Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እረኛውና መንጋው እንዴት ይግባቡ?

እነሆ መንገድ። ከመገናኛ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። የወር ፍጆታውን ግጦ እንደጨረሰ በሬ አንድ ሸበቶ ጎልማሳ አጠገባችን  እየተጎንራደደ፣ “በደርግ ጊዜ ያነበብኩት መጽሐፍ ላይ . . . ‘ኑሮ ዜማቸው በተበላሸ እንጉርጉሮዎች ሲበደል አይ ነበር’ ሲል ገጸ ባህሪው እኔን እኔን ይመስለኝ ነበር፤” ብሎ ብድራቱን ያስቀሩበትን ጭሰኞች በንቀት እንደሚበድል ፊውዳል ቁልቁል ያየናል። “ምነው ኢሕአዴግ ማንበብ የከለከለ ይመስል አንድ ዓረፍተ ነገር ለማስታወስ ደርግ ዘንድ ሄድክሳ?” ቀናነት የወረሰው ፈፈግታ የተላበሰች ዘመናይ ጠየቀችው። “ተይው ማንበቡን መቼ በቅጡ መኖር ችለን አሁንማ፤” አላት። የመንገደኛው ቁጥር እየጨመረ ነው። ባቡራችን ደብዛዋ የለም። “ደግሞ በየት አገር ነው ኑሮ የሚበደለው? እሱ መስሎኝ በዳያችን፤” አሉ በሥጋቸው የተሸከሙት ሥውር ሸክም አጉብጦ በገሃድ የሳላቸው አዛውንት። “አይ እባት ያው እኮ ነው። የስም ለውጥ ናቸው ፍቅርና ወረት’  ብሏል እም  . . .” ጎልማሳው ከትውስታው ሲታገል ሳለ፣ “ይኼንንም ያነበብከው በደርግ ጊዜ እንዳይሆን?” አለው አንድ ወጣት እያላገጠ።

መንገደኛው በየአምስት ደቂቃው ቁጥሩ ወደ ላይ ያሻቅባል። ከዚያም ከዚህም ጉርምርምታ ይደመጣል። “በየስድስት ደቂቃው ነው የምትመጣው እያሉ ጉራቸውን ሲነዙ አልነበረም? የታል እሺ? የታል?” አንዱ ይወራጫል። መናገሪያ ሰበብ፣ ማደናገሪያ ሜዳ ያገኘ የመሰለውም በልቡ ጮቤ እየረገጠ፣ “ካወራን መቼ አነሰን? ለታይታ ከኖርን አይበቃም? ባቡር አላቸው ከተባለልን በየስድስት ሰዓቱ እየመጣ ቢያግዘን ምን አለበት? በአፍሪካ አንደኛ ቅብጥርሶ፣ የጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ ሥርዓት ውጤት ቅባጥርሶ ከተባለልን ቆመን ብንውል ኢኮኖሚው ማደጉን አይተው፤”  እያለ  ተደረበ። ይኼኔ፣ “ማን ተጣልቶ ነው?” ብለው አዛውንቱ አንዱን ወጣት ሸሚዙን ጎተቱት። “ኧረ ማንም አልተጣላም። ባቡሩ ያረፍዳል፣ አርፍዶ ሲመጣ ደግሞ ሞልቶ ይተነፍጋል የሚል የብሶት ወግ ተቀጣጥሎ ነው፤” ሲላቸው፣ “በአጭሩ ሁሉም ከራሱ ጋር ገጥሞ ነው አትለኝም?” ብለው ፈቀቅ አሉ። ወደ ውጭ ነው ወደ ውስጥ የአንዳንዱ ሰው ግጭት ያስብላላ ነገርዬው!

ከመሬቱ ይልቅ ሐዲዱን አምነን ባቡር ላይ ወጥተናል። “አይ ባቡር! ባቡር ብሎ ዝም! ጥንት ማንም ሳያውቀው እያወቅነው ዛሬ እንዳዲስ ከች ሲል ግን ሰው አይደነግጥም?” ይላል አንዱ አፍንጫውን አሥር ጊዜ እየጨመቀ።  “እኛ ኢትዮጵያውያን መደንገጥ አልፈጠረብንም። ደንግጠን ምን ለመፍጠር?” አለው ምኑም ያልገባው ችኩል። “ሰው ሲደነግጥ ምን ይሆናል? ወይም የሚሄድበት ሥፍራ ትልቅነት፣ ግርማዊነት ሲያስፈራው ምን ያደርጋል? እ? ቀላል እኮ ነው። የግል ንፅህናውን ይጠብቃል። አይደለም? የክት የሚላትን ይለብሳል። በተቻለው አቅም ዓይን ለመሙላት ይጥራል፤” ሲል አቅጣጫውን መለየት ያቃተን የጫማ ሽታ የወሬው መነሻ እንደሆነ የገባን ተጠቃቀስን። “ጉድ በል ያገሬ ሰው። ሐበሻ ለክብሩ ሟች፣ ለአገሩ ሟች፣ ለሚስቱ ሟች ነበር የሚባለው። የዛሬን አያድርገውና፡፡ ይኼው ሙት ይዞ ይዞራል፤” ሲል ሌላው ፈገግ አሰኘን።

ምፀቱ የከነከነው አንድ ጎልማሳ፣ “ልብስ አምሮ ልብ ቢቆሽሽ ምን ዋጋ አለው? ሥጋ ደልቦ መንፈስ ቢቀጭጭ? ዘንድሮ እኮ ያስቸገረን ከላይ እያማረ ውስጡ የቆሻሻ የአስተሳሰብና የልብ ጥመት ነው፤” እያለ አንዱን ቡድን ለሁለት ከፈለው። “እውነት ነው” ሲል የወዲኛው፣ የወዲህኛው ደግሞ፣ “ሰው ባለው ነው። እስኪ መጀመርያ በትንሹ እንታመን። መጀመርያ ከግል ንፅህና እንጀምር። ከዚያ ወደ ልብ እንሄዳለን፤” እያለ ተቃወመ። ይኼን ጊዜ አዛውንቱ “የደላችሁ!” ብለው ዘው አሉ። “ማ?” አለ ሁለቱም ጎራ ዓይኑን እሳቸው ላይ ተክሎ። “ሁልሽም! ምን ታፈጫለሽ? ውኃ ሳይኖር ልብስ ይታጠባል? ጥበብስ ደብዝዞ፣ አዋቂ በአላዋቂ ተረግጦ ልብ ይለወጣል እንዴ? ወዶ መሰላችሁ የተዳፈነ የሚጨሰው? ከእሳት ጉያ ሽሽት እንጂ፤” ብለው  ጀማውን ዝም አሰኙት። ዝም የሚያስብል ሰው እንደዚህ ብርቅ ሆኗል ዘንድሮ?!  

መተፋፈጉ ያስመርራል። ምሬቱን መቋቋም ያልቻለ ወጣት፣ “ሳንሠራ እንዲህ ካላበን ብንሠራማ ምን ልንሆን ነው?” እያለ ነገር ይጎነጉናል። “ምን ጥያቄ አለው ሌላ ግድብ መገደብ እንጀምራለን፤” ትለዋለች ሰበዝ የመሰለች ቀጭን ለግላጋ። “ውኃ እንጂ ላብ ይገደባል እንዴ?” አሉዋት አዛውንቱ። “ለአገር ጠቃሚ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ እንኳን ላቡ ሰውም ይገደባል፤” እያለች ፈገግ ስትል ክንፏን የበተነች ባይተዋር ቢራቢሮ ትመስላለች። “ይኼ የእረኛና የመንጋ ጨዋታ ማብቂያ አለው ይሆን?” ባዩ አጠገቤ የቆመ ወጣት ነው። “አሁን ምን አለበት እዚህ ጥግ ጥጉ ላይ አረንጓዴ ተክል ቢያስቀምጡልን?”  የሚል አንድ ህልመኛ ወጣት ደግሞ ሰውን ለማንጫጫት አቅዶ የተሳፈረ ይመስላል፡፡ “የት? እኮ ባቡሩ ውስጥ ‘ጋርደን?” ተሳፋሪው ጮኸ። “ምን ችግር አለው?” ወጣቱ ሂሱን መዋጥ አልፈለገም። “መጀመርያ የተተከሉትን ዛፎች ተንከባክበን ባሳደግን፤” ጎልማሳው ሳይጨርስ፣ “ተወው ያልምበት አቦ። ህልምና ምኞት አይከለከልም” ብላ ወይዘሮዋ በስስት አየችው።

 “እንዴት ያለ ህልም ነው ይኼ? ባቡሩ እኮ እንኳን ለጋርደን ለእኛም አልበቃንም፤” ጎልማሳው ከአንጀቱ ነው። “እሱማ እንኳን ባቡሩ መሬቱም፣ ኮንዶሚኒየሙም፣ ሀብቱም አልበቃንም፤” አሉት አዛውንቱ። “ምነው ይኼን የሚያህል ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው አገር ይዘን እንዴት ብሎ ነው መሬቱ የማይበቃን? ጎልማሳው ዝም አልል ብሏል። “እሱን ሂድና  የሚመለከታቸውን ጠይቅ፤” ብላ ሸጊት ፋይሉን ዘጋችላቸው።“እግዚኦ! ከላይ ፀሐይ ከሥር ፀሐይ! መጨረሻችንን እሱ ይወቀው፤” እያሉ ሳለ አዛውንቱ አፈናቸውና ሦስቴ ካሳሉ በኋላ ዝም አሉ። “አስም አለብዎ?”  አንዱ ቢጠይቃቸው፣ “ማን የሌለበት አለ? አልስለው ብሎ እንጂ አፋኙ በበዛበት ዓለም ማን የሌለበት አለ?” እያሉት ንዴት ሲበረታባቸው  ማባሪያ የሌለው ሳል ወጥሮ ያዛቸው። እስኪ አሁን አንድ ሠዓሊ ይጥፋ ሳላችንን የሚስል ያስብላል ሁኔታው!

ጉዟችን ቀጥሏል። በሩን ታከው ሸብረክ ብለው የቆሙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዶርም ሲገቡ በሚያዩት ፊልም ምርጫ ተጣልተዋል። “ጌም ኦፍ ትሮንስ’ን ሳንጨርስ ‘ኢምፓየር’ ብሎ ፊልም አይታሰብም፤” ይላል አንደኛው። “ምነው አንተ ከእሱ ፊልም ጋር እንዲህ ችክ አልክ? ዘውዱን አንተም ፈለግከው እንዴ?” ሌላኛው ያበሽቀዋል። “የት ነው የምትማሩት?”  አንድ በዕድሜ ጠና ያለ ተሳፋሪ ጠየቃቸው። ክርክራቸውን አቁመው፣ “አምስት ኪሎ” አሉት እኩል። “ታዲያ ምን ሰዓት ተርፏችሁ ነው ከፊልምም ተከታታይ ፊልም ስታዩ የምትውሉት?” ሲላቸው አንደኛው ሽቅብ አንጓጠጠው። “ዲኑም አልጠየቀን እንኳን አንተ፤” ብሎ ደግሞ የወዲያኛው ቡጢ ጨብጦ ‘ምን ታመጣለህ አስተያየት’ አየው። “ስምንተኛው ሺሕ ብለህ ማለፍ ነው ልጄ። ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ ይሆናሉ ይላል ቃሉ፤” እያሉ ሊቀጥሉ ሲሉ አዛውንቱ፣ “እርስዎን የጠየቀዎት የለም፤” ብሎ የታዳጊዎቹ ታላቅ የአዛውንቱ ታናሽ ተራውን ክው አስባለን።

ይኼን የሚያስተውል ያ አብሮኝ የሚወዛወዝ ተሳፋሪ፣ “ተዋረዳዊ አሠራር ነው። ምንም ማድረግ ስለማይቻል መቻል ነው፤” ሲለኝ በጎን ወይዘሮዋ፣ “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ ማለትስ አሁን ነው። ‘ከእጅ አይሻል ዶማ’ አለ ያገሬ ሰው፤” ስትል ሰማን። “እኔ ምለው” ጎልማሳው ነገር ለማብረድና የአዛውንቱን የተሸማቀቀ ገጽታ ለማፍካት አስቦ ወሬ ቀየረ። “… ዓለም እንዲህ በተከታታይ ፊልም፣ በተከታታይ የሽብር ጥቃት እኩል ስትታመስ መንግሥታት በቃ ከዲስኩር የዘለለ መፍትሔ አጡ ማለት ነው? እ አባት?” ብሎ ሲጠይቃቸው፣ አዛውንቱ በእርጋታ የዕድሜና የሐሳብ ጣራቸውን በተከታታይ ሳሎች አስተንፍሰው፣ “መንግሥታትም እኮ ቀረፃ ላይ ናቸው ልጄ፡፡ ሙሉው ፊልም አልቆ ብንወቃቀስ አይሻልም?” ብለው አሳቁን። ተከታታይ ሳቅና ተከታታይ እንባ እኩል ሲገናኙ ሕይወት ቅኝቱ በተዛነፈ ዜማ የታጀበች የጀማሪዎች ፊልም ትመስል ነበር!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል።  “ኋለኛው ወደፊት ፊተኛው ወደኋላ’ ሆነ እኮ ነገረ ዓለሙ እናንተ፤” ለግላጋዋ ወጣት በለበጣ ሳቅ ታጅባ ነገር ታሸሙራለች። “እንደሌስተር ሲቲና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማለትሽ እንዳይሆን?” ይላታል ዘይታም ከንፈሩን በምላሱ እያበሰ አንዱ። “አይ እኛ ካልጠፋ ማነፃፀሪያ ካልጠፋ ማያስተያያ ምሳሌያችን ሁሉ ኳስ ሆኖ ቀረ በቃ?!” ጎልማሳው ገባበት። “መለኪያ ሲጠፋ ሁሉ ተናጋሪ ሁሉ ነገር ተንታኝ ሲሆን የሁሉ የሆነውን ከማውራት ሌላ ታዲያ ምን ታሪክ እንፍጠር?” አለው ወጣቱ ተናዶበት። “ታሪክ መፍጠሩን ትታችሁ እስኪ መጀመርያ ታሪክ ድገሙ፤” አሉ አዛውንቱ ለመጀመርያ ጊዜ ቆጣ ብለው። “ኦኦ እሱ እንኳን አያዋጣም አባት። የድግምት ነገር ብዙ ያነጋግረናል። ያውም አብዮቷ ባልተጠናቀቀባት አገር?” ቆንጂት ተቃወመች።

“እና እንግዲያ ኋለኛው ወደፊት ፊተኛው ወደኋላ ከሆነ የዚህ ዓለም ነገር፣ ‘ፊተኛው ወደኋላ ኋለኛው ወደፊት’እንዲሆን ማድረግ ነዋ። ከመገለባበጥ በቀር ታዲያ ሌላ የሰው ልጅ  ዕጣ ፈንታው ምንድነው?” ብለው ሰውን ግራ አጋቡት። “ደገሙት ልበል አባባሉን?” ብትል ወጣቱዋ “ያው ነው። የቦታ ለውጥ ነው ያደረግኩት። መቀያየር መድገም፣ መድገም መቃየያር ነው ያልሽው አንቺው ነሽ። ስለዚህ ወደ ኋላ ከሆንሽ ወደፊት ነይ። ከፊት ከሆንሽ ደግሞ ለኋለኞቹ ዕድል ስጪ፤” ብለው በትዝብት ሊያዩዋት ሲጀምሩ፣ “ለመሆኑ ይኼ ባቡር ወደፊት ነው ወደኋላ የሚሄደው? ራሱና ጅራቱ ይምታታብኛል፤” በማለት ወይዘሮዋ ጠየቀች። “እሱ እንደ መንገዱ ነው፤” ሲላት አጠገቧ ቆሙ ፌስበቡክ የሚጎረጉር ወጣት፣ “እንግዲያስ እስኪ ራስ እንጂ ጅራት የማያደርገንን መንገድ እንፈልግ?” ብላ ከመቀመጫዋ ተነሳች። ሜክሲኮ ወራጆች ተጠራርገን ወረድን። አዛውንቱ፣ “እረኛና መንጋው ያልተግባቡበት ምን ዓይነት ዘመን ነው?” እያሉ ሲያጉተመትሙ ዝም ብሎ ከማዳመጥ ውጪ መልስ የሰጠ አልነበረም፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት