Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የባንኩን አመራሮች አስጠነቀቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የተጠየቀው የደመወዝ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ምላሽ እየተጠበ ነው››

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ዓመታት በላይ ያስጠናው አዲስ መዋቅር ሲጠናቀቅ፣ ሠራተኞችና የባንኩ አመራር የተሰማሙባቸው ነጥቦች ሳይካተቱ በመቅረታቸው፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ሠራተኞችን ወክሎ አመራሩን አስጠነቀቀ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ መዋቅር ለማሠራት የወጣውን የንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ ጨረታ ያሸነፈው ፍራንክፈርት ስኩል ኦፍ ፋይናንስ ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ጥናቱን አጠናቆ መዋቅሩን ለባንኩ ማስረከቡን የሠራተኛ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሃይማኖት ለማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አዲስ በተሠራው መዋቅር ሠራተኞች በጉጉት የሚጠብቁት የደመወዝ ማስተካከያ ቢሆንም፣ ያለ ደመወዝ ማስተካከያ መዋቅሩ በመሠራቱ በሠራተኞች ላይ ቅሬታ ተፈጥሯል፡፡ የቅሬታው ምክንያት ባንኩ የደመወዝ ማስተካከያ ካደረገ አምስት ዓመታት በማለፉ ነው፡፡ ከባንኩ አመራሮች ጋር በተደረገ ተደጋጋሚ ውይይት፣ በአዲሱ መዋቅር የደመወዝ ማስተካከያ እንደሚደረግ መተማመን ላይ ተደርሶ ስለነበር መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡

‹‹የሠራተኞችን ችግር የተነገራቸው የባንኩ አመራሮች አዲሱ መዋቅር ተግባራዊ ሲደረግ ችግሩ አብሮ እንደሚፈታልን ቃል ገብተውልን ነበር፤›› የሚሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ምንም እንኳን  የመዋቅር ለውጡ ጥናት ሲካሄድ የሠራተኛ ማኅበሩ የሠራተኞች ውክልና ይዞ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ባይሳተፍም፣ ከሠራተኞች ጋር በመሆን መዋቅሩን በከፍተኛ ተስፋ ሲጠብቅ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የሠራተኛውን ደመወዝ ማስተካከያ ሳያካትት ተግባራዊ መሆን የጀመረው አዲሱ መዋቅር በሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑን ያስታወቁት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ከአዲሱ መዋቅር ጋር ተያይዞ ሠራተኞች የሚያነሱት ቅሬታ ባልተመለሰበት ሁኔታ ተግባራዊ መደረጉ አግባብ ስላልሆነ እንዲቆም የባንኩን አመራር መጠየቃቸውንም አስረድተዋል፡፡

የባንኩ አመራርና የሚመለከተው የመንግሥት አካል የሠራተኛው ጥያቄ አግባብ መሆኑን ተመልክተው ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ፣ ማኅበሩ ከሠራተኞች ጋር በመሆን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅና ሕገ መንግሥቱ የሚፍቅዱለትን ማንኛውም ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡ ጥያቄያቸው ለፖለቲካ ፍጆታ የሚውል ሳይሆን፣ ሠራተኞችንና የሠራተኛውን ጥያቄ ብቻ የሚመለከት መሆኑንም መንግሥት እንዲረዳቸው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የባንኩን ደንበኞች በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ላለፉት 75 ዓመታት የሕዝብ አለኝታ መሆናቸውን እያስመሰከሩ እንደሆነ አቶ ሃይማኖት ጠቁመው፣ የ75 ዓመታት ስኬት የመጣው በተዓምር ሳይሆን በሠራተኞች ያላሰለሰ ጥረት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ የአስተዳደር ዕርከን ላይ ያሉ የሥራ መሪዎች ለሠራተኞች እየሰጡት ያለው ክብርና ተደማጭነት እየተሸረሸረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን ሠራተኞች የሚጠይቁት መብት የማግኘትና ግዴታቸውንም እንዲወጡ ለመወሰን በባንኩና በሠራተኞች መካከል የተደረገ የስምምነት ውል ቢኖርም፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል ሊስተካከል እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የባንኩ ሠራተኞች ያቀረቡትን ቅሬታ በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ እንደገለጹት፣ በባንኩ ዕድገትና ስፋት ምክንያት ዕድገቱን ሊሸከም የሚችል አዲስ መዋቅር ተሠርቷል፡፡ ከመዋቅሩ ጋር ተያይዞ የደመወዝ ጭማሪና ማስተካከያ እንደሚደረግ ባንኩ ከሠራተኞች ጋር በተስማማው መሠረት፣ ፕሮፖዛል ተሠርቶ ለሚመለከተው አካል መተላለፉንና ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሠራተኛ ምደባን በሚመለከት ባንኩ ያስቀመጣቸው መሥፈርቶች ስላሉ በመሥፈርቶቹ መሠረት እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው፣ ይኼንንም የሚያስፈጽም ኮሚቴ ስለተቋቋመ ሁሉም ነገር ፍጻሜ የሚገኘው በዚያ በኩል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሠራተኞች የሚመደቡት በሥራ ምደባ መመርያ ላይ በተቀመጡት መሥፈርቶች መሠረት ተወዳድረው መሆኑንም አክለዋል፡፡ ያለው ቦታ ውስን በመሆኑ ሁሉንም ሠራተኛ ማስደሰት እንደማይቻል የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ቅሬታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች