በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን የገጠር መሠረተ ልማቶችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የሚያሳይና መረጃዎችን በዝርዝር የሚገልጽ አትላስ፣ ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ይፋ ሆነ፡፡
አትላሱ የተዘጋጀው በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አማካይነት ሲሆን፣ ወጪው የተሸፈነው ደግሞ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ አትላሱ በዋነኛነት የአገሪቱን የውኃ፣ የጤናና የትምህርት ሥርጭትና በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ተደራሽነት እንደሚያሳይ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
‹‹ብዙው የአገሪቱ ኅብረተሰብ የሚኖረው በገጠር ነው፡፡ ስለሆነም የገጠሩ ኅብረተሰብ አኗኗር ምን ይመስላል? በትክክል የጤና ተቋማትን በቅርበት ያገኛል ወይ? ትምህርቱስ ምን ያህል ነው? የሚጠጣውን ውኃስ የቱን ያህል ያገኘዋል? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ይመልሳል፤›› ሲሉ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የካርቶግራፊና ጂአይኤስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጉታ የአትላሱን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡
መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ብቻ ሳይሆን እነዚያን መሠረተ ልማቶች ሄዶ ለመጠቀም ወይም ለማግኘት የሚያስችል የመንገድ ዝርጋታስ አለ ወይ? የሚለውም አትላሱ ከያዛቸው መረጃዎች አንዱ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
አትላሱ በአገሪቱ የገጠር ክፍሎች ያሉትን መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በዝርዝር መረጃ በመያዙ፣ አንድ ወረዳ ላይ ምን ምን እንደጎደለ በቀላሉ ለመለየት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ የልማት አጋዥ ድርጅቶች ይህን ዝርዝር መረጃ በመጠቀም፣ እዚህ ቦታ ላይ ይህን ብሠራ የሚል ውሳኔ ለማሳለፍ ይረዳቸዋል፡፡ በተለይ የውሳኔ ሰጪ አካላት የገጠሩን ኅብረተሰብ ኑሮ ለማሻሻል በሚያስችል እዚያ ቦታ ላይ በደንብ መሥራት እንዲችሉ ያደርጋል፤›› በማለት አቶ ሲሳይ የአትላሱን ተጨማሪ ጠቀሜታ አመልክተዋል፡፡
ይህ አትላስ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀ በመሆኑ በዚህ ላይ ከሶማሌ፣ ከአፋርና ከአዲስ አበባ በስተቀር ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሩ ተካተዋል፡፡ ሶማሌ፣ አፋርና አዲስ አበባ ለምን እንዳልተካተቱ የተጠየቁት አቶ ሲሳይ፣ ‹‹በሶማሌ ክልል ላይ የመረጃ እጥረት በመኖሩ መረጃውን ማካተት አልቻልንም፡፡ የአፋር ክልልን በተመለከተ ግን መረጃው ተሠርቶ አልቋል፡፡ የሚቀረው ኅትመት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ይወጣል፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ ደግሞ አዲስ አበባ የራሱን አትላስ ያዘጋጀ ስለሆነ፣ አቅምንና ሀብትን ከብክነት ለማዳን ሲባል አልተሠራም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ሁሉም ወረዳዎች ላይ ለውጥ አለ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በጣም ከፍተኛ ለውጥ ሲኖር አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የተወሰነ ለውጥ አለ፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በሁሉም ወረዳዎች ላይ ለውጥ መኖሩን ነው፤›› ሲሉ አቶ ሲሳይ ይህ ሁለተኛው አትላስ ከመጀመሪያው አትላስ የሚለየውን ጉዳይ አስረድተዋል፡፡
በዚህ አትላስ ላይ ትኩረት የተሰጣቸው ሦስት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማለትም ትምህርት፣ ጤናና ውኃ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች እ.ኤ.አ. ከ2007 እስከ 2014 ድረስ ያለውን የለውጥ መጠን ለማሳየት እንደተሞከረም በወቅቱ ተነስቷል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 442/98 አማካይነት የተቋቋመ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ተቋሙ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የሥነ ሕዝብ ስታትስቲክስ መረጃዎች በቆጠራ፣ በናሙና ጥናቶችና ከአስተዳደራዊ መዛግብት በመሰብሰብ አጠናቅሮ፣ ተንትኖና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የሚሠራ ነው፡፡