Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሰላም የተዘረጉ እጆች እንዳይታጠፉ!

‹‹ጥላቻ ካንሰር በመሆኑ ተሸክሞት የሚዞረውን ሰው ይገድላል፤›› እንዲሉ፣ የዓመታት ጥላቻና ቂምን በፍቅርና በይቅርታ መፋቅ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ግዴታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እሑድ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. አስመራ ሲገቡ መታዘብ የተቻለው፣ ፍቅርና ይቅርታ ባሉበት የጥላቻ ግድግዳ አቅም እንደሌለው ነው፡፡ ፍቅርና ይቅርታ እልህም ያስተነፍሳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ወትሮ ፈገግታ ታይቶባቸው የማይታወቁት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በፈገግታና በሳቅ ሲንፎለፎሉ መታየታቸው፣ ጥላቻ ፅኑ ደዌ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት አገር ሲሆኑ ሁሉም ነገር በሥርዓት ባለመከናወኑና በርካታ ጉዳዮች በመበላሸታቸው ምክንያት፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖች በከንቱ ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ በርካታ ሺዎች ናቸው፡፡ በሁለቱ ደሃ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ደርሷል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ለሃያ ዓመታት እንደ ጠላት ተፈራርጀው ተለያይተዋል፡፡ አስተዋይና አርቆ አሳቢ አመራር በመጥፋቱ ወርቃማ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ አዲስ ወንድማዊ ግንኙነት እንዲጀመር፣ ለሰላም የተዘረጉ እጆች እንዳይታጠፉ በርትቶ መሥራት ተገቢ ነው፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ለማድረግ በአስመራ አደባባዮች ከተገኙ ኤርትራውያን ጀምሮ እስከ ፕሬዚዳንቱ ድረስ በገጽታቸው ላይ የታየው ስሜት፣ ሰላም ምን ያህል ኃይል እንዳለው በሚገባ ያስገነዝባል፡፡ ከዚህ ቀደም ቀናነትና አዎንታዊ አመለካከቶች በመጥፋታቻው ብቻ ድንበር ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራዊትና ከባድ መሣሪያዎች መከማቸታቸው የፈየደው ባለመኖሩ፣ ይቅርታና ፍቅር በመሻት መነጋገር ሲቻል የሚሊዮኖች ልብ ተማርኳል፡፡ ብዙዎችን በእንባ ያራጨውና በሕልሜ ነው ወይስ በውኔ ያሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስመራ አቀባበል የታሪካችን አንድ ምዕራፍ ሆኗል፡፡ ይህ አስደማሚ ምዕራፍ ለዘለቄታው በአስተማማኝነት እንዲቀጥል ደግሞ ከውስጣችን ጥላቻን አንጠፍጥፈን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ የዘረጋነው የሰላም እጅ በኤርትራውያን ወንድሞቻችን በፍቅር እንዲጨበጥ ስንፈልግ፣ እርስ በርሳችንም ሰላም ማውረድ አለብን፡፡ እኛ እርቁንና ሰላሙን ከቤታችን ስንጀምር፣ ለሃያ ዓመታት የተለያዩን ኤርትራውያን የሰላም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ይቀበሉናል፡፡ የአስመራ እናቶችና አባቶች ይኼንን ምልክት አሳይተውናል፡፡

አስተዋዩና ብልሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤርትራዊያን ወንድሞቹ ሕመም ውስጡ ዘልቆ እንደገባ በግልጽ ታይቷል፡፡ ሕዝባችን ድሮም ቢሆን ወገኖቹን የሚጠላበት ምክንያትም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከሕዝቡ ፍላጎት በተቃራኒ የቆሙ የሰላም ጠንቆች፣ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ መሽገው ሲያደሩት የነበረው ተንኮልና የሚረጩት መርዝ አደብ መግዛት አለበት፡፡ ሕዝብን አንዴ ማታለል ቢቻልም፣ ደጋግሞ ለማታለል መሞከር ግን እርቃን ያስቀራል፡፡ የሁለቱን አገሮች የወደፊት ብሩህ ተስፋ ከማመላከት ይልቅ፣ ጨለማው ላይ ብቻ ማፍጠጥ የሚቀናቸው ጨለምተኞች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ የኪሳራ ፖለቲከኞች ‹ወተት ለምን ነጭ ሆነ? ኑግ ለምን ጠቆረ?› እያሉ ከማወዛገብ አልፈው ስለሰላም ሲሰበክ ስለጦርነት፣ ስለደኅንነት ሲነገር ስለሥጋት እያወሩ ያደናግራሉ፡፡ በተለይ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንደገና የመጀመር ተስፋ በአደባባይ በግልጽ እየታየ፣ ስለዕልቂትና ውድመት መለፈፋቸው ለሕዝብ ደንታ እንደሌላቸው አጋልጧቸዋል፡፡ አሁን ጊዜው ስለነዚህ ከንቱዎች መነጋገር ሳይሆን በባከኑት ዓመታት እየተቆጩ ለሁለቱ አገሮች ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ሲባል ተባብሮ መሥራት ብቻ ነው፡፡

ለማንም አገሩን ለሚወድ ሰው አዕምሮ ሰላም የሚሰጠው ንፁህ ህሊና ነው፡፡ ከሴራና ከአሻጥር በመፅዳት ጥርጣሬና ፍራቻን ከማስተጋባት መላቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ጥላቻ፣ እልህና ቂም ያተረፉት ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ እነ አቶ ኢሳያስ ውስጥ ይንተከተክ የነበረውን እልህ ያስተነፈሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይዘው የተነሱት የፍቅር፣ የይቅርታና የሰላም ጥሪ ነው፡፡ ይህ ከልብ የቀረበ የፍቅር ጥሪ የዓመታት ጥላቻና እልህን ካረገበ፣ መጪውን ጊዜ በሰላም አብሮ ለመጀመር ምንም የሚያስቸግር ሰበብ አይኖርም፡፡ በቃል መገኘትና ለሕዝብ ክብር መስጠት ጥላቻና ጥርጣሬን ያጠፋል፡፡ እንጥፍጣፊ ጥርጣሬ ቢኖር እንኳ እንደ ፀሐይ ፍንትው ብሎ የሚታየው ቀናነት ባዶ ያስቀረዋል፡፡ ካሁን በኋላ የፖለቲካ ብልኃቱ ለሁለቱ አገሮች የጋራ ዕድገትና ብልፅግና እንዲውል እንጂ፣ ጊዜ ያለፈበት የመጃጃል ሴረኝነት ሰለባ እንዳይሆንም መትጋት ይገባል፡፡ የዓመታት ጠባሳ የሚታከመው የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የጋራ ጥረት ሲደረግ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና መረጋጋት ማስፈን የሚቻለው፣ ሁለቱ አገሮች ወትሮ ከሚታወቁበት ጥላቻና ቂም ውስጥ ሲወጡ ነው፡፡ የሰላም እጆች ተዘርግተው አንድ ላይ መቆም ሲቻል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ከሚታሰበው በላይ ይሆናል፡፡

እርግጥ ነው በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት መከናወን ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሁለት መንግሥታት ግንኙነታቸውን እንደገና ሲያድሱ ቀድሞ የተበላሹና የተዛቡ ነገሮችን ከማስተካከል ጀምሮ፣ የአመራሮች ባህሪ ድረስ የሚታዩ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስኮች በሚደረጉ ግንኙነቶች ደግሞ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ፍላጎት ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ ምን ያህል ሰላም እንደተጠማና እርስ በርሱ እንደተነፋፈቀ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኤርትራውያን ወንድሞችና እህቶች ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ጋር በቀና መንፈስ እንዲገናኙና አብረው እንዲያድጉ ማበረታታት የመንግሥታቱ የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ የሰላም እጆች የሚዘረጉት ለታይታ ወይም ለፕሮቶኮል ሳይሆን፣ የሁለቱም ወገኖች እኩል ኃላፊነት እንዳለ ለማረጋገጥ ጭምር ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበሩ መጀነኖችና መኮሳተሮች ተወግደው የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ማቀራረብ የሚቻለው፣ በቂምና በጥላቻ የላሸቁ ልቦች በአግባቡ ታክመው ሲድኑ ነው፡፡ የቀድሞው ማናለብኝነትና እብሪተኝነት ለዚህ ለይቅርታና ለፍቅር ዘመን ስለማይመጥን፣ የአገሮቹን ሰላምና ልማት አንድ ላይ ለማስኬድ የሚያስችል ልብና አደብ መግዛት ያስፈልጋል፡፡ ለጋራ ሰላሙ የሚበጀው ይኼው ነው፡፡

የአስመራ ከተማ እናቶች ያቺን ታሪካዊ እሑድ ለዓመታት ሲመኟት እንደነበሩ በዕልልታ ድምፃቸውን ሲያሰሙና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን እያገላበጡ ሲስሙ፣ ደም ያፋሰሰው ጦርነት አሳዛኝ ምዕራፍ እንዲዘጋ መፈለጉን ከበቂ በላይ መረዳት ተችሏል፡፡ ለብዙዎች የህሊና ቁስል ሆኖ የኖረው በድንበር ተሳቦ የተቀሰቀሰው ጦርነት ላለፉት ሃያ ዓመታት አካባቢውን የሥጋት ቀጣና አድርጎት ቆይቷል፡፡ የሁለቱ አገሮች ዜጎች፣ በተለይም በድንበር አካባቢ የሚኖሩት ከመሠረተ ልማት ተራርቀው የድህነት መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ለአገሮቹ ልማት ይውል የነበረው ውስን ሀብት ድንበር ላይ ለተፋጠጡ ሠራዊት መሣሪያ ግዥና ለተለያዩ ተጓዳኝ ጉዳዮች እየዋለ ሲባክን ቆይቷል፡፡ በድህነት ላይ ጦርነት ተጨምሮ ይቅርና እንዲሁም ስንትና ስንት መከራ ባለባቸው አገሮች፣ የሰላም እጆች ሲዘረጉ በአንድነት በመቆም ከመቀበል ውጪ የሚያዋጣ ነገር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የተለያዩ ዓይነት መሣሪያዎች ያላሸነፉትን በፍቅርና በይቅርታ የተሞላ ልብ ሲያሸንፍ ማስተዋል ተችሏል፡፡ ቀናነትና አዎንታዊ አመለካከት ሲኖሩ ድብርት ከተጫጫናቸው ጨፍጋጋዎች ይልቅ፣ የብርሃን ወገግታ የፈካባቸው ፊቶችን ማየት ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ልቦች በብርሃን ተሞልተው ጨለማውን መሻገር በመሆኑ፣ የተዘረጉት የሰላም እጆች እንዳይታጠፉ ቁርጠኛ መሆን የወቅቱ ዋነኛ ጥያቄ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...