Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሲቪል አቪዬሽን የተዘጋውን የኢትዮ ኤርትራ የአየር ክልል ለመክፈት ጥረት ላይ ነው

ሲቪል አቪዬሽን የተዘጋውን የኢትዮ ኤርትራ የአየር ክልል ለመክፈት ጥረት ላይ ነው

ቀን:

በግንቦት 1990 ዓ.ም. ባጋጠመው የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ምክንያት ላለፉት 20 ዓመታት ተዘግቶ የቆየውን የሁለቱ አገሮች አዋሳኝ የአየር ክልል ለማስከፈት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ታወቀ፡፡

      ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ከደረሱባቸው በርካታ ስምምነቶች መካከል በሁለቱ አገሮች መካከል ተቋርጦ የነበረው የአየርና የየብስ ትራንስፖርት መጀመር በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አባል የነበሩበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪው ሳምንት ከአዲስ አበባ አስመራ በረራ እንዲጀምር ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ከሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዘመናዊ በሆነው ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ዕለታዊ በረራ ወደ አስመራ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 27 ቀን 1993 ዓ.ም. የፈረሙት ስምምነት በመኖሩ አዲስ ስምምነት መፈረም አላስፈለገም፡፡ በቀን አንድ ጊዜ የሚጀምረው በረራ በሒደት ፍላጎቱ እየታየ ቁጥሩ እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሁለቱ አገሮች የተፈረመው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነት ጥሩ የሆነ ስምምነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ያቋረጠው ግንቦት 5 ቀን 1990 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ የሁለቱ አገሮች አዋሳኝ የአየር ክልል ለማንኛውም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዝግ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በወቅቱ ባለሥልጣኑ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሲቪል ኢቨዬሽን ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ክልሉ የጦር ቀጣና በመሆኑ የአየር ክልሉ ለአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዝግ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ ጥያቄውን የተቀበለው ዓለም አቀፉ ድርጅት የአየር ክልሉን ዘግቶታል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ብቻ ሳይሆን፣ በኤርትራ አየር ክልል አቋርጦ ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ የበረራ መስመር በመቀየር በሱዳንና በጂቡቲ በኩል ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ይኼም የአየር መንገዱን የነዳጅ ፍጆታ (ወጪ) በተወሰነ መጠን እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የአየር ክልሉ ለሃያ ዓመታት ተዘግቶ በመቆየቱ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይንና ሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን አሳፍሮ ወደ አስመራ የበረረው ቦይንግ 737-800 ኔክስት ጄኔሬሽን አውሮፕላን የተከተለው ቀጥታውን የአዲስ አበባ አስመራ የበረራ መስመር ሳይሆን፣ በጂቡቲ በኩል እንደሆነ ታውቋል፡፡

አየር መንገዱ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ አስመራ በረራ የሚጀምር በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋውን የኢትዮ ኤርትራ የአየር ክልል እንዲያስከፍቱለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋው የአየር ክልል እንዲከፈት የሚጠይቅ ደብዳቤ እየጠበቀ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአየር ክልሉ እንዲዘጋ በደብዳቤ የጠየቀ በመሆኑ እንዲከፈት በደብዳቤ መጠየቅ እንደሚኖርበት የገለጹት ኃላፊው፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትዕዛዙን ከተቀበለ ባለሥልጣኑ ለዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ወዲያውኑ ደብዳቤ እንደሚጽፍ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ የተዘጋውን የአየር ክልል የሚከፍት በመሆኑ፣ ይህንኑ ተከትሎ ለሁሉም አገሮች ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት የአየር ክልሉ መከፈት የሚያበስር ማስታወቂያ (ኖታ በመባል ይታወቃል) ይተላለፋል፡፡ ይህ ሒደት የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ይሁንታ እንደሚፈልግ የገለጹት ኃላፊው፣ በሁለት ወይም በሦስት ቀናት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአቪዬሽን ባለሙያዎች የኢትዮ ኤርትራ አዋሳኝ የአየር ክልል በመዘጋቱ የተጎዳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ የአየር ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ የተለያዩ አገሮች አየር መንገዶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአየር ክልሉ መከፈት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ ገበያ ከማምጣቱ በተጨማሪ፣ ነዳጅ የሚቆጥብበት አቋራጭ የበረራ መስመር እንዲጠቀም ያስችለዋል፤›› ያሉት ባለሙያዎቹ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንም ከበረራ ፈቃድና ኤር ናቪጌሽን አገልግሎት በውጭ ምንዛሪ የሚያገኛቸውን ክፍያዎችን እንደሚያሳድግለት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ካበቃ ከዓመታት በኋላ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሁለቱ አገሮች አዋሳኝ የአየር ክልል እንዲከፍት ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት የድርጅቱ ፕሬዚዳንት በናርድ አሊዩ (ዶ/ር)፣ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጥያቄውን አቅርበው ነበር፡፡

የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመር ተቆራርጠው የቆዩትን የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች በማቀራረብ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡ የሁለቱን አገሮች የሆቴል፣ የንግድና የቱሪዝም ዘርፎች እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...