– በማዕድን ፍለጋ የተሰማሩ ፈቃድ ለማደስ እንደተቸገሩ ገለጹ
መንግሥት ከማዕድን ዘርፍ ብዙ ቢጠብቅም ከፍተኛና ነባር ጂኦሎጂስቶች እየፈለሱ በመሆኑ የሥራ አፈጻጸሙን ደካማ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ማዕድን ፍለጋ ለማካሄድ ጥያቄ ያቀረቡና በማዕድን ፍለጋ ላይ ያሉ ኩባንያዎች ፈቃድ ለማግኘትና ለማደስ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፍተኛ ጂኦሎጂስቶች መሥሪያ ቤቱን እየለቀቁ ነው፡፡ ማስታወቂያ በሚወጣበትም ጊዜ ሌሎች ከፍተኛ ባለሙያዎች ወደ መሥሪያ ቤቱ አይመጡም፡፡
‹‹በመሥሪያ ቤቱ የከፍተኛ ጂኦሎጂስቶች መመናመን ጠንከር ያለ ተግዳሮት ፈጥሮብናል፤›› በማለት አቶ ቶሎሳ ተናግረዋል፡፡ የከፍተኛ ጂኦሎጂስቶች ፍልሰትን በሚመለከት አቶ ቶሎሳ ጨምረው እንደገለጹት፣ ‹‹ከሁለት ሳምንት በፊት በጣም የምናከብረው፣ ብዙ ሥራ የሚሠራልን ሲንየር ጂኦሎጂስት (አቶ በርሔ ገብረ ሥላሴ) መሥሪያ ቤቱን ለቋል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ያለው መዋቅር ከሚፈልገው ባለሙያዎች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ከ60 በመቶ በታች እንዲሆኑ ማስገደዱን አቶ ቶሎሳ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በተለይ ከባህላዊ ወርቅ ሽያጭ በየወሩ 1,100 ኪሎ ግራም ወደ ውጭ መላክ አቅዶ ነበር፡፡ ይህ እንኳን ባይሳካ ከ700 እስከ 800 ኪሎ ግራም ወርቅ የመላክ ዕቅድ ነበረው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውስጥ ማሳካት የቻለው 50 በመቶ ያህሉን ነው፡፡
ለዚህ አፈጻጸም ከባለሙያዎች እጥረት በተጨማሪ የዓለም የወርቅ ዋጋ በማሽቆልቆሉ ምክንያት ቢሆንም፣ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡
አቶ ቶሎሳ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት አገር በመሆኗ ከማዕድን ወጪ ንግድ የተሻለ ሊገኝ ይገባ ነበር፡፡ በባለሙያዎች ፍልሰትና በተለያዩ ሌሎች ችግሮች ይህን ማሳካት ያለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው አቶ ቶሎሳ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 200 ኩባንያዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ጠንካራ የሚባሉት ከ30 አይበልጡም፡፡
እነዚህ ኩባያዎች የፈቃድ ዕድሳት ለማድረግ ወደ ሚኒስቴሩ በሚሄዱበት ወቅት በቂና ፈጣን አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በወርቅና በመሳሰሉት ማዕድናት ፍለጋ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውንም እየገለጹ ነው፡፡
አገልግሎት አሰጣጡ ደካማ የሆነው በከፍተኛ ባለሙያዎች ፍልሰት ብቻ ሳይሆን፣ በሙስናና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት እንደሆነም እየተገለጸ ነው፡፡ አቶ ቶሎሳ ለዚህ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ አገልግሎት የዘገየበት ኩባንያ ወይም የተቸገረ ኩባንያ የለም ብለው እንደማያምኑ፣ ነገር ግን እሳቸው ዘንድ ሪፖርት ያደረገ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
‹‹በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና በዋና ኦዲተር የተነገሩ ችግሮች አሉብን፡፡ በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ኩባንያዎች የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ባለሙያዎችን እያሳሳቱ ለመግባት ይሞክራሉ፡፡ የአገር ሀብት መጠበቅ ስለሚገባ ጨክነን ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ሲሉም አቶ ቶሎሳ አክለዋል፡፡ ጥፋት የፈጸሙ ባለሙያዎችን ለመገሰጽ በሚሞከርበት ወቅት ባለሙያዎች መሥሪያ ቤቱን የመልቀቅ አዝማሚያ እንደሚያሳዩም ጠቁመዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን መልካም አስተዳደር ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ ዕርምጃ ከመውሰድ እንደማያግድ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከባለሀብቶች ጋር ለመነጋገር በቅርቡ ስብሰባ እንደሚጠራ አቶ ቶሎሳ ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይ ግልጽ ውይይት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡