Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተሰናባቹ ከንቲባ ቀጣዩ አስተዳደር ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ጠቆሙ

ተሰናባቹ ከንቲባ ቀጣዩ አስተዳደር ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ጠቆሙ

ቀን:

ተሰናባቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ማጠቃለያ ሪፖርት፣ ቀጣዩ የከተማው አስተዳደር ነዋሪዎችን እያስጨነቁ የሚገኙ ችግሮች በተለይም ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ መልካም አስተዳደርና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ከተማውን ሲያስተዳድር የቆየው የከንቲባ ድሪባ ካቢኔ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን አጠቃሏል፡፡ ነገር ግን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ምርጫ ባለመካሄዱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማው አስተዳደር የሥራ ዘመን እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ነገር ግን ከንቲባ ድሪባ በኃላፊነታቸው ለመቀጠል ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ፣ በዚህ ሳምንት ለኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከንቲባው በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥልቀት ሊሄድባቸው ይገባል ያሏቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች በመተንተን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ከንቲባው እንዳሉት፣ የከተማውን ነዋሪዎች እያስጨነቁ ያሉት ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ደረጃ በደረጃ መቅረፍ የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ድህነትንና የወጣቶች ሥራ አጥነትን መቀነስ ላይ ትኩረት ያደረጉ የሥራ መስኮችን በመለየት በቂ ፋይናንስና የሰው ኃይል በመመደብ መምራት ይገባል፤›› ያሉት ከንቲባ ድሪባ፣ ‹‹ድህነትና ሥራ አጥነት በፍጥነትና በበቂ ሁኔታ ካልተቀረፉ የተረጋጋ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ማስፈን ካለመቻሉም በላይ ብሩህ ተስፋ ያለው ዜጋ መፍጠር ከባድ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአጭርና የረዥም ጊዜ ፕሮግራም፣ ማለትም በፈጣን መፍትሔ አምጪና በዴሊቨሪ ዩኒት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥሉ በማድረግ የሰው ሀብትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 አሥረኛው ማስተር ፕላን በፅኑ ዲሲፕሊን ተግባራዊ እንዲደረግም በማሳሰብ፣ ‹‹በተለያዩ ጫናዎች የከተማ ፕላን ለመጣስ የሚደረጉ ኋላ ቀር አካሄዶች እንዲቀሩ ማድረግ፣ በከተማው የሚካሄድ የትኛውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስተር ፕላኑ በሚፈቅደውና በሠለጠነ አግባብ ብቻ እንዲከናወን ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህ ተግባር ምክር ቤቱም ሆነ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፕላን አፈጻጸም ላይ መረጃ የሚያገኙበትና የፕላን ጥሰትን የሚከላከሉበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹ቀጣዩ የአዲስ አበባ ልማት የሚካሄደው በዋና ማዕከልና በሌሎች ንዑስ ማዕከላት ላይ ትኩረት አድርጎ መሆኑ ተቀምጧል፡፡ ማዕከሎቹ የከተማው የዕድገትና የአገልግሎት ሞተር በመሆን ስለሚያገለግሉ፣ ከተማው ያለውን ሀብትና አቅም አሰባስቦ ማዕከሎቹን የሚያስተሳስሩ ኮሪደሮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል፤›› በማለት የገለጹት ከንቲባው፣ በአረንጓዴ ልማት ላይም ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

የእንጦጦ ልማት መዳረሻ፣ የወረገኑ ፓርኮች፣ የአዲስ አበባ ዙ ፓርክ፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮግራምና የከተማውን አረንጓዴ ሽፋን ለማስፋት የተያዙ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይ የእንጦጦ ቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክት በ413 ሔክታር ላይ የሚለማ በመሆኑ ጥብቅ ደኑን በማይነካ መንገድ ማልማት ይገባል ያሉት ከንቲባው የወንዝ ዳርቻዎች በአረንጓዴ እንዲሸፈኑና ለመዝናኛ እንዲውሉ አሳስበዋል፡፡

ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ የመኖሪያ ቤት ችግርን መቅረፍ እንደሆነ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ከንቲባው እንዳሉት፣ ባለፉት ዓመታት ለመንግሥት ሠራተኞችና ለመምህራን በዝቅተኛ ኪራይ የተሰጡ አሥር ሺሕ ቤቶች ጨምሮ ከ178 ሺሕ በላይ ቤቶች ለነዋሪዎች በመተላለፋቸው 700 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በቤቶች ልማት ፕሮግራም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው እየተፋጠነ የሚገኙ 132 ሺሕ ቤቶች በዕጣ እንደሚተላለፉና 2,000 ቤቶችም በማኅበራት እየተገነቡ እንደሚገኙ ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከቤቶች ልማት አንፃር የተደረገው ጥረትና የመጣው ውጤት ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ ግንባታውን ለማፋጠን የተለያዩ አማራጮችን ማስፋትና ከየትኛውም ሥራ በተለየ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፤›› ያሉት ከንቲባ ድሪባ፣ ‹‹ይህ የቤቶች ግንባታ ሥራ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የአስተዳደሩ ወሳኝ ሥራ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...