Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኢትዮጵያ 138 ቀናት ለቀረው የሪዮ ኦሊምፒክ ምን ሰንቃለች?

ኢትዮጵያ 138 ቀናት ለቀረው የሪዮ ኦሊምፒክ ምን ሰንቃለች?

ቀን:

ኢትዮጵያ በመጪው ነሐሴ በብራዚል በሚከናወነው የሪዮ ኦሊምፒክ ትሳተፋለች፡፡ በኦሊምፒክ መድረክ ለ13ኛ ጊዜ በምትገኝበት የዘንድሮው 31ኛ ኦሊምፒያድ፣ በአራት የስፖርት ዓይነቶች መሳተፍ የሚያስችላትን ዝግጅትም ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ እስካሁን ባለው በአትሌቲክስ፣ በውኃ ዋና እና በብስክሌት ለሪዮ ኦሊምፒክ የሚያበቃትን መስፈርት ማሟላቷም ተረጋግጧል፡፡ ዝግጅቱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፋይናንስና መሰል ግብዓቶችን ማሰባሰብ የሚችሉ የተለያዩ ኮሚቴዎች አዋቅሮ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ አገሪቱ በዋናነት በምትወከልበት አትሌቲክስ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ)  ተጠርጥረው በምርመራ ላይ መገኘታቸው በሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ላይም ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚሉ ሥጋቶች እየተደመጡ ይገኛል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ይናገራሉ፡፡ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡-  የሪዮ ኦሊምፒክ 138 ቀናት ቀርተዋል፡፡ ዝግጅቱ እንዴት እየሄደ ነው?

አቶ ብርሃነ፡- የሪዮ ኦሊምፒክ የቀረው የአራት ወር ጊዜ ነው፡፡ በዕቅድ የተያዙትን ስፖርተኞች ሚኒማ የመለየት ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሌላው ለሪዮ የሚያስፈልገው የበጀት ዝግጅት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዘንድሮው ተሳትፏችን በአራት የስፖርት ዓይነት በመሆኑ ለዚያ የሚበቃ በጀት ለማሰባሰብ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡ በቅርቡም ሥራው ይጀመራል፡፡ በሕዝብ ግንኙነት በኩል በተመሳሳይ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ ኮሚቴው ስለ ሪዮ ኦሊምፒክ ምንነትና ፋይዳ ስለሚመለከተው አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶች በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡ በተሳትፎ ደረጃ በአትሌቲክስ፣ ብስክሌትና ውኃ ዋና የተሳትፎ ማረጋገጫ ተገኝቷል፡፡ ዝግጅቱም እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሌሎች ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካሎች ጋር በመሆን የለንደን ኦሊምፒክን መነሻ በማድረግ ግምገማዎችን አድርጓል፡፡ የግምገማው መነሻና ፋይዳው ምንድነው?

አቶ ብርሃነ፡- ሁሉም እንደሚረዳው ስፖርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠና እያደገ ከመምጣቱም ባሻገር ሳይንሳዊ ግኝቱም በዚያው መጠን እያደገ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም የዚሁ አካል እንደመሆኗ ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ካለፉት የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻል ዘንድ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ አትሌቶቻችን በአካላዊና በሥነ አዕምሮ ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ ምን መደረግ እንዳለበት፣ ለዚያ ደግሞ በቂ የሕክምና ባለሙያዎች ሊኖሩ እንደሚገባ፣ በምንገኝበት በዚህ ወቅት ስፖርተኞች ባመጋገብ፣ በአካላዊ እንቅስቃሴና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር የሚሹበት ወቅት በመሆኑ፣ መጠንና ዓይነቱን መለየትና ለማወቅም ስለሚረዳን ያንንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ቴክኒካዊ የሆኑ ጉዳዮችም በተመሳሳይ ልዩ ትኩረት መስጠት ስላለብንም ጭምር ነው፡፡ በእነዚህ መነሻነት ተወዳዳሪዎች ሊሟሉላቸው የሚገቡ ነገሮችን ለማሟላት አስበንም ያደረግነው ነው፡፡ እነዚህን ማድረግ ከቻልን ደግሞ በሁሉም ስፖርቶች ከተሳትፎም በላይ ውጤት የምናገኝበት አግባብ ስለሚኖር ማለት ነው፡፡ እንደተገለጸው በሪዮ ኦሊምፒክ አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ለማግኘት አቅድናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከገቢ አሰባሰቡ ጋር ተያይዞ እስካሁን ከማቀድ ባለፈ ወደ ተግባር  አልገባችሁም፣ አልዘገያችሁም?

አቶ ብርሃነ፡- አጠቃላይ ዕቅድ አዘጋጅተናል፡፡ በዕቅዱ መሠረት ደግሞ የሥራ ክፍፍል መኖር እንዳለበት ከመዘጋጀት ውጪ እንደተባለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልጀመርንም፡፡ እርግጥ ነው ዕቅድ የተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዱ አካል ነው፡፡ ምክንያቱም የዕቅድ ዝግጅት ወደ ተግባር ለመሸጋገር ግማሽ መንገድ የመሄድ ያህል ስለሆነ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካለፈው ተሞክሮ የአገሪቱ የኦሊምፒክ ተሳትፎ በዋናነት አትሌቲክስ ነው፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አካባቢ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር የተገናኙ አለመግባባቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይኼ ለኦሊምፒክ ዝግጅቱ ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡

አቶ ብርሃነ፡- የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራር ከጽሕፈት ቤቱ ጀምሮ ዝግጅቱን በሚገባ እየተከታተለው መሆኑን ነው የምናምነው፡፡ የዕቅድ ዝግጅቱም በሪዮ ኦሊምፒክ ካለፈው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያለመ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በፌዴሬሽኑ አካባቢ የተወሰኑ አለመግባባቶች እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡ ያም ቢሆን ያን ያህል ጉዳት ይኖረዋል፣ ለዝግጅቱም እንቅፋት ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በአትሌቲክሱ ሥራን ማዕከል ያደረገ አለመግባባትና መሳሳብ ወደፊትም ይኖራል፣ መኖርም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለተሳታፊ ፌዴሬሽኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የሚያደርገው ድጋፍ በምን አግባብ ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያደርገው ክትትል ምን ያህል ነው?

አቶ ብርሃነ፡- በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሌሎች ለየት የሚልበት ለክትትልና ቁጥጥር ብቻም ሳይሆን ለሁሉም ሥርዓት አለው፡፡ ከፋይናንስ አጠቃቀም ጀምሮ እንዴትና በምን አግባብ እንደሚሠራ ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ የፋይናንስ መመሪያም አለው፡፡ አንዳንዱ ሥራና እያንዳንዱ ወጪ የሚገመገምበት መቆጣጠሪያ (ቼክ ሊስት) አለው፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ማናቸውንም ሥራዎች የሚያከናውነው በዚህ አግባብ ስለሆነ የሚያደርጋቸው ድጋፎችና ክትትሎችም ይህንኑ መስመር የተከተሉ ናቸው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚያንቀሳቅሰው የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በዚህ ረገድ ጎልቶ የወጣ ክፍተት የለም፡፡ አሠራሩ በራሱ ለዚያ የሚያመችም ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ እንደሌሎች አገሮች የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ሰፊ አይደለም፡፡ የምትሳተፍባቸው ስፖርቶች ውስን ናቸው፡፡ ወጪውም በዚያው መጠን ውስን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ያን ያህል ለአሠራርም ሆነ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ስለማይሆን ብዙም ችግር አይፈጥርም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፊቱ ለፊቱ ሁለት ትልልቅ ጉዳዮች ይጠብቁታል፡፡ አንደኛው ሪዮ ኦሊምፒክ  ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የሚከውነው የኦሊምፒክ አካዴሚዎች ግንባታው ተጀምሯል፡፡ ኮሚቴው አሁን ካለው የፋይናንስም ሆነ የሰው ኃይል አቅም አኳያ ሁለቱን ፕሮጀክቶች በጥምረት ለማስቀጠል አይቸገርም?

አቶ ብርሃነ፡- በኦሊምፒክ ኮሚቴው የሚንቀሳቀሱት ፕሮጀክቶች በተለይ የስፖርት አካዴሚዎቹ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ይኼ ባለበት ነው የሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት እየተከናወነ የሚገኘው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከሕዝባችንና ከመንግሥታችን ጋር በመሆን ይኼንን ዕውን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም የአገራችን ስፖርት ከችግርና ከውድቀት ሊወጣ የሚችለው እነዚህን የመሰሉ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ሲከናወኑ ጭምር ነው፡፡ የግድ ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡ እንደተባለው ሊገነባ የታቀደው የኦሊምፒክ አካዴሚ ለአገሪቱ ስፖርት ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህን ታሳቢ አድርጎ ነው ዕቅዱን እያስፈጸመ ያለው፡፡ ካለው የፋይናንስና የሰው ኃይል አቅም አኳያ ይከብዳል፤ እውነት ነው፡፡ ግን ደግሞ ቁርጠኝነቱ ካለ ያለውን በማብቃቃት የምንወጣው ይሆናል፡፡ ለፕሮጀክቶቻችን ቅደም ተከተል አውጥተን እየሠራን ነው፡፡ ደግሞሞ የሕዝብና የመንግሥት ድጋፍ ካለ ይሳካል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በትኩረት የምንከታተለው የሪዮ ኦሊምፒክን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሕዝቡና ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አቋሙን ለማጠናከር ምን ዓይነት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እየተጠቀመ ይገኛል?

አቶ ብርሃነ፡- ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በዚህ ረገድ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠበት ወቅት የለም፡፡ አቅሙን ለማጠናከር የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኢንተርናሽናልና የቢዝነስ ተቋማት ጋር የሚሠራው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም በተለያየ አጋጣሚ ያገኘናቸው የቢዝነስና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ አካላትም ይህንኑ ለመደገፍ አዝማሚያና ፍላጎት ያሳዩንም አሉ፡፡ ሌላውና ዋነኛው ሕዝባችንና መንግሥታችን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህንን ላደርግ ስለሆነ እባካችሁ የገንዘብ ድጋፍ አድርጉልኝ በማለት ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ሕዝቡ በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ድጋፍ የሚያደርግበትን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጭምር በማዘጋጀት ነው፡፡ እያዘጋጀም ይገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ወጪ የሚገኙ የቢዝነስ ተቋማትም ራሳቸውን ጠቅመው አገሪቱን የሚጠቅሙበት ስለሚሆን የምንሄድበት ይሆናል፡፡ ብዙዎቹንም በአካል አግኝተን እያግባባናቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጊዜ መውሰዱ ካልሆነ በእርግጠኛነት የምናነሳካው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አሁን ላይ አቅሙ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ብርሃነ፡- ተቋሙ አቅሜ የሚለው አደረጃጀቱ፣ የአሠራር ሥርዓቱ፤ የፋይናንስ ሥርዓቱንና የሰው ኃይሉን በድምር ስናየው የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ተቋማዊ ቁመና ተልዕኮውን ለመፈጸም የሚያስችል ነው፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሒደት ከሚመጡ አዳዲስ አሠራሮችና መዋቅራዊ ለውጦች ጋር ራሱን ማብቃትና ማሳደግ ያለበት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአበረታች ንጥረ ነገር ጋር ተያይዞ ስማቸው እየተነሳ ይገኛል፡፡ አገሪቱንም እያስተቸና እያስወቀሰም ነው፡፡ ይህን አደገኛ ጅምር እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ብርሃነ፡- ዜናው አስደንጋጭም አሳዛኝም ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ እንደ አገር ይህን ነገር በፍጹም የምንቃወመውና የምናወግዘው ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ውጤትና መዘዝ ለስፖርቱም ሆነ ለአገሪቱ አደገኛ እንደሆነ የምንገነዘበውም የምንረዳውም ትልቅ ጉዳይ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ጥርጣሬም ቢሆን ችግሮች እንዳሉ ተረድተናል፡፡ ችግሮቹን ፈትሸን ማጣራት ይኖርብናል፡፡ እየተደረገ ያለውም ይኼው ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን ከዚህ ነፃ የሆነ ስፖርትና ስፖርተኛ እንዲፈጠር ነው መሥራት የሚኖርብን፡፡ በዚህ ጉዳይ እንደ ኦሊምፒክም ሆነ እንደ መንግሥት ጠበቅ ያለ ቁጥጥርና ክትትል ስናደርግ ነው የቆየነው፣ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያሁኖቹም ሆነ የቀድሞዎቹ በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ተፈጥሯዊ በሆነ ብቃታቸው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ያኮሩ መኖራቸውን ነው የምናውቀው፡፡ አሁንም ቢሆን ምንም እንኳ ውጤቱ ወደፊት በይፋ የሚታወቅ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ በጥርጣሬ የተያዙት አትሌቶች ድርጊታቸው እውነት ከሆነ አገሪቱ በዚህ እንደማትደራደር ሊያውቁ ይገባል፡፡ ያም ሆኖ ይኼ ጉዳይ በሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ወቅት መነሳቱ አንዳችም ችግር ሊፈጥር እንደማይችል እግረ መንገዴን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደሚነገረው ጥቂትም ቢሆኑ በዓለም አቀፍ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) ተጠርጥረዋል፡፡ አገሪቱ ደግሞ በዚህ ረገድ ዕርምጃ የምትወስድበት አካሄድ የዘገየና እንዲያውም ጥፋተኞችን የመጠበቅ ዓይነት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይኼ ለወደፊቱ ሌሎች አትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገሩን ለመጠቀም እንዲነሳሱ ያበረታታል የሚሉም አሉ፡፡ እንዴት ያዩታል?

አቶ ብርሃነ፡- ዞሮ ዞሮ ጥርጣሬው ወደፊት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ምንም ሆነ ምን አገሪቱ ይኼን ጉዳይ አሁንም ሆነ ወደፊት ለድርድር እንደማታቀርበው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከለላ የሚሰጥ አንዳችም ሊኖር አይችልም፡፡ ስለሆነም በዚህ ነገር የመጀመሪያ ተጠያቂዎቹና ተጎጂዎቹ ራሳቸው አትሌቶቹ ስለሚሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ነገር ይኼ ነገር እንደማይጠቅም አትሌቶቹ ያውቃሉ፣ ያደረጉትም ይኼንኑ እያወቁ በመሆኑ ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በአጠቃላይ ግን ይኼ ጅምር በምንም መመዘኛ አያስኬድም፡፡ ሌላው አትሌቶቹ ወደ እዚህ ውሳኔ ሲገቡ ከሐሳባቸው ጎን ለጎን የሚኖሩ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና ሌሎችም አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ጉዳቱ ከአትሌቶቹም ሊያልፍ እንደሚችል ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ ማንም ሰው ከለላ መስጠት የሚችል አይኖርም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...