Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ማይክራፎናችን የሌሎች ሰዎችም ነው›› ድምፃዊት ወይና

‹‹ማይክራፎናችን የሌሎች ሰዎችም ነው›› ድምፃዊት ወይና

ቀን:

ወይና በሚለው መጠሪያዋ የምትታወቀው ወይነአብ ወንደሰን የተወለደችው ኢትዮጵያ ሲሆን፣ በሕፃንነቷ ከእናቷ ጋር ወደ አሜሪካ አቅንታ ኑሮዋን እዛው አደረገች፡፡ የሙዚቃ ፍቅር ያደረባት በልጅነቷ ሲሆን፣ በትምህርት ቤትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለችም በሙዚቃ ትሳተፍ ነበር፡፡ ስቲቪ ዋንደር፣ ቢሊ ሆሊደይ፣ ዶኒ ሀታዌይ፣ ኤሪካ ባዱናና ሎረን ሂል መነሻዎቿ ከሆኑ ድምፃውያን መካከል ናቸው፡፡ አሁን ከስቲቪ ወንደር ጋር ቱር በማድረግ ሙዚቃ ታቀርባለች፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ በእንግሊዝኛና ስፒች ኮሙዩኒኬሽን ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ ወደ ኋይት ሐውስ አምርታ የቢል ክሊንተን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል (በስፒች ራይተርነት) ለሦስት ዓመታት ሠርታለች፡፡

የዘወትር ህልሟ ድምፃዊት መሆን ነበርና ኋይት ሐውስን ለቃ ወደ ሙዚቃው ገባች፡፡ በአጭር ጊዜ ሙዚቃዎቿ በቢል ቦርድ የሙዚቃ ደረጃ ሰንጠረዥ ከፍተኛ ቦታ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ‹‹ላቪንግ ዩ›› የተሰኘው የማይኒ ኒፕተንን ሙዚቃ ዳግም ሠርታ የግራሚ ዕጩ ለመሆን በቃች፡፡ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞችና ፕሮዲውሰሮች ጋር የሠራችው ወይና፣ ‹‹ሞመንትስ ኦፍ ክላሪቲ ቡክ ዋን›› (እ.ኤ.አ. በ2004)፣ ‹‹ሀየር ግራውንድ›› (እ.ኤ.አ. በ2008) እና ‹‹ዘ ኤክስፓትስ›› (እ.ኤ.አ. በ2013) የተሰኙ አልበሞችን ለቃለች፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በነበራት ቆይታ በሙዚቃዎቿ ዙሪያ ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራታለች፡፡           

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ የመጣሽበት ጉዳይ ምን ነበር?

ወይና፡- የመጣሁት ማርዮት ሆቴል ለመዝፈን ነበር፡፡ ከአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ጀምሮ እስከ ቫለንታየንስ ደይ ድረስ ሠርቻለሁ፡፡ አሁን የፎቶና የቪዲዮ ፕሮጀክት ጀምሬያለሁ፡፡ በእናቴ የወጣትነት ዘመን የነበረው ትውልድ አኗኗር ይስበኛል፡፡ ከውጪ የሚያዩትን ፋሽን ከራሳቸው ዘዬ ጋር የሚያደባልቁ ፋሽን ተከታዮች ነበሩ፡፡ እነሱን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ፎቶግራፎቹ ጥንታዊነት እንዲኖራቸው የተነሱት ፒያሳ አካባቢ ነው፡፡ የ1960ዎቹን የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ገጽታ ያንፀባርቃሉ፡፡ ለወደፊት በሙዚቃዎቼ ወይም በማኅበረሰብ ድረ ገጾች እጠቀምባቸዋለሁ፡፡ ስለኢትዮጵያ ሙዚቃም ትምህርት እየወሰድኩ ነው፡፡ ልጆቼን ከባህላቸው ጋር የማስተዋወቅ ዓላማም ይዤ ነው የመጣሁት፡፡ ልጄ ኢትዮጵያ ስትመጣ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ስለዚህ አመጣጤ ሙያዊም ግላዊም ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ የወጣሽው በሕፃንነትሽ ነው፡፡ በአሜሪካ ስትኖሪ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር የሚያስተሳስሩሽ ነገሮች ነበሩ?

ወይና፡- ቤታችን ሁሌም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ይከፈት ነበር፡፡ ያደግኩትም የኢትዮጵያን ሙዚቃ እየሰማሁ ነው፡፡ የምወዳቸውን አስቴር አወቀና ጂጂን እሰማ ነበር፡፡ ሙዚቃው እንደተዋሀደኝና በሥራዎቼ እንደሚንፀባረቅ የተገነዘብኩት ግን በቅርቡ ነው፡፡ የጀመርኩት በአርኤንድቢና ሶል ሙዚቃ ነው፡፡ ራሴን የማየው የአሜሪካ ሙዚቃ እንደምትጫወት ኢትዮጵያዊት ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን በደምስሬ ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነቴ ለኔ ራሱ ሳይታወቀኝ በሙዚቃዎቼ እንደሚወጣ አወቅኩ፡፡ ስለዚህ ያንን ማንነት በይበልጥ እያጠናሁት ነው፡፡ ቶሮንቶ በተሠራው የመጨረሻው አልበሜ ላይ ሁለት ኢትዮጵያውያን ከሚገኙበት ባንድ ጋር ሠርቻለሁ፡፡ ከስቲቪ ዋንደር ጋር ቱር ሳደርግ የምዘፍናቸው ነገሮች ይሰጠኛል፡፡ እሱ ባሳየኝ መልኩ ስዘፍን እንኳን ኢትዮጵያዊ ድምፅ እንዳለኝ ይነግረኛል፡፡ ይህን እኔ ራሴ አላውቅም ነበር፡፡ የማንነቴ አካል ስለሆነ ሳላውቀው የማደርገው ነበር፡፡ የሚያስደስተው ነገር አውቄው የበለጠ እያጠናሁት መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተማሪ ሆኛለሁ፡፡ አሁን ብዙነሽ በቀለንና ከዘመዶቼ የወሰድኳቸውን ሌሎችም የድሮ ባህላዊ ሙዚቃዎች እያዳመጥኩ ነው፡፡ በቅርቡ ወደ አሜሪካ ብሄድም ተመልሼ እመጣለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሜሪካ እንደምትኖር ጥቁር ሴት ስትመለከችው የኢትዮጵያ ሙዚቃም ሌሎች ሙዚቃዎችም በአስተዳደግሽ ምን ዓይነት ተጽእኖ ነበራቸው?

ወይና፡- ሙዚቃ ማምለጫዬ ነበር፡፡ ደስታ፣ ሐዘን፣ ግራ መጋባት ወይም ሌላ ስሜት መግለጽ ስፈልግ ሙዚቃን እጠቀማለሁ፡፡ ሙዚቃ ምቾት ይሰጠኛል፡፡ ቤታችን ያን ያህልም ሙዘቃዊ ነበር ለማለት ባልችልም ከልጅነቴ ጀምሮ በሙዚቃ እሳብ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ እንደ መዝናኛና ስሜትን መግለጫ ብቻ ነበር፡፡ እያደግኩ ስሄድ ግን የምወዳቸውን ዜማዎች ከግላዊ ታሪኮቼ ጋር እያስተሳሰርኩ የበለጠ ራሴን በሙዚቃ መግለጽ ጀመርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- በቢል ክሊንተን አስተዳደር ሥር ለሦስት ዓመት ኋይት ሐውስ ውስጥ ሠርተሻል፤ ተሞክሮሽ ምን ይመስል ነበር?

ወይና፡- በጣም አስደሳች ነበር፡፡ ሰዎቹ በአጠቃላይ ጎበዞች ነበሩ፡፡ ብዙ መሥራት ይጠበቅብን ነበር፡፡ ሥራው በጣም አስፈላጊ ስለነበር የልዩ ነገር አካል እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር፡፡ በክሊንተን አመራር በነበሩ ብዙ ነገሮች አምን ነበር፡፡ ስኬታቸው ያኮራኝ ነበር፡፡ የሕይወቴ ልዩ ወቅት ነበር፡፡ ከኮሌጅ እንደወጣሁ ሕይወቴን የምመራበትና በዓለም ላይ ለውጥ የማመጣበትን መንገድ አስብ ነበር፡፡ ኋይት ሐውስ ገብቼ ልዩ ችሎታ ካላቸው ሰዎች ጋር መሥራት መቻሌ ብዙ አስተምሮኛል፡፡ የምንሠራው ነገር በሙሉ ፕሬዚዳንቱን ስለሚወክል ፍፁምነት ይጠበቅብን ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሰው ነንና ስህተት ሊፈጠር ቢችልም ስህተት እንዳይፈጸም የሚከላከል ጠንካራ ሥርዓት ነበር፡፡ ከቆይታዬ የወሰድኩት ትልቁ ትምህርት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ማለም ያለውን ዋጋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኋይት ሐውስ ሳትገቢ በፊት ኮሌጅ ውስጥ እያለሽ ኳየር መሥርተሽ ነበር፡፡ ለሙዚቃ ሕይወትሽ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

ወይና፡- ዩኒቨርሲቲ እያለሁ በሜሪላንድ ጎስፔል ኳየር ውስጥ እዘፍን ነበር፡፡ ከኳየሩ አራት ሆነን ወጥተን በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ መዝፈን ጀመርን፡፡ በዓለም ላይ ካሉ ድንቅ ድምፃውያን መካከል የወንጌል ዘማሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ችሎታ ካላቸው ድምፃውያን ጋር እሠራ ስለነበር ብዙ ተምሬበታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከኋይት ሐውስ ወጥተሽ ከፖለቲካ ወደ ሙዚቃ ያደረግሽው ሽግግር ምን ይመስል ነበር?

ወይና፡- ኋይት ሐውስ እየሠራሁ በነበረበት ወቅት ወደ ሁለት ዓመት ለሚሆን ጊዜ ተነሳሽነቴ እየቀነሰ ነበር፡፡ የተማርኩትን ጥቅም ላይ እያዋልኩ ቤተሰቦቼንም እያኮራሁ እንደነበር ቢሰማኝም ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ምሉዕነት ሊሰማኝ አልቻለም፡፡ የልቤን ፍላጎት ለመከተልና ያንን ሥራ አቋርጦ ለመውጣት ጊዜ ወስዶብኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ህልሜ የሚሳካ አልመሰላቸውም፡፡ እኔ ግን ፍላጎቴ ከፍርኃቴ በለጠና ወደ ሙዚቃ ገባሁ፡፡ ኋይት ሐውስ ሳለሁ ሙዚቃ መጻፍ፣ ከፕሮዲውሰሮች ጋር መሥራትና ዓርብ ምሽት በአቅራቢያዬ ባሉ የምሽት ክለቦች መዝፈንም ጀመርኩ፡፡ ከኋይት ሐውስ ከወጣሁ በኋላ በምን መንገድ መሥራት እንዳለብኝ ባቅድም፣ ስወጣ ትክክለኛውን የፈጠራ መንገድ እስካገኝ ወደ ሁለት ዓመት ወስዶብኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እ.ኤ.አ. በ2009 ‹‹ላቪንግ ዩ›› በተሰኘው ዘፈን የግራሚ ዕጩ ሆነሽ ነበር፡፡ ዕጩነትሽ በሙዚቃ ሕይወትሽ ያመጣው ለውጥ አለ?

ወይና፡- ትልቅ ነገር ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያት በዛ ደረጃ ታዋቂ ለመሆን ከጀርባዬ ግዙፍ ድርጅት እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ያምኑ ነበር፡፡ እኔ የምሠራው ግን በግሌ ነበር፡፡ በግሌ እየሠራሁ ያን ያህል እውቅና ማግኘቴ ለእኔም ከእኔ ጋር ለሚሠሩም ትልቅ ዜና ነበር፡፡ አልበሜን ሳስገባ አትልፊ፣ አትሞክሪ ያሉኝ ነበሩ፡፡ ይቻላል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ በእኔ እምነት ዕጩ መሆን የቻልኩት አዘጋጆቹ ለአዳዲስ ድምፃውያን ጆሯቸውን በመስጠታቸው ነው፡፡ ሙዚቃው በጣም ብዙ የተለፋበት ስለነበረ ጥሩ ነገር ይዞ መጥቷል፡፡ ዕጩ መሆኔ ለእኔ ተስፋ ለሥራዬ ደግሞ ምስክር ሆኗል፡፡ በኢንዱስትሪው ካሉ ትልልቅ ባለሙያዎች ጋር ለመሥራትም መንገድ ከፍቶልኛል፡፡ አሁንም እየረዳኝ ነው፡፡ ቀጣይ ግቤ ለመታጨት ብቻ ሳይሆን ለማሸነፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ማማስ ሰክሪፋይስ››ን የዘፈንሽው ለናትሽ ነው፡፡ ‹‹ማይ ላቭ›› የተሰኘው ዘፈን የሴቶችን ጥቃት ይቃወማል፡፡ ሴቶች ዕለት ከዕለት የሚገጥሟቸውን ፈተናዎችና የቤት ውስጥ ጥቃትን በመታገል ረገድ ሙዚቃዎችሽ ምን ሚና አላቸው ብለሽ ታምኛለሽ?

ወይና፡- ለእኔ የሙዚቃ ዓላማ ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መስጠት ነው፡፡ እንደ ሙዚቃ ግጥም ጸሐፊነቴ ሰዎች ያላነሱትን ነገር ከተለየ እይታ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃት ሲደርስ እንደ ሴትነቴ ስለጉዳታቸው መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ግንዛቤ መፍጠርና ድምፄን ለጠቃሚ ነገር ማሰማት እሻለሁ፡፡ ‹‹ማይ ላቭን›› የጻፍኩት ኤሰንስ ሜጋዚን ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡ ዲሲ አቅራቢያ በምኖርበት አካባቢ ስላለው የሴቶች ጥቃት ያወራል፡፡ አካባቢው ጥሩ ገቢ ያላቸው ጥቁሮች የሚኖሩበት ነው፡፡ ከውጪ ሲታይ ደስተኛ ማኅበረሰብ ይመስላል፡፡ እውነታው ግን ከሜሪላንድ ከፍተኛ የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት የሚደርስበት አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ ላይ ላዩን ሁሉም ነገር የተሟላላት የምትመስል ነገር ግን በውስጧ እንደ አብዛኛዎቹ ሴቶች እየተሰቃየች ስላለች ሴት ሕይወት ለመናገር የተሠራ ሙዚቃ ነው፡፡ ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር በተያያዘ በግሌ የደረሰብኝ ነገር የለም፡፡ ታሪኩ ግን የጥቁር አሜሪካውያንን ትግል ያሳያል፡፡ አንድ ምሽት ያረፍኩበት ሰሚት አካባቢ ጩኸት ሰማሁ፡፡ በረንዳ ላይ ስወጣ አንድ ሴት ከባለቤቷ ጋር እየተጨቃጨቀች ነበር፡፡ በጣም ስለጮኸች ብዙ ሰው ሰምቶ ወጥቶ ነበር፡፡ ባልየው ሰዎች ሲመለከት ትቷት ሄደ፡፡ ቤቷ ገብታ ለሊቱን በሙሉ ስታለቅስ አደረች፡፡ ኢሰንስ ሜጋዚን ጋር ካነበብኩት ጋር ቢመሳሰልም በተለየ ባህልና የኑሮ ደረጃ መከሰቱ ያስገርማል፡፡ በየትኛውም ቦታ ያሉ ሴቶች የሚገጥማቸው ችግር እንደሆነ አስታውሶኛል፡፡ ብዙ እንዳልተጐዳችና ልጆችም እንደሌሏቸው ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ምንም አይደለም ብለው ተበተኑ፡፡ ምንም አይደለም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ሴትየዋ ተጐድታ ነበር፡፡ ስለነዚህ ነገሮች ማውራት አለብን፡፡ ሙዚቃ በዚህ ረገድ ሊጠቅም ይችላል፡፡ ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ወይም ሌላ የኪነ ጥበብ ሥራ ለውጥ ለማምጣትና የኅብረተሰቡን አመለካከት ለመለወጥ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ያላግባብ መሣሪያ ስለመጠቀምና የፍትሕ ሥርዓት መዛባት ከዘፈንሽው ዘፈን ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት ሒውስተን ውስጥ ታስረሽ ነበር፡፡ የሙዚቃው ይዘትና የመታሰርሽ መገጣጠም ምን ያመለክታል? መታሰርሽ ያሳደረብሽ ተጽእኖ አለ?

ወይና፡- ‹‹ቢሊ ክለብ›› የተሰኘና የፖሊሶች ርኅራኄ አልባነት ላይ ያተኮረ ዘፈን አለኝ፡፡ ዘፈኑን ሳቀርብ የመሣሪያ መያዣ እጠቀማለሁ፡፡ መያዣውን ቦርሳዬ ውስጥ አስቀምጬ ረስቼው ከሒውስተን ወደ ቦስተን ልሄድ ስል ተያዝኩ፡፡ ሌላ ስቴት ቢሆን መያዣውን ይጥሉትና ያሳልፉኝ ነበር፡፡ ቴክሳስ ከመሣሪያ ጋር በተያያዘ ውስብስብ ፖለቲካ ያለበት አካባቢ ስለነበር ታሰርኩ፡፡ አጋጣሚው በተወሰነ መልኩ አመለካከቴን ቀይሮታል፡፡ አንዳንዴ ሰዎች የሕግ ሥርዓት ተዛብቶ ወይም በፖሊስ ጥቃት ካልደረሰባቸው ስለችግሩ ጥልቀት አይገነዘቡም፡፡ ምን ያህል አስፈሪና ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ አይረዱም፡፡ በስህተት የአንድ ሰው ሕይወት አቅጣጫ ሊለወጥ ሕይወትም ሊጠፋ ይችላል፡፡ አጋጣሚው ይኼን አሳውቆኛል፡፡ ድንጋጤው እስኪለቀኝ ጊዜ ወስዶብኛል፡፡ ስለከባድ ጉዳዮች የማወራ ከሆነ ከባድ ነገሮችን መጋፈጥ እንዳለብኝም አውቄያለሁ፡፡ አጋጣሚው ቢያምም ጠንካራም አድርጐኛል፡፡ የእውነት ጥንካሬዬንና ድክመቴን አውቃለሁ፡፡ በዚህ ዓለም ታላቅ ነገር ማድረግ ከፈለግኩ ራሴን ማወቅ አለብኝ፡፡ በከባድ ጫናዎች ሥርም ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ውጪ የኢትዮጵያ ያልሆነ ሙዚቃ የሚሠሩ ድምፃውያን ሲነሱ የአገሪቱም ስም ተያይዞ ይጠራል፡፡ ታዋቂም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳወቅ ድምፃውያኑን መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነው ወይስ ሀገር ውስጥ ያሉ ሙዚቀኞች ላይ መተኮር አለበት?

ወይና፡- ሁለቱም ያስኬዳል፡፡ እዚህ ሀገር ባሉ ድምፃውያን ችሎታ እገረማለሁ፡፡ ነገር ግን ሰፊ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ዕድሉን ያገኘነው ባለሙያዎች መጥተን መሥራትና ያገኘነውን መመለስ አለብን፡፡ በዚህ መንገድ የባህሉን ዕድገት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እኛንም የሚያስተምሩን ነገር ይኖራል፡፡ ቱባ ሙዚቃችን ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህን ለመጠበቅና ለማሳደግ የሚረዱ መንገዶች አሉ፡፡ ከሌሎች ሙዚቃ ዓይነቶች ጋር የሚዋሀድበትና የሚጠናበትንም መንገድ መፍጠር ይቻላል፡፡ መንገዱ ውጪ ሆኖ ሌላ ዓይነት ሙዚቃ መሥራት ወይም እዚህ ሆኖ የኢትዮጵያን ኦሪጅናል ሙዚቃ መሥራት ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚሠሩት ሙዚቃዎች እንዲደመጡ የተመቻቸ መንገድ አለ ብለሽ ታስቢያለሽ?

ወይና፡- በማኅበረሰብ ድረ ገጽ አማካይነት መንገዱ አለ፡፡ ኦሪጅናል የሆነ ሙዚቃ ከተሠራ የየትኛውም ድምፃዊ ሥራ ሊሰማ ይችላል፡፡ አድማጮች ድምፃውያን በተለያየ የሙዚቃ ዘዬ እንዲመራመሩና አዲስ ነገር ይዘው እንዲወጡ ዕድሉን በሰጧቸው ቁጥር ፈጠራ ይጐለብታል፡፡ እንደ ጃኖ ባንድ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከተለያዩ ዘዬዎች ጋር በመቀላቀል የሚሠሩ ድምፃውያን ያስደስታሉ፡፡ አድማጮች ለዚህ ዓይነት ሙዚቃ ጆሮ እስከሚሰጡ ጊዜ ሊወስድ ግን ይችላል፡፡ የአርቲስቶች ነፃነት ካለ አርቲስቶቹ ያድጋሉ ሙዚቃውም ለማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ የወጣሽው በልጅነትሽ ነው፣ ከኢትዮጵያዊ ማንነትሽና ከባህሉ ጋር ትስስር እንዳለሽ ይሰማሻል?

ወይና፡- አዎ፡፡ እናቴ በጣም ባህላዊ ሴት ናት፡፡ ያሳደገችኝም በዛ መንገድ ነው፡፡ አሁን ስትታይ ከ30 ዓመት በላይ አሜሪካ የኖረች አትመስልም፡፡ ባህሏና ዓለምን የምታይበት መንገድ አልተለወጠም፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃዎችሽ ምን ያህል ሕይወትሽን ያንፀባርቃሉ?

ወይና– ለእኔ አስደሳቹ ነገር ያ ነው፡፡ የሕይወት ታሪኬና የሌሎችንም ተሞክሮ በሙዚቃዬ እገልጻለሁ፡፡ አንዳንዴ ሙዚቃዬን ሰምቼ ጆርናሎቼን ሳነብ በማስበውና በተዘፈነው ነገር መመሳሰል እገረማለሁ፡፡ ሙዚቃ ስሜቶቼን የምጋፈጥበትና የማገግምበት መሣሪያ ነው፡፡ የሙዚቃ ሥራዎቼን በቁም ነገር እንደምወስዳቸው ሁሉ እዝናናባቸዋለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- የአብዛኞቹን ዘፈኖችሽን ግጥም የጻፍሽው አንቺ ነሽ፡፡ ግጥም ጸሐፊ መሆንሽ የምትፈልጊውን ሙዚቃ ለመሥራት ነፃነት ሰጥቶሻል?

ወይና፡- ለአንድ ድምፃዊ ሌሎች ሰዎች ግጥም ቢጽፉለት ችግር የለውም፡፡ በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑ ድምፃውያን ዕውቅ ሥራዎቻቸው በሰው የተጻፉ ናቸው፡፡ ስቲቪ ወንደር ምርጥ ግጥም ጸሐፊ ቢሆንም ከሌሎች ጸሐፊዎች ጋርም በጥምረት ይሠራል፡፡ ራስን ለተለያዩ ሐሳቦች ክፍት ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ የምመለከተውን ነገር በደንብ ለመግለጽ ስለሚያመቸኝ ግጥም መጻፉን እወደዋለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ለአፍሪካውያን ሴቶች መታሰቢያ የሚሆን ዘፈን እንድዘፍን ተጠይቄ የምፈልገውን ዓይነት ዘፈን አጣሁ፡፡ ያኔ ግጥሞቼን ራሴ መጻፍ እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ የምወደውና እኔን የሚነካኝ ቅንብር፣ ዜማና ግጥም ካገኘሁ ከመሥራት ወደኋላ አልልም፡፡ ማሪዮት ስሠራ የብዙ ድምፃውያንን ዘፈኖች ሠርቻለሁ፡፡ ከዚህ በፊት እንደዚህ በስፋት ሠርቼ አላውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን ግሩምና የሚያነሳሱኝ ሙዚቃዎች ካገኘሁ መሥራት እንደሚያስደስተኝ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ለዳዊት መለሰና በአቅራቢያዬ ላሉ የጃዝና አርኤንድቢ ሙዚቀኞችም ግጥም ጽፌ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ አሁን የሁለት ሴት ልጆች እናት ነኝ፡፡ እንደ ቀድሞ ለሥራዬ በተለያዩ አገሮች መዘዋወር ብዙም ስለማልፈልግ ጽሑፍ ላይ ማተኮሩ ያስደስተኛል፡፡ ልጆቼ ያስደስቱኛል፡፡ የሥራና ቤተሰብን ሚዛን ጠብቆ የመሄድ ነገር ፈታኝ ነው፡፡ የባለቤቴና የእናቴ እገዛ ዘወትር አይለየኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከተወሰኑ ሙዚቃዎች ጋር ታቀላቅያለሽ፡፡ በቪዲዮ ክሊፕሽም የኢትዮጵያን አኗኗር ለማንፀባረቅ ትሞክሪያለሽ፡፡ ለምን?

ወይና፡- በመጠኑ እሞክራለሁ፡፡ የመጨረሻ አልበሜ ላይ ‹‹አስ ሎንግ አስ ዩ ኖ›› የተሰኘ ዘፈኔ ላይ አሜሪካ የሚኖረው ሙዚቀኛ ሰጠኝ መሰንቆ ተጫውቷል፡፡ በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ ‹‹ታይም ዊል ካም›› የሚለው ሙዚቃ ላይ ከእውቁ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ንግግር የተወሰደ ስንኝ አለ፡፡ አልበሜ ላይ ከቴዎድሮስ ታደሰ ጋር የተጣመርኩበት ሥራም አለ፡፡ በቀጣይም ብዙ ተመሳሳይ ሥራዎች እንደሚኖሩኝ አምናለሁ፡፡ አሁን ለመናገር ጊዜው ገና ቢሆንም በአማርኛ ብቻ ከሚዘፍኑ ሙዚቀኞች ጋር በጥምረት የመሥራት ዕቅድ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነቴ የእኔነቴ መሠረት ነው፡፡ እንደ አርቲስት ሙሉነት የሚሰማኝ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ማንነቴን መግለጽ ስችል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ጌጣጌጥ እንደመጠቀም ቀላል በሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ማማስ ሰክሪፋይስ››ን መድረክ ላይ ሳቀርብ የኢትዮጵያን ባህል የሚያንፀባርቁ ነገሮች አሉት፡፡ የማንነቴ አካል ስለሆነ ማካተቴ ያስደስተኛል፡፡ ከሰዎችም ጥሩ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ሙዚቀኛ ለሥራዎችሽ የሚያነሳሳሽ ምንድን ነው?

ወይና፡- ኢፍትሐዊነትና የፍርድ መዛባት ይረብሹኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊዋጥልኝ ያልቻለው በመደብ ልዩነት ሳቢያ ያለው መከፋፈል ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ለማውራት ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ የኢትዮጵያን ባህልና ልብስ ብቻ ወደን ለሌሎቹ ነገሮች ትኩረት አለመስጠት አይቻልም፡፡ በምርጫ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ ድምፅ ለሌላቸው ሰዎች ድምፅ መሆን የሁሉም ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ማይክራፎኔ የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ ማይክሮፎናችን የሌሎች ሰዎችም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጨረሻ አልበምሽ ‹‹ኤክስፓትስ›› ላይ የኤርትራ፣ የኬንያ፣ የህንድና የሌሎችም ሀገሮች ሙዚቀኞች መሳተፋቸው ለአልበሙ ምን ጨምሮለታል? በተያያዥም ‹‹ኤክስፓትስ›› የሚለው አገላለጽ ስደተኛነትን ያንፀባርቃል፡፡ አንቺ መኖሪያዬ የትምይውና ለማንነትሽ የሚቀርብሽ ቦታ የቱ ነው?

ወይና፡- አልበሙ የተለዩ ባህሎች ተንፀባርቀውበታል፡፡ በእያንዳንዳችን ፍላጐትና ተሞክሮ ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ናቸው፡፡ በየባህሉ መካከል ያለው ትስስር ልዩ ነገር ፈጥሯል፡፡ ሙዚቀኞቹ ቶሮንቶ ውስጥ እንደሚኖሩ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካሎችም የራሳቸውን ግብአት ጨምረውበታል፡፡ የአልበሙ ሥራ እያንዳንዱ ቅጽበት አስደሳችና በነፃነት የተሞላ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው የየራሱን ሐሳብ እየሰነዘረ የተሻለ ያልነውን በሙዚቃዎቹ አካተናል፡፡ በማንነት ጥያቄ ረገድ ራሴን በአንድ ቦታ ላለመወሰን እሞክራለሁ፡፡ የመጀመሪያው ኃላፊነቴ ነፃነቴን መጠበቅ ነው፡፡ ራሴን ሳልወስን ከሰዎች ጋር ስገናኝ ነፃነቴን አገኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ መወለዴ፣ ከኢትዮጵያ ወጥቼ መኖሬና አሁን ወደ ኢትዮጵያ መመለሴ የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ እግዚአብሔር ያስቀመጠልኝን ዕጣ ፈንታ ለማግኘት እያንዳንዱ ተሞክሮዬ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለእያንዳንዱ ሁኔታ ትኩረት ለመስጠትና ትምህርት ለመውሰድ እሞክራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃዎችሽ አርኤንድቢ፣ ሶል፣ ሬጌ፣ የአፍሪካ ሙዚቃና ሌሎችም ዘዬዎች አሉ፡፡ የቱ የበለጠ ይገልጽሻል?

ወይና፡- ሙዚቃዬ ከልብ ከመነጨ ጥልቅ ስሜት ስለሚፈልቅ ሶል ሙዚቃ በሚለው እገልጸዋለሁ፡፡ ለነገሩ ሁሉም ዓይነት ሙዚቃ ሶል ሊሆን ይችላል፡፡ መከፋፈሉን አልወደውም፡፡ ይህ ጥሩ ወይም መጥፎ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሙዚቃው ከገባሽበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያለው ጉዞሽ ምን ይመስላል?

ወይና፡- በሙያውም በግል ሕይወቴም አድጌያለሁና አስደሳች ነው፡፡ የልፋቴን ውጤት እያየሁ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ነው፡፡ የምወደውን ነገር ለመሥራት ዕድሉን በማግኘቴና ከሚያነሳሱኝ ሰዎች ጋር በመጣመሬ ደስተኛ ነኝ፡፡ የሰዎችን ሕይወት የሚነካ ሥራ በመሥራቴ እስከገፋሁበት ድረስ ዕድገቱ ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡- የቅርብ ጊዜ ዕቅድሽ ምንድን ነው?

ወይና፡- ሙዚቃዎች እያዘጋጀሁ ነው፡፡ ከተሳካልኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ላይቭ አልበም የመቅዳት ዕቅድ አለኝ፡፡ ሰዎች ሙዚቃዬን እንዲሰሙና በማኅብረሰብ ድረ ገጽም እንዲከታተሉኝ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የቀረጽኩትን የሬጌና ሂፕ ሃፕ ውህድ ሙዚቃዬንም በቅርቡ እለቃለሁ፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...