Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርዓለም አቀፍ የፀረ ሰቆቃ ውልና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት

ዓለም አቀፍ የፀረ ሰቆቃ ውልና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት

ቀን:

በመርሐጽድቅ መኮንን ዓባይነህ

ማክሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በምሽቱ የኢቲቪ የዜና እወጃ ላይ ግንባር ቀደም ርዕሰ ጉዳዮች ከነበሩት አንዱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጉብኝት ነበር፡፡ ዛሬስ ማን ሊሞት ነው? ባሰኘኝ በዚያ ያልተለመደ ዜና እንዴት እንደተፈቀደለት ባላውቅም፣ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በአካል ተገኝቶ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ በርካታ ታራሚዎች በእስር ቤቱ ቆይታቸው ይፈጸሙብናል የሚሏቸውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችና ሌሎች በደሎች በድፍረት ሲዘግብ ተመልክቻለሁ፡፡

ከዚህ አስደማሚ ክስተት በመነሳት ኢቲቪ ገና አሁን ሥራ መጀመሩን ለሸሪኮቼ ስነግራቸው በሳቅ ፍንድት ነበር ያሉት፡፡ እኔ ግን የመረጥኩት በለውጡ ተገርሜ ዕርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቅንነት ማደፋፈርን ነው፡፡

የስቃይ ሰለባዎች እሮሮዎችና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አስተያየት

ምሥጋና ለኢቲቪ ይድረሰውና በዚያ ያልተለመደ ዘገባው ስለሕግ ታራሚዎች አስከፊ አያያዝ፣ በቂና ከጥርጣሬ በላይ የሆነ ማስረጃ አግኝተናል፡፡ እስረኞች በከባድ ድብደባና በግርፋት ክፉኛ የቆሰሉ ወይም የተጎዱ አካሎቻቸውን በገሃድ እያሳዩ የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ለቀናት፣ ለወራትና ለዓመታት ያደረሰባቸውን ወደር የለሽ ፍዳና መከራ በድፍረትና በሲቃ እንዲያ ሲያጋልጡ ማየትና መስማት ፍፁም የማይታመን ነበር፡፡

አልፎ አልፎ ዕንባቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው ሲናገሩ ከነበሩት የስቃይ ሰለባዎች ጋር በተደረገው በዚያ ቃለ ምልልስ፣ ገሃድ የወጣውንና ለማንም በማያሻማ ሁኔታ የተጋለጠውን ፈርጀ ብዙ የግፍና የሰቆቃ ተግባር በዓይናቸው በብረቱ ተመልክተውና በጆሯቸው ሰምተው ያምኑ ወይም ያስተባብሉ እንደሆን በጊዜው የተጠየቁት በዕድሜያቸው ጠና ያሉ አንድ የከፍተኛ ጥበቃ ሹም በበኩላቸው፣ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ‹አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም ይህ ዓይነቱ ጫፍ የረገጠ ሰብዓዊ በደል በማረሚያ ቤታችን ውስጥ ተፈጽሞ አያውቅም› ሲሉ ለኢቲቪ ጋዜጠኛ በደምሳሳው ይነግሩታል፡፡

እምብዛም ያልተብራራውና ግድ የለሽነት የተጠናወተው የሚመስለው ያ የሰውየው የዘልማድ ምላሽ ከሰቆቃው በላይ በጣም ያማል፡፡ በአሥራ አንደኛው ሰዓት እንኳ አፍጥጦ የወጣውንና ሊያስተባብሉ የማይችሉትን እውነታ አምኖና ተፀፅቶ ከመቀበል ይልቅ፣ ክዶ መሟገቱን መምረጣቸው አስገርሞኛል፣ አሳዝኖኛልም፡፡

‹ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም› ይሉ ነበር ነፍሳቸውን ይማረውና ሴቷ  አያቴ፡፡ የምር መሳሳቱ እየተነገረው ብቻ ሳይሆን፣ በስህተቱ ክፉኛ መጎዳቱን ልቦናው እያወቀ የለመደውን መስመር ላለመልቀቅ ሲል ባልሸነፍም ባይነት አጥብቆ የሚንገታገት ቀሽም ሰው ሲያጋጥማቸው እኮ ነው አሮጊቷ እንዲያ የሚሉት፡፡

ለነገሩ በከፍተኛ ጥበቃ ሹሙ ብቻ መፍረድ ያዳግታል፡፡ ዘገባው ለሕዝብ ከተላለፈ በኋላ የኢቲቪ ጋዜጠኛ በተመልካቾቹ አሳሳቢነት ወደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጎራ ብሎ የክቡር ኮሚሽነሩን አስተያየት ጠይቆ ነበር፡፡ ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለ በማለት ወደ ምላሹ የተንደረደሩት የሥራ ኃላፊ፣ ይህ ለእሳቸውና ለመሥሪያ ቤታቸው እንግዳ ዜና እንዳልሆነ ቀለል አድርገው ሲናገሩ የማዳመጥ ዕድል ያገኘ ማንኛውም ሰው የሰማውን ለማመን ሳይቸግረው አይቀርም፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ጉዳዩ ላለፉት ዓመታት መሥሪያ ቤታቸው ደጋግሞ የክትትል ሪፖርት ያቀረበበትና ምላሽ ያላገኘበት ነው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ በወንጀል ምርመራና በጥበቃ ስም በዜጎች ላይ ሲፈጸም የቆየውንና አሁንም የቀጠለውን አስከፊ የሰቆቃ ድርጊት ተጠያቂዎች በተመለከተ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ አጣርተው ተገቢውን ዕርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም ሲሉ አማረዋል፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን ኮሚሽኑ ከዚህ የመንግሥት ቸልተኝነት የተነሳ አቅመ ቢስነት እየተሰማው ስለመጣ እርማችሁን አውጡ ሊሉን ምንም አልቀራቸውም ነበር፡፡

የሰው ልጅ ክብርና ዋጋ ያለው ፍጡር ነው

የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ምንጩ ከሁሉም በላይ ሰውነት ነው (The Dignity and Worth of the Human Person) ሲል፣ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ በወርኃ ታኅሳስ 1948 ያወጣውና ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በባህላዊ ሕግነት ያላንዳች ልዩነት በተባበረ ድምፅ የተቀበለው ታላቁ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ገና በመቅድሙ ላይ ያውጃል፡፡ በዚህ መግለጫ የማይናወጥ እምነት መሠረት የሰው ልጅን ያህል ክብርና ዋጋ ያለው ፍጡር ከቶ የለም፡፡

አገራችን የዚህ ባህላዊ ሕግ ክፍልና አካል ለመሆን የወሰነችው ከደርግ አገዛዝ ውድቀት ማግሥት መንበረ ሥልጣኑን በኃይል የተቆጣጠሩት የያኔዎቹ የኢሕአዴግ አማፅያን፣ በሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. በጠሩት የአዲስ አበባው ጉባዔ ባወጣው የሽግግር ወቅት ቻርተር አማካይነት እንደነበር እዚህ ላይ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ይህ አልበቃት ብሎ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 39/46 እ.ኤ.አ ዲሴምበር 10 ቀን 1984 ያፀደቀውን ፀረ ሰቆቃ ስምምነት ተሯሩጣ ተቀብላለች፡፡ ይህንን አዎንታዊ ዕርምጃዋን በአትኩሮት የተከታተለ ማንኛውም ታዛቢ ታዲያ በወንጀል ተጠርጥረው በተያዙ፣ በተከሰሱና በጥበቃ ሥር በዋሉ ዜጎች ላይ በስፋት ሲፈጸም የቆየውንና ምን ያህል እንዳቋረጠ ልናረጋግጥ የማንችለውን ገደብ የለሽ የማሰቃየት ተግባር ለመረዳት ቢሳነው፣ እምብዛም የሚገርም አይሆንም፡፡

ፀረ ሰቆቃ ስምምነቱና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት

ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እ.ኤ.አ. ከጁን 26 ቀን 1987 ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ያደረገውን ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢሰብዓዊና ክብርን የሚያዋርደውን አሰቃቂ አያያዝና ቅጣት መከላከያ ስምምነት ኢትዮጵያ በኦፊሴል የተቀበለችው እ.ኤ.አ ማርች 14 ቀን 1994 ሲሆን፣ አሁን የምትጠቀምበትን ሕገ መንግሥት ከማፅደቋ አሥር ወራት ቀደም ብሎ መሆኑ ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ሕገ መንግሥቱ ራሱ በተለይ ሰቆቃን በሚመለከት የዚህ ገናና ዓለም አቀፍ ስምምነት ተከታይና ጥገኛ በመሆኑ፣ ከእሱ ጋር ተገናዝቦ መተርጎምና በጥብቅ ተናቦ ገቢራዊ መደረግ እንደሚኖርበት ከወዲሁ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (4)፣ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (2) እና አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌዎች በዝርዝር ይመለከቷል፡፡

የሰቆቃ ትርጓሜ

አገሪቱ በተቀበለችውና የብሔራዊ ሕግ ሥርዓቷ ክፍልና አካል ባደረገችው በዚህ ዓለም አቀፍ ውል ክፍል 1 አንቀጽ 1 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ መሠረት ሰቆቃ የሚለው ቃል እንደሚከተለው ተተርጉሟል፡፡ ትርጓሜው በግርድፉ ወደ አማርኛ ቋንቋ ሲመለስ፣ ‹‹አንድ ሰው ከፈቃዱ ውጪ ስለራሱ ወይም ስለሦስተኛ ሰው አንድን መረጃ ወይም የእምነት ቃል በግዴታ እንዲሰጥ፣ እርሱ ወይም ሦስተኛ ሰው ስለፈጸመው ወይም ፈጽሞታል ተብሎ ስለተጠረጠረበት ድርጊት እንዲቀጣ፣ ወይም እርሱን ወይም ሌላ ሦስተኛ ሰው ለማስፈራራት ወይም በኃይል ለማስገደድ በማለም ወይም የትኛውንም ዓይነት አድልዎ መሠረት ባደረገ ማናቸውም ሌላ ምክንያት በአካሉም ሆነ በአዕምሮው ላይ ከባድ የሆነ ሕመም ወይም ስቃይ እንዲሰማው በሚያደርግ የጭካኔ ዕርምጃ በመንግሥት ባለሥልጣን ወይም በዚሁ ሥልጣን ይሠራበት ዘንድ መብት በተሰጠው ሌላ ማንኛውም ሰው አማካይነት፣ አነሳሽነት፣ ፈቃድ፣ ስምምነት ወይም ዓይቶ እንዳላዩ አላፊነት ሆነ ተብሎ የሚፈጸምበት የማሰቃየት ተግባር ሲሆን፣ በሕግ መሠረት የተሰጠ ፍርድ ወይም የተላለፈ ማናቸውም የቅጣት ውሳኔ ቢኖር የዚህ ዓይነቱ ውሳኔ አፈጻጸም በፀባዩ ሊያስከትል የሚችለውን ማናቸውንም ተጓዳኝ ሕመም አይጨምርም፤›› ይላል፡፡

ሰቆቃ ለምን ይፈጸማል?

የሆነስ ሆነና ከሁሉም በላይ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው የሚባለውና ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የሥርዓቱ አጋፋሪዎች በየጊዜው የሚረገረጉለት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌው ሥር ጭካኔ የተመላበት፣ ኢሰብዓዊ የሆነና ክብርን የሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት በግልጽ መከልከሉን እያወቁ የፖሊስ፣ የደኅንነትና አንዳንዴም የአገር መከላከያ ኃይሎቻችን ከመደበኛው ሕግና ሰላም የማስከበር ተልዕኳቸው ባፈነገጠ መንገድ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ፣ የተከሰሱና በጥበቃ ሥር የሚገኙ ዜጎችን ክፉኛ የሚያንገላቱትና በድብደባ የሚያሰቃዩት ለምንድነው? አድራጎቱስ በእርግጥ በወንጀል ምርመራ፣ በደኅንነት ጥበቃና በሕግ ታራሚዎች አያያዝ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ኦፊሰሮች ብቻ የሚመለከት ነውን? በዝርዝር ተጣርቶ ካልታወቀ በስተቀር ይህ ዓይነቱ የሰቆቃ ድርጊት ለሕዝብ ይፋ ባልተደረገ የተዛባ ፖሊሲ ተደግፎ ሲፈጸም ላለመቆየቱስ ምን ማረጋገጫ ይኖራል?

ወንጀልን በመመርመርና እውነቱን አፍረጥርጦ በማውጣት ረገድ አቅሙ ደካማ የሆነ የትኛውም የፖሊስ መኮንን በእጁ የገባ ተጠርጣሪ ያልፈጸመውንም ወንጀል ቢሆን፣ ፈጽሜያለሁ ብሎ በግዴታ እንዲያምንለት ኃይል የተቀላቀለበትን የምርመራ ሥልት መጠቀሙ ወትሮም ቢሆን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ እንደማይፈቅድለት ቢረዳም አቅመ ቢስነት የሚሰማው ፖሊስ ምን ጊዜም ቢሆን የያዘውን ወይም በሌሎች ተይዞ የተሰጠውን ተጠርጣሪ የሚመረምረው ጥሬ ጉልበቱን እንጂ፣ ታክቲካዊና ቴክኒካዊ የምርመራ ዘዴዎችን ተጠቅሞ አይደለም፡፡

ይህ ጸሐፊ ከድፍን አሥር ዓመታት በላይ ዓቃቤ ሕግ ሆኖ በተለያዩ ደረጃዎች እንደማገልገሉ መጠን፣ የአንዳንድ መርማሪ ፖሊሶቻችንን የነውር ሥራ የሚያውቀው በግምት ብቻ አይደለም፡፡ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ውስጥ ያገለግል በነበረበት ወቅት፣ የወንጀል ምርመራ መዛግብትን አጥንቶ ክስ ከመመሥረት ወይም የክስ አይቀርብም ውሳኔ ከመስጠት ባሻገር፣ እንዳስፈላጊነቱ እስር ቤቶችንና ፖሊስ ጣቢያዎችን በአካል እየተገኘ የመጎብኘትና የሕግ ታራሚዎችን የማነጋገር ዕድል ነበረው፡፡

ሕገ መንግሥታዊ አንድምታዎች

እንደ እውነቱ ከሆነ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች ቁልፍ ተግባር በአገርና በሕዝብ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ወንጀል ገና ከጥንስሱ ተከታትሎ ማክሸፍ፣ ተፈጽሞ ሲገኝ ደግሞ ወንጀሉን በረቀቀ የምርመራ ጥበብ በበቂ ማስረጃ አጣርቶ ተጠርጣሪዎች በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡና ለፈጸሙት ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲወሰንባቸው ማድረግ ነው፡፡ በሳይንሳዊ ዘዴና በተሟላ ሥነ ምግባር መከናወን ያለበትን ይህንኑ ተግባር በሚቃረን ሁኔታ፣ ሕገ መንግሥቱንና አገሪቱ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በግልጽ ተላልፎ በንፁኃን ዜጎች ላይ በወንጀል ምርመራና እርማት ስም መለኪያ የሌለው ሰቆቃ መፈጸም አይደለም፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በሰለባዎች ላይ የማሰቃየት ተግባር የሚፈጸመው የጥፋተኝነት ማስረጃ ለማግኘት እንደሆነ በተሳሳተ መንገድ ይታመናል፡፡ ይህ እምነት ምናልባት ወደ እውነት የመጠጋት ዕድል አለው ቢባል እንኳ፣ በዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ የተገኘ ማስረጃ በሕግ ፊት ዋጋ እንደሌለው አስቀድሞ መታወቅ በተገባው ነበር፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ (5) በአፅንኦት እንደሚደነግገው፣ የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ የሚገደዱ ካለመሆናቸውም በላይ፣ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን እየተወሰደ ያለውን አበረታች የለውጥና የተሃድሶ ዕርምጃ ተከትሎ ይሆናል ተብሎ ፍፁም ባልተገመተ ሁኔታ ቅድመ ፍርድ ክሳቸው እንዲቋረጥና ድኅረ ፍርድ ደግሞ ይቅርታ እየተደረገላቸው፣ ከየተጋዙባቸው እስር ቤቶች ተከታትለው በመውጣት ላይ ያሉ በርካታ ዜጎች በወንጀል ምርመራና በታራሚዎች ጥበቃ ስም ከአካላዊ ግርፋት አንስቶ እስከ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት የዘለቀ ምን ያህል አስከፊ ቁም ስቅል ይፈጸምባቸው እንደነበር በራዲዮና በቴሌቪዥን እየቀረቡ ያላንዳች ፍርኃትና መሸማቀቅ ይነግሩን ዘንድ መደፋፈራቸውን ታዝበናል፡፡ እንደ ማዕከላዊ፣ ቃሊቲና ቂሊንጦ በመሳሰሉት የማሰቃያ ሥፍራዎች ተግዘው አንዳንዴም የት እንዳሉ እንኳ በውል ሳይታወቅ ዓመታትን ካስቆጠሩት ከእነዚሁ የስቃይ ሰለባዎች መካከል፣ በድብደባ ብዛት አካሎቻቸውን ያጡ ወይም ቋሚ ጉዳት የደረሰባቸው፣ እርቃነ ሥጋቸው ተጋልጦ በኤሌክትሪክ ሽቦ የተገረፉ፣ የፊጥኝ ታስረው ወይም ቁልቁል ተሰቅለው ማለቂያ የሌለው መከራን የተቀበሉና የእግር ጥፍሮቻቸው ሳይቀር በፒንሳ እየተሳቡ የተነቀሉባቸው ወገኖች ይገኙባቸዋል፡፡

እንግዲህ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በግብር ከፋዩ ገንዘብ በሚንቀሳቀሱት የወንጀል ተጠርጣሪዎች ማቆያና የሕግ ታራሚዎች መጠበቂያ ተቋማት ውስጥ፣ ርኅራኄ በጎደለውና ግፈኝነት በተጫነው አኳኋን በዘፈቀደ ሲፈጸም የኖረው ፈርጀ ብዙ የሰቆቃ ተግባር ባለቤት የለሽ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ሰቆቃ በመፈጸም የበቀል ዕርምጃ ለመውሰድ እምብዛም ማሰላሰል ሳያስፈልግ፣ የድርጊቱን ግንባር ቀደም ፈጻሚዎችና ኃላፊነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን የቅርብና የሩቅ አለቆቻቸውን ማንነት ያለ ድካም መለየትና በወንጀሉ አፈጻጸም ውስጥ የነበራቸውን የተሳትፎ መጠን በቀላሉ ማረጋገጥ አይገድም፡፡

ይህንን በተደራጀ መንገድ ማከናወን ሞራላዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታም ጭምር እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተመላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት እንዳለው በማወጅ ብቻ አያበቃም፡፡ አገሪቱ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት ዕርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ እንደማይታገድና በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በየትኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔ በምሕረትም ሆነ በይቅርታ እንደማይታለፍ ወደር በማይገኝለት ኃይለ ቃል ደንግጓል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ፀረ ሰቆቃ ስምምነቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ተዋዋይ መንግሥታት ሁሉ በግዛት ወሰናቸው ውስጥ በሚሸፈን በየትኛውም ሥፍራ ለማናቸውም ዓላማ ቢሆን በሰዎች ላይ ቁም ስቅል እንዳይፈጸም ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ዳኝነት ነክና ሌሎች ውጤታማ ዕርምጃዎችን በመውሰድ አስቀድመው የመከላከልና የመዋጋት ግዴታ እንዳለባቸው በአንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 90 (1) ሥር ይደነግጋል፡፡

ሌላው ቀርቶ በአገር ውስጥ የሚያጋጥም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ይህንኑ ተንተርሶ የተደነገገ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወይም ከጠላት ጋር የሚካሄድ ጦርነት በዜጎች ላይ ለተፈጸመ ወይም ለሚፈጸም ሰቆቃ በቂና አጥጋቢ የመከላከያ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ ካለመቻሉም በላይ፣ የማሰቃየቱን ተግባር ለመፈጸም የተገደድኩት በቅርብ አለቃዬ ታዝዤ ወይም በበላይ አካል መመርያ ተሰጥቶኝ ነው የሚለው ሰበብ እንኳ የድርጊቱን ባለቤት በከባድ የወንጀል ኃላፊነት ከመጠየቅና ለተቀጪነት ከመዳረግ እንደማያድነው የዚሁ ዓለም አቀፍ ውል አንቀጽ ፳፳ 2. ንዑስ አንቀጽ (2)ና ንዑስ አንቀጽ (3) ድንጋጌዎች መረር አድርገው ያስጠነቅቃሉ፡፡

ምን ቢደረግ ይበጃል?

በመሠረቱ የስቃይ ሰለባዎች ከእስር ተፈተው የደረሰባቸውን ጉዳት ሳይሸማቀቁ በገሃድ እያወጡ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸው፣ ከመጋረጃ በስተጀርባ ተደብቆ የኖረውን የሥርዓቱን በሽታ በአደባባይ ማጋለጣቸው የመጀመርያው በጎ ዕርምጃ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን በሰለባዎቹ በራሳቸው፣ በቤተ ሰቦቻቸውና በአገራችን ክብር ላይ የደረሰውን ዘላቂ የሥነ ልቦና ስብራት እስከ ወዲያኛው የመጠገን አቅም ይኖረዋል ተብሎ አይታመንም፡፡ ይልቁንም ሰለባዎቹ ጭካኔ በተመላበት፣ ኢሰብዓዊ በሆነና ክብርን በሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የተቀበሉትን ፍዳና መከራ የሚገልጹበት የምሬት ደረጃ በስም እየጠቀሱና በጣት እየጠቆሙ በበደል አድራሽነት የሚከሷቸው ፈጻሚና አስፈጻሚዎች፣ በሚጠረጠሩበት ምግባረ ብልሹ አድራጎት መፀፀታቸው ቀርቶ ያላንዳች ይሉኝታና የሕግ ተጠያቂነት በነፃነት መመላለሳቸው ሳያንስ፣ አልፎ አልፎ በስቃይ ሰለባዎቹ ዋይታ አብዝተው ሲያላግጡ ከሚስተዋልበት ያፈጠጠ እውነታ ጋር ተስማምቶ መቀጠል ከባድ ይሆናል፡፡

ሕዝባችን የሰቆቃ ሰለባዎችን ምሬት ብቻ ሳይሆን የበዳዮቻቸውን ታሪክ ጭምር እኩል መስማትና ማየት ይፈልጋል፡፡ እንዲያውም በበዳዮች ንስሐ ያልተደገፈ የሰለባዎች ኑዛዜ የቱንም ያህል ሲተረክ ውሎ ቢያድር ለእውነተኛ ይቅርታ በር አይከፍትም፡፡ ለዘላቂ ሰላምም ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም› ነውና፡፡

ይታወስ እንደሆን ኢሕአዴግ የደርግ ሥርዓት በተገረሰሰ ማግሥት ያቋቋመው የሽግግር መንግሥት በቀዳሚነት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች አንዱ፣ በ17 ዓመቱ የደርግ አገዛዝ ተፈጽመዋል ያላቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች የሚያጣራና ጥፋተኞች ሆነው የተገኙትን የቀድሞ ባለሥልጣናት ለፍርድ የሚያቀርብ አካል በሕግ መሰየም ነበር፡፡ ለዚህ ነበር የያኔው የልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በአዋጅ ቁጥር 22/1984 ዓ.ም ከተቋቋመ በኋላ ሰብዓዊ አቅሙና የተመደበለት ሀብት በፈቀደለት መጠን፣ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንትና የየዕርከኑ ታዛዦቻቸው የሰው ዘር ማጥፋትን ጨምሮ በሰብዕና ላይ ፈጽመዋቸዋል የተባሉትን ከባድ ወንጀሎች በማጣራትና ሁሉም ባይገኙ እንኳ የተወሰኑት ወደ ፍርድ አደባባይ ቀርበው እንዲቀጡ በማድረግ ሥራ ላይ ተጠምዶ የቆየው፡፡

ታዲያ በሕገ መንግሥቱ አማካይነት (ውጉዝ ከመአርዮስ) የተባለውና አገሪቱ በፈረመችው ፀረ ሰቆቃ ስምምነት አጥብቆ የተከለከለው የማሰቃየት ተግባር በፊታችን ሲፈጸም መኖሩ ከተረጋገጠ፣ ሰለባዎቹ ከታወቁና በዳዮቹ ከተለዩ ዛሬስ ቢሆን እንደ ትናንቱ ይህንን ለማድረግ ምን ይሳነናል?

ሌላው ቢቀር እንኳ ሀቁን በገለልተኝነት የሚያጣራና በውጤቱ መሠረት በወንጀሉ አፈጻጸም ከነበራቸው ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ከመጠየቅ የማይድኑ በዳዮችን በሰለባዎቻቸው ፊት አቁሞ፣ በግፍ ያጎሳቆሏቸውን ዜጎች በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ የሚያስገድድ ኮሚሲዮን በሕግ ማደራጀትና ሥራውን በአፋጣኝ እንዲጀምር ማድረግ ለምን ያቅተናል?

ከዚህ ባፈነገጠ መንገድ ጉዳዩን ከመጠን በላይ አቃሎ በማየት እውነቱን ለመሸፋፈን የሚደረግ የቀቢፀ ተስፋ ሙከራ ቢኖር ለየትኛውም ወገን አያዋጣም፣ አይመከርምም፡፡ ይልቁንም ሀቁ በሚገባ ታውቆና በዝክረ ሰቆቃ ዶሴ ተመዝግቦ መያዝና ከሰለባዎቹ ቋሚ መታወሻነት ባለፈ የመጪው ትውልድ መማርያ መሆን ይኖርበታል፡፡

ያም ሆኖ ታዲያ በአንድ ነገር ላይ እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡  መፃዒው ዕድላችን በአስተማማኝ የሚወሰነው ከጊዜያዊ ትኩሳት ተላቀንና ከጭፍን በቀልተኝነት ተቆጥበን ዛሬ በምንወስደው የአርቆ አስተዋይነት ዕርምጃ መሆኑን ፈጽሞ ልንስተው አይገባም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...