Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ኲሉ ንምርዓይ ምቕናይ ምቕናይ›› - ሁሉን ለማየት መሰንበት መሰንበት

‹‹ኲሉ ንምርዓይ ምቕናይ ምቕናይ›› – ሁሉን ለማየት መሰንበት መሰንበት

ቀን:

በ1970ዎቹ መጨረሻ የትግርኛ ኮከብ ድምፃዊ ነፍስ ኄር ኪሮስ ዓለማየሁ በብዙዎች ዘንድ ሠርፀው ከገቡት ሥራዎቹ አንዷ ‹‹ሉ ንምርዓይ ምቕናይ ምቕናይ…›› ሁሉን ለማየት መሰንበት መሰንበት – ነች፡፡ ለዓመታት ‹‹በፖለቲካ›› ሰበብ ከመቐለ ወህኒ ቤት እስከ አዲስ አበባው ከርቸሌ ዘብጥያ ወርዶ ከሞት መለስ ተሰቃይቶ ከወጣ በኋላ ነበር፣ ሁሉን ለማየት መሰንበት በሕይወት መኖር፣ እያለ ኪሮስ በጥዑም ዜማ ያቀነቀነው፡፡

ይህች እምርት (የታወቀች) ዘፈኑ በሐምሌ መባቻ በዕለተ ሰንበት፣ በአስመራ ቤተ መንግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ክብር የራት ግብዣ በኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካይነት በተደረገበት ምሽት ነበር ኤርትራዊቷ ድምፃዊት እንደ ኪሮስ ክራር እየገረፈች በተመስጦ ያቀነቀነችው፡፡

ለሃያ ዓመታት ዓይንና ናጭ የሆኑት የሁለቱ አገሮች መንግሥታት የጠብና የቁርሾ ግድግዳ ፈርሶ የኢትዮጵያ ልዑካን በኤርትራ መናገሻ ከተማ ተገኝተው መታየቱን  ሁሉን ለማየት ሁሉን ለመመልከት መሰንበት መሰንበት በተሰኘው የኪሮስ ዘፈን ተመስጥሯል፡፡

      ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ለኤርትራ ታሪካዊ ቀን ያሰኛል፤ ለሁለት አሠርታት በባላንጣነት የተያዩ የነበሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ሲተቃቀፉ መታየት ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ለመቀበል ከአስመራ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እስከ አገራዊ ቤተ መንግሥት ድረሰ በነቂስ የወጣው በ100 ሺዎች (በአዕላፍ) የሚቆጠር ከሕፃን እስከ አዋቂ አውራ ጎዳናውን ጭምር በማጣበብ ‹‹ዓብይ ዓብይ›› ሲል የነበረው፡፡

‹‹ሓዳስ ኤርትራ›› ጋዜጣ በማክሰኞ ዕትሙ እንደዘገበው፣ የሁለቱ መሪዎች ፎቶ የተለጠፈበት ነጭ ማሊያዎች ለብሰው ‹‹ዓሸ. . .ሸ ኣቢ! ዓሸ. . .ሸ ወዲ-ኣፌ!!›› እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ‹‹ኣቢ››፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ‹‹ወዲ-ኣፌ›› እያሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

‹‹መጺኻለይ ’ዶ ክጽበየካ. . . እታ ዝምነያ ሎሚ ረኺበያ. . .›› ስጠብቅህ የነበረው መጣህልኝ ወይ፤ ስመኛት የነበረችውን ዛሬ አገኘኋት [አገኘኋት እንደ ተመኘኋት ዓይነት]  እያሉ፣ ከበሮን እየደለቁ፣ እልልታና ሆታን እያሰሙ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን የተቀበሉት፡፡ እሳቸውም በመስኮት እጃቸውን አውጥተው ሲጨብጡም ታይተዋል፡፡

ዘንባባ የያዙት አስመራዎች ከያዟቸው መፈክሮች ውስጥ ‹‹ፍቅር ትስዕር›› [ፍቅር ታሸንፋለች]፣ ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› (በአማርኛ ይዘው)፣ ‹‹ዘ ጌም ኢዝ ኦቨር›› ይገኙበታል፡፡ ካህናትና ዲያቆናት፣ መዘምራንም በጸናጽልና በከበሮ የተዋደደ ዜማም ለአምላክ ምስጋና እያቀረቡ አስተጋብተዋል፡፡

‹‹ዘመናዊት የአፍሪካ ከተማ›› ተሰኝታ በዩኔስኮ ዓምና በሐምሌ ወር የተመዘገበችው የአስመራ ሰማይ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሰንደቅ ዓላማ በምሰሶ ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በሚያሰኝ መልኩ በእጅ ጭምር ተይዞ ተውለውልቧል፡፡  የኤርትራ ቴሌቪዥን (ኤቲቪ) እንዳሠራጨው፡፡

‹‹የቅዱስ ያሬድ ልጆች››

‹‹ይቅርታና ቅንነት ተገናኙ! ጽድቅና ሰላምም ተሳሳሙ!››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን በአስመራ ኤርፖርት ከተቀበሉት ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምነት ጋር የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ነበሩበት፡፡ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ወዘተ ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል፡፡

በኤርትራ ‹‹ባህቲ ሓምለ››፣ በኢትዮጵያ የሐምሌ መባቻ የዋለባት ዕለተ ሰንበት እሑድ፣ በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓተ አምልኮ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አላት፡፡ የግእዝ ሊጡርጊያ (ሥርዓተ አምልኮ) ተብሎ የሚታወቀውና ከቅዱስ ያሬድ የፈለቀው ሥርዓት በኢትዮጵያም በኤርትራም ህያው ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡

በሁለቱም አገሮች ሰኔ ሰኞ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የፀደይ/ፅዳይ ወቅት አብቅቶ በማግሥቱ ሰኔ 26 ማክሰኞ ክረምት ገብቷል፡፡ ሐምሌ 1 ቀን ደግሞ የክረምት ወቅት (ዘመነ ክረምት) የመጀመርያው እሑድ (ሰንበት) የዋለበት ነው፡፡

በዕለተ ሰንበቱ ማለዳ በአዲስ አበባም ሆነ በአስመራ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም. . . ›› የሚለው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር- የዝናብ ኮቴ ተሰማ፣ በዘነበ ጊዜም የተራቡ ይጠግባሉ፣ ያዘኑም ይደሰታሉ፣ ሰንበትንም በሰላሙ ቀዳሳት፤›› በትግርኛም ‹‹አእጋሩ ንዝናም የድምጽ፣ ዝናሙ ምስ ኣፍሰሰ ከዓ ጥሙያት ይጸግቡ ድኻታት ይሕጐሱ. . . ንሰንበት ብሰላሙ ቀደሳ›› ነበር የተዘመረው፡፡ ይህንን ዝማሬ ነው የአስመራ ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ዳግም ያስተጋቡት፡፡

የቅዱስ ያሬድ ልጆች በዚህም ብቻ አልተወሰኑም፡፡ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ‹‹ይቅርታና ቅንነት፣ ይቅርታና ቸርነት ተገናኙ! ጽድቅና ሰላም ተሳሳሙ!›› እያሉም ነበር ያንፀባረቁት፡፡  

በዕለተ ሰንበት ምሽት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና አብረው ለተጓዙ ልዑካን በማዕከላዊ ዞን አስተዳደር አዳራሽ የራት ግብዣ ከሙዚቃ ድግስ ጋር ተከናውኗል፡፡ የትግርኛና የሌሎች የኤርትራ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ በተጓዳኝ የመሐሙድ አህመድ ‹‹ለሰው ልጆች ፍቅር›› የእነ ነዋይ ደበበ፣  ‹‹ሁሉም ቢተባበር. . .›› ኤርትራውያን ድምፃውያን አቀንቅነዋቸዋል፡፡

በኤረቲቪ እንደተላለፈው በምሽቱ የነበረው ተድላና ደስታ አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን በሁለቱ ቋንቋዎች የሰላምን መዝሙር ‹‹ሓደ ኢና፡፡ ባህልና ሓደ መጻኢና ሓደ›› – አንድ ነን፤ ባህላችን አንድ መጪውም አንድ – በሚያሰኝ ቅኝት ታዳሚዎቹን ዘና አድርገዋል፡፡

በመስተንግዶው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ንግግራቸውን ሲጀምሩ ‹‹ዛሬ ትግርኛ የለ አማርኛ የለ- ሁሉም ቋንቋ ጠፍቶብኛል፡፡ ውስጣዊ ስሜቴ ግን ከፊቴ ታዩታላችሁ፤›› ብለው፣ ‹‹ክቡር ፕረሲዳንት ሃገረ ኤርትራ ኣቶ ኢሳይያስ ኣፈወርቂ- ከም አስመራ ድማ ወዲ ኣፈይ!›› – የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ እንደ አስመራዎች አጠራር ወዲ ኣፈይ –  ብለው ሲቀጥሉ የሰሙት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ከዘወትራዊ ሳቅ ባለፈ ከትከት ብለው ነበር የሳቁት፤ አስከትለውም አጨበጨቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ንግግራቸውን ከመቋጨታቸው በፊት በትግርኛ ካነሱት ነጥብ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹ዛሬ በአስመራ የዘነበው የፍቅር ውኃ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ቀንድም እንደደረሰ አይቼዋለሁ፡፡ እናንተም እንዳያችሁትም አንዳች ጥርጣሬ የለኝም፡፡››

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ በበኩላቸው «ይህን የዶ/ር ዓብይ ጉዞ ሕዝቡ እስኪዘጋጅ ድረስ ያዘገየነው ሆን ብለን ነው። ይህንንም ከሕዝቡ ስሜት መረዳት ትችላላችሁ። መናገር አያስፈልገኝም፤» ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኤርትራ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ጋር በሁለቱ አገሮች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም ጉዳዮች ላይ ከተወያዩ በኋላ ከደረሱበት ስምምነት ውስጥ ለሁለት አሠርታትቋርጦ የነበረው የሁለቱ አገሮች ዓለም አቀፍ የስልክ መስመር ሐምሌ 2 ቀን ሥራውን ጀምሯል፡፡ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአየር በረራም ሐምሌ 10 ቀን እንደሚጀምር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብስሯል፡፡

የባህል ግንኙነትን በተመለከተ የአዲስ ዓመት (ቅዱስ ዮሐንስ) በዓል መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች በአስመራ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚያቀርቡ፤ በተመሳሳይም ኤርትራውያን ሙዚቀኞች ወደፊት በአዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ጅማ፣ ሐዋሳና ባህርዳር ሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚያቀርቡ፣ በየዓመቱ በነሐሴ አጋማሽ በሚከበረው የአሸንዳ በዓልም ኤርትራ ሁለት ቡድን ወደ መቐለና አክሱም እንደምትልክ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ የክረምቱን መግባት ተከትሎ፣ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም››- የዝናብ ኮቴ ተሰማ- እንደተባለው ሁሉ፤ በቅኔያዊ ነጠቃ በሁለቱ አገሮች ሰማይም ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለሰላም›› – የሰላም ኮቴ ተሰማ- ብለን ዘለቅን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...