እ.ኤ.አ. በ1973 ቬትናምን ጎብኝተው ሲመለሱ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ስላላት ግንኙነት ተጠይቀው የነበሩት ፊደል ካስትሮ፣ ‹‹አሜሪካኖች ጥቁር ፕሬዚዳንት ሲኖራቸውና ዓለም ላቲን አሜሪካዊ ጳጳስ ሲኖረው ያናግሩናል፤›› ማለታቸው ይነገራል፡፡ ይህ አሁን በሥልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኩባን ሲጎበኝ ከሞላ ጎደል ከ90 ዓመታት ወዲህ የመጀመርያ የሆነው የባራክ ኦባማ ጉብኝት ትንቢት ነው እየተባለ ነው፡፡
ምንም እንኳ ፊደል ካስትሮ አሉት የተባለው ነገር በተለያዩ ጋዜጦችና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ቢወጣም እውነተኛነቱን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ይልቁንም ለዘመናት እንደታየው የዓለም ኃያሏ አገር አሜሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ይኖራታል፣ ብዙዎቹ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በጣሊያን በተለይም ሮም የተወለዱ በመሆናቸው ላቲን አሜሪካዊም ጳጳስ ይሆናል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው ተብሎ ይታመን ስለነበር፣ የካስትሮ ንግግር ትንቢት ሳይሆን ስላቅ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡
የካስትሮ ንግግር ትንቢትም ይሁን ስላቅ የፕሬዚዳንት ኦባማ የሰሞኑ የኩባ ጉብኝት ታሪካዊ መሆኑ ግን አከራካሪ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ጉብኝቱ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ትልቅ የአሠላለፍ ለውጥ የታየበት ነውና፡፡ በሥልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ካሪቢያን ደሴትን የጎበኘው እ.ኤ.አ. በ1928 ነው፡፡ ይኼም ኦባማን ጨምሮ ወደ ኋላ ሲቆጠር ከ14 የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በፊት የነበሩት ፕሬዚዳንት ካልቪን ኩሊጅ ላይ ያርፋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1959 ወንድማማቾቹ ፊደል ካስትሮና ራውል ካስትሮ ሥልጣን እስከያዙበት ድረስ አሜሪካና ኩባ ወዳጆች ነበሩ፡፡ ወዲያው ግን የካስትሮ መንግሥት በኩባ የአሜሪካ ቢዝነሶችን በሙሉ ወረሰ፡፡ ይህ በግል የተያዙ ንብረቶችን የሕዝብ የማድረግ ትልቅ ዕርምጃ አካል ነበር፡፡ ከሬዲዮ ጣቢያዎች እስከ መኖሪያ ቤቶች በዚህ መንገድ ተወርሰው ነበር፡፡ በአፀፋው አሜሪካ ከኩባ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ንግድም አቋረጠች፡፡ የሁለቱ አገሮች የንግድ ግንኙነት ለ50 ዓመታት ተቋርጧል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1961 አሜሪካ ኩባን ወርራ ካስትሮን ከሥልጣን ለማውረድ ሙከራ ብታደርግም አልተሳካም፡፡ ኩባ ወዲያው ፊቷን የአሜሪካ ጠላት ወደነበረችው ሶቪየት ኅብረት አድርጋ ወዳጅነታቸውን አጠናከሩ፡፡ ይኼኔ ሶቭየት ኅብረት በኩባ ሚሳይል አጠመደች፡፡ አሜሪካም ውጥረት ውስጥ ገባች፡፡ ዓለምም ተሸበረ፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ወላፈን አገሮችን በሩቁ ያስፈራ ጀመረ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሜሪካና ኩባ ግንኙነት ኖሯቸው አያውቅም፡፡ አሜሪካ ኩባ ወደ አሜሪካ ምድር ዕቃዎች እንዳትልክ አደረገች፡፡ ለሁለቱም አገሮች ዜጎች አንደኛውን አገር መጎብኘትም ከባድ ነበር፡፡
ከሶቭየት ኅብረት መውደቅ በኋላም በኩባ መንግሥት አቋም ብዙም የተቀየረ ነገር ስላልነበር፣ የአሜሪካና የኩባ መሪዎች ሲጨባበጡ ማየት የሚታሰብ ሳይሆን ቀረ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 ፊደል ካስትሮ ለወንድማቸው ራውል ካስትሮ ሥልጣን ማስረከባቸውን ተከትሎ ግን ለውጦች መታየት ጀመሩ፡፡ ራውል ካስትሮ ኩባ የአሜሪካን ተቀባይነት ወደምታገኝበት አቅጣጫ መምራት ጀመሩ፡፡ የኩባን የኮሙዩኒዝም ሲስተም ቀለል በማድረግ እንደ ሞባይልና ኮምፒዩተር ያሉ ኩባንያዎች በግል ዘርፍ እንዲያዙም አደረጉ፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የአሜሪካ በኩባ ኤምባሲ መክፈት ሁለቱ አገሮች ንግግር የመጀመራቸው ግልጽ ምልክት ሆነ፡፡ ቅዳሜ መጋቢት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ባራክ ኦባማ ባለቤታቸውን ሚሼል ኦባማና ልጆቻቸውን ይዘው በኩባ ሐቫና በመገኘት ታሪካዊውን ጉብኝታቸውን (የሦስት ቀናት) ጀመሩ፡፡ ይህ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ኦባማና ራውል ካስትሮ በጓንታናሞ ስለሚገኘው የአሜሪካ እስር ቤት፣ የኩባ የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይም ተነጋግረዋል፡፡ በውይይታቸው ሚስተር ካስትሮ የእስረኞች ዝርዝር ቢሰጣቸው ወዲያው እንደሚለቋቸው ሲናገሩ፣ የእስረኞቹን ስም ዝርዝር አሜሪካ ቀደም ብላ መስጠቷን ኦባማ ገልጸዋል፡፡ ካስትሮ እነዚህን እስረኞች እንደ ተቃዋሚ እንደማይመለከቷቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ፡፡ ይህ የሁለቱ አገሮች አለመስማማት ነጥብም ነው፡፡ ራውል ካስትሮ አሜሪካ ኩባ ላይ የጣለችው የንግድ ማዕቀብ መነሳት እንዳለበት ሲናገሩ ኦባማም ማዕቀቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚነሳ አሳውቀዋል፡፡ ‹‹የኩባ ዕጣ ፈንታ በአሜሪካ ወይም በሌላ አገር የሚወሰን አይደለም በኩባውያን እንጂ በሕዝብ አምናለሁ፤›› ብለዋል ኦባማ፡፡
ሰኞ ዕለት ቀደም ብሎ ሚስተር ካስትሮ የኩባን የሰብዓዊ መብት ሪከርድ ጥሩ መሆኑን አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ሰብዓዊ መብትን እንጠብቃለን፡፡ በእኛ አመለካከት የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች የማይከፋፈሉና የማይነጣጠሉ ናቸው፤›› ያሉት ካስትሮ ይልቁንም አሜሪካ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ጠቅሰዋል፡፡ ከካስትሮ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ኦባማ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ለካስትሮ አገራቸው እንዲለቀቁ የምትፈልጋቸውን እስረኞች ዝርዝር እንደምትሰጥ በቀጥታ አልተናገሩም፡፡ ‹‹ባለፉት ጊዜያት ዝርዝር ሰጥተናቸዋል፡፡ እነሱም ወጥ ባልሆነ መንገድ ምላሽ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከዝምታና ከማዕቀብ ይልቅ ይህ ውጤታማ አካሄድ እንደሚሆን አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል ኦባማ፡፡
ኦባማ እንዳሉት ላለፉት 50 ዓመታት በሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሆነው ነገር ማንንም አልጠቀመም፣ የኩባን ሕዝብም፡፡ ኩባ ላይ የተጣሉ የንግድ ዕገዳዎች እንዲነሱ አስተዳደራቸው ብዙ ነገር ማድረጉን የገለጹት ኦባማ፣ ምንም እንኳ በምርጫ ወቅት እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ባይቻልም ጉዳዩ በተጨማሪ የኮንግረሱን ውሳኔ የሚሻ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
በተጨማሪም የንግድ ማዕቀቦቹን የማንሳት ነገር ከሁሉም በላይ ኩባ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ በምትወስደው ዕርምጃ የሚወሰን እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ አሜሪካ ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ የገባችው ከኩባ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከቻይናና ከቬትናም ጋር ጭምር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በማንም አገር ላይ ለውጥ እንዲመጣ ጫና መፍጠር አልችልም፡፡ ይህ በዋነኝነት መምጣት ያለበት ከውስጥ ከሕዝብ ነው፡፡ ጠቃሚው ይህ ስትራቴጂ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡
ኦባማና ሚሼል የእንኳን ደህና መጣችሁ እራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን፣ የተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላትና የዋይት ሐውስ ሠራተኞችም በግብዣው ላይ ተገኝተዋል፡፡ በሌላ በኩል ኦባማና ካስትሮ በጋራ በመሆን የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ውጥረት የነገሠበት እንደነበር ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ካርላ ኦሊቫሬስ የተባለች ኩባዊ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፣ ካስትሮ ከተለመደው ውጪ ብዙ አውርተዋል፡፡ በኩባ የፖለቲካ እስረኞች የሉም ሲሉ መናገራቸው ደግሞ አወዛጋቢ መሆኑን ገልጻለች፡፡
የኦባማ የሐቫና ጉብኝት በካስትሮ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች የታጀበም ነበር፡፡ ብዙዎች ይህ በራሱ የሚናገረው ብዙ ነገር አለ ይላሉ፡፡ አሜሪካ ከኩባ ጋር ግንኙነቷን እያደሰች ቢሆንም፣ በኩባ ነገሮች ዛሬም እንደ ቀድሞ መሆናቸውን ከተቃውሞው መመልከት ይቻላል የሚል አስተያየት እየተሰነዘረም ነው፡፡ ነገሩን ለጥጠው የራውል ካስትሮ መንግሥት እንደ ሰሜን ኮሪያው አምባገነን በመሆኑ የኦባማ የኩባ ጉብኝት በአገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉ ሰዎችን የመክዳት ያህል ነው በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡