Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የለውጥ ማሳያው ጎዳና

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ ሙያ አሠልጥኖ ሥራ የሚያሲዝ ‹‹አዲስ ራዕይ›› የተባለ ማሠልጠኛ ከአዲስ አበባ 222 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አሚባራ ወረዳ ከፍቷል፡፡ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ15 ሺሕ የሚበልጡ የጎዳና ተዳዳሪዎችን አሠልጥኖ ሥራ አስይዟል፡፡ ስለማሠልጠኛ ማዕከሉ አመሠራረትና አጠቃላይ የተቋሙን ሁኔታ በተመለከተ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሸን ሥር የአዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ ዋና ኃላፊ የሆኑትን ኮሎኔል ገብሩ ገብረፃጽቅን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጎዳና ልጆችን አሠልጥኖ ሥራ የማስያዝ ፍላጎቱ እንዴት ተፈጠረ? ሥራውን ከጀመራችሁስ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ?

ኮሎኔል ገብሩ፡- ማሠልጠኛ ማዕከሉ ከተቋቋመ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡   አገራችን ሰፊ የልማት ሒደት ላይ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ልማቱ  የልማት ተቋዳሽ ያልሆኑትን፣ ተስፋ ቆርጠው መዋያና ማደሪያቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ እንደዚሁም በልመና ተሰማርተው የሚገኙ ወጣቶች ካላካተተ ትርጉም የለውም፡፡ የፈለገ ብናለማ፣ ሰውን ካላለማን ልማት የሚባል ነገር የለም፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ወጣቶቹን የመርዳት ሐሳቡ ነበረን፡፡ ሐሳቡን ዕውን ለማድረግም ከኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሴዬሽን ጋር በመተባበር የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ወጣቶችን ራሳቸውን ለማስቻል ይህን አዲስ ራዕይን የተባለውን የማሠልጠኛ ተቋም አቋቋምን፡፡

ሪፖርተር፡- ለመጀመርያ ጊዜ የተቀበላችሁት ምን ያህል ሠልጣኞችን ነበር? ከቦታው የአየር ባህሪና ርቀት አንፃር ያጋጠማችሁ ችግር አለ?

ኮሎኔል ገብሩ፡- ምንም አላስቸገረንም፡፡ ቦታው በእርግጥ ጫካና ሙቀታማ ነበር፡፡ እንደዚሁም ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ባልተዘረጋለት ትንሽ ቦታ ነበር የጀመርነው፡፡ ግን ከጎዳና በላይ ምንም የከፋ ነገር የለምና ሠልጣኞች ራሳቸው ጫካውን መንጥረው፣ መንገድ ሠርተው፣ ድንኳን ደኩነውና ለሰው ልጅ መኖሪያ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሠርተው እንዲገቡ ነው የተደረገው፡፡ ሠርቶ መለወጥን ከዚህ መጀመር እንዳለባቸው ታስቦ የተደረገ ሲሆን፣ ውኃና ኤሌክትሪክ ደግሞ በተቋሙ ተዘርግቶላቸዋል፡፡ በመጀመርያ ዙር 2,400 ወጣቶችን ነበር የተቀበልነው፡፡ አቅማችንን አጠናክረን በሁለተኛው ዙር 4,139 አስመርቀናል፡፡ በዘንድሮው ደግሞ 10,375 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማስመረቅ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራውን ስትሠሩ አጋሮቻችሁ እነማን ናቸው?

ኮሎኔል ገብሩ፡- የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደርም በገንዘብና ባለሙያዎችን በመላክ እየረዳን ነው፡፡ ኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሴሽንም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶቹን የምታሰባስቡት እንዴት ነው? በተቋሙ ያሉ ነፍሰጡር ሴቶችን በተመለከተ የተለየ አሠራር አላችሁ?

ኮሎኔል ገብሩ፡- የሚሰበሰቡት ከመላው ኢትዮጵያና በብዛት ደግሞ ከዋና ዋና ከተሞች ነው፡፡ የሚሰበስባቸው ደግሞ ኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሴይሽን ከማኅበራዊና ሠራተኛ ጉዳይ ጋራ በመተባበር ነው፡፡ በየወረዳው፣ በየደረጃው ባሉ አደረጃጀቶች በሚያደረጉ የማጣራት ሥራዎች በትክክል የጎዳና ተዳዳሪ መሆናቸው ተረጋግጦ ዕድሉን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ካለን አቅም አንፃር የምንቀበለው የሴቶች ቁጥር በጣም ውስን ነው፡፡ ይህም ለወደፊቱ በትኩረት የምንሠራበት ጉዳይ ነው፡፡ ከምንቀበላቸው ሴቶች መካከልም ነፍሰጡሮች ያጋጥሙናል፡፡ ነገር ግን አንመልሳቸውም፡፡ እዚሁ እንዲወልዱና ሥልጠናቸውን እስኪጨርሱ  ልጆቻቸው ቅርብ ቤተሰብ ዘንድ እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ ይህ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ሲሆን ወደፊት ጥናት በማድረግ ወላጆች እየሠለጠኑ ልጆቻቸው ደግሞ የሚማሩበት ሁኔታን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከዛም ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተመልምለው የመጡ ጎዳና ተዳዳሪዎችን እንደየደረጃቸውና እንደችሎታቸው በመደልደል እንዲማሩ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ዕድሜያቸውና ሲመጡ የነበራቸው የትምህርት ደረጃ ምን ይመስላል? ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎችም አጋጥመውናል፡፡ ጎዳና የሚወጡበት ምክንያታቸውስ ይታወቃል?

ኮሎኔል ገብሩ፡- እኛ ስንቀበል ዕድሜ አንጠይቅም፡፡ምክንያቱም የምናሠለጥነው ውትድርና ሳይሆንም  ልማትን ነው፡፡ የልማት ዓላማ ደግሞ ማንኛውም መሥራት የሚችልን ሰው አሠልጥኖ ወደ ሥራ ማሰማራት ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 55 የሚጠጋ ሰዎች ወደ ማሠልጠኛችን ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን ከ18 እስከ 35 የሚሆኑ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ይበዛሉ፡፡ በዛው ልክ ደግሞ ጥሩ የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ ያላቸው በተለያዩ ሱሶች ጎዳና ላይ የወጡ ያጋጥሙናል፡፡ ቤተሰብ በመበተኑና በድህነት ወደ ጎዳና የሚወጡት ግን በርካታ ናቸው፡፡ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ለመሄድ በደላሎች አማካይነት ብራቸው ተበልቶ ወደ ቤተሰብ መመለስ ፈርተው እዚሁ ጎዳና ተዳዳሪ ሆነው የቀሩም አሉ፡፡ ዕድሜያቸው፣ ባህሪያቸውና የመጡበት አካባቢ ቢለያይም ወደእኛ ማዕከል ሲገቡ ሁሉም እኩል ትምህርት፣ እኩል መኝታና እኩል የሥራ ድርሻ እንዲያገኙ በማድረግ አምራች ዜጋ እንዲሆኑና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ነው የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- በምን በምን ሙያ ታሠለጥኗቸዋላችሁ?

ኮሎኔል ገብሩ፡- ሠልጣኞች እንደሚነግሩኝ ከሆነ ከጎዳና ሕይወት መላቀቅ በራሱ እንደገና እንደመወለድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ማሠልጠኛ በመግባታቸው ደስተኛ ናቸው፡፡ እኛም ይህን ደስታቸውን የበለጠ እንዲሆንና ራዕይ እንዲኖራቸው በማድረግ ተስፋ የሚጣልባቸው ዜጎች እንደሆኑ በማስረዳት ሞራላቸውን እንገነባለን፡፡ ይህም መንግሥት ምን ያህል እንደሚያስባቸው እንዲረዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ገና ከበር መልካም አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ ልብስና ጫማም ይሰጣቸዋል፡፡ ከዛም የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ የሳይኮሎጂ ትምህርት፣ የሥነ ምግባር ትምህርት ለሁለት ወራት በደንብ እንዲከታተሉ ከተደረገ በኋላ ወደ ዋናው ሥልጠና ይገባሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ሥልጠናውን የሚወስዱት በፍላጎታቸው ነው ወይስ እናንተ በምታደርጉት ድልደላ ነው?

ኮሎኔል ገብሩ፡- አሁንም እንዳልኩህ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተዋሽና አስተማሪ ያጡ ዜጎች ናቸው፡፡ በተቻለን መጠን ፍላጎታቸውን ለመጠበቅ እንሞክራለን፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ግን እነዚህን ዜጎች በሥነ ምግባር የታነፁና አምራች ዜጋ ሆነው ወደ ኅብረተሰቡ እንዴት ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚለውን ነው ማየት ያለብን፡፡ ሌላው ዋናው ትልቁ መታየት ያለበት የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንዴት ከድህነት እናስመልጥ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ለሁለት ወራት የሥነ ምግባር እንዲሁም ሌላውን ትምህርት ከጨረሱ በኋላ ወደ ሥልጠና እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የመግቢያ ፈተናም ይወስዳሉ፡፡ ባሉት የመሠልጠኛ ቦታዎች ማለትም አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ በሾፌርነት፣ በመካኒክነት፣  በፓወር ኢንጂነሪንግ፣ ኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ በኃይቴክ፣ በፋብሪኬሽን፣ በኮንስትራክሽንና ማሽን ኦፕሬት በማድረግ እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎች አልያም በሌላ የሙያ ዘርፎች ይሠለጥናሉ፡፡ ከዚህ ሲወጡ ብቁ እንዲሆኑ  የብቃት ማረጋገጫ ምዘና COC ፈተና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ብዙዎቹም በትምህርታቸው ጠንካራ ናቸው፡፡ እኛም በተሟላ የትምህርት መስጫ ክፍሎች እንዲሁም ሰፊ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ በቂ መሣሪያዎች በማዘጋጀት እንረዳቸዋለን፡፡ በአጠቃላይ በአዲስ ራዕይ ገብቶ የወጣ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ሠልጣኝ በጤና፣ በሥነ አዕምሮ፣ የሥራ ፍቅርና የአገር ፍቅር ብቃቱ እንደማንኛውም ዜጋ ተወዳዳሪ ሆኖ በአሸናፊነት ነው የሚወጣው፡፡     

      ከዚህ በፊት በዚህ ማሠልጠኛችን የሠለጠኑ በመንግሥትና በግለሰብ በተያዙ ፕሮጀክቶች ተቀጥረው አመርቂ ውጤት በማስመዝገባቸው ጥሩ ምስጋና ደርሶናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጎዳና ተዳዳሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር የተራራቁ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በትምህርትም እንደዚሁ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የገጠማችሁ ችግሮች ይኖሩ ይሆን?

ኮሎኔል ገብሩ፡- እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከሌላው ማኅበረሰብ የሚለያቸው አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ ይህም የሚናገሩት እውነትና የተሰማቸውን መሆኑ ነው፡፡ እከሌ ምን ይለኛል? ይህን ብናደርግ እንትና ይከፋው ይሆን? በደል ይደርስብኛል በማለት ማጎብደድ የሚባል ነገር በፍፁም የለባቸውም፡፡ ለእኛም አንዱ የረዳን ግልጽ ስሜታቸው ነው፡፡ እኛም ስሜታቸውን በመጠበቅ ትክክል ያልሆኑትን በማስረዳት አንዳንዴም ጠበቅ ያለ ዕርምጃ በመውሰድ ችግሮችን እንፈታለን፡፡ በሱስ የተያዙትም እንዲሁ ሥልጠና ከመጀመራቸው በፊት በቂ የሥነ ልቦና ትምህርት ስለሚሰጣቸው ምንም ችግር አይገጥመንም፡፡

      ሌላው እንዲያውም እንደመደበኛ ማኅበረሰብ ነገን ተቀይረው ለማየት ተስፋ ስለሚያደርጉ ትኩረታቸው ሁሉ ሥልጠናው ላይ ነው ለዚህም ነው፡፡ እንደሌላው ትምህርት ቤት ብዙ ጊዜ የማይወስዱት፡፡ ቶሎ ሠልጥነው ሥራ የማግኘት ጉጉት ስላላቸው የተሰጣቸውን ሥልጠና በአጭር ቀናት ውስጥ በተግባር ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡  የኖሩበት ሕይወት አለ፣ ያን ሕይወት እንዲተዉት ይፈለጋል፡፡ ነገር ግን በመተውና ባለመተው መካከል ከባድ ትግል አለ፡፡ ከነሱ ጋር መዋል ማደር ያስፈልጋል፡፡ እኛም እያደርን ነው፡፡ እንደ መከላከያ ሠራዊት ከእኛ በላይ ለነሱ የሚቀርባቸውና የሚጠጋቸው የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ አገራዊ ፕሮጀክት ከዓመት ዓመት እያደገ ይገኛል፡፡ አብረዋችሁ የሚሠሩ ድርጅቶችስ ወጣቶቹን ካስረከቡ በኋላ ሌላ የሚያደርጉት እገዛ አለ? ዓመታዊ በጀታችሁስ ምን ያህል ነው?

ኮሎኔል ገብሩ፡- የምናወጣው ወጪ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በዚህ ያህል በጀት እንተዳደራለን ብለን አልወሰንም፡፡ ለወደፊቱ ግን በደንብ ዝርዝር ጥናት ተሠርቶለት ማስፋፊያዎቹ ሲጠናቀቁና አንድ ማሠልጠኛ ሊያሟላ የሚገባውን አሟልቶ ቅርፅ ሲይዝ የተወሰነ ዓመታዊ በጀት ይኖረናል፡፡ አሁን ግን የሠልጣኞች ቁጥር እየጨመረ፣ ማደሪያና መማሪያ ክፍል እያስፋፋን ገና ግንባታ ላይ ነን፡፡ ሌላው ከላይ እንደገለጽኩልህ ከእኛ ጋር የሚሠሩት ድርጅቶች ብዙ ናቸው፡፡ የተለያየ ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ራሱ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከ375 በላይ ሠራተኞችን በመቅጠር ብዙውን ነገር ይሸፍናል፡፡  ትልቁ አጋዣችን ደግሞ ኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሽየሽን በተለያዩ ነገሮች ይረዳናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት የተመረቁት ሥራ ላይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ የዘንድሮ 10,375 ሰዎች ደግሞ ተመርቀዋል፡፡ እነዚህስ ቦታ አላቸው?

ኮሎኔል ገብሩ፡- እንግዲህ እዚህ ላይ የሚዲያ ሚና ትልቅ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ኅብረተሰቡ አንድ ልጅ ወደ ጎዳና ከወጣ ስሙ አጭበርባሪ፣ የማይታረም እንደሆነና እንደማይጠቅም ይታሰባል፡፡ ጎዳና መውጣታቸው በችግር እንጂ በምርጫ አይደለም፡፡ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንደማንኛውም ዜጋ መሆናቸውን እነዚህ ሠልጣኞች ምስክር ናቸው፡፡   እኛ በሁሉም ነገር ብቁ አድርገናል ብለን እናስባለን፡፡ ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ደግሞ ወደ ቀድሞ ኑሯቸው እንዳይመለሱ፣ ፍቅር በመስጠት ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀራረቡና ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እርስ በርስ መደጋገፍ ግድ ይላል፡፡ ሌላው በተለይ የግል ቀጣሪዎች ተያዥ፣ የሥራ ልምድና ሌላም ሌላም ነገር በመጠየቅ እነዚህን ወጣቶች ወደ ጎን የሚገፉበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ይህንን እንደምሳሌ በመውሰድ ቢያሠሯቸውና ቢያስተምሯቸው የሚለወጡ ልጆች እንደሆኑ ቀጣሪዎችም ያለምንም ልዩነት እነዚህን ሠልጣኞቹን መቅጠር እንዳለባቸው ማሳወቅና ማስተማር ከሚዲያው የሚጠበቅ ነው፡፡ ሠልጣኞቹ ጥሩ ባህሪ አላቸው፡፡ ሥራ መምረጥ አይታይባቸውም፡፡ ፍፁም ታማኞችም ናቸው፡፡ መንግሥትም ሠልጣኞቹን እየቀጠረ ይገኛል፡፡ የዘንድሮ ተመራቂዎቹንም ከመንግሥትና ከኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ጋር በመተባበር ትልቅ ፕሮጀክት በመቅረፅ ለመንግሥት አቅርብን ይሁንታ እየጠበቅን እንገናኛለን፡፡ እሱ ካለቀ ወዲያው ወደ ሥራው እንገባለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን አቅዳችኋል?

ኮሎኔል ገብሩ፡- ይህን ማኅበራዊ ቀውስ ለመፍታት እኛ ጀማሪዎች ሆነናል፡፡ በትንሽ ሀብትና በአጭር ጊዜ እንዴት ሰዎችን በጥሩ ሥነ ምግባር ቀርፆ ለኃላፊነት እንዲበቁ ማድረግ እንደሚቻል አሳይተናል፡፡ ይህንን ተሞክሮ ኅብረተሰቡ እንዲማርበትና ችግሩን መፍታት እንዲቻል ሚዲያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡  ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅም የቤተሰብና የትምህርት ቤቶች ዕርዳታ ያሻል፡፡ በእኛ በኩል ይህ አዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ የያዘውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከተራ ማሠልጠኛ ተቋምነት ወደ ቴክኒክና ሙያ ከዛም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያድግበትን ሁኔታ እያጠናን እንገኛለን፡፡ አቋሙም ምን መምሰል አለበት? የሚለውን ተጠንቶ ለሚመለከተው አካል አቅርበን እንዲፀድቅ እየጠበቅን እንገኛለን፡፡ እሱ ከፀደቀ በቀጥታ ወደ ሥራ በመግባት ለበርካቶች አለኝታም ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች