ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ
ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አምስተኛ ዓመት አስመልክቶ ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከማብራሪያው በኋላ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሾች ሰጥተዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለው ነአምን አሸናፊ ወ/ሮ ፍሬሕይወት የሰጡትን ማብራሪያና የተነሱትን ጥያቄዎች እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡ ግድቡ የደረሰበት ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ከጀመረ እንደቆየ የጠቆሙት ወ/ሮ ፍሬሕይወት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጽሕፈት ቤት የጋራ ዕቅድ አውጥቶ በዓሉን ለማክበር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
‹‹በተደጋጋሚ እንደምናነሳው የህዳሴ ግድብ ብዝኃነታችንን ያከበረና አንድነታችንን ያረጋገጠ ግድብ ነው፡፡ ልዩነታችን ጥንካሬያችን የሆነበት በተለይም ደግሞ የአይቻልም መንፈስ የተሰበረበትና በከፍተኛ ሁኔታ የሉዓላዊነታችን መገለጫ ሆኖ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ፣ ሁሉም ዓይነት የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ሕዝቦች በመንግሥትም፣ በግልም፣ በሠራተኛም ይህ ቀረ በማይባል መንገድ የአንድነት መንፈስ የተንፀባረቀበት ግድብ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት ይህ መንፈስ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ግድቡ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ዕድገትን፣ የአካባቢ አገሮች ትስስርንና መረጋጋትን በማረጋገጥ ረገድ አሁንም ትልቅ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለን፡፡ በዚሁ መሠረት መንግሥት በራሱ ብቻ ሳይሆን ግድቡ ከሚነካቸው የተፋሰሱ አገሮች ጋር በጋራ እየሠራ ነው፡፡ ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ መሠረታዊ የሆነውን መግባባትን ይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን በጋራ ውይይት እየፈታ ፍትሐዊ የሆነ ተጠቃሚነትን፣ የሕዝቦች የአንድነትና የጋራ መንፈስ ትብብርን በሚያረጋግጥ መንገድ መንግሥት ለመንግሥትም፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርም በተጠናከረ ሁኔታ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስካሁን ቀጥሏል፡፡ ስለዚህ ይኸው ሥራ አሁንም ቃል በተገባው መሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተፋሰሱን አገሮች መርሆዎችን መጀመርያ ይዞት የነበረውን ሐሳብ በማያፋልስበት መንገድ አጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል፤›› ሲሉም የግድቡን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት የያዘው አቅም በተቋቋመው የጋራ ምክር ቤትና በጽሕፈት ቤቱ አማካይነት የበለጠ እየተጠናከረ እንደሚሄድም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የሚነሱ ሐሳቦችንና ችግሮችን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጠቀሜታ አንፃር፣ ከመንግሥትና ከሕዝብ ግንኙነት አንፃር በማየት እየተቃለለ የሚሄድበት በውይይት የጋራ ሐሳብ እየተያዘ የሚኬድበት አሠራር አለ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
መንግሥት ከመርሆዎቹና ከአቋሞቹ ጋር የተያያዙ የሚወስዳቸው እንቅስቃሴዎች ለሕዝብ ግልጽ እያደረገ እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የግድቡን ግንባታና ያለበትን ደረጃ ማንኛውም ዜጋ በግልጽ የሚያውቅበትና የሚረዳበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መንግሥት እነዚህን ሥራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡ ከማብራሪያው በኋላ ለተነሱት የሚከተሉት ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጥያቄ፡- ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አይችልም የሚል መረጃ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር የፕሮጀክቱን መዘግየት መንግሥት እንዴት ያየዋል? ዘግይቶስ ከሆነ የመዘግየቱ ምክንያት ምንድነው?
ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ግድቡ ኃይል የማመንጨቱ ጉዳይ አሁንም እንደዚያው እንዳለ ነው፡፡ በተወሰነ መልኩ የሙከራ ሥርጭቱ ይጀመራል፡፡ ከዕቅዱ በጣም የተፋለሰ ነገር አለ የሚል እምነት መንግሥት የለውም፡፡ መንግሥት ባወጣው ዕቅድ መሠረት እየተጓዘ ነው፡፡ በእርግጥ በመሀል የተለያዩ ጉዳዮች አጋጥመው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህን ያህል ከዕቅዱ ውጪ የሆነ ሥራውን የሚያደናቅፍ ወይም ሥራውን የሚያስተጓጉል ነገር አለ የሚል እምነት መንግሥት የለውም፡፡ ስለዚህ ለሙከራ ያመነጫሉ የተባሉት ተርባይኖች አሁንም በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት ብዙም የጊዜ መፋለስ ሳያመጡ የሙከራ ሥርጭቱን ይጀምራሉ፡፡ ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡
ጥያቄ፡- ለህዳሴው ግድብ መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ገንዘብ ይሰበስባል፡፡ ነገር ግን የተገኘው የገንዘብ መጠንና ወጪ አይገለጽም፡፡ መንግሥት እስካሁን የሰበሰበው ገንዘብ ምን ያህል ነው?
ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- መንግሥት የሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተ በዚህ ዓመት ብቻ በህዳሴው ግድብ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ እንደተገለጸው፣ ቃል ከተገባው 63 በመቶ የሚሆነው ያህል ተሰብስቧል፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ቃል ከተገባው 11 ቢሊዮን ብር ውስጥ 8.1 ቢሊዮን የሚሆነው በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በአጠቃላይ ከነበረው መነሳሳትና ዕቅድ አንፃር ሲታይ ጥንካሬው ያመዝናል ማለት ይቻላል፡፡ ሕዝቡ በገንዘቡ ብቻ ሳይሆን በጉልበቱም፣ በዕውቀቱም ትብብር እያደረገ ነው፡፡
የግልጽነትን ጥያቄ በተመለከተ ጽሕፈት ቤቱ ወይም በግንባታው አካባቢ ያሉ ኃላፊዎች የሚሰጡት መግለጫ ምን ያህል ለሁሉም ኅብረተሰብ በተገቢው መንገድ ተደራሽ ይሆናል የሚለው ነገር በቀጣይ በስፋት ማየት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ግን በየጊዜው በየዓመቱ በየአደረጃጀቱና በየሚመለከታቸው አካላት ለምሳሌ ሠራተኛው፣ ባለሀብቱና ነዋሪው ኅብረተሰብ በአጠቃላይ የሚያደርገውን መዋጮ በተመለከተ አንድ ወጥ በሆነ አገር አቀፍ የዜና ማሠራጫ ብቻ ሳይሆን፣ በየአካባቢው ራሱ ሕዝቡም እንዲያውቀው የሚደረግበት አሠራርና አካሄድ አለ፡፡
እዚህ ላይ ወጣ ገባነት ሊኖር ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን እየዋለ ያለውን ገንዘብ በመንገር ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡ ገንዘብ ምን ላይ እየዋለ እንዳለ ተከታታይ የሆኑ ጉብኝቶችን በማዘጋጀት እንዲያየውም ጭምር በማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በመንግሥት ደረጃ ያለው የመረጃ ችግር ያን ያህል የሚያደናግር ነው የሚል እምነት የለንም፡፡ ግን መረጃዎቹን ከዚህ በላይ በስፋት ማሠራጨት፣ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ እንዲገባ የማድረግና ቀጣይነቱን የማስጠበቅ ሥራ በቀጣይ ሊታይ የሚችልበት ዕድል ሊኖር ይችላል የሚል እምነት አለን፡፡
ጥያቄ፡- ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ በግድቡ ግንባታ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?
ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ድርቁ በግድቡ አጠቃላይ አካሄድ ላይ መሠረታዊ ተፅዕኖ አለው ወይ የሚለውን ነገር በተመለከተ አሁን የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የሚታወቅ ሳይሆን የሚታይ ነገር የለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግድቡ በተያዘለት ዕቅድ በተቀመጠለት አቅጣጫ ነው እየተጓዘ ያለው፡፡ ወደኋላ የተጐተተ ወይም የቅደም ተከተል መዛነፍ በሚያመጣ መንገድ የሄደ ነገር የለም፡፡ መንግሥት ድርቁን በራሱ መንገድ እየመከተ ነው፡፡ ህዳሴ ግድብም በራሱ መንገድ እየተገነባ ነው፡፡
ጥያቄ፡- መንግሥት ከድርቁ አደጋ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ለጋሽ አገሮች የሚፈለገውንና የሚጠበቀውን ያህል ዕርዳታ እንዳልተገኘ ገልጾ ነበር፡፡ አሁንስ የዕርዳታው መጠን ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- የዕርዳታ መጠን ላይ ያን ያህል ትልቅ ልዩነት የለም፡፡ የተወሰነ ፈቅ ፈቅ እያለ የሚሄድ ነገር አለ፡፡ ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪዎች የሚመጣ ዕርዳታ የሚያኮራና ያን ያህል የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ነገር ግን ለውጦች አሉ፡፡ መጀመሪያ ከነበረበትና ዝግ ካለው ሁኔታ የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ከተለያዩ አካላት የሚመጣ ዕርዳታ አለ፡፡ ያም ሆኖ የመንግሥት አቅምና እምነት በማንኛውም አቅጣጫና በማንኛውም ሁኔታ ድርቁን የመቋቋም ሥራ ይሠራል፡፡
የውጭ ዕርዳታ ቢመጣ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ብቻ ሳይሆን ያግዛል፡፡ ብዙ ነገሮችን እንድንቋቋም ያደርገናል፡፡ በተረፈ ግን የመንግሥት እምነትና ተነሳሽነት እስከ መጨረሻው ድረስ በራስ የመቋቋም ባህሪን ጠብቆ መሄድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለውጦች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ የሚጠበቀውን ያህል ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ነገር ግን የተወሰነ እየሄደ ያለ ነገር እንዳለ ማየት ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሦስትዮሽ ድርድሩ አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ድርድሩን በተመለከተ ከላይ የገለጽኩትን መርህ ነው አሁንም ተከትሎ እየሄደ ያለው፡፡ መንግሥት ለመንግሥትና ሕዝብ ለሕዝብ ያለን ግንኙነት የሚያሻክርና የሚያበላሽ፣ መጀመሪያ የያዝነውን መርሆ የሚያፋልስ ነገር እስካሁን የለም፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎች የሚነገር ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ግን መደበኛ የሆነውንና መጀመሪያ ያስቀመጥነውን የግንኙነት መርሆ፣ ፍትሐዊ የሆነውን ተጠቃሚነት፣ በራስ መተማመን የመፍጠርን ነገር፣ የአካባቢው አገሮች የተረጋጉ ሆነው እንዲቀጥሉ የማድረግ መርህ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለመንግሥት ያለው ግንኙነትም ሆነ ሕዝብ ለሕዝብ ያለው ግንኙነት እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ መርህ መንግሥታችንና የአገራችን ሕዝቦች ካላቸው የሰላም ፍላጐትና ቀናኢነት ጋር ተያይዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት አለን፡፡
መንግሥታችን በመሠረቱ የሚሠራውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ የሚሠራው የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት እያመጣ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ በዚያ መንገድ እየተሠራ ስለሆነ፣ በድርድሩም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለየ መርሁን የሚያፋልስና የሚሄድበትን መንገድ የሚያዛባ ነገር የለም፡፡
ጥያቄ፡- በወልቃይት አካባቢ ሰሞኑን ግጭቶች እንዳሉ ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የመንግሥት የመጨረሻ የመፍትሔ ሐሳብ ምንድነው? በተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ በቅርቡ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት አስመልክቶ ያወጣው ሪፖርት አለ፡፡ መንግሥት ይህን ሪፖርት እንዴት ይመለከተዋል?
ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ምንም እንኳን ይህን መግለጫ የምሰጠው በመሠረቱ በህዳሴው ግድብ ላይ በማተኮር ቢሆንም ጥያቄ ለመመለስ ያህል ግን፣ መንግሥት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን አስመልክቶ ዕቅዶችን ይዞ እንቅስቃሴ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በየአካባቢው ያሉ ግጭቶች በኦሮሚያም ይሁን በአማራ ክልል አካባቢ ያሉ ግጭቶች መንግሥት በያዘው የመጀመሪያው ዕቅድ ነው እየተመራና እየተሠራ ያለው፡፡ የመልካም አስተዳደር ዝርዝር ጥያቄዎች ሥር ነቀል የሆነ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ ይዞ፣ ከየአካባቢው ሁኔታ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት እየሠራ ነው፡፡ መንግሥት ባሰበው መንገድ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር እየተወያየ እንደገና ተመልሶ ወደሚመለከታቸው አካላት እየሄደ፣ እንደገናም ወደ ሕዝብ እየሄደና እየተመላለሰ መሠራት ያለበት በጣም ብዙ ሥራ አለ፡፡
የመልካም አስተዳደር ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ አይደለም፡፡ በአንድ ጊዜ የሚጨረስ ሥራም አይደለም፡፡ በተለይም ደግሞ የአስተሳሰብ ቀረፃው ሥራ የአደረጃጀትና አሠራር የማስተካከል ሥራ በአንድ ወቅት ላይ ተጀምሮ በዚህ ወቅት ላይ የሚያልቅ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በመሠረቱ ግን ከሕዝብ ጋር ተከታታይ የሆነ ግንኙነትን በመፍጠር ይፈታል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ስለዚህ እዚህም እዚያም የተለያዩ ጥያቄዎችና የተለያዩ ግጭቶች አሉ፣ ይኖራሉ፡፡ ግጭቶቹ በተለያዩ ቦታዎች ስለታዩ መንግሥት በያዘው ዕቅድ የመፍታቱን ነገር ያጠናከረው ካልሆነ በስተቀር የተለየ ነገር የለም፡፡ ግጭቶቹ በሁለት መንገዶች ሊነሱ የሚችሉ ናቸው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በአንድ በኩል የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በፍጥነት ካለመመለስ ጋር ተያይዞ ሕዝቡ ያለውን ተቃውሞ በተለያየ መንገድ የሚገልጽበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የሕዝብ ትክክለኛ ፍላጐትና ጥያቄ በተለያየ መንገድ ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ ጥያቄውን ከጥያቄው ይዘት ውጪ በመጐተት ለማውጣት የሚደረግ ጥረት አለ፡፡ እነዚህን ሁለት ነገሮች ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ግጭቶቹ በተነሱበት አካባቢ ሁለቱም ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ የሕዝቡን ጥያቄ በጠየቀበት መንፈስና መንገድ ለይቶ የመመለስ ነገር መሠራት አለበት፡፡ ጥያቄውን በሌላ መንገድ አጣሞ ለመተርጐም ይሁን ለመውሰድ የሚደረግ ነገር ደግሞ ተነጥሎ በአግባቡና በርሱ በኩል መፈታት ያለበት ነገር ይኖራል፡፡
ስለዚህ በፀገዴም ሆነ በኦሮሚያ አካባቢ ያለው ነገር በዚህ መንገድ ነው የሚሄደው፡፡ ውይይቶቹና ሥራዎቹ ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ መንገድም ጊዜያዊ ማረጋጋት ብቻ ሳይሆን፣ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ የሚረጋገጠው መልካም አስተዳደር ላይ በምንሠራው ሥራ ነው ብለን ስለምናምን መንግሥትም ይህን እየሠራ ነው፡፡