[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት በጣም ተጨናንቀው ተክዘው ቁጭ እንዳሉ ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ገቡ]
- አንተ ምን ሆነሃል ዛሬ?
- ምን ሆንኩኝ?
- እንደዚያ ስልክ ስቀጠቅጥልህ የማታነሳው ለምንድነው?
- ቀኑን ሙሉ ስብሰባ ላይ ነበርኩ፡፡
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስብሰባ ቅዳሜ ቅዳሜ ብቻ ነው ብለዋል አይደል እንዴ?
- እኔ እኮ አሁንስ በጣም ግራ ግብት እያለኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው ግራ የገባህ?
- አንቺ ደግሞ ቤቱ ውስጥ ሌላ አለቃ ልትሆኚብኝ ነው?
- እሱ የእኔ ችግር አይደለም፡፡
- አለቃ ስለበዛብኝ ሰልችቶኛል እያልኩሽ ነው፡፡
- እኔ እኮ አለቃ ልሆንብህ ፈልጌ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን ፈልገሽ ነው?
- በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ላማክርህ ነው፡፡
- የምን አንገብጋቢ ጉዳይ?
- እየተወራ ያለውን ነገር አልሰማህም እንዴ?
- አገሩ ሁሉ ወሬኛ ብቻ አይደለም እንዴ? ከእኛ ውጪ ማን የሚሠራ አለ ብለሽ ነው? የምን ወሬ ነው?
- አደገኛ ነገር መጥቷል፡፡
- እኮ ምኑ ነው አደገኛው ነገር?
- ቤት ውስጥ በካዝና ያስቀመጥነውን ገንዘብ ምንድነው የምናደርገው?
- የራሳችን ገንዘብ እኮ ነው፣ እዚሁ ነዋ የሚቀመጠው፡፡
- የራሳችን ገንዘብ ነው ስትል ትንሽ እንኳን አታፍርም?
- እና የማን ገንዘብ ነው?
- የደሃው ሕዝብ ገንዘብ ነዋ፡፡
- ሴትዮ ዝም ብለሽ አትመፃደቂ፡፡
- ስማ ያኛው ካዝና የስንት ሺሕ ሰው ኮንዶሚኒየም፣ ያኛው ካዝና ደግሞ የስኳር ፋብሪካዎችን፣ ይኼኛው ደግሞ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ገንዘብ የያዙ መሆኑን ረሳኸው?
- ስሚ አንቺም ከእኔ ጋር መሰለኝ የዘረፍሽው?
- እኔ አልዘረፍኩም እያልኩህ አይደለም?
- ታዲያ አንቺን ማን ነው የካዝና ኦዲተር ያደረገሽ?
- ዋናው ኦዲተር ከመምጣቱ በፊት ራሳችንን ኦዲት ብናደርግ ይሻላል ብዬ ነው፡፡
- ለምን ዝም ብለሽ ነገር ትቆሰቁሻለሽ?
- ሰውዬ ጣጣ ሳይመጣብን ይኼን ብር ወደ ዶላር እንቀይረው፡፡
- እሱንማ ፈጽሞ አላደርገውም፡፡
- ለምን?
- ስሚ የዶላር ዋጋ መውደቁን አልሰማሽም እንዴ?
- እሱማ ሰምቻለሁ፡፡
- በዚያ ላይ ደግሞ ይኼንን ብር አራጣ እያበደርኩበት መሆኑን ታወቂያለሽ አይደል እንዴ?
- አራጣ ወንጀል መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
- ሴትዮ እኔ እንዲያውም በቅርቡ ባንክ ለመክፈት እያሰብኩ ነው፡፡
- የምን ባንክ?
- ሚኒስትሩ የሚባል ባንክ፡፡
- ስማ እንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ሌብነት ውስጥ ገብተህ መማማሪያ እንዳያደርጉህ ነው የምፈራው?
- ምንም ሊያደርጉኝ አይችሉም ስልሽ?
- የቤት ለቤት አሰሳ ሊጀመር ነው ሲሉ ሰምቻለሁ?
- የምን አሰሳ ነው?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገወጥ ባንኮች አገሪቱ ውስጥ እንዳሉ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
- የእኛ በድብቅ ኔትወርክ ስለሚሠራ ማንም አይደርስበትም፡፡
- ብቻ እኔ ከመዋረዳችን በፊት ዕርምጃ ብንወስድ ጥሩ መሰለኝ፡፡
- ምን ዓይነት ዕርምጃ?
- ከቻልን በዶላር መቀየር ካልሆነ ደግሞ ንብረት መግዛት ይሻለናል፡፡
- ቆይ ገንዘቡን ቆፍረን ብንቀብረውስ?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኮ ወደ ባንክ ካመጣችሁት ሳትጠየቁ በምሕረት ትቀጥላላችሁ ብለዋል፡፡
- ስሚ ‹ሊበሏት ያሰቧትን ጅግራ ቆቅ ናት ይሏታል› አሉ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አሁን እኛ ገንዘባችንን ወደ ባንክ ብናስገባ ማን ይለቀናል?
- ማን ይነካናል?
- ስሚ ገንዘባችንን ወደ ባንክ ከተው፣ እኛን ወደ ቂሊንጦ ነው የሚልኩን፡፡
- ሰውዬ በዚህ አካሄዳችን ግን ባዶአችንን ነው የሚያስቀሩን፡፡
- እንዴት አድርገው?
- ሊቀየር ነው እየተባለ ነው፡፡
- ምን?
- የብር ኖት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የዓረብ አገር ዲፕሎማት ጋር እያወሩ ነው]
- በጣም ረዥም ጊዜ ሆነን ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እባክህ ሥራ ስለሚበዛብኝ ነው፡፡
- ለነገሩ ኢትዮጵያ ያለችበት ሩጫ ይገባኛል፡፡
- የአትሌት አገር ናት ብለው ነው መሰለኝ ይኸው እኛንም እያሯሯጡን ነው፡፡
- ያው መቼም ሩጫው ለእርስዎ አይከብድዎትም፡፡
- ኧረ አንዳንዴ ከአቅሜ በላይ እየሆነ ነው፡፡
- ለነገሩ ዕድሜዎም ስለገፋ ሊያስቸግርዎት እንደሚችል አውቃለሁ፡፡
- ልባችንን ሊያስተፉን እኮ ነው፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር አሁን ያለው አመራር በእውነት የሚያስደስት ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- አሁን የአገሪቱ ዋነኛ ችግር የተፈታ ይመስለኛል፡፡
- ምንድነው የአገሪቱ ዋነኛ ችግር?
- እኛ ሁሌም የኢሕአዴግ ችግር፣ የችግሩን መንስዔ ውጫዊ ማድረጉ ነው እንላለን፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ሁሌም ቢሆን እኮ የኢሕአዴግ ዋነኛ ጠላት ኢሕአዴግ ነው ስንላችሁ አትሰሙም ነበር፡፡
- እየተሳሳትክ እኮ ነው፡፡
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን እያልክ ነው ታዲያ?
- ችግራችሁ ውስጣችሁ ሆኖ የምትጠቁሙት ግን ወይ ወደ ግብፅ፣ ካልሆነ ደግሞ ኤርትራና ሶማሊያ ላይ ነበር፡፡
- እነሱማ አሁንም ጠላቶቻችን ናቸው፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር አዲሱ አመራር እኮ ይኼን አመለካከት ቀይሮታል፡፡
- እንዲያውም ዋነኛ ችግራችን የውጭ ኃይሎች እየመጣችሁ በውስጣችን ስለምትፈተፍቱ ነው፡፡
- አዲሱ አመራር እኮ ከውስጣችሁ የበሰበሰውን ቆርጦ ስለጣለ ነው ሰላም የመጣው፡፡
- ሰውዬ ብንከባበር አይሻልም? እኔ ነኝ የበሰበስኩት?
- ኧረ እንደዚያ ለማለት ፈልጌ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ኢሕአዴግን እዚህ ያደረስነው እኮ እኛ አንጋፋዎቹ ነን፡፡
- እሱማ ሀቅ ነው፣ እኔ እንደዚያ አይደለም ያልኩት፡፡
- ታዲያ ምን እያልክ ነው?
- የውስጣችሁ ችግር ሲፈታ ይኸው የአካባቢያችሁንም ሰላም በማስጠበቅ ኃያልነታችሁን እያስመሰከራችሁ ናችሁ፡፡
- የምን ኃያልነት ነው?
- ይኸው የደቡብ ሱዳን መሪዎችን ከስንት ጊዜ በኋላ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ያጨባበጧቸው፡፡
- ምን ይጠበስ ታዲያ?
- ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ጠላትነት አብቅቶ ሁለቱ አገሮች በፍቅር ወድቀዋል፡፡
- እሱ ላይ እኔ ተቃውሞ አለኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መሪዎቹ እንዴት ሲፍለቀለቁ እንደነበሩ ሲታይ እኮ ምን ያህል በፍቅር እንደወደቁ ያስታውቃል፡፡
- እኔ ግን ከኢሕአዴግ ያፈነገጡ አካሄዶችን እያየሁ ነው፡፡
- የተባለውን ሰምተዋል ግን ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ተባለ?
- ኤርትራውያን እኮ ባድመን ወስዳችሁ ዓብይን ስጡን እያሉ ነው፡፡
- ቀልዱን ብትተወው ጥሩ ነው፡፡
- ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር እኔ አንድ ነገር ሆኛለሁ፡፡
- ምን?
- ተደምሬያለሁ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም ነህ?
- ምነው ድምፅዎ ኮስተርተር አለብኝ?
- እንዴት አልኮሳተር?
- አሁንማ ሊስቁበትና ሊፈነድቁበት የሚገባ ጊዜ ነው፡፡
- ምን ተገኘ ብዬ?
- ከኤርትራ ጋር ሰላም ወረደ አይደል እንዴ?
- ታዲያ ሰላም መውረዱ እኔን ለምን ያስፈነድቀኛል?
- ክቡር ሚኒስትር አየር መንገዱ እኮ ሥራ ሊጀምር ነው፡፡
- ሰውዬ እኔ እኮ ፓይለት አይደለሁም፡፡
- ወደቡም በቅርቡ ሥራ መጀመሩ አይቀርም፡፡
- እኔን መርከበኛ ነው ብሎ የነገረህ ሰው አለ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር አንዳንዴ ነገሮችን ሰፋ አድርገው ማየት አለብዎት፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ይኼ እኮ ለእኔና ለእርስዎ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡
- አልገባኝም?
- ሁለቱ አገሮች ሰላም ከሆኑ እኮ አዳዲስ ቢዝነሶች አቆጠቆጡ ማለት ነው፡፡
- የምን አዳዲስ ቢዝነስ?
- ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያን በ11 በመቶ ስናሳድጋት ምን ያህል እንደተጠቀምን ያውቃሉ አይደል?
- እሱማ ልክ ነህ፡፡
- ኤርትራንም በዚሁ ፍጥነት አሳድገን የድርሻችንን መጠቀም አለብን፡፡
- እኔ የኤርትራ ማደግ መቼ አስጨነቀኝ አልኩህ?
- ክቡር ሚኒስትር የኤርትራ ዕድገት ያስጨንቅዎታል ብዬ ሳይሆን የእርስዎን ጥቅም አስቤ ነው፡፡
- የእኔ ጥቅም ምንድነው?
- እርስዎ እንደ ምንም ብለው የኢትዮጵያ ገንዘብ ኤርትራ ውስጥ እንዲሠራ ያስደርጉ፡፡
- ለምን ተብሎ?
- እዚህ በጥሬው የያዝነውን ገንዘብ እዚያ ይዘን ሄደን መሥራት እንችልበታለና፡፡
- እንዴት? እንዴት?
- አዩ ቤት ያለው ገንዘባችን ሕገወጥ ነው ሊባል ስለሚችል፣ ኤርትራ ወስደነው ኢንቨስት ልናደርገው እንችላለን፡፡
- ለሚስቴ ጭንቀት መፍትሔ ተገለኘት ነው የምትለኝ?
- ክቡር ሚኒትር ቆሻሻው ብራችን እዚያ ታጥቦ ይነፃል፡፡
- የት?
- ቀይ ባህር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ይደውልላቸዋል]
- ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
- እንዴት ነህ?
- ያው እኛም ይመጣሉ ብለን ዝግጅቱን አጧጡፈነዋል፡፡
- ማን ነው የሚመጣው?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊመጡ አይደል እንዴ?
- አዎ ይመጣሉ፣ እውነትህን ነው፡፡
- እርስዎ አይመጡም እንዴ?
- ያው የዶላር እጥረት ስላለ እንደ ድሮው ተግተልትለን መሄድ ቀርቷል፡፡
- ለነገሩ እርስዎ እዚህ ከመጡ ከፍተኛ ተቃውሞ ነው የሚገጥምዎት፡፡
- ዋናው የአገሬ ሕዝብ ከወደደኝ ችግር የለውም፡፡
- ለማንኛውም እዚህ የሕዝቡ ደስታ ወደር የለውም፡፡
- ምን ተገኝቶ?
- ልትበተን የነበረችው ኢትዮጵያ ይኸው ሰላሟ ተጠብቆ በሚገርም ፍጥነት እየሄደች ነዋ፡፡
- እ. . .
- ክቡር ሚኒስትር የውስጥ ችግራችን ተፈትቶ በአካባቢው ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናችን እየታየ ነው፡፡
- እሱን እንኳን ተወው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከግብፅ ቢሉ ከኤርትራ ጋር በምናደርገው ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተደነቅን ነው፡፡
- ተደምረሃል ልበል?
- ከተደመርኩማ ቆየሁ፡፡
- አሁን ገባኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር የፕሬዚዳንቱ አንድ መቶ ቀናት የሚባል ነገር አለ፡፡ የእኛም ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት መቶ ቀናት ይሞሉዋቸዋል፡፡
- ታዲያ ምን ይጠበስ?
- መቼም ኢሕአዴግ ነፃ ምርጫ ሳያደርግ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ማለቱን ያምናሉ?
- ሰውዬ እኛ በትክክለኛ ምርጫ ነው ያሸነፍነው፡፡
- እሱን ይተውትና ሕዝቡ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በመቶ ቀናት ውስጥ ፈትኖ ውጤት ሰጥቷል፡፡
- ስንት ተሰጣቸው?
- መቶ በመቶ!