የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወራት ያለ አሰልጣኝ ለቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ዋና አሠልጣኝ መሾሙ ታወቀ፡፡ የየመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆኖ የቆየው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለዚህ ኃላፊነት የበቃው ከቀረቡት አምስት ዕጩ አሠልጣኞች መካከል ተመርጦ መሆኑ የፌዴሬሽን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከአወዛጋቢው የምርጫ ክርክር በኋላ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የተረከበው አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ለብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝነት ቅጥር መስፈርት አውጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በመስፈርቱ መሠረት የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም፣ በፌዴሬሽኑ በኩል ለቀረቡት ዕጩዎች የተሰጠው ምላሽ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ሥራ አስፈጻሚው ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለአምስት አሠልጣኞች እንደገና ጥሪ አድርጎ ምርጫ አድርጓል፡፡
ለድጋሚው ምርጫ ከቀረቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል፣ የጅማ አባ ጅፋር ክለብ ዋና አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ፣ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ የመከላከያ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ፣ የሐዋሳ ከተማ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከአገር ውስጥ ሊግ ሲሆኑ፣ ከውጭ የየመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆኖ እየሠራ የሚገኘው ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ ይጠቀሳሉ፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ፣ ፌዴሬሽኑ የቀረቡትን አምስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በተናጠል ካነጋገረ በኋላ፣ ከአምስቱ ሁለቱ ማለትም የጅማ አባ ጅፋሩ ገብረመድህን ኃይሌና የመከላከያው ሥዩም ከበደ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት እንደ እንደማይፈልጉ መግለጻቸውን አሳውቀዋል፡፡ አመራሩም ከቀሩት ሦስቱ ተወዳዳሪዎች መካከል በየመን ለሚገኘው አብርሃም መብርሃቱ የዋሊያዎቹን ሙሉ ኃላፊነት መስጠቱ ታውቋል፡፡