Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጠፋሁት ነገር እንደሌለ ሲያውቁ ይቅርታ እንደሚጠይቁኝ እርግጠኛ ነኝ››

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጠፋሁት ነገር እንደሌለ ሲያውቁ ይቅርታ እንደሚጠይቁኝ እርግጠኛ ነኝ››

ቀን:

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድጋፍ ለማድረግ ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በወጣው ሕዝብ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ፣ ‹‹ኃላፊነታቸውን አልተወጡም›› ተብለው ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የአዲስ አበባ ፖሊስ የቀድሞ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጠፋሁት ነገር እንደሌለ ሲያውቁ ይቅርታ እንደሚጠይቁኝ እርግጠኛ ነኝ፤›› አሉ፡፡  

እስከ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ቦታን ተክተው ይሠሩ የነበሩት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ይኼንን የተናገሩት፣ ሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡበት ዕለት ነው፡፡

በቦምብ ፍንዳታው የተጠረጠሩትን ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላትንና ሰባት የሠልፉ ታዳሚዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን፣ በምክትል ኮሚሽነር ግርማና ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ላይ በተሰጠው 14 ቀናት የሠራውን ምርመራ ሥራ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ በወቅቱ የዋና ኮሚሽነሩን ቦታ ተክተው ይሠሩ ነበር፡፡ በመሆኑም በሥራቸው የጥበቃ ቀለበት ሦስትና ቀለበት አራት ላይ የሚደረግን ፍተሻ መከታተል፣ መቆጣጠርና ክትትል ማድረግ ሲገባቸው ባለማድረጋቸው አደጋ በመድረሱ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብለው ተጠርጥረዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ኮማንደር ገብረ ኪዳን አስገዶም የቀጣና ኃላፊ ሲሆኑ በዕለቱ በሥራቸው የተሠማራውን የፀጥታ ኃይል ማዘዝ፣ መቆጣጠር፣ መከታተልና ማስተባበር ሲገባቸው፣ ይኼንን ባለማድረግ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ተጠርጥረዋል፡፡ ኮማንደር ገብረ ሥላሴ ተፈራም የፌዴራል ፖሊስ አባል ሲሆኑ፣  የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አዛዥ ናቸው፡፡ እሳቸውም የተጠረጠሩት ማጀብ፣ ፍተሻ ማድረግና በመስቀል አደባባይ ዙሪያ ያለውን ሥፍራ መቆጣጠር ሲገባቸው፣ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ነው፡፡ ኮማንደር ግርማይ በርሄም የፌዴራል ፖሊስ አባል ሲሆኑ፣ ኃላፊነታቸውም የወንጀል መከላከልና ኢንተለጀንስ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ የአካባቢውን ሁኔታ ማጥናት፣ የኢንተለጀንስ ቡድኑን መከታተልና ከባልደረቦቻቸው ጋር በመመካከር መምራት ሲገባቸው ሳያደርጉ በመቅረታቸው ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት መጠርጠራቸውን አስረድቷል፡፡ ኮማንደር አንተነህ ዘለዓለም የተባሉ ተጠርጣሪም የቀጣና አራት ዲቪዥን አዛዥ ሲሆኑ፣ ያሰማሯቸው የፀጥታ ሰዎች በአግባቡ ፍተሻ ማድረጋቸውን መከታተል፣ መቆጣጠርና ትዕዛዝ መስጠት ሲገባቸው ባለማድረጋቸው ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት መጠርጠራቸውን ገልጿል፡፡ ምክትል ኮማንደር አባቡ ዳምጤ ሻለቃ አዛዥ ሲሆኑ፣ እሳቸውም የሰጡት ትዕዛዝ መፈጸሙን መከታተል፣ መቆጣጠርና መጠየቅ ሲገባቸው ባለማድረጋቸው ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብለው መጠርጠራቸውን አስረድቷል፡፡ የሻለቃ አዛዥ ናቸው የተባሉ ምክትል ኮማንደር አብዲሳ ባይሳ፣ የኃይል አዛዥ ናቸው የተባሉ ምክትል ኢንስፔክተር አገሬ ቀነኔ፣ የጋንታ አዛዦች ዋና ሳጅን ድራር ታረቀኝና ዋና ሳጅን ከድር ዓሊም በተመሳሳይ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብለው መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክሮች ቃልና የእምነት ክህደት ቃል መቀበሉን፣ ልዩ ልዩ ማስረጃዎችን እንደኃላፊነታቸው ማስረጃ ማሰባሰቡን፣ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን መያዙን፣ የተሰበሰቡ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ለምርመራ መስጠቱንና ብዙ ምርመራዎችን ማድረጉን አስረድቷል፡፡ የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ተጠርጣሪዎች በክልሎችም ስላሉ ምስክሮችን ማምጣት፣ የተከሳሽነት ቃል መቀበል፣ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን መያዝ፣ ለምርመራ የተሰጡ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ውጤት መቀበልና አሻራ መቀበል እንደሚቀረው ገልጾ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡  

የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ቀን ጥያቄ የተቃወሙት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ‹‹የተሳሳተ መረጃ ሊኖር ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለማጥፋቴን በሒደት ሲያውቁ ይቅርታ እንደሚጠይቁኝ እርግጠኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የድጋፍ ሠልፍ የሚመራበት የሥራ መመርያ ሰነድ በእጁ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ፣ ሥራው የተመራው በዘጠኝ ኮማንድ መሆኑን ጠቁመው፣ እሳቸው የተለየ የሥራ ድርሻ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡ የሥራ ድርሻቸው ከሌሎቹ ኮማንድ ኃላፊዎች ጋር ተመሳሳይና ዕቅድ ማውጣት፣ ጥበቃ በሚደረግባቸው ቀለበቶች ኃላፊዎችን መመደብ መሆኑንና ያንን በተገቢው ሁኔታ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡ ከአንድ እስከ አራት ባሉ የጥበቃ ቀለበቶች ለተመደቡት የፖሊስ፣ የደኅንነትና ሌሎች የፀጥታ ኃላፊዎች የዘጠኙም ኮማንድ ኃላፊዎች በጋራ መመርያ መስጠታቸውን አስታውሰው በዕቅዱ መሠረት ሌሊት ወደ ሥራ ገብተው ሥምሪቱን መቆጣጠራቸውንና ምንም ዓይነት ክፍተት እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡ እሳቸውም ሆኑ ሌሎቹ የኮማንድ ኃላፊዎች የተደራጀ ኃይል ማሰማራታቸውን ገልጸው፣ ‹‹እኔ እኮ አልፈትሽም›› በማለት በእሳቸው በኩል ምንም ዓይነት ክፍተት እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በእሳቸው ላይ ምንም ማስረጃ እንደሌለውና ያጠፉት ጥፋት እንደሌለ ተናግረው፣ ሥራው በጋራ የተሠራ መሆኑንና የሠሩትም ሆነ ያጠፉት ጥፋት እንደሌለ ደጋግመው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ጠበቃቸው አክለው እንደገለጹት፣ ሰዎች በመጠርጠራቸው ብቻ ወንጀለኛ አይደሉም፡፡ ዜጎች በወንጀል ከተጠረጠሩ መያዝ የሚችሉት ማስረጃ ከተሰበሰበባቸው በኋላ እንጂ አስሮ ማስረጃ መሰብሰብ አይቻልም፡፡ መንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑ በሕግ ተደንግጎ እያለ፣ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ለ16 ቀናት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ መታሰራቸው አግባብ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

መርማሪው በ16 ቀናት ውስጥ ተጠርጣሪዎቹ ስለሠሩት የወንጀል ጥፋት ያቀረበው ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ እነዚህ 16 ቀናት በፖሊስ የሥራ ሰዓት ቢታሰቡ ከ200 ሰዓታት በላይ መሆናቸውንና ከበቂ በላይ እንደሆኑም አክለዋል፡፡ ፖሊስ ገና የሚይዛቸው ተጠርጣሪዎች ስላሉት ታሳሪዎች መያዣ መሆን እንደሌለባቸው፣ የተቀበላቸው ምስክሮች በምን ላይ ቃላቸውን እንደሰጡ ባላብራራበት ሁኔታ፣ መያዣ አድርጎ ማሰር ሕግን የሚጣረስ አሠራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከአንድ ቀን በላይ አነጋግሯቸው እንደማያውቅ የምክትል ኮሚሽነር ግርማ ጠበቃ ገልጸው፣ የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቅ ተገቢ ባለመሆኑ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሆኑት ተጠርጣሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በሠልፉ ወቅት የተሰጣቸውን ሥራ በአግባቡና በብቃት መወጣታቸውን ገልጸው፣ መርማሪ ቡድኑ የሚፈልገውን ጥያቄ ጠይቋቸው ማጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መሆናቸውንና 27 ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው በእንደዚህ ዓይነት ወንጀል መጠርጠራቸው አግባብ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ለውጥ ፈላጊ መሆናቸውንና በዕለቱ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሥራውን የሠሩት በጋራ ማለትም ፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ደኅንነትና የተለያዩ አካሎች ጋር ሆኖ ሳለ ለምን እነሱ ብቻ ተጠያቂ እንደሆኑ እንዳልገባቸውም ተናግረዋል፡፡ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት ሠርተው ምግብ እንኳን ሳይመገቡ ‹‹ሪፖርት አድርጉ›› ተብለው ተጠርተው ለእስር መዳረጋቸውንም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ የተመደቡበትን ሥራ በአግባቡ በመሥራታቸው ኃላፊነታቸውን እንደተወጡና ምንም ጥፋት እንደሌለባቸው በመግለጽ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡

በሌላ መዝገብ ተጠርጥረው በመጀመርያው ችሎት ከቀረቡት 16 ግለሰቦች መካከል መርማሪ ቡድኑ አጣርቶ ዘጠኙን መልቀቁን በመግለጽ፣ በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡ በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ የበርካታ ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ቤታቸው ሲፈተሽ የተገኙ ማስረጃዎችን በኤግዚቢትነት መያዙን፣ የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው የሚገልጹ ማስረጃዎች በማግኘቱ ለሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ደብዳቤ መጻፉን፣ በፍንዳታው የሞቱ ሰዎችን አስከሬንና የሆስፒታሎች ምርመራ ውጤት መጠየቁን፣ ሁለት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን መያዙን፣ እንዲፈነዳ የተጣለ ቦምብ ተገኝቶ እንዲመረመር መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል ከክልል ጭምር እንደሚቀበል፣ የአስከሬንና የሐኪም ቤቶች የምርመራ ውጤት መቀበል እንደሚቀረው፣ የፈነዳውና እንዲፈነዳ የተጣለው ቦምብ ምርመራ ውጤትና የቪዲዮና የሰዎች ማስረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚቀረው ጠቁሞ ተጨማሪ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎች ለድጋፍ ሠልፉ ከመውጣታቸው ውጪ ምንም የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለ ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡ ላለፉት 16 ቀናት ቤተሰብ እንዳልጠየቃቸው፣ ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ብርሃንና ሕክምና እንደማያገኙም ተናግረው፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብትና በነፃ እንሰናበት ጥያቄ በመቃወም ተከራክሯል፡፡ የፖሊስ አባላት ቤተሰቦቻቸው ደመወዝ እንዳላገኙ የተናገሩት በስህተት መሆኑንና በወንጀል የተጠረጠረ የፖሊስ አባል ጥፋተኛ እስከሚባል ደመወዝ እንደሚከፈለው በአዋጅ የተደነገገ መሆኑን በማስረዳት፣ ቤተሰቦቻቸው መውሰድ እንደሚችሉና እየወሰዱ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በጨለማ ቤት መታሰራቸውን፣ ቤተሰብ እንደማጠይቃቸውና ሕክምናን በሚመለከት መርመሪ ቡድኑ እውነት መሆኑንና አለመሆኑን እንደሚያጣራ ገልጾ፣ ሁሉም እንዲስተካከል እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡ በመሆኑም የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ስለሚያስፈልገው እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዕለቱንም ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠርጣሪዎች የጠየቁት ዋስትናን በማለፍ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቃቸው ተጨማሪ ቀናት ውስጥ 11 ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ጨለማ ቤት ታሰርን ያሉት እንዲስተካከል፣ ቤተሰብና ዘመድ እንዲጠይቃቸው፣ ሕክምና እንዲያገኙና ይኼንን አረጋግጦ መርማሪ ቡድኑ ለቀጣይ ቀጠሮ ሪፖርት እንደያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...