Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲሱ የጡት ወተት ፕሮጀክት

አዲሱ የጡት ወተት ፕሮጀክት

ቀን:

በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ላሉ እናቶች የ120 ቀናት የወሊድ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ይህ ቀድሞ ከነበረው የ90 ቀን ፈቃድ ጋር ሲነፃፀር ለውጡ ተጠቃሽ ቢሆንም፣ አሁን ያለው የወሊድ ፈቃድ ሕፃናትን በሚፈለገው ሁኔታ ጡት ለማጥባት የሚያስችል አይደለም፡፡

ተቀጥረው የሚሠሩ እናቶች ከወሊድ በኋላ በአራተኛው ወር ላይ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ ሰዓት ልጆቻቸውን ተለዋጭ ምግብ እንዲጀምሩ ያደርጋሉ፡፡ ለስድስት ወራት ያህል ያለተጨማሪ ምግብ የእናት ጡት መጥባት እያለባቸው ምግብ እንዲጀምሩ በመደረጋቸውም ሕፃናቱ ለተለያዩ የጤና እክሎች ሲጋለጡ፣ እናቶች ደግሞ ሠርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ውድ በሆኑ የሕፃናት ምግብ ላይ እንዲያውሉ ይሆናል፡፡  በአሁኑ ጊዜ አንድ ቆርቆሮ የሕፃን ወተት ቢያንስ 200 ብር ሲሆን፣ ሕፃኑ በአንድ ሳምንት የሚያስፈልገው አራት ቆርቆሮ ወተት ነው፡፡ ይህም ተለፍቶ የተገኘውን ገንዘብ በአብዛኛው በታሸጉ ምግቦች መግዣ እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡

ቀጥሎም እናቶች ከሥራ ቀርተው የታመሙ ሕፃናትን ለማሳከምና ለመንከባከብ እናቶች ከሥራ እንዲከራተቱ ይሆናል፡፡ በሙያቸው ማደግ በሚገባቸው ፍጥነትና ደረጃ እንዳያድጉ እንቅፋት እስኪሆንባቸው ተፅዕኖው ከባድ ይሆናል፡፡ በጥናት እንደታወቀው፣ በኢትዮጵያ ከስድስት ወር በታች ከሆኑ ሕፃናት መካከል ያለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናት ጡት ብቻ የሚያገኙት 57.7 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡

በሥራ ምክንያት ልጆቻቸውን በተገቢው መጠን ጡት ማጥባት የማይችሉ ደሞዝተኛ እናቶችን ችግር ለመቅረፍ አንድ ዕርምጃ የሆነ ፕሮጀክት ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሕክምና ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ትምህርት ክፍልና በማህፀንና ጽንስ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኙ ተመራማሪዎች በጋራ በመሆን የቀረፁት በሥራ ቦታ የጡት ወተትን አልቦ ማስቀመጥ የሚያስችል አጋዥ ፕሮጀክት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክቱ በግራንድ ቻሌንጅ ካናዳና የካናዳ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ የሚተገበረውም በሙከራ ደረጃ በተመረጡ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ውስጥ ነው፡፡ በባንኩ ውስጥ የሚሠሩ እናቶች ወደ ሥራ ገበታቸው ከተመለሱ በኋላ ልጆቻቸውን በአግባቡ ማጥባታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ነው፡፡

ፕሮጀክቱ እናቶች ጡታቸውን አልበው ወተት እንዲያጠራቅሙና ልጆቻቸውን እንዲመግቡ ያሠለጥናል፤ የጡት ወተት ማለቢያና ማቀዝቀዣ እንዲሁም በምቾትና ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ የጡት ወተታቸውን የሚያልቡበትን ቦታ ከባንኩ ጋር በመተባበር ያቀርባል፡፡  

ጡት ማጥባት ከልጆች በተጨማሪ ለእናቶች ጤና ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ለረዥም ጊዜ ያጠቡ እናቶች ካላጠቡ ሴቶች ጋር ሲነፃፀር በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያ እውነት ገብረሃና (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሕፃናት እስከ ስድስት ወራቸው ድረስ የእናት ጡት ብቻ እንዲሰጡ ይመከራል፡፡ ተግባራዊነቱ ላይ ግን ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ፡፡ ከእክሎቹም መካከል አንዱና ዋነኛው እናቶች ከቤት ወጥተው መሥራትና ማደግ ካለባቸው አራስ ልጆቻቸውን ጥለው ለመውጣት መገደዳቸው ነው፡፡ ሠራተኛ እናቶች ጡት የሚያጠቡበት ከልጆቻቸውም ጋር አብረው የሚኖሩበት ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡

ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል የተባለው ፕሮጀክት ‹‹ግራንድ ቻሌንጅ ካናዳ›› በሚባል ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እንደቀረበ፣ በውድድሩ ከቀረቡትም 1,000 ፕሮጀክቶች መካከል ከተመረጡ 100 ፕሮጀክቶች አንዱ ሆኖ መመረጡን እንዳለፉ ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡ በውድድሩም አዲስ የፈጠራ ሐሳብ አላቸው ወይ? ለኅብረተሰቡ ይጠቅማሉ ወይ? በተለይ ሴቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና ከፍ ያደርገዋል ወይ? መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ይጠቅማል ወይ? ከሚሉ መሥፈርቶች አንፃር የተመዘነ ነው፡፡

‹‹የፕሮጀክት ሐሳቡንም ይዘን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሄድነው ባንኩ የመንግሥት ተቋም ከመሆኑ ባሻገር በመላው አገሪቱ ውስጥ ወደ 30 ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞችና በርካታ ቅርንጫፎች ስላሉት ነው፡፡ ስለዚህ ከባንኩ ጋር አብረን ብንሠራና በውስጡም ያሉት ሴቶች ቢጠቀሙ ባንኩ ለሌሎች መሥሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ሁኔታዎችን በመተግበር ምሳሌ ይሆናል በሚል እምነት ነው፤›› ብለዋል ዶ/ር እውነት፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኙ አምስት ቅርንጫፎች በሙከራ ደረጃ ለመተግበር ስምምነት እንደተደረገና ለተግባራዊነቱም ቅርንጫፍ ባንኮችን ለመምረጥ የሚያስችል የጋራ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ እንደሆነም ዶ/ር እውነት ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሥራ ቦታዎች ላይ የሕፃናት ማቆያ ማዘጋጀት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከአንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስተቀር በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ቢኖሩም ማቆያ ቤቱን ማዘጋጀት፣ ሕፃናቱን የሚንከባከቡ ሠራተኞች መቅጠር፣ ፅዳቱን መጠበቅና የመሳሰሉ ተግባራትን ለማከናወን የሚወጣው ወጪ የትየለሌ ነው፡፡ በከተማው የሚታየው የትራንስፖርት ችግር ሲታከልበት ደግሞ ውጣ ውረዱንና  ተግዳሮቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ አኳያ መፍትሔው ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ ብቻ መሆኑን ከዶ/ር እውነት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ዳይሬክቶሬት የሥርዓተ ምግብ ባለሙያ ወ/ሮ ሕይወት ዳርሰና ‹‹በአገራችን ጡት ማጥባት እንደነውር አይታይም፡፡ ይህ ጥሩ ባህላችን ነው፡፡ በተለይ በገጠር ያሉት ያጠባሉ፡፡ ነገር ግን ልጆቹ እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻና በመጀመርያው አንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ማጥባት፣ እንዲሁም ልጁ በፈለገው ቁጥር ቀንና በማታ ቢያንስ በቀን ከስምንት እስከ 12 ጊዜ መጥባት እንዳለበት አያውቁም፤›› ብለዋል፡፡

የእናት ጡት ወተት ላክቶስ ወይም ካርቦሃይድሬት በብዛት እንዲሁም ለዕድገት የሚያገለግል ፕሮቲንና ኃይል ሰጪ ስብ (ፋት) በተመጣጠነ መልክ መያዙን፤ በአንፃሩ ደግሞ የእንስሳት ወተት ሦስቱንም ነገሮች የያዛቸው ባልተመጣጠነ መልክ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የጣሳ ወተት የሚጠቀሙ ሕፃናት ለተቅማጥ፣ ለአለርጂና ሌሎች ነገሮች የመጋለጥ ዕድላቸው በጣም ሰፊ እንደሆነ ነው ባለሙያዋ ያመለከቱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...