Wednesday, February 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ተቋማትና ነዋሪዎች በተከማቸ ቆሻሻ መማረራቸውን እየገለጹ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የከተማው አስተዳደር ችግሩን የፈጠሩት ቆሻሻ አንሺዎች ናቸው ይላል

ከንግድና ከመኖሪያ አካባቢዎች የሚያነሳው ያጣ ቆሻሻ ዕለት ዕለት በመከማቸቱ ንግድ ሥራቸውንም ሆነ ጤናቸውን በማወኩ መማረራቸውን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ 

ሥራ ከጀመረ ሦስት ወራት ማስቆጠሩን የገለጹት የሰንዳፋው ቆሻሻ ማከማቻና ማቀነባበሪ ጣቢያ፣ ለዋናው ሥራ ብቻ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት፣ በጠቅላላው ግን አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስወጣ ሲነገርለት የቆየ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይሁንና ይህ ጣቢያ ሥራ ጀምሯል ቢባልም፣ ቆሻሻ የማንሳት ተግባር መደናቀፉንና በበርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች፣ በተለይም በኮንዶሚኒየም፣ በሬስቶራንቶች፣ በሆቴሎችና በመሰል ተቋማት አካበቢ የሚያነሳው ያጣ የቆሻሻ ክምችት እንደሚታይ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡

በጀሞ አካባቢ ይህ ችግር ጎልቶ እንደሚታይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በመካኒሳ አካባቢ በሚገኙ የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎችም አሁንም ድረስ ቆሻሻ ተከማችቶ እንደሚገኝ ሪፖርተር ታዝቧል፡፡

ቆሻሻው ሊነሳ ያልቻለባቸውን ምክንያቶች ለማጣራት ሲሞከርም ሁለት ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ ከነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውና በተለምዶ ቆሼ ተብሎ የሚጠራው ረጲ የቆሻሻ መጣያ፣ በአሁኑ ወቅት ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚውል ፕሮጀክት እየተገነባበት ይገኛል፡፡ ይህ የቆሻሻ መጣያ ከእንግዲህ አገልግሎቱን የማይሰጥ በመሆኑ፣ በቆሻሻ ማሰባሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩና በጥቃቅንና አነስተኛ የተሰማሩ ሰዎች መጣያ አጣን፣ ተከለከልን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ሌላኛውም ምክንያት ደግሞ ቆሼ ይደፋ የነበረው ቆሻሻ ከአዲስ አበባ 38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ ከተማ በተገነባው ዘመናዊ የቆሻሻ መድፊያና ማቀነባበሪያ ሥፍራ በሰሞኑ በኦሮሚያ በተከሰተው ቀውስ ሳቢያ የሰንዳፋ ቆሻሻ ማከማቻ ጣቢያ አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉን የገለጹ ወገኖች፣ በዚህ ምክንያት በአዲስ አበባ በየዕለቱ መነሳት የነበረበት ቆሻሻ ሳይነሳ መቆየቱን የሚገልጹ አሉ፡፡

ይህንን የማይቀበሉት የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አለየ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ በተከሰተው ብጥብጥብ ሳቢያ ሳይሆን፣ ቆሻሻ የሚያነሱ የግል ኩባንያዎች ወደ ሰንዳፋ ቆሻሻ ወስደው ለመድፋት ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁትም ቢሆኑ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለውን ከማይፈለገው ቆሻሻ የሚለዩበትን ዘመናዊ አሠራር እንዲከተሉ በመደረጉ ቆሻሻ ሳይነሳ እየተከማቸ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በቆሻሻ ማንሳት ሥራ የተሰማሩ የግል ኩባንያዎች ወደ ሰንዳፋ መመላለስ ከርቀቱ አኳያ የማያዋጣና አትራፊነታቸውንም የሚጎዳ እንደሆነ በመግጽ አቤቱታ ሲያቀርቡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳዊት፣ አንዳንዶቹ ይሰጡ የነበረውን አገልግሎት በራሳቸው ጊዜ በማቋረጣቸው ሳቢያ አገልግሎቱን ያገኙ በነበሩ የግል ድርጅቶች ላይ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን አቶ ዳዊት አስታውሰዋል፡፡

ቆሻሻ ባለመነሳቱ ምክንያት ሥራቸው ላይ እክል መፍጠሩን በመጥቀስ ለከተማው አስተዳደር አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ከነበሩ የንግድ ተቋማት መካከል፣ ጁቬንቱስ ክለብ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ተቋም አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አካባቢ የሚገኝና በብዛት በውጭ አገር ዜጎች የሚዘወተር፣ ታዋቂ ሬስቶራንትና ሌሎች መዝናኛ ማዕከሎች የሚገኙበት ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ተቋም መግቢያ ላይ የተከማቸው ቆሻሻ የሚያነሳው በማጣቱ ለመመገብም ሆነ ለመዝናናት በሚመጡ እንግዶች ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደር አልፎ ነባር ደንበኞቹን እያሸሸበት እንደሚገኝ በመግለጽ አቤቱታውን ሲያሰማ እንደቆየ ታውቋል፡፡

እንዲህ ያለው ነገር ማጋጠሙን፣ በጀሞና በኮልፌ መኖሪያ አካባቢዎችም ቆሻሻ የማንሳት ችግር መከሰቱን ያመኑት አቶ ዳዊት፣ በተለይ ውል ገብተው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩትና ሰንዳፋ ርቆናል በማለት በገዛ ፈቃዳቸው አገልግሎት መስጠት ያቋረጡ የግል ኩባንያዎች ላይ ኤጀንሲው ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቆሻሻ  በሰንዳፋ በተዘጋጀው ማከማቻ እየተስተናገደ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ በቆሻሻ ማንሳት ሥራ የተሰማሩ 14 ያህል የግል ኩባንያዎች በራሳቸው ተሽከርካሪዎች ከንግድ ተቋማት ቆሻሻ በመሰብሰብ ሥራ ተሰማርተው እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከወራት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከዚህ ቀደም ሲነሳ የሚመደመጠው ሌላው የቆሻሻ አነሳስ ችግር መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለውም የማይውለውም በአግባቡ ሳይለይ፣ ለሚያቀነባብሩ ተቋማት ለማቅረብ በሚል ሰበብ በየሰፈሩ ጥጋጥግና በየገንዳው ተቆልሎ መቆየቱ ነው፡፡

በሌላ በኩል ተብላልቶ፣ ተቀነባብሮ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚዘጋጅ ቆሻሻ ትልቅ ገቢ የሚያስገኝ፣ ራሱን የቻለ የንግድ ሥራ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በተለይ ለፕላስቲክ ጠርሙሶችና ጀሪካኖች በአንድ ኪሎ ቆሻሻ ከአምስት ብር እስከ 12 ብር እየተከፈለ በመሆኑ ለበርካቶች አዋጭ የንግድ መስክ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት መልሶ ጥቅም ላይ ከሚውል ቆሻሻ በዓመት እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሰንዳፋ በሚገኘው በአዲሱ ዘመናዊ የቆሻሻ ማከማቻ ላይ እያከናወነ እንደሚገኝ  አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡

ትልቅ የገቢ ምንጭ እየሆነ የመጣውን ቆሻሻ በከፍተኛ ደረጃ የሚገዙት ቻይኖች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚገኝበት ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መያዝ እንደሚገባውም ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት ኤጀንሲ በ2006 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የነበረውን አፈጻጸም ባስታወቀበት ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፣ በከተማዋ ከሚገኙ 113 ወረዳዎች ውስጥ በሚንቀሳቀሱ 568 የጽዳት ማኅበራት አማካይነት 670 ሺሕ ሜትር ኩብ የሚጠጋ ደረቅ ቆሻሻ ከመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በማንሳት ከ35 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ክፍያ ሊያገኙ መቻላቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በሌላ ጎኑ በቆሼ የረጲ ቆሻሻ መድፊያ ቦታ ላይ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ በተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ አማካይነት እየተገነባ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በቅርቡ ሲጠናቀቅ ከ50 ሜጋ ዋት ያላነሰ ኃይል ከቆሻሻ እንደሚያመነጭ ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ የካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል አለማየሁ ከወራት በፊት ለሪፖርተር ሰጥተውት በነበረ መግለጫ፣ በ120 ሚሊዮን ዶላር በመንግሥት ባለቤትነት የሚገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በቀን 1.5 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ቆሻሻ የማቀነባበር አቅም አለው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እንዲህ ያሉ ተግባራት የሚከናወኑባት አዲስ አበባ በዓለም ላይ ቆሻሻ ተብለው ከተፈረጁ ከተሞች ተርታ ለመመደብ መገደዷ ተሰምቷል፡፡ በቅርቡ በተለያዩ ድረ ገጾች በተሰራጨ መረጃ መሠረት ከአሥር ቆሻሻ ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ሆናለች፡፡

በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ከተከሰተባቸው ምክንያቶች አንዱ ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ አካባቢን እንዳይበክል አድርጎ በተገቢው መንገድ ካለማንሳት ጋር በተያያዘ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ የግልና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ጋር የሚያያዝ በሽታ የሆነውን አተት፣ በአሁኑ ወቅት በአርባ ምንጭ ከተማ መከሰቱም ይታወቃል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች