እየተካሄደ ባለው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ 98 ቤቶች በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸው በመረጋገጡ፣ በሕገወጥነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
እስከ ዓርብ መጋቢት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ 94,101 ቤቶች መቆጠራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ቆጠራው መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
በሕገወጥ መንገድ የተያዙት ቤቶች በአብዛኛው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ ቤቶቹን ሰብረው በመግባት መኖር የጀመሩ፣ የሚያከራዩ፣ ከራሳቸው ቤት ጋር ቀላቅለው የያዙ እንደሆኑ የአዲስ አበባ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ሕገወጥ ተግባር የተፈጸመባቸው ቤቶች ለልማት ተነሽዎች ተብለው የተቀመጡ ነበሩ፡፡ ለልማት ተነሽዎች ለመስጠት በሚታሰብበት ወቅት አብዛኛዎቹ የልማት ተነሽዎች ፍላጎት ባለ ሁለትና ባለ ሦስት መኝታዎች በመሆኑና እነዚህ ቤቶች ደግሞ ስቱዲዮና ባለ አንድ መኝታ በመሆናቸው ያለ አገልግሎት ተቀምጠው ነበር፡፡
ቤቶቹ ባዷቸውን በመቀመጣቸው ለሕገወጥ አገልግሎት የዋሉ በመሆኑና አስተዳደሩም ሕግ ማስከበር ስላለበት ዕርምጃ መውሰዱን አቶ ይድነቃቸው ተናግረዋል፡፡
ለልማት ተነሽዎች ተብሎ ባዷቸውን ተቀምጠው ከነበሩ ከስምንት ሺሕ በላይ ቤቶች ውስጥ እስካሁን 1,200 የሚሆኑት በነበሩበት ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
ቆጠራው ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በሕገወጦቹ ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ይፋ እንደሚሆን አቶ ይድነቃቸው ተናግረዋል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ከዕጣ ውጪ በሌላ መንገድ ሊተላለፉ ስለማይችሉ እጅግ መጠነ ሰፊ የቤት ችግር ባለባት አዲስ አበባ፣ እነዚህ ቤቶች ያለተጠቃሚ እንዲቆዩ መደረጉን ሪፖርተር ከአስተዳደሩ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡