Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያለፈውን ክፉ ጊዜ መርሳት የመሰለ ነገር የለም!

‹‹የተወደዳችሁ የታክሲ ደንበኞች፡፡ በቅርቡ አዲስ ታፔላ ለጥፈን አንድ ላይ ተሳፍረን ወደ ኤርትራ መሄዳችን እንደማይቀር ቃል እገባላችኋለሁ፤›› የሚለን ወያላው ነበር፡፡ ሾፌሩ፣ ‹‹መቼም አንተ እንደለመድከው የኢትዮጵያ ሴቶች ስላማረሩኝ እዚያ ሄጄ ማግባት እፈልጋለሁ የምትለው ፀሎት ሳይሰማልህ አይቀርም፤›› ሲለው ወያላው በደስታ፣ ‹‹እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡ እንዲያውም እዚያ ሄጄ የታክሲ ሥራ ፈልጌ አደራዋለሁ፡፡ በዚያውም ከተማዋን ቶሎ ብዬ እንድግባባት ይረዳኛል፤›› እያለ ቀባጠረ፡፡

ዳሩ ግን ሾፌሩ ያላሰበውን ነገር ይዞበት መጣ፡፡ ‹‹ምን መሰለህ አንተ ወደ አስመራ ስታዘግም፣ ቆንጂት የአስመራ ልጅ ደግሞ ያንተን ራዕይ ሰንቃ ወደ ኢትዮጵያ ትመጣለች፡፡ ይኼኔ ተለያያችሁ ማለት አይደል? እየተያየን ተለያየን ይሉሃል ይኼ ነው፤›› እያለ በወያላው ሐሳብ ላይ ውኃ ቸለሰበት፡፡ ወያላው ግን የዋዛ አልነበረም፡፡ ጉዟችን ከመገናኛ ፒያሳ እንደሆነ ልብ በሉልኝ፡፡

በዚህ መሀል አንድ ሰው ወሬያቸውን ተቀላቀለ፡፡ ‹‹ዛሬ አንዱ ከአስመራ ደውሎ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?›› ሲል የሁላችንንም ትኩረት ጠራርጎ ወሰደው፡፡ ‹ምን አለህ ይሆን?› በሚል ስሜት አፈጠጥንበት፡፡ ሰውየውም፣ ‹‹ስልኩን አንስቼ ሃሎ ስለው …›› በማለት ወሬዋን ትንሽ አራዘመብን፡፡ እኛም ምንም አመራጭ ስላልነበረን፣ ‹‹እሺ?›› እያልን የወሬውን መጨረሻ በጉጉት መጠባቅ ጀመርን፡፡ ‹‹የደወለለልኝ ሰውዬ ‹ማን ልበል 1991 ላይ ሚስድ ኮል አጊንቼ ነበር› አለኝ፤› ሲል በስሱ ፈገግ አልን፡፡ ሁሉም ለካ ቀልደኛና ተጫዋች ሆኗል፡፡

በመሀል አንድ ሰው፣ ‹‹እኔ ግን ኢሳያስ እንዲህ ያለ ምስኪን ሰው ይሆናል ብዬ በሕልሜም በእውኔም አስቤው አላውቅም፤›› እያለ የግርምት አስተያየቱን ሰጠ፡፡ ይኼን ጊዜ ነበር አንዲት ሴት መንጣጣት የጀመረችው፡፡ የእሷን ንግግር ለሰማ ኤርትራዊት ሳትሆን አትቀርም ያሰኛል፡፡ ‹‹ምናልባት ለኢትዮጵያዊያን ሁኔታው አስደሳች ሊሆን ይችላል፡፡ ለኤርትራዊያንም ደስ አያሰኝም ለማለት አይደለም፡፡ ዳሩ ግን በኢትጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ነው፤›› ስትል ብዙዎች ስለኤርትራ የኑሮ ሁኔታ የሚጠረጥሩት ነገር ቢኖርም፣ በግልጽ ግን የሚያውቁት ስለሌለ የእሷን ማብራሪያ ለመስማት ቋመጡ፡፡

ልጅት ብዙ የምትለው ነገር እንዳላት ታስታውቃለች፡፡ ‹‹ኤርትራ ውስጥ ካሉት ካፌዎች በላይ እስር ቤቶች ይበልጣሉ፤›› ስትለንማ ይበልጥ ትኩረት ተሰጣት፡፡ ‹‹በርካታ ወጣቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ተቃዋሚዎችና ሴቶች ሳይቀሩ ታስረው ነው የሚገኙት፡፡ ይህ ብቻም አይደለም . . . ›› እያለች ወሬዋን አረዘመች፡፡ ይኼን ጊዜ ወያላው፣ ‹‹ምናለ በሉኝ ኢቲቪ ወደ ወህኒ ቤቶቻቸው ሳይሄድ አይቀርም፤›› እያለ ለመቀለድ ሞከረ፡፡

ወጣቷም የወያላው ቀልድ የገባት አትመስልም፡፡ ‹‹አይምሰልህ ኤርትራ ውስጥ የተጣሱ በርካታ ሰብዓዊ መብቶች አሉ፡፡ ወጣቱን አገሩን ጥሎ ያስኮበለለው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ባለመቻሉ ነው፡፡ ኧረ ስንት ጉድ አለ? እኔን ምስኪን ያድርገኝ ኢሳያስን ነው ምስኪን ነው ያልከው?›› እያለች ምሬቷን በጥቂቱም ቢሆን አካፈለችን፡፡

ይኼን ጊዜ አንድ ሰው፣ ‹‹ዘመኑ እኮ የመወነጃጀል አይደለም፡፡ አንቺም ብትሆኚ ይቅርታ አድርጊለትና በሰላም መኖር ይሻላል፤›› የሚል የመደመር ሐሳብ አነሳ፡፡ ይኼን ጊዜ አንድ አዛውንት፣ ‹‹ያልተነካ ግልግል ያውቃል . . . ›› በማለት ወሬውን ተቀላቀሉ፡፡ እኛም ትኩረት ሰጠናቸው፡፡፡ ‹‹ብዙዎች መገደላቸውን፣ መገረፍና መታሰራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ጠቅላዩም ቢሆኑ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ በመሆን ኃላፊነታቸውን ከመወጣታቸው በፊት ያለፈውን መቀየር ባይቻልም የወደፊቱ ላይ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ እንጠብቃለን፤›› በማለት የመሰላቸውን ሰነዘሩ፡፡ ልጅቷ በእሳቸው ሐሳብ ላይ ተደርባ፣ ‹‹እኔም ያልኩት ይህን ነበር፤›› አለችን፡፡ ዘንድሮ ሁሉም ‹ብዬ ነበር› እያለን ነው ያለው፡፡  ማዳመጥ ነው እንግዲህ፡፡ 

ጎልማሳው ከጥግ በኩል ወሬያቸውን ተቀላቅሎ የኢሳያስን ጉዳይ ዳግም ማንሳት ጀመረ፡፡ ‹‹እዚህ ታክሲ ውስጥ ከተሳፈርነው ኤርትራዊያን እንደሚበዙ ያስጠረጥራል፡፡ ወዳጆቼ ሳዋን ያላየ ማዕከላዊን ያማርራል፤›› ሲለን አግራሞት ቢጤ ፊታችን ላይ ታየ፡፡ ወያላው ተቀብሎት፣ ‹‹ሳዋን ያላየ ሄዶ ይይ፤›› ሲለን የአየር መንገዱን በረራ መጀመር የምንጠባበቅ አስመሰለን፡፡

ይኼው ስለሳዋ አስከፊነት ሲያብራራ የነበረው ሰው፣ ‹‹መንገዱ ተከፍቶ ሁሉም መውጣትና መግባት ሲጀምር ምን ያህል ኤርትራዊ ኮብልሎ እንደሚመጣ የምናየው ይሆናል፤›› እያለም ትንሽ አስፈራራን፡፡ የመጀመርያዋ ሴት ከአፉ ቀልባ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ወደ ኤርትራ ሄደው ለመኖርና ለመጎብኘት ከሚጓጉት በላይ አያሌ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ዳግም ፊታቸውን አዙረው ሳይመለሱ ሲቀሩ ያን ጊዜ የኢሳያስ ማንነት በጥቂቱ ይገባናል፤›› ስትለን ‹እንግዲህ ወንድሞቻችን ቢመጡ ደስታችን ነው› የሚል ዓይነት ፊት ተሰጣት፡፡

አንድ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹ኢሳያስ በርካታ ኤርትራዊያንን አገር ከድታችሁ ሄዳችኋል በማለት ከሱዳንና ከኡጋንዳ አግቶ መውሰዱን ሰምቻለሁ፤›› አለ፡፡ ይኼን ጊዜ ወጣቷ፣ ‹‹ያኔ ለእግር ኳስ ብለው ከሄዱት የቡድን አባላት መካከል አንድ ወጣት ብቻ ነበር ወደ አገሩ የተመለሰው፡፡ እሱም ደግሞ እናቱ ፈርማ ስለሰደደችው ባይመለስ እናቱን ወህኒ እንደሚጨምሯት በማወቅ ለእናቱ በመሥጋት ነው የተመለሰው፤›› ስትለን ትንሽ ሥጋት ቢጤ ታክሲ ውስጥ እንድታንዣብብ ምክንያት ሆነ፡፡ በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ የተለመደ ቢሆንም የወጣቱን መረጃ እንደ ዋዛ ሰማነው፡፡

‹‹አሁን ዘመኑ የሰላም፣ የእርቅና የፍቅር ነው፤›› በማለት አዛውንቱ በድጋሚ አስተያየታቸውን ሰነዘሩ፡፡ ይኼን ጊዜ ሾፌሩ፣ ‹‹የመሪዎቹን ሳቅና ጨዋታ ለተመለከተው ሰማኒያ ሺሕ ሰው ያለቀበትን ጦርነት አውርተው አይመስልም፤›› አለ፡፡ ወያላው ደግሞ፣ ‹‹እና ምንድነው የሚመስሉት?›› የሚል ጥያቄ መልሶ አቀረበለት፡፡ ሾፌሩ ድምፁን ጎርነን አድርጎ፣ ‹‹የሆነ ግዳይ የጣሉ አዳኞች እኮ ነበር የሚመስሉት፤›› ብሎ መለሰለት፡፡ ይኼን ጊዜ እኛም ወደ መጨረሻችን ደርሰን ነበር፡፡ ሁሉም በልቡ ከፍቅር የሚበልጥ ምን አለ . . . የሚል ይመስል ነበር፡፡ ፒያሳችን ዛሬም ሞቅ እንዳለች ተቀበለችን፡፡ የሰማነውን እያሰላሰልን የፒያሳ ትርምስ ውስጥ ገባን፡፡ ሥጋት፣ ፍራቻና ጥርጣሬ የተሞላበት ኑሮአችን በየፈርጁ ብዙ ቢያናግረንም፣ ለእርቅና ለፍቅር ስንል ያለፈውን ክፉ ጊዜ መርሳት የመሰለ የለም፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት