Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልደራሲና አዘጋጅ ደመረ ጽጌ (1959-2008)

ደራሲና አዘጋጅ ደመረ ጽጌ (1959-2008)

ቀን:

‹‹ጉዲፈቻ›› በ1999 ዓ.ም. ለዕይታ የበቃ ፊልም ነው፡፡ ወቅቱ እንዳሁኑ ፈልሞች የተበራከቱበት አልነበረም፡፡ ዛሬ ላይ የፊልም ቁጥር ጨምሮ ርዕስ ለማስታወስም ሊከብድ ይችላል፡፡ የ‹‹ጉዲፈቻ›› ደራሲ ደመረ ጽጌ በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ፈልሙ ጥሩ ምላሽ ያገኘበት ሥራው እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን የተመልካች ብዛትም ያስታውሳል፡፡ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ መሠረት መብራቴና ተስፉ ብርሃኔ በመሪነት የተወኑበት ‹‹ጉዲፈቻ›› የደመረ ለመጀመሪያ ጊዜ በሲኒማ ቤት ስክሪን የቀረበ ፊልሙ ሲሆን፣ ከዛ ቀደም የሠራቸው ሁለት ፊልሞች በቪኤችኤስ የቀረቡ ነበሩ፡፡

ደራሲና አዘጋጅ ደመረ ገጸ ታሪኩ እንደሚያመለክተው፣ በአዲስ አበባ በተለምዶ ቡልጋሪያ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከእናቱ ወ/ሮ አየለች መስፍንና ከአባቱ አቶ ጽጌ እርገጤ በ1959 ዓ.ም. ተወለደ፡፡ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ወንድማማቾች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአብዮት ቅርስ (ጂስኤ) አጠናቀቀ፡፡ ከፈረንሣይ መንግሥት በተገኘ ነፃ ትምህርት ዕድል ኤኮል ቴክኒክ የተባለ ትምህርት ቤት ገብቶ በምሕንድስና በ1984 ዓ.ም. ተመረቀ፡፡

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ ነበር ጎን ለጎን የሥነ ጽሑፍ ችሎታውን ማዳበር የጀመረው፡፡ በታዳጊነቱ ብዙ የሥነ ጽሑፍ ውድድሮችን ተካፍሏል፡፡ መምህራኑም ያበረታቱት ነበር፡፡ በተመረቀበት የሲቪል ኢንጂነሪንግ ሙያ ግን አልሠራም፡፡ ከሲቪል ኢንጂነሪንግ ሙያው ተፋታ፡፡ በኪነጥበብ ፍቅር ወደቀ፡፡ ከኪነ ጥበብ ጋርም ተሞሸረ፡፡ ከኪነ ጥበብ ጋር ኖረ፡፡

በ1985 የመጀመሪያ የቪኤችኤስ ሥራው ከነበረው ‹‹የነቀዘች ሕይወት›› ፊልም በኋላ በ1989 ዓ.ም. ‹‹ሥጋ ያጣ መንፈስ››፣ በ1992 ዓ.ም. ‹‹ስውር ችሎት››፣ በ1994 ዓ.ም. ‹‹ጉዲፈቻ››፣ በ1997 ዓ.ም. ‹‹ንጉሥ ናሁሰናይ››፣ በ2002 ዓ.ም. ‹‹ስደት›› እና በ1987 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለተመልካች ቀርቦ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎ የነበረው ‹‹ፍሬሕይወት›› የተሰኘ ተውኔት ጽፏል፡፡

አጫጭር የሬዲዮና የቴሌዥን ድራማዎችም በማቅረብ ይታወቃል፡፡ የደመረ ሰባተኛ ፊልም ‹‹አብስትራክት›› ሰኔ 1  ቀን 2007 ዓ.ም. በአዶት ሲኒማ ተመርቆ አሁንም በመታየት ላይ ነው፡፡ ‹‹ዓለማችን በማይታዩ ግን አብረውን በሚኖሩ ምስጢሮች የተሞላት ነች›› የሚል ኃይለ ቃል በያዘው ልብ አንጠልጣይ ፈልሙ ኤልሳቤጥ መላኩ፣ ቃል ኪዳን ጥበቡና ኃይለማርያም ሰይፉ በዋናነት ተውነውበታል፡፡ ባለሙያው ብዙ ጊዜ በአንድ ፊልም ካስት ካደረጋቸው ተዋንያን ጋር ደግሞ ይሠራ እንደነበር ፊልሙ በተመረቀበት ወቅት ለሪፖርተር ተናግሮ ነበር፡፡

ደመረ ‹‹በሬ ካራጁ›› የተሰኘ የመድረክ ተውኔት ድርሰትና ዝግጅቱን አጠናቅቆ ለማስመረቅ ተፍ ተፍ እያለ ባለበት ሰሞን ነው ሕይወቱ ያለፈው፡፡ የሕይወት ታሪኩ እንደሚያስረዳው፣ ለአጭር ቀናት ታሞ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ በተወለደ በ49 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የጥበብ ባለሙያዎችና አድናቂዎቹ በተገኙበት ቅዳሜ መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...