Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቻይኖች በአዳማ የራሳቸውን ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገነቡ ስምምነት ተደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በሐዋሳ እያስገነባው የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ የሚያስጀምርበት ጊዜ ይፋ እንደሚደረግ በሚጠበቅበት ወቅት፣ ያልታሰበ ስምምነት ከቻይና መንግሥት ጋር በማድረግ በአዳማ በቻይኖች የሚተዳደር ግዙፍ ፓርክ እንደሚገነባ ታወቀ፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የተመራ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ልዑክ በቻይና የሁናን ግዛትን በመጎብኘት፣ ከግዛቲቱ አስተዳደሮች ጋር ስምምነት አድርገው ተመልሰዋል፡፡

ይህንኑ በማስመልከት ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተገኘው መረጃ መሠረት የሁዋን ግዛት ምክትል ገዥ ካይ ዤኒንግ፣ ከዶ/ር አርከበና ከባለሟሎቻቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡ ከውይይታቸውም ባሻገር ከኢትዮጵያ ወገን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ፣ ከሁዋን ግዛት የንግድ ዘርፍ ዋና ዳይሬክተር ሹ ሺያንግፒንግ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ነጋሽ ስምምነቱን በማስመልከት ከሪፖርተር ተጠይቀው እንዳብራሩት ከሆነ፣ በቻይኖች አዳማ ከተማ ላይ የሚተከለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው በዚህ ዓመት ይጀመራል፡፡

ፓርኩ 4.12 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ የሚንሰራፋ ይሆናል ተብሏል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ1.2 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት ላይ የሚካሔድ እንደሆነና 300 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚደረግበትም ተገልጿል፡፡

የሚመጡት ኩባንያዎች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ እንዳልተቻለ የጠቀሱት አቶ ጌታሁን፣ ከሚመጡት ውስጥ በቻይና ግዙፍ ከሚባሉት ውስጥ የሚመደቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሳኒ ግሩፕ ኩባንያ እንዲሁም ቲቢኢኤ ሳውዘርን ፓወር ትራንስሚሽን ኤንድ ዲስትሪቢውሽን ኢንዱስትሪ ግሩፕ የተባሉ ኩባንያዎች ከሚመጡት ውስጥ ስማቸው ተጠቅሷል፡፡ ቻይኖቹ ይህንን የኢንዱስትሪ መንደር ተሳክቶላቸው ከገነቡ፣ በኢትዮጵያ ከመንግሥት ውጭ ሁለተኛውን የኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት ቻይኖች ተጠቃሽ ይሆናሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በዱከም የተገነባው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በቻይኖች የተገነባ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን፣ በአብዛኛው የቻይና ኩባንያዎች ማምረቻ ቦታዎችን ተከራይተው እያመረቱበት የሚገኝ ነው፡፡ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በ500 ሔክታር ላይ ተጨማሪ ማስፋፊያ ለማካሔድ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡

ሙሉ በሙሉ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ የተባሉት የቻይና ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም እንደሚታየው ሳይሆን በጥራትና በብቃታቸው የሚመረጡ ኢንቨስትሮች የሚካተቱበት እንደሆነም አቶ ጌታሁን ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ከአሁን በኋላ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ኢንቨስትሮች ጥራት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አብራርተው፣ የራሳቸውን ገንዘብ፣ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂና የውጭ ገበያ ይዘው የሚመጡት ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ መጀመሩን አቶ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ246 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ የሚገኝና በጥቂት ወራት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከወዲሁ በፓርኩ የማምረቻ ቦታ በሊዝ ለማግኘት ከመንግሥት ጋር ድርድር የጀመሩ የውጭ ኩባንያዎች እንዳሉ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይመጣሉ ከተባሉት የውጭ ኩባንያዎች መካከል በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያተረፉ የአሜሪካ፣ የህንድና የታይዋን ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ጌታሁን፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መጠናቀቅና ስለሚገቡበት የውጭ ኩባንያዎች ማንነት ዝርዝር ማብራሪያ በከፍተኛ ባለሥልጣናት በቅርቡ እንደሚሰጥበት ከመግለጽ ውጭ ሌሎች መረጃዎችን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡

እንደ አቶ ጌታሁን አባባል ከሆነ በሐዋሳ ፓርክ የሚጠለሉ የውጭ ኩባንያዎች ማንነታቸው ከወዲሁ እንዳይገለጽባቸው ከመንግሥት ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡ አንዳንዶቹ እዚህ በመምጣታቸው ፖለቲካዊና መሰል ሌሎች ጫናዎች በተቀናቃኞቻቸውና በሌሎች መብት አራማጆች በኩል ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል በመስጋት ስማቸው በሚዲያ ከወዲሁ እንዳይገለጽ መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች