- Advertisement -

ሕዝብን ማዳመጥ የመንግሥት የዘወትር ሥራ መሆን አለበት!

በየትም አገር በሕዝብና በመንግሥት መካከል እንደ ጥሩ መገናኛ ድልድይ የሚያለግለው መተማመን ነው፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እየዳበረ የሚሄደው መንግሥት በቅርበት ሲያዳምጠው ነው፡፡ ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥት ማንም ስለማያዳምጠው፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ዘመን በበርካታ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው ያለው፣ መንግሥት በተቻለው መጠን የሕዝብን አመኔታ እንዴት እንደሚያገኝ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ማናቸውም ፖሊሲዎች ሆኑ ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት የሕዝቡንም ሆነ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ይሁንታ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ የበርካታ መንግሥታት የዘወትር ሥራ ነው፡፡

መንግሥት ሕዝብን ማዳመጥ አለበት ሲባል ምሁራንን፣ ተማሪዎችን፣ በተለያየ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ወዛደሮችን፣ ነጋዴዎችን፣ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ነፃና ዴሞክራቲክ በሆነ መንገድ መነጋገር ለሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ግብዓት ለማግኘት ከመርዳቱም በላይ፣ የሕዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያረጋግጣል፡፡ በነፃነትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው ጉዳይ የባለቤትነት መንፈሳቸው እንዲነቃቃ ያደርጋል፡፡ ፍራቻና ጥርጣሬ ይወገዳሉ፡፡ ሐሜትና አሉባልታ፣ ጥላቻና በክፉ መፈላለግ ይወገዳሉ፡፡ ለነፃ ማኅበረሰብ ግንባታ የተመቻቸ ምኅዳር ይከፈታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ከምሁራን ጋር ውይይት አድርገው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውይይት መደረጉ በራሱ ጥሩ ጅምር ሆኖ፣ ከዚህ በፊት ግን መታሰብ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ምሁራኑ የሚሠሩባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚያዊ ነፃነት ምን ይመስላል? ምሁራኑ በግላቸውም ሆነ በቡድን ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸው ምን ያህል የተከበረ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነሳ የሚገኘው መልስ አሳዛኝ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚያዊ ነፃነት ተከድኖ ይብሰል የሚባል ሲሆን፣ ምሁራኑ በግላቸው የሚሰማቸው ነፃነት ደግሞ በፍርኃት የተወረረ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጠው ቢሆንም፣ መሬት ላይ የሚታየውና ወረቀት ላይ የሠፈረው የሰማይና የምድር ያህል ርቀት አላቸው፡፡ ምሁራኑ በነፃነት ለአገር ጠቃሚ ነው የሚሉትን ሐሳብ ማቅረብ የሚችሉት ምኅዳሩ ሲሰፋና ደኅንነት ሲሰማቸው ብቻ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከምሁራኑ ጋር የሚደረገው ውይይት አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ ወይም በየቦታው ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሲነሱ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ከብሔራዊ ፀጥታና ደኅንነት አንስቶ እስከ የትምህርት ጥራት ድረስ የሚደረጉ ውይይቶች ተከታታይነት ያላቸው፣ ዘላቂና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው በአገሪቱ ሕግና ሥርዓት ማስከበር፣ ለሕግ የበላይነት ተገዢ መሆን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር፣ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ሙስናን በብቃት መታገል፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በነፃነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ፣ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማስወገድ፣ የአገሪቱን አንድነት ማረጋገጥ፣ ወዘተ ያስፈልጋል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ የተቀደሰ ተግባር ደግሞ የምልዓተ ሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ሕዝብና መንግሥት በመካከላቸው ያለው አለመተማመን ሥር እየሰደደ በሄደ ቁጥር ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ፣ አመፅና ብጥብጥ የበላይነት ይይዛሉ፡፡ በዓለም ዙሪያ ያለውን የዘመኑን ክስተት ለሚያስተውል ደግሞ አመፅና ብጥብጥ አገርን እንደ ሶሪያና የመን ከማውደም የዘለለ ውጤት አይገኝበትም፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተጠናከረ መተማመን መፍጠር የሚቻለው፣ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ላይ በሠፈረው መሠረት አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ሲኖርበት ነው፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈሩት መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ፣ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ሲካሄድ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሰፋና በአገር ጉዳይ ሁሉም ዜጎች ባለቤትነት ሲሰማቸው ብቻ ነው፡፡ አገር በአኩራፊዎች ተሞልታ ዕድገት አይታሰብም፡፡ ሰላም አይታሰብም፡፡ ዴሞክራሲ አይታሰብም፡፡ አኩራፊነት እንዲወገድ ሕዝብ ይደመጥ፡፡ ሕዝብ ሲደመጥ በሕዝብ ስም የሚታቀዱ ልማቶችም ሆኑ የተለያዩ ተግባራት ስኬታማ ይሆናሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ የሕዝብ ራስ ምታት የሆኑት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች፣ የፍትሕ መዛባቶችና መጠነ ሰፊ ሙስናዎች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑት፣ ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ግልጽና አሳታፊ ሥራዎች ስለሌሉ ነው፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በመጥፋቱ ሕዝብን ለአመፅና የሕይወት መስዋዕትነት ለሚያስከፍሉ ብጥብጦች መፈጠር ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ሥጋት የሆኑ ችግሮች ታቅፎ ሁሉንም ጉዳይ በፓርቲ መዋቅርና በተልፈሰፈሱ አደረጃጀቶች ለመፍታት መሞከር ውጤቱ አደጋ ነው፡፡ ከምሁራኑም ሆነ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ለአገር የሚበጁና ለሁሉን አቀፍ መፍትሔ የሚረዱ ካልሆኑም ዋጋ የላቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን አምኖ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ እንታረቅ ማለት ከልብ ካልሆነ ትርፉ የበለጠ ቁርሾ መፍጠር ነው፡፡ ይልቁንም ሕዝብን በቅርበት አግኝቶ ስሜቱን ማወቅና ለተግባራዊ ዕርምጃው ፈጣን መሆን ጠቃሚ ነው፡፡ የአገር ህልውና ከምንም በላይ ነውና፡፡

- Advertisement -

ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የመሳተፍ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ደግሞ ከነፃነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገሪቱ ሕጎች ከለላ መስጠት አለባቸው፡፡ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው፡፡ ይህ በተግባር ሲረጋገጥ ደግሞ ምሁርም ሆነ ነጋዴ፣ አርሶ አደርም ሆነ ወዛደር፣ ከተሜም ሆነ ገጠሬ፣ ወጣትም ሆነ አዛውንት፣ ወዘተ በአገራቸው ጉዳይ እኩል ናቸው፡፡ ዜግነትን ማንም ለማንም እንደማይሰጥና እንደማይነሳ ሁሉ፣ መብትንም እንዲሁ ማንም ሰጪና ተቀባይ አይሆንም፡፡ በሞራል ልዕልና ላይ የተገነባ ማኅበረሰብ እንዲኖር የሚፈለግ ከሆነ፣ ዜጎች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በአገራቸው ጉዳይ በነፃነት ሊነጋገሩ ይገባል፡፡ ተሳትፎአቸውም የበለጠ መዳበር አለበት፡፡ ሕዝብ በሚገባ ፍላጎቱ እየተደመጠ መሆኑን የሚያምነው በዚህ መንገድ ሲስተናገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚከናወኑ ድርጊቶች ብልሹ በመሆናቸው ውጤታቸው ለአገር ጠንቅ ነው፡፡ ለሕዝቡም አደጋ ነው፡፡

በመሆኑም መንግሥት ምሁራንንም ሆነ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለውይይት ሲጋብዝ፣ ውጥረት ውስጥ ወይም ጭንቀት ውስጥ ሆኖ ሳይሆን የዘወትር የቤት ሥራው ማድረግ አለበት፡፡ በውይይት ወቅት የሚሰነዘሩ አስተያየቶችም ሆኑ የሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ ለአገር ፋይዳ እስካላቸው ድረስ በነፃነት ይደመጡ፡፡ የአመራር ክህሎት ከሚለካባቸው መሥፈርቶች አንዱ የሌሎችን ሐሳብ በአንክሮ ማዳመጥ ነው፡፡ የሚመሩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እንኳ ቢቀርቡ በግድ መደመጥ አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የውኃ ልክ መሆን ያለበት፣ የደጋፊን ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚን ድምፅ መስማት ነው፡፡ ከመሬት ላይ አልነሳ ያለው ዴሞክራሲም ዳዴ ማለት የሚጀምረው፣ ለተለያዩ ሐሳቦች በሩን ብርግድግድ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት ገበያ መሆን የሚችለውም የኅብረተሰቡ የተለያዩ ድምፆች ሲደመጡ ብቻ ነው፡፡ ይህንን የማስተናበር ኃላፊነት ያለበት ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝብን ማዳመጥ የመንግሥት የሁልጊዜ ሥራ መሆን አለበት!   

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

እየፀደቁ ያሉ አዋጆች ለሕዝብና ለአገር የሚኖራቸው ፋይዳ ይታሰብበት!

መንግሥት በስኬት አገር ለማስተዳደር ሕጎችን ሲያወጣም ሆነ ፖሊሲ ሲነድፍ፣ የሚቀርቡለትን ምክረ ሐሳቦች በአግባቡ ማስተናገድ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታት የተለያዩ ሕጎች ተረቀው...

የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ያሉ ዕርምጃዎች ይታሰብባቸው!

መንግሥት የዋጋ ንረቱን ከ30 በመቶ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማድረጉን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካይነት በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ገበያው ውስጥ ያለው የምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋ የሚያሳየው...

አስፈሪውን የርዕደ መሬት አደጋ ለመከላከል አቅም ይገንባ!

የስምጥ ሸለቆ አካል በሆነው አዋሽ አካባቢ ለወራት የዘለቀው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉልበቱ እየጨመረ ከፍተኛ ሥጋት እየደቀነ ነው፡፡ በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ...

አገራዊ መልካም እሴቶች በፋይዳ ቢስ ድርጊቶች አይጎዱ!

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚኮሩባቸውና ለመጪው ትውልድ ጭምር ከሚያስተላልፏቸው መልካም እሴቶቻቸው መካከል በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር፣ የብሔር ወይም የእምነት ገደብ ሳይኖር ተጋብቶ መዋለድ፣ ችግሮች...

ሰቀቀን!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ሰነበታችሁ ወገኖች በሙሉ፡፡ እኔ ወንድማችሁ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሳምንት አልፎ ሳምንት ሲተካ፣ ሁላችንም ሰላም ሆነን አገራችንን ባለን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና...

በተቃርኖ ፖለቲካ አገር እንዳትጎዳ ጥንቃቄ ይደረግ!

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየተሰሙ ያሉ ተቃርኖዎች አድማሳቸው ከመስፋቱ በፊት መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአገር ሁለንተናዊ ጉዳዮች ብሔራዊ የምክክር መድረክ ሊዘጋጅ ደፋ ቀና እየተባለ ባለበት ወቅት፣...

አዳዲስ ጽሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ቀኑን ሙሉ ከዋሉበት የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው]

የምን ስብሰባ ላይ ዋልኩ ነበር ያልከኝ? የሥራ አስፈጻሚ። የምን ሥራ አስፈጻሚ? የገዥው ሥራ አስፈጻሚ። ምን ገጥሟችሁ ነው የተሰበሰባችሁት? ለመረጠን ሕዝብ ቃል የገባናቸውን ተግባራት አፈጻጸም የምንገመግምበት የተለመደ ስብሰባ ነው። የገባችሁት ቃል...

ሕወሓትን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው መመርያ

በሁለት አንጃ ተከፍሎ የእርስ በርስ የቃላት ጦርነት ውስጥ የገባው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ልዩነቱን ትቶ ወደቀድሞው አንድነቱ በመመለስ የሚጠበቅበትን ጠቅላላ ጉባዔ የማድረግ አልያም...

ባንኮች እየፈጸሙት ያለው አቅርቦትንና ፍላጎትን ያላገናዘበ የውጭ ምንዛሪ ግዥ

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ ዋጋ እንዲገበይ የወጣው ሕግ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሰባት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ሕጉ ተግባራዊ በተደረገበት የመጀመርያው ቀን የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ...

አሳረኛው ኑሮ!

የዛሬው ጉዞ ከቦሌ ወደ ፒያሳ ይሆን ዘንድ ግድ ሆኗል፡፡ ለምን? በኑሮ  ምክንያት፡፡ የታክሲ መሠለፊያው ወሬ የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ ስለሚመጣው ተጨማሪ ታሪፍ ነው፡፡ ‹‹የእኛ ኑሮ...

የግለሰቦች ለመብታቸው ኃላፊነት አለመውሰድ ለአገር ያለው አደጋ

በያሬድ ኃይለመስቀል አንድ የማከብረው ኢኮኖሚስት አንድ መጽሐፍ እንዳነብ መራኝና ማንበብ ጀመርኩኝ። ይህንን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ሐሳብ ወጣ ብሎ ስለ “የነፃ ተጓዦች ሀተታ” (The Free Rider...

‹‹የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ማጠናከር ያስፈልጋል›› አቶ ፍፁም አብርሃ፣ የአሚጎስ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተመሠረተ አሥራ ሁለት ዓመታት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 8,500 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ አሚጎስ ስለተመሠረተበት ዓላማ፣ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት፣ የብድርና...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን