Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የጃንሆይን ነገር አደራ!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የጃንሆይን ነገር አደራ!

ቀን:

በአያሌው አስረስ

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ተማሪው፣ የመንግሥት ሠራተኛውና ወታደሩ ‹‹ኃይለ ሥላሴ ይሙት›› እያለ ቃለ መሐላ የሚገባባቸው ንጉሥ ነበሩ፡፡ ሕዝቡ ‹‹በኃይለ ሥላሴ አምላክ›› ሲባል ባለበት ቆሞ ያለ ምንም አስገዳጅ ኃይል ወደ ፍትሕ አካል የሚሄድላቸው፣ እሳቸውም መንገድ ላይ ጠብቆ አቤት ከሚል ደሃ ማመልከቻ የሚቀበሉ ንጉሥ ነበሩ፡፡

ንጉሡ ከሳምንት አንድ ቀን በየሆስፒታሉ እየተገኙ ሕሙማንን የመጠየቅ ልማድ ነበራቸው፡፡ በዘመናቸው ከነበሩት ወጣት ዲፕሎማቶች አንዱ አቶ አስፋው ተፈራ ‹‹እኔ ማነኝ?›› በሚል ርዕስ በጻፉት የግል ታሪካቸው ላይ፣ ‹‹ሩህሩህና ማንንም ሰው ዝቅ አድርገው የማይመለከቱ፣ ለዜጎቻቸውና ለአገራቸው መልካም ምኞትና ዓላማ ያላቸው፣ አገሪቱና ሕዝቡ ከፍ ከፍ እንዲሉ ከፍተኛ ምኞትና ፍላጎት የነበራቸው ሰው ናቸው፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

አቶ አስፋው በዚህ አልቆሙም፣ ‹‹ግርማዊነታቸው ለሥልጣናቸው ቀናዒ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ሌላ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሐሳብና ሥራ ሊያከናውን የሚችል ሰው የተፈጠረ አይመስላቸውም፤›› በማለትም ሌላኛውን የንጉሡን ጠባይ አሳውቀዋል፡፡

ይኼን ፀባያቸውን የሚያረጋግጠው ደግሞ በ1923 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አሁን ላለችበት ዕድገት በቂ ምስክር ነው፡፡ የሕግ መወሰኛውና የሕግ መምርያው ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ግን በትክክል ተለያይቶ መወሰን እንዳለበት የገለጹት፣ ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ጉዳይ ናቸው፡፡ ‹‹ዛሬ ብዙዎቻችን በዕድሜ እየገፋን የትውልዱ አስተሳሰብ ደግሞ እየተለወጠና ወደ ሌላ የአስተዳዳር ዘይቤ እያመራ ነው፡፡ አምላክ ፈቃዱ ሆኖ እዚህ ካደረሰን አንድ ብቁ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾም፡፡ ዘውዱን አክብረንና አስከብረን የአስተዳደር ሥልጣኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ማስረከብ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝቡ፣ እንዲሁም ለንጉሣዊ ቤተሰቡ መልካም ነው፤›› ብለው የመከሩት ወልደ ጊዮርጊስ ከጸሐፌ ትዕዛዝነትና ከአገር ግዛት ሚኒስትርነት ተነስተው የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ገዥ ተደረጉ፡፡

ይህ ከሆነ ከአምስት ዓመታት በኋላ በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደረገ፡፡ በግብግቡ ከክቡር ዘበኛና ከጦር ሠራዊቱ ወገን ብዙዎች አለቁ፡፡ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በጄኔራሉ ከተገደሉት አሥራ አምስት ሰዎች ውስጥ ቢያንስ ሦስቱ ራስ አበበ አረጋይ፣ ራስ ሥዩም መንገሻና ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ አገር ዕድሜ አጥግባ በክብር ልትሸኛቸው የሚገባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡

ጃንሆይ ከዚህ አልተማሩም፡፡ አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ የመከሯቸውን አልሰሙም፡፡ የሜጀር ጄኔራል ዓብይ አበበ ‹‹አውቀን እንታረም›› ጩኸት አልተደመጠም፡፡ መንግሥታቸው በቆየው መንገድ ቀጠለ፡፡ የየካቲት 1966 ዓ.ም. የሕዝብ አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ የወታደሩ ክፍል ራሱን በኮሚቴ አደራጅቶ መንግሥቱን ያዘ፡፡ ንጉሡን ከሥልጣን አወረደ፡፡ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. ከፍተኛ የንጉሡን ባለሥልጣናትና ባለ ሌላ ማዕረጎችን በፖለቲካ ውሳኔ ረሸነ፡፡ ቆይቶ ንጉሡም ተገደሉ፡፡ ከተገደሉት ስልሳ ሰዎች ውስጥ ሃያ የሚሆኑት በፀረ ፋሺስት ኢጣሊያ ትግል የተሳተፉ ክብርና ጥበቃ የሚገባቸው አርበኞች ነበሩ፡፡

ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶምን በመግደል የኤርትራን ችግር ያባባሰው ደርግ ዘመኑን የጨረሰው ፀረ ኃይለ ሥላሴ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ ነው፡፡ ኢሕአዴግም በዚያው ነው የቀጠለው፡፡

የሁሉም የፕሮፓጋንዳ ማጠንጠኛ በማይጨው ጦርነት ከተሸነፉ በኋላ አገር ውስጥ ተዋግቶ እንደ መሞት መሰዳዳቸው፣ ገንዘብ ወደ ውጭ አገር ማሸሻቸው፣ የወሎን ረሃብ መንግሥታቸው መደበቁና የአስተዳደር በደል ማድረሳቸው ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

የአስተዳደር በደል ሁልጊዜ መንግሥታት የሚከሰሱበት የማይነጥፍ ችግር በመሆኑ የንጉሡም የተለየ አይደለም፡፡ ገንዘብ ስለማሸሻቸው ከመነገሩ በስተቀር እስከ ዛሬ ድረስ በማስረጃ ያረጋገጠ አላጋጠመኝም፡፡ የወሎ ረሃብን መደበቅ ከእሳቸው መንግሥት ራስ የማይወርድ ጥፋት መሆኑን አምናለሁ፡፡

‹‹የማይጨው ዘመቻ ታሪክ›› ጸሐፊ ገብረ ወልድ እንግዳ፣ ‹‹ከወልወል አስከ ማይጨው›› ጸሐፊ ብርሃኑ ድንቄ ጃንሆይ በጦርነቱ እንደ አንድ ወታደር መዋጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጦርነቱ የኢትዮጵያ ጦር ተሸናፊ የሆነው ለጣሊያን ባደሩ የራያና የአዘቦ ሰዎች ከጀርባ በመወጋቱ መሆኑን ‹‹የአበሻ ጀብዱ›‹ ጸሐፊ አዶልፍ ፓርለስክ መስክሯል፡፡

ስደት ጃንሆይ ያመነጩት ሐሳብ አልነበረም፡፡ በቅርቡ ወደ ማይጨው በሄድኩበት ጊዜ የአገር ሽማግሌዎች በተለይም ዶ/ር ኪሮስ ሙሉ የነገሩኝ፣ ጃንሆይ እንዲሰደዱ የመከሯቸው የዋጅራት ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ በማይጨው አውራጃ ገዥ በደጃዝማች አበራ ተድላ አቅራቢነት ንጉሡን ያነጋገሩት ዋጅራቶች ጣሊያን ለአርባ ዓመታት ተዘጋጅቶ ሲመጣ መንግሥት ምን ሲሠራ እንደቆየ ጠይቀው ያሏቸው፣ ‹‹የእርስዎ በጦርነት እየተዋጉ መሞት ለገአገር የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ወደ ዓለም መንግሥታት ሄደው ዕርዳታ ይጠይቁ፣ እኛ በዱር በገደሉ እንቆያለን፤›› ነው ያሉት፡፡

በወቅቱ ራስ ካሳ ስደቱን እንደደገፉት ሁሉ ዛሬ ከስደቱ ደጋፊዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ንጉሡ አገር ውስጥ ቆይተው ቢሆን ኑሮ የሚጠብቃቸው የራስ እምሩ ወይም የራስ ደስታ ዕጣ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ መሰደዳቸው ግን ሕዝቡ የነፃነት ትግሉን በራሱ መንገድ ጀምሮ በራሱ መንገድ እንዲመራው አስችሎታል፡፡ አንድ ማዕከል እንዳይኖር በማድረግም የመከላከል ጦርነቱ ከዳር እስከ ዳር እንዲዘረጋ፣ ጣሊያን በየትኛውም አካባቢ በጦርነት እንዲጠመድ አድርጓል፡፡ ቢሞቱ ኖሮ እኔ እነግሥ እኔ እነግሥ ሊፈጠር የሚችለውን ግብግብና ለጣሊያን አድርባይነት አስቀርቶ፣ ሁሉም ክንዱን በጠላቱ ላይ እንዳያሳርፍ አስችሏል፡፡ ሁሉም ንጉሡንና ነፃነቱን በተስፋ እንዲጠብቅ አስገድዷል፡፡ ይኼንን ደግሞ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጎል፣ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በፋሽስት የወረራ ዘመን የሕዝባቸው ተስፋና ሕይወት ሆነው በመጨረሻ ድል ያደረጉ ንጉሠ ነገሥት ናቸው፤›› በማለት አረጋግጠውታል፡፡

ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት አራት ትልልቅ አጀንዳዎችን በትዕሥትና በጥበብ ጎን ለጎን በማራመድ ከግቡ አድርሷል፡፡

በተለይም ሱዳን በቆዩበት ጊዜ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ዕርዳታ በውል እንዲታሰር ንጉሡ ቢፈልጉም ተቀባይ አላገኙም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ እንግሊዞች፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከተለቀቁ ግዛቶች አንዷ በመሆኗ ከእኛ ፈቃድ ውጪ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉም፤›› በማለት ንጉሡን ማወክ ቀጠሉ፡፡ አርበኞች የተዋጋነው ጣሊያንን አስወጥተን እንግሊዝን ለማስገባት ነው ወይ ብለው ተቆጡ፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የወደቁት ንጉሡ ቀስ በቀስ ሴራውን በመበጣጠስ የእንግሊዝ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በሁለት ዓመት ተኩል እንዲያበቃ፣ በተጨማሪም እንግሊዝ ከጋምቤላና ከኦጋዴን በአሁኑ አጠራር (ኢትዮጵያ ሶማሌ) እንድትወጣ አደረጉ፡፡

የእንግሊዞች ሴራ ፈተናውን ቢያበዛውም ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል በማድረግ አገራችን የባህር በር እንድታገኝ አድርገው ነበር፡፡ በፌዴሬሽኑ መፍረስ የተቀሰቀሰው ጦርነት እየተባባሰ በሄደ ጊዜ፣ ፌዴሬሽኑን ወደ ነበረበት ለመመለስ ፈልገው በሚስጥር ወደ ኤርትራ የላኳቸው መልዕክተኛ ታፍነው አድራሻቸው በመጥፋቱ፣ ሐሳባቸው ከዳር ሊደርስ እንዳልቸለ የንጉሡ የእልፍኝ አስከልካይ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል መኰንን ደነቀ ነግረውኛል፡፡ ጄኔራሉ የሰዎችን ማንነት ሊገልጹልኝ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡

ጣሊያኖች በአምስቱ ዓመት ቆይታቸው ሆን ብለው የተማሩ ኢትዮጵያዊያንን ጨፍጭፈዋል፡፡ የንጉሡ መንግሥት አንዱ ሥራ የተማሩ ሰዎችን ማፍራት ነበር፡፡ የትምህርት ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ራሳቸው ይዘው ልጆች ትምህርት ቤት እንዲገቡ ከማባባል ጀምሮ፣ ወደ ውጭ ለትምህርት ሲሄዱ በክብር ሸኝቶ ሲመለሱ በክብር በመቀበል፣ ዋና ዋና ቦታዎችን በኢትዮጵያዊያን እንዲያዙ በማድረግ የመንግሥቱ ሥራ የተቃና እንዲሆን አስችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በባላባታዊ ሥርዓት ውስጥ የኖረች አገር ናት፡፡ ራሶች፣ ደጃዝማቾች፣ ፊታውራሪዎች፣ ወዘተ የየራሳቸው ጦር ነበራቸው፡፡ ንጉሥ ሚካኤልን፣ ራስ ጉግሳን፣ ወዘተ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከድል በኋላ ግን የሠለጠነ መደበኛ ሠራዊት በማቋቋም የመሳፍን ሠራዊት በራሱ ጊዜ እንዲበተን በማድረግ ብቻቸውን እንዲቀሩ አስገድዷቸዋል፡፡ ራስ መስፍን በቀላሉ በደርግ እጅ የወደቁት የሚያዙበት ጦር ስላልነበራቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለ1,600 ዓመታት የግብፅን መንበረ ማርቆስ ተሸክማ ጳጳሳት ስታስመጣ ኖራለች፡፡ ይኼን ሸክም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትከሻ ላይ ያወረዱት ንጉሡ ናቸው፡፡ ንጉሡ ቅዱስ ቁርዓን በአማርኛ ቋንቋ እንዲተረጎም በማድረግም ሙስሊሙን ኢትዮጵያዊ አገልግለዋል፡፡

በፍትሐ ነገሥት ይመራ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓት በሕገ መንግሥት እንዲመራ ከማድረጋቸውም በላይ፣ በቅርቡ የተሻሻለው የወንጀል ሕግና እየተሻሻለ የሚገኘው የንግድ ሕግ፣ እንዲሁም የፍተሐ ብሔር ሕግ የእሳቸው ዘመን የሥራ ፍሬዎች ናቸው፡፡

ጃንሆይ በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል እንድትሆን አድርገዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት አንዷ መሥራችም እሷ ናት፡፡ ምንም በድህነቷና በሥልጣኔ ወደ ኋላ በመቅረቷ የተነሳ ድምጿ ገኖ ባይሰማም፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተካፋይና ባለድል አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ሆና እንድትመዘገብ አድርገዋል፡፡

በኮሪያና በኮንጎ ሰላም ለማውረድ ሠራዊቷን ያሠለፈችው ኢትዮጵያ አሁን ድምፁ የጠፋውን የገለልተኛ አገሮች ጉባዔ እንዲመሠረት አገሮች ለጦር መሣሪያ ቅነሳ እንዲጮሁ በማድረግ ድርሻዋን እንድትወጣ አስችለዋል፡፡ የደቡብና የሰሜን ሱዳንን፣ የሞሮኮና የአልጄሪያን፣ የጊኒና የሴኔጋልን፣ ወዘተ ችግሮች ለመፍታት ያደረጉትን የአደራዳሪነት ሚና በማየት የገለልተኛ አገሮች መንግሥታት ጉባዔ በ1965 ዓ.ም. የሰላም ኮከብ ብሎ ሰይሟቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወርቅ ሜዳሊያ በዋና ጸሐፊው ኩርት ቫልዶሂም እጅ ሸልሟቸዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ባላቸው ተሰሚነት በሁለት ጎራ የቆመውን የካዛብላንካንና የሞሮኮን ቡድን ወደ አንድ ከማምጣትና ከማሰባሰብ አልፎም፣ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋሚያ ቻርተር ሳንፈርም ከዚህ አዳራሽ አንወጣም፤›› በማለት እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ድረስ ቆይተው ቻርተሩን ያስፈረሙና ማኅበሩ እውን እንዲሆን ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡ ለአባ ዲና ፖሊስ ኮሌጅ የተሠራውን አዲስ ሕንፃ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት እንዲሆን በመስጠትም፣ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ሥራ ሠርተዋል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሰማንያኛ ዓመት የልደት በዓላቸው በመላ አፍሪካ እንዲከበር ከማድረጉም በላይ፣ በቅርቡም የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ወስኗል፡፡

ወሎዬዎች በልጅ እያሱ፣ ጎጃሞች በደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ጎንደሮች በራስ ጉግሳና በደጃዝማች አያሌው ብሩ፣ ኦሮሞዎች በእነ ጀኔራል ታደሰ ብሩ፣ ትግሬዎች በመጀመርያው ወያኔ ዘመቻ፣ ሌሎች አካባቢዎችም በልዩ ልዩ ምክንያት በንጉሡ ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ እነዚህ በደሎቻቸው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የሠሩት እጅግ ብዙውን ውለታቸውን ሊደመስሱ ይችላሉ ብዬ አላምንም፡፡ አስተዋፅኦዋቸውን በቅን ልቡና በሚዛናዊነት የሚያይ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ሐረሪ ላይ የዓለማያ (አሁን ሐሮማያ) ኮሌጅ የከፈቱት ንጉሠ ነገሥቱ ተገፍተው፣ ገጣሚ የነበረው ፈረንሣዊው የጦር መሣሪያ ደላላ አርተር ራንቦ ባልተከበረም ነበር፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቤት! አቤት! የምለው ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ከራስዎ ጀምረው ከጠቅላይ ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያስታርቋቸው ነው፡፡ ከሃያ በመቶ የማያልፈው በደላቸው ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን መልካም ሥራቸውን ገደል ይዞት እንዳይገባ እንዲታደጉ ነው፡፡ እሳቸውን በመጥላቷና በማጥላላቷ ኢትዮጵያ ያጣቸውን ክብር መልሳ እንድታገኝ እንዲያደርጉ ነው፡፡

 ከዋና ዋና የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪኮች ልናወጣቸው የማንችላቸውን ሰው እናወጣለን ብለን በምናደርገው ትግል የሚያደርስብንን የመንፈስ መቁሰል እንዲከላከሉልን ነው፡፡ እሳቸውን በመጥላት፣ በእሳቸው ዘመን የነበሩ የታሪክ ሰዎችን ክብርና ዋጋ እየነፈግን በመሆኑ ከታሪክ ተወቃሽነትም እንዲያድኑን ነው፡፡

ሕዝብ ‹‹ተፈሪ መኰንን›› እያለ መንግሥት ‹‹እንጦጦ የቴክኒክ ኮሌጅ›› እያለ እስከ መቼ ይዘለቃል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር? በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፋሽስት ኢጣሊያን ድል ባደረገች የመጀመርያ አገር ኢትዮጵያ፣ ድል አድራጊው መሪ አፄ ኃይለ ሥላሴ ብለን የምንናገርና ለቱሪዝም ዕድገት የምንገለገልባቸው ያድርጉን፡፡ በ126ኛ የልደት በዓላቸው ዋዜማ ላይ ስለሆንን አደራ! አደራ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...