Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአሜሪካ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል ተጠቃሚዎቹ አፍሪካውያን ናቸውን?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሥልጣን ዘመን፣ በምዕራባውያኑ ሚሊኒየም 2000 ላይ ተጠንስሶ በአሜሪካ ኮንግረስ ጸድቆ ‹‹አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት አጎዋ›› በሚል ስያሜ የወጣው ሕግ፣ አፍሪካውያንን በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ ለማገዝ ሲተገበር ከ15 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡

የመጀመርያው ምዕራፍ ለ15 ዓመታት እንዲቆይ የተፈረመ ሕግ ነበር፡፡ 15 ዓመታቱ ከተገባደዱ ሦስት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ግን ለተጨማሪ አሥር ዓመታት እንዲራዘም በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ስምምነት ተደርሶበት ጸድቆ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይህ የገበያ ዕድል በሕግ ለ40 ያህል የአፍሪካ አገሮች የሰጠው መብት ሊጠናቀቅ ሰባት ዓመታት ቀርተውታል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ባስተናገደችው ዓመታዊው የአጎዋ ፎረም ወቅት ትልቁ ርዕሰ ጉዳይ የነበረው፣ ላለፉት 15 ዓመታት የተተገበረው አጎዋ የሚጠናቀቅበት ጊዜ እንዲዘራም ግፊት ሲደረግበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ ሚኒስትሮችና ዲፕሎማቶች ሽንጣቸውን ገትረው አጎዋ ለተጨማሪ ዓመታት እንዲዛረም ወተወቱ፡፡ አሜሪካ ብዙ ስታቅማማና ስትከራከር ቆይታ በመጨረሻው ተስማማች፡፡ እነሆ ባለፉት 15 ዓመታት የአጎዋ ቆይታ እንደሚፈለገው መጠን አፍሪካ ባለመጠቀሟ ሳቢያ ይዘራም የተባለው የገበያ ዕድል፣ እነሆ ለአሥር ተጨማሪ ዓመታት እንዲቀጥል በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ዘመን ተወስኗል፡፡

የአጎዋ መራዘም ምን ዕድል አመጣ?

ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የኮታና የታሪፍ ነፃ ገበያ ከወትሮው የተለየ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዕድል ለአፍሪካ አስገኝቷል ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል የተሟላ መረጃ ሲቀርብ አይታይም፡፡ ከሰኞ፣ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዋሺንግተን ዲሲ የሚካሄደው 17ኛው የአጎዋ ፈረም (እየተፈራረቀ አንዴ በአሜሪካ አንዴ በአፍሪካ ይካሄዳል)፣ የአጎዋን ወቅታዊ አተገባበር እንደሚገመግም ከአሜሪካ የወጣው መግለጫ ይጠቁማል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአጎዋ ፎረምን በተመለከተ ለአፍሪካ ጋዜጠኞች ከአሜሪካ የስልክ ኮንፈረንስ አካሂደው ነበር፡፡ ሮበርት ኬ. ስኮት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ አፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ተጠባባቂ ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡ በአሜሪካ ንግድ ጽሕፈት ቤት የአፍሪካ ተወካይዋ ኮንስታንስ ካይሊ ሐሚልተን ጋር በመሆን ስኮት እንዳብራሩት፣ አጎዋ አሜሪካ በአፍሪካ ለምታካሂደው የኢንቨስትመንትና የንግድ መስፋፋት አስተዋጽኦ ሲያበርክት ቆይቷል፡፡

ሁለቱ ኃላፊዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ አጎዋ ለአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ብቻም ሳይሆን፣ መልካም ገጽታም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በርካታ የአሜሪካ ባለሀብቶች ስለ አፍሪካ ያላቸው ግንዛቤ በሌላኛው ጫፍ ላይ የሚገኝ ወይም የተዛባ በመሆኑ ይህንን ለማረቅ ድልድይ ስለመሆኑ የተነገረለት አጎዋ፣ በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል የሚካሄደውን የንግድ ልውውጥ በስድስት በመቶ ማደጉን ሚስ ሐሚልተን ጠቅሰዋል፡፡ ዘንድሮ በዋሺንግተን ዲሲ ‹‹ፎርጂንግ ስትራቴጂስ ፎር ዩኤስ አፍሪካ ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት›› በሚል መርህ የሚካሄደው የአጎዋ ፎረም፣ የፈጠራቸው ዕድሎችና ያስገኛቸው ለውጦች እንደሚገመገሙበትም አብራርተዋል፡፡

አጎዋ እንዲራዘም ምክንያት ከሆኑት መከራከሪያዎች አንዱ የአፍሪካ አገሮች ለገበያው ዕድል በተሰጣቸው ዕድል ለመጠቀም የመሠረተ ልማት አውታሮችን ሲገነቡ መቆየታቸው አንዱ ነበር፡፡ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ተገቢነት ያላቸውን መሠረተ ልማቶች እየገነቡ በነበረበት ወቅት የአጎዋ ማጠናቀቂያ ጊዜ በመምጣቱ፣ በተቀመጠለት ጊዜ መሠረት እንዲጠናቀቅ ከሚደረግ ይልቅ ለተጨማሪ ዓመታት ይራዘም የሚለው ጥያቄ በመጠናከሩ የአሜሪካ መንግሥትም ፈቃዱን በመስጠት አራዝሞታል፡፡

እስካሁን ምን የተለየ ዕድልና ለውጥ አስገኘ የሚለውን ለመቃኘት የተሟላ መረጃ ባይገኝም፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ለአጎዋ ብዙም ለውጥ ያልታየበት አካሄድ ውስጥ እንደሚገኝ አመላካች ይመስላል፡፡ የንግድ ሚዛኑ ለአሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ ያጋደለው የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ የአጎዋን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡

ይህንን አባባል በምሳሌ ለማጠናከር እንዲረዳ በሁለቱ አገሮች መካከል ስለነበሩ የንግድ ለውውጦች የሚያሳዩ ዋቢዎችን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2014 ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከተላኩ ምርቶች አሜሪካ ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የአጎዋ ድረ ገጽ ያሰፈረው አኃዛዊ መረጃ ያመላክታል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በዚሁ ወቅት ወደ አሜሪካ ከላከቻቸው ምርቶች ያገኘችው ገቢ 300 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተላኩ ምርቶች ለአሜሪካ ያስገኙት ገቢ ወደ 874 ሚሊዮን ዶላር ሲቀንሱ፣ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተላኩ ምርቶችም ከ292 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ገቢ አስመዝግበዋል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግም ሪፖርተር ሁለቱን ባለሥልጣን ስለ አጎዋና የአፍሪካውያን ተጠቃሚነት ጉዳይ ጠይቋል፡፡ አጎዋ የአፍሪካ አገሮች በአሜሪካ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ዕድሉን ያመቻቻል ተብሎ የወጣ የሕግ ማዕቀፍ ቢሆንም፣ በአመዛኙ ተጠቃሚዋ ግን አሜሪካ ሆናለች፡፡ ይህ ከሆነ አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው፡፡ አጎዋም ሳያስፈልግ አገሮች ከአሜሪካ ጋር በመነገድ አሁን የሚታየውን ዓይነት የንግድ ልውውጥ ማደረግ ይችሉ የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

ለሪፖርተርም ሆነ ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠታቸው ቀደም ብለው፣ ሮበርት ስኮት ባጣቀሱት አኃዛዊ መረጃ መሠረት፣ አጎዋ ሲጀመር ከነበረው የ13 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ መጠን በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ያደገበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በአሜሪካና በአፍሪካ አገሮች የንግድ ልውውጥ የተነሳ እያዳንዱ አፍሪካ የአምስት ዶላር ገቢ ሊገኝ የሚችልበት ዕድል እንደተፈጠረ አብራርተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአጎዋ አማካይነት በርካታ የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስሮች መፈጠራቸውን ስኮት ይጠቅሳሉ፡፡ 1600 የአፍሪካ ሴት የሥራ ፈጣሪዎችን በመደገፍና በርካታ የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠትም ከአጎዋ ባሻገር አሜሪካ ለአፍሪካ ስለምትሰጣቸው ድጋፎች ተብራርቷል፡፡

አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2050 ተጨማሪ 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ እንደሚኖራት ስለሚታሰብ ለዚህ ሕዝብ ቁጥር የሥራ ዕድልና መተዳደሪያ ለመፍጠር እንደ አጎዋ ያለው የገበያ ዕድል ወሳኝ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በተደረገው የንግድ ልውውጥ ባለፈው ዓመት የ35 በመቶ ጭማሪ መታየቱንም ስኮት ይናገራሉ፡፡ በዚህም 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ኢትዮጵያ ማስመዝገቧን፣ ሌሎችም እንደ ማዳጋስካር ያሉ አገሮችም የንግድ ገቢያቸው ጭማሪ ማሳየቱ ተወስቷል፡፡ አጎዋ ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ ይልቅ አሜሪካን ተጠቃሚ በማድረጉ አስፈላጊ አይደለም በሚለው ሐሳብ ላይ ሚስ ሐሚልተን እንዳብራሩት፣ ከኢትዮጵያ አኳያ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ሒደት መንግሥትን በማማከርና የራሱን ፋብሪካ ጭምር በመትከል የተሳተፈው የአልባሳት ኩባንያ ፒቪኤችን በአብነት ጠቅሰውታል፡፡ ኩባንያው 17 ሺሕ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አግዟል የሚል ሐሳብም ቀርቧል፡፡ እውነታው ግን ፒቪኤች ብቻውን ያስገኘው የሥራ ዕድል አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ፒቪኤችን ጨምሮ ከሌሎች አገሮች የተውጣጡ በርካታ ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

ይህም ሆኖ አጎዋ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ የአቅም ግንባታ፣ የቴክኒክ ድጋፎችንና መሰል ሥራዎችን በማቀላጠፍ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የአሜሪካውያንን አስተሳሰብ በመቀየር አፍሪካ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ለማሳወቅ አግዟል የሚለው ነጥብ ተወስቷል፡፡ ሚስ ሐሚልተን እንደሚሉት ከሆነ፣ አጎዋ በተጀመረበት ወቅት አብዛኛው አሜሪካዊ ስለ አፍሪካ የሚያወራው በግጭትና በጦርነት የተወጠረች አኅጉር ስለመሆኗ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ አፍሪካ በመምጣት ኢንቨስት ማድረግ ስለቻልባቸው መንገዶች መነጋገርና ጉብኝት ማድረግ እየተበራከተ መምጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡ 

እንዲህ ያሉት መከራከሪያዎች ቢቀርቡም፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከአጎዋ የታሪፍና የኮታ ነፃ ገበያ ያገኙት ተጠቃሚነት በአኃዝ ሲተመን ብዙ የሚያስብል አይደለም፡፡ ይባስ ብሎም ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራፕ አስተዳደር ከአጎዋ ተጠቃሚነታቸው የታገዱ ሦስት አፍሪካ አገሮች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ኡጋንዳ ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነታቸው የመታገዳቸው ዜና ከተሰማ ቢሰነባብትም፣ ሚስ ሐሚልተን እንዳብራሩት ከሆነ ግን ሩዋንዳ ከአጎዋ ተጠቃሚነቷ የምትታገደው በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ብቻ ነው፡፡ ሩዋንዳ ከአሜሪካ የሚላኩ ልባሽ ጨርቆች ላይ የታሪፍ ጫና በማድረግ ወደ አገሯ እንዳይገቡ ማድረጓ ለዕገዳው እንዳበቃት ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች