በአራት ክልሎች በአማራ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ በደረጃ 3 እና 4 የግብርና ትምህርት በሚሰጡ ኮሌጆች የአይሲቲ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ሊሰጥ ነው፡፡ በትግራይ ክልል በውቅሮና በወረታ አካባቢ ተሞክሮም ጥሩ ውጤት ማስገኘቱን ዲጂታል ግሪን ፋውንዴሽን ቅዳሜ መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ አስታውቋል፡፡
ለ4 ዓመታት በሚቆየው ይህ ፕሮግራም 14 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ ተልዕኮውም አይሲቲን በመጠቀም ወጥ የሆነ መረጃ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ ፕሮግራሙን ከአራት ዓመታት በኋላ ግብርና ሚኒስቴር እንደሚቀበለውና በሁሉም ክልሎች ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ የግብርና ልማት ሠራተኞችን በአይሲቲ ቴክኖሎጂ በማብቃት እና ጠቃሚ መረጃዎችን ለገበሬው እንዲያስተላልፉ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ላይ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኗል፡፡
በኢትዮጵያ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ወንደሰን ኃይሉ እንደሚሉት ትምህርቱ የሚያተኩረው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም፣ ቪዲዮዎችን ቀርፆ እና አዘጋጅቶ ማሠራጨት የሚቻልበትን ቴክኒክ ላይ ነው፡፡
ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ግብርና በአራቱ ክልሎች እንደሚገኝ ይህም ለፕሮጀክቱ ትግበራ ተመራጭ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት አቶ ወንደሰን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በክልሎቹ በሚገኙ 65 ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች በቪዲዮ የታገዘ ሥልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡ የልማት ሠራተኞችም ሥልጠናዎቹን ለማዘጋጀት እንዲችሉ በአይሲቲ ሙያ ይሠለጥኑ ዘንድ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ላይ ለሚጀመረው የትምህርት ፕሮግራም በየኮሌጁ 4000 የሚሆኑ ካሜራዎችና ፕሮጀክተሮች መሠራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙ ከተለያዩ የምርምር ተቋማት የተመረጡ፣ በግብርና የታገዙና የፀደቁ ፕሮጀክቶችን ባዮ ፈርትላይዘር አጠቃቀም፣ የመሬት አሲድነትን መቀነስ የሚቻለበትን መንገድና በመሳሰሉት ዙሪያ በክልሎቹ የሚገኙ አርሶ አደሮች ሲያስተምር ቆይቷል፡፡
እንደ አቶ ወንደሰን ገለጻ ቀድሞ በነበረው አሠራር አንድ የልማት ሠራተኛ በአንዴ የሚሰጠው ሥልጠና የሚደርሰው ለ15 አርሶ አደሮች ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በአንዴ 65 አርሶ አደሮችን መድረስ እንደሚቻል በክልሎቹ በተደረገው ሙከራ ተረጋግጧል፡፡
በአንድ በተወሰነ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች በአካባቢው በሚገኝ ሞዴል አርሶ አደሮቹ መማር መቻላቸው ፕሮግራሙን ይበልጥ ውጤታማ ማድረጉን ‹‹አርሶ አደሮቹ የልማት ሠራተኞች ከሚሰጧቸው ሥልጠና ይልቅ እርስ በርስ ሲማማሩ ነገሮችን በይበልጥ ይረዳሉ፡፡ በዚህም ፕሮጀክቱ የልማት ሠራተኞቹ ቪዲዮውን ቀርጸው እንዲያዘጋጁና አርሶ አደሩ ራሱ እንዲያስተምር አድርጓል›› በማለት አርሶ አደሩን ያማከለው ፕሮግራሙ ውጤታማ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አያይዘውም ከዚህ ቀደም 15 ኩንታል ስንዴ ያመርቱ የነበሩ አርሶ አደሮች አሁን ላይ እስከ 80 ኩንታል ስንዴ እያመረቱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
የአዳ ወረዳ የልማት ሠራተኛው አዲሱ አሰፋ እንደሚለው ከዚህ ቀደም ሥልጠና ይሰጡበት በነበረው መንገድ አርሶ አደሩን ለማሳመን ይቸገሩ እንደነበር፣ አርሶ አደሮቹ በልማት ሠራተኞቹ አቅም ሊመለሱ የማይችሉ ውስብስብ ጥያቄዎች ያነሱ እንደነበረ እና በዚህም ጭቅጭቅ ይፈጠር እንደነበር አስታውሶ በቪዲዮ የታገዘውን ሥልጠና መስጠት ከጀመሩ በኋላ ችግሮቹ መቀረፋቸውን ያስረዳል፡፡
ፕሮግራሙ ለምርታማነት የላቀ ፋይዳ እንዳልው አሠራሩን ለማስፋፋትም መንግሥት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የግብርና ኤክስቴንሽን ምክርና ሥልጠና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ገዛኸኝ ጠቁመዋል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአግሪካልቸር ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ እና ከኢትዮጵያ የቲቬት አጀንሲ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ፣ ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላም በሌሎች ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የተለየ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚሠሩ አቶ ወንደሰን ተናግረዋል፡፡