በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ መሿለኪያ አሸዋ ተራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ፣ የአካባቢው ተወላጅ መሆኑ የተገለጸውን ወጣት መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በመግደል የተጠረጠሩ ሦስት ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡
ሟች ወጣት ሽመልስ ታሪኩ ሲባል የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ሁለተኛ አስጨፋሪና ታዋቂ ደጋፊ መሆኑንም የቅርብ ጓደኞቹ ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ ሲሆን መሿለኪያ አሸዋ ተራ በሚገኘው ኢየሩስ ግሮሰሪ አጠገብ አንድ ዘመዱ በመግደል ወንጀል ከተጠረጠሩት ፖሊሶች ጋር ሲነጋገር በማየቱ፣ ወንድሙ እንደሆነ ገልጾላቸው እንዲተውት እንደጠየቃቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ ፖሊሶች አንዱ ሟችን በቦክስ ሲመታው ወደ ኋላው አስፋልት ላይ መውደቁንም አክለዋል፡፡
ሟች ሽመልስ ወደኋላ ሲወድቅ አስፋልት ላይ በማረፉ ጭንቅላቱ መጎዳቱንና ደም ወደ ውስጥ መፍሰሱ በሐኪም መረጋገጡን የሚገልጹት የዓይን እማኞች፣ ሕይወቱ ማለፉንና ሥርዓተ ቀብሩ ለቡ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ፖሊሶች መሿለኪያ የሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል ጠባቂዎች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ፖሊሶቹ በቁጥጥር ሥር ውለውና በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸው፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረዳት ተችሏል፡፡