የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለፈው እሑድ መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በአሜሪካዋ ፖርትላንድ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያ ርስቷ በሆነው የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች በተለይም በ3,000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች የወርቅ ሜዳሊያዎች፣ እንዲሁም በ1,500 ሜትር ሴቶች ብርና ነሐስ በማግኘቷ በሜዳሊያ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ አስቀምጧታል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ የ3,000 ሜትር ሩጫ ድሏን ያጣጣመችው የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ገንዘቤ ዲባባ፣ በሰባት ሰከንድ ያህል ብልጫ በ8 ደቂቃ 47.43 ሰከንድ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያውያን ያጠለቀችውን መሠረት ደፋርና ለነሐስ ሜዳሊያ የበቃችውን አሜሪካዊት ሻኖን ሮውበሪ ቀድማ ገብታለች፡፡
ዘገባዎች እንዳመለከቱት ገንዘቤ የገባችበት ከዚህ ቀደም ካስመዘገበችው ጊዜ ጋር የሚቃረብ አይደለም፡፡ የሁለት ጊዜ ኦሊምፒክ ወርቅ ተሸላሚዋና አራት ጊዜ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ወርቅ አሸናፊዋ መሠረት ደፋር ከሁለተኛነቷ ባለፈ አልተፎካከረቻትም፡፡
‹‹ውድድሩ ቀሎኛል ያን ያህል ጠንካራም አልነበረም›› ያለችው ከ1,500 እስከ 5,000 ሜትር የስድስት ጊዜ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ገንዘቤ፣ ‹‹ቤተሰቤና የአገሬ ሕዝብ በተገኘው ውጤት እንደሚደሰቱ አምናለሁ›› ብላለች፡፡
በወሊድ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከውድድር ርቃ የነበረችው ኦሊምፒያዊቷ መሠረት ደፋር ሁለተኛ በመውጣቷ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ያጠለቀቻቸውን ሜዳለያዎች ቁጥር ሰባት አድርሳዋለች፡፡ ቀደም ሲል መሠረት አራት ወርቅ፣ አንድ ብርና አንድ ነሐስ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
የዮሚፍ ቀጀልቻ ልዕልና
ኢትዮጵያዊው የ18 ዓመት ወጣት ዮሚፍ ቀጀልቻ ከአሜሪካው ሪያል ሂል እና ከኬንያዊው አጉስቲን ቾጌ ከፍተኛ ፉክክር ቢገጥመውም፣ አንዳቸውም ሳያቆሙት የ3,000 ሜትር ውድድሩን በ7 ደቂቃ 57.21 ሰከንድ በድል በማጠናቀቅ ወርቁን አጥልቋል፡፡
በመጨረሻው መስመር ላይ በደጋፊዎቹ የአገሩ ሰዎች ድጋፍ ታጅቦ የተፎካከረው አሜሪካዊ ሪያን ሂል በ7፡57.39 ኬንያዊን ከማለፍ በስተቀር ተወንጫፊውን ዮሚፍን መርታት አልተቻለውም፡፡ ቾጌ በ7፡57.43 የነሐስ ሜዳሊያውን ጨብጧል፡፡ በሻምፒዮናው ታሪክ ሁለተኛው ዝግ ያለ ጊዜ ማስመዝገቡ ከቁብ ያልቆጠረው ዮሚፍ፣ ሐቻምና በዩጂን በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና በ5000 ሜትር ወርቅ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ እንዲሁም ዓምና በዳይመንድ ሊግ በተመሳሳይ ቦታ በ5000 ሜትር ድል መቀዳጀቱ አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ የብር እና ነሐስ ሜዳሊያዎች ያገኘችው በቅዳሜው (መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም.) የ1500 ሜትር ሴቶች ውድድር ዳዊት ሥዩምና ጐደፋይ ፀጋዬ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ባስመዘገቡት ውጤት ነው፡፡ ቀዳሚ ሆና የፈፀመችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት ሲፈን ሐሰን ናት፡፡
የሻምፒዮናው ደረጃ
በዘንድሮው የፖርትላንድ ሻምፒዮና አሜሪካ የበላይነቱን በ13 ወርቅ 6 ብር እና 4 ነሐስ በድምሩ በ23 ሜዳሊያዎች ስትጨብጥ፣ ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ፣ 2 ብር እና 1 ነሐስ በድምሩ በ5 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ሆናለች፡፡ ፈረንሣይ በ1 ወርቅ፣ 1 ብርና 2 ነሐስ ሦስተኛነትን ይዛለች፡፡
የኢትዮጵያ ውጤት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሲያደርጋት የቅርብ ተፎካካሪዋ ኬንያ በ800 ሜትርና በ3000 ሜትር ሁለት ነሐስ ሜዳሊያዎች ብቻ በማግኘት 25ኛ መውጣቷ አነጋግሯል፡፡ በመጀመሪያዎቹ 10 ባለደረጃዎች የገባችው ሌላዋ የአፍሪካ አገር ቡሩንዲ ስትሆን አንድ ወርቅና አንድ ብር በማግኘት አምስተኛ ሆናለች፡፡