ካለሰው ቢወዱት
ከጐራው ዘልቄ – እስኪ ልነጋገር፤
ካለሰው ቢወዱት – ምን ያደርጋል አገር?
ሕንፃ መች ሆነና – የድንጋይ ክምር፣
መንገድ መች ሆነና – የድንጋይ አጥር፣
ሕንፃው ምን ቢረዝም – ምን ቢፀዳ ቤቱ፣
መንገዱ ቢሰፋ – ቢንጣለል አስፋልቱ፣
ሰው ሰው ካልሸተተ – ምንድነው ውበቱ
የኔ ውብ ከተማ – የኔ ውብ አገር፣
የሰው ልጅ ልብ ነው፣
የሌለው ዳርቻ – የሌለው ድንበር፣
– በዓሉ ግርማ ‹‹ኦሮማይ›› (1975)
* * *
ካዛኪስታን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስማርት ፎን ከለከለች
በካዛኪስታን የመንግሥት መረጃዎች እንዳይሾልኩ በሚል በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስማርት ፎን መጠቀም መከልከሉ ባለፈው ሳምንት ተሰማ፡፡ ይህ የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተው የመንግሥት ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችም ሆኑ ወደነዚህ ተቋማት አገልግሎት ፈልገው የሚሄዱ ሰዎች ስልካቸውን በር ላይ እንዲያስቀምጡ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ በፊት ምስጢራዊሰ የመንግሥት ተቋማት መረጃዎች በስማርት ፎን አማካይነት በመውጣታቸው ሠራተኞች ኢንተርኔትና ካሜራ የሌላቸውን ስልኮች እንዲጠቀሙ ማድረግ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ገልጸዋል፡፡
* * *
በኬንያ አውራ ጐዳና አንበሳ አንድ ሰው ላይ ጉዳት አደረሰ
ባለፈው ዓርብ አንድ ወንድ አንበሳ በናይሮቢ አውራ ጐዳና ላይ በመውጣት አንድ ሰው ላይ ጉዳት ማድረሱን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ አንበሳው በኬንያ የዱር እንስሳት አገልግሎት ከሚተዳደረው ከናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክ ነበር ያመለጠው፡፡ አንበሳው ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ ሊያዝ የቻለው ከፓርኩ ወጥቶ በፓርኩ አካባቢ እንዲሁም በመዲናዋ አውራ ጎዳናዎች ላይ ሲንጐራደድ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመለቀቃቸው ነበር፡፡ በአንበሳው ጥቃት የተሰነዘረባቸው አዛውንት ወዲያው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውንና በደህና ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ናይሮቢ ከተማ ዳርቻ ላይ ከሚገኘው ፓርክ አንበሶች አጥር እየጣሱ በተለያየ ጊዜ መታየታቸውም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
* * *
‹‹ልመታ.. አልመታ…?››
ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሥራ ውዬ ቤቴ ስገባ፤ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ከአንዳንድ ሌሊቶች በስተቀር አይቼው የማላውቀውን ታላቅ ክስተት አየሁ፡፡
የሻወር ቧምቧ ቀዳዳዎቹ ውኃ ጠብ…ጠብ ያደርጋሉ፡፡
‹‹ዓይኔ ነው ወይስ እውነት ነው!›› ብዬ ጠጋ አልኩና ለወራት ልከፍተው ያልሞከርኩትን የሻወር ውኃ መክፈቻ ወደ ቀኝ ዘወርኩት፡፡
ውኃ! በጠራራ ፀሐይ ውኃ! ያውም የሻወር ቤት ውኃ!
በምወደው እምልላችኋለሁ፤ ውስን ነገሮች ብቻ ሊያስደስቱኝ የሚችሉትን ደስታ ተደሰትኩ፡፡
በመሀል ስልኬ ሲጠራ ሰማሁ፡፡ አላነሳሁትም፡፡
ወሳኝ የሆነውን ትእይንት መከታተሌን ቀጠልኩ፡፡ ወዲያው፤ ‹‹ይኼ ሙቅ ውኃማ መሬት ፈሶ አያልቅም፤›› ብዬ ስናፍቀው ወደነበረው ጉዳይ ገባሁ፡፡ ቤቴ ውስጥ ሥልጣኔ እንዳለመው ሻወር መውሰድ፡፡
በፍጥነት ተዘጋጀሁ፡፡
ተዘጋጅቼ ሳበቃ ‹‹ካሁን ካሁን ይጠፋል›› ሰቀቀኔን እየታገልኩ ራሴን ለውኃው አቀረብኩ፡፡
እ…ሰ…ይ…ውኃ ሕይወቴ!
እንዲህ ሐሴት እያደረግኩ፤ ለጥቂት ደቂቃዎች የውኃውን ዘላቂ አፈሳሰስ ካየሁ በኋላ ሳሙና የመመታት እምነት አሳደርኩበት፡፡
እምነቴ ግን ሙሉ አልነበረም፡፡
ስለዚህ ምን አደረግኩ…? ከጣቶቼ እግሮች ጀመርኩ፡፡
ተመታሁ፡፡
ውኃው አልቆመም፡፡
ከፍ አልኩ፡፡
እስከ ጉልበቴ ተመታሁ፡፡
ውኃው አሁንም አልቆመም፡፡
እንዲህ እንዲህ እምነቴም ሳሙና የሚመታው አካሌም ከፍ ከፍ እያለ ጸጉሬ ጋር ደርሼ ጸጉሬን ሳሙና ተመታሁ፡፡
በእንዲህ ያለ ሁኔታ፤ ጸጉሬን ሳሙና መምታቴ በውኃው ዘላቂነት ላይ ያለኝን እምነት ያሳየሁበት ከባድ ምልክት መሆኑን ማንም ኢትዮጵያዊት ሴት ታውቀዋለች፡፡
ውኃውም አላሳፈረኝም፡፡ መፍሰሱን ቀጠለ፡፡
ረጋ ብዬ ተለቀለቅኩ፡፡
የመጀመሪያ ዙር ሳሙናዬን አስለቅቄ ስጨርስ አንድ ሊታመን የማይችል ሐሳብ መጣልኝ፡፡
ድጋሚ ሳሙና መመታት፡፡ ግን ፈራሁ፡፡ የእውነት ፈራሁ፡፡ ‹‹ዛሬ ከመምጣቱ አብዝቼው ይሆን!›› የሚል ፍርኃት…ሰቀቀን ነገር፡፡
ውኃውን አየሁት፡፡ መፍሰስ አቁሞ እንደማያውቅ ይፈሳል፡፡
እጄን ወደ ሳሙናው ዘረጋሁ፡፡
አሁን ግን ከእግሮቼ ጣቶች ሳይሆን ከጸጉሬ ጀመርኩ፡፡ ጸጉሬን በሳሙና ድብን አድርጌ መታሁ፡፡ ድብን አድርጌ መትቼ ስጨርስ ለማበጠር አሰብኩና ማበጠሪያዬን ሳሙና ዓይኔ ውስጥ እንዳይገባ እየታገልኩና እየተደናበርኩ ብድግ አድርጌ በአንድ የከፈልኩትን የጸጉሬን ክፍል መላግ ስጀምር….
ቀጥ፡፡
ውኃው ቀጥ አለ፡፡ መጥቶ እንደማያውቅ ሒድት፡፡ ፈሶ እንደማያውቅ ድርቅ፡፡
ብዙ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ወይም ስለ ሀገራቸው ምንነት ለማውራት ሲፈልጉ የሚጠቅሷት፤ በመጠቀስ ብዛት ውበቷ የደበዘዘ የምትመስል ግን ቆንጆ ግጥም አለች፡፡ የበድሉ ዋቅጅራ ግጥም፡፡ ‹‹ሀገር ማለት ልጄ…›› እያለች የምትፈስ፡፡ የዛች ግጥም ነጥብ ሀገር መሬት፣ ወንዝ፣ ገለመሌ ሳይሆን ሰው እንደሆነ መንገር ነው፡፡
እኔ ግን ዛሬ በሀገሬ ውኃ ሰጪና ከልካዮች እምነቴ ተበልቶብኝ፣ ሳሙና ተለቅልቄ ቆሜ እንዲህ እላለሁ..
‹‹ሀገር ማለት ልጄ… በየሰላሳ ቀኑ የደመወዝህን ግማሽ እየተፋህ በምትኖርበት ዋና ከተማ ውስጥ የሚገኝ ቤት ውስጥ፤ የሻወር ውኃ ስታይ የምኒልክ ድኩላን መታጠቢያ ቤትህ ውስጥ ያየህ ያህል አለመደነቅ ነው፡፡
ሀገር ማለት ልጄ….
ስንት የሚሞግት ነገር ባለበት ሀገር ውስጥ እየኖርክ ዋነኛው የሕይወት ሙግትህ ሻወር እየወሰድክ ‹‹ሳሙና ልመታ አልመታ›› ሳይሆን ሲቀር ነው፡፡
- ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር
* * *