁለት ሴትና ሁለት ወንዶች ልጆች አባት የሆኑ አንድ ወላጅ ኃላፊነቱን ለቤተሰቦችና ለሃይማኖት ተቋማት ይሰጣሉ፡፡ ሁለቱ ልጆቻቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ፤ ወንዶቹ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ናቸው፡፡ ከልጆቻቸው ጋር በየዕድሜ እርከናቸው ሊገጥሟቸው የሚችሉ ነገሮችን በግልጽ የመነጋገር ልማድ ባይኖራቸውም፣ የዘወትር ቁጥጥር እንዳልተለያቸው ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም ልጆቻቸው ከቁጥጥር መውጫ መንገድ እንደማያጡ ያዩበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡

በቅርቡ አንድ ቅዳሜ ጠዋት ማጠናከሪያ (ሜካፕ ክፍል) ሄደው ከከሰዓት ደይ ፓርቲ ይሄዳሉ፡፡ ልጆቻቸው ጠጥተው አመሻሽ ላይ ይገቡና በፍጥነት ወደ መኝታ ክፍላቸው ያመራሉ፡፡ ነገሩ ያላማራቸው አባት ይከተሏቸዋል፡፡ ልጆቻቸው ዓይናቸው ደም ለብሶ፣ አፋቸው እየተያያዘ፣ እየተንገዳገዱ አገኟቸው፡፡ ከሁለቱ በዕድሜ ትልቋን በጥፊ መቷት፡፡ ጩኸትና ለቅሶ የሰሙ እናት መጥተው አገላገሏቸው፡፡ በወቅቱ በንዴት ስሜት ሆነው ቢማቱም ምክር የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡

አባትየው ልጆቻቸውን እንደሚቆጣጠሩና በልጆቻቸው እንደሚፈሩ ያምኑ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ያ አጋጣሚ ግን ብዙ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ከዛ ቀደም በተለይ ስለታዳጊዎች አደገኛ ዕፅ ተገዢነት ሲወራ ቢሰሙም፣ ልጆቻቸው በማንኛውም ዓይነት መንገድ በዚህ ነገር ውስጥ ይገኛሉ ብለው አስበው አያውቁም፡፡ በዕለቱ ልጆቻቸውን እጅ ከፍንጅ ያዟቸው እንጂ አልፎ አልፎ ይጠጡ እንደነበር ኋላ ደርሰውበታል፡፡ እሳቸው መፍትሔ ያሉት ልጆቻቸውን ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ መገፋፋት ነው፡፡ ‹‹ለታዳጊዎች መጠጥ፣ ጫትና ሐሽሽ የሚሸጥ ምን ዓይነት ህሊና ያለው ሰው እንደሆነ አላውቅም፤›› የሚሉት አባት የሃይማኖት ተቋሞች ከፍተኛ ንቅናቄ ቢያደርጉ ለውጥ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡

ታዳጊዎችን ምንም ያህል ቤተሰቦቻቸው ቢቆጣጠሯቸው ማምለጫ መንገድ እንደማያጡ ይናገራሉ፡፡ የንግድ ተቋሞቹን በአጠቃላይ መዝጋትም ይቻላል ብለው አያምኑም፡፡ ‹‹መፍትሔው ታዳጊዎቹ በሱስ ላለመጠመድ የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ልጆቻው ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆነው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ሲገቡ ስለሚኖራቸው ጊዜ እንደሚሰጉ ይናገራሉ፡፡

ሶሻል ወርከር ኡመር ወልዴ ከአብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ጋር በመስማማት ትልቁን ኃላፊነት ለመንግሥት ይሰጣል፡፡ ባለሙያው ታዳጊዎች በአደገኛ ሱስ ሲሸበቡ መላ ሕይወታቸው ይመሰቃቀላል ይላል፡፡ በታዳጊዎች ጤናና፣ ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ በላይ የትውልድ ክፍተት እንደሚፈጠር ይናገራል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ለመንግሥት ቀላል ነው፤ በአንድ አንቀጽ ለአደገኛ ሱስ የሚያጋልጡ ቤቶችን በሕግ መከልከል ነው፡፡ ደንብ አስከባሪዎችም በሙስና የመደለልና ለነጋዴዎቹ የመገዛት ነገር ይታይባቸዋል፡፡ መንግሥት ገንዘብ ማግኘቱን እንጂ የትውልዱን መጥፋት እያየ አይደለም፤›› ይላል፡፡

በየጊዜው እነዚህ ቤቶች ቢዘጉም ሳይዘገይ ቁጥራቸው ይጨምራል፡፡ መንግሥት ቤቶቹ በሚያስገኙት ገቢ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸውን የሚፈልግ እንደማይመስል ሌሎችም አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ለዚህ መንግሥት በጫት ንግድ ላይ ያለውን የተለሳለሰ አቋም ብዙዎች እንደ ማስረጃ ያስቀምጣሉ፡፡ ኡመር በበኩሉ የመንግሥት ቁርጠኝነት ከሌለ የቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች የተናጠል ውጊያ ጉልህ ለውጥ እንደሚያመጣ ይገልጻል፡፡

ሌላው በሱሶች ለሚያዙ ታዳጊዎች በቂ የማገገሚያ ቦታ ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ ሱሰኛ ታዳጊዎች ቁጥር ቢጨምርም በበቂ ሁኔታ ማገገሚያ አያገኙም፡፡ አንድ ሰው ከአደገኛ ሱስ ቢወጣ እንኳን ማገገም አለመቻሉ ሌላ ችግር እንደሚፈጥር ይናገራል፡፡ የምክር አገልግሎት መስጫና ማገገሚያ በስፋት መቋቋም እንዳለበትም ያሳስባል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች የማብቃትና ተጠቃሚነት ዋና የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ መንግሥቱ አሻግሬ እንደሚናገሩት፣ መሥሪያ ቤታቸው ከሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋሞች ጋር በመተባበር ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ለሱስ የሚያጋልጡ ሥፍራዎችን ማሸግና ለታዳጊዎችና ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡

ዋነኛ ትኩረታቸው ግንዛቤ መፍጠር ቢሆንም ሁሉንም ታዳጊ ለመድረስ እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በክፍለ ከተሞችና በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን ለመድረስ ጥረት ቢደረግም ከዛ ውጪ ያሉትን የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥናት እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች ታዳጊዎች፣ ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት ተቋሞች በጥምረት እንደሚመካከሩ ይገልጻሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች በሚኒሚዲያና በወጣት አደረጃጀቶች የሚተላለፉ መልዕክቶች የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱም ያስረዳሉ፡፡ የወጣት ማዕከላትና የስፖርት ማዘውተሪያዎች መስፋፋት ለችግሩ አንድ መፍትሔ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ‹‹አንድም ይሁን ሁለት ታዳጊ ሲጐዳ አገር ተረካቢ እያጣን ነው፤ የእኛ ቢሮ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የመንግሥት ባለድርሻ አካሎች ለውጥ እንዲመጣ መረባረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት ከጥናትና በመገናኛ ብዙኃን ከሚተላለፈው መረጃ ባለፈ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፤›› ይላሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ፣ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ ጤና ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ስፖርት ኮሚሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፍትሕ ቢሮና ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በ2005 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ጥናት ሠርተው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ያሉ አሥሩም ክፍለ ከተሞች ላይ ያተኮረው ጥናቱ፣ የችግሩን መንስዔ፣ ስፋትና መፍትሔ አስቀምጧል፡፡

ጥናቱ ካስቀመጣቸው ግላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መንስዔዎች በተጨማሪ የፖሊሲና የሕግ ክፍተትና እንዲሁም የተፈጻሚነት መላላት ይጠቀሳል፡፡ በታዳጊዎችና በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ያለው ይህ ችግር ሊቀረፍ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ለአደገኛ ሱስ የሚያጋልጡ ሥፍራዎችን ከትምህርት ተቋማት ማስወገድ ነው፡፡ ቦታዎቹ የዕድሜ ገደብ እንዲጣልባቸውና ቁጥጥሩ እንዲጠብቅ ያሳስባል፡፡ ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች ላይ የሚያደርጉትን ቁጥጥር እንዲያጠብቁ፣ በልጆች አስተዳደግና በቤተሰብ መካከል ስላለው ጤናማ ግንኙነት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንዲኖር በጥናቱ ተጠይቋል፡፡

ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሀከል ከ15 እስከ 29 ዕድሜ ክልል ያሉት 42.42 በመቶ ይሆናሉ፡፡ በወቅቱ በተሠራው ጥናት ለሱስ የሚውሉ ወደ 3,691 የሚደርሱ ቤቶች እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ሊገደብ ካልቻለው መጠጥ ባለፈ የአደንዛዥ ዕፆች ዝውውር በትምህርት ተቋሞችና መኖሪያ አካባቢዎች ጭምርም ተስፋፍቷል፡፡ ጥናቱ የትምህርት ሥርዓቱ በታዳጊዎች ባህሪ ለውጥ የሚያመጣና ተጋላጭነታቸውን መቀነስ የሚችል መሆን አንዳለበት ያመለክታል፡፡

ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ በተሠራው ጥናቱ የተሳተፉት 2,529 ሰዎች ሲሆኑ፣ 1,535 (60.7 በመቶ) የሚሆኑት አልኮል ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከነዚህ ከ15 እስከ 29 ዓመት የሆናቸው ታዳጊዎች 25.3 በመቶውን ይይዛሉ፡፡ በጥናቱ ከተካተቱት ውስጥ 717 (28.4 በመቶ) አደንዛዥ ፅዕ ተጠቅመው የሚያውቁ ሲሆን፣ ከ15 እስከ 29 ዓመት ያሉ ታዳጊ ወጣቶች (22.5 በመቶ) ናቸው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን ሲነሳ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የችግሩን አለመፈታት ነገር ግን ተቋማቸው የሚጠበቅበትን መሥራቱን ይገልጻሉ፡፡ በተመሳሳይ እነዚሁ ተቋማት መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስድ ሁሉ ያሳስባሉ፡፡ ነገር ግን የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ችግሩ እንዲፈታ የበኩላቸውን ሚና ከተጫወቱ ክፍተት ያለው የቱ ጋር ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...