ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ምሁራን ጋር በተገናኙበት የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ መግባባትና በበርካታ አገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከምሁራኑ ጋር በጉባኤ አዳራሽ ባደረጉት ውይይት ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ፣ የወጣቱን አቅም የሥራ ተነሳሽነት እየገደለ የሚገኘውና በአገሪቱ እየተንሰራፋ የሚገኘውን ጫት መቃም ለማስወገድ መንግሥት ምን አስቧል? በግልዎስ ያልዎት አቋም ምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡ ጫትን እንደማይደግፉ፣ እንደማይቃወሙም ያመላከቱት አቶ ኃይለ ማርያም አያይዘው በአጽንዖት የተናገሩበት ፍሬ ጉዳይም አለ፡፡ ‹‹ጫት ለመንግሥት ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተጨማሪ ሃይማኖታዊ መልክም ይይዛል፡፡ ስለዚህ በጥቅሙና ጉዳቱ ላይ ኅብረተሰባዊ ክርክር ያስፈልጋል፡፡ የማውቃቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች መምህራን ጊዜያቸውን ጫት ላይ የሚያጠፉ አሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ ባልተቀየረበት ሁኔታ ሾፌሩን ለመቀየር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡››