Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ ልዩ የመንግሥት ቦንድ ሽያጭ ፈቃድ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የመንግሥት የፋይናንስ አቅም ደግሞ በቂ ስላልሆነ፣ ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ለመሸጥ በአዋጅ እንዲፈቀድለት ተጠየቀ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በኩል አልፎ ለፓርላማው ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የቀረበው ረቂቅ ሰነድ፣ የልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የሚውለው ገንዘብ በልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲከፈል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ይህንኑ የሚፈቅድ አዋጅ እንዲታወጅለት ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተከፈለ ካፒታሉ በአሁኑ ወቅት ሦስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በመንግሥት የታቀደው ወደ 7.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በአንድ ጊዜ ለማሟላት የመንግሥት የፋይናንስ አቅም የማይፈቅድ በመሆኑ፣ ካፒታሉን ለማሳደግ የሚያስችል ቦንድ ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል፡፡

መንግሥት የልማት ባንክን ካፒታል ወደ 7.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ከሚፈለገው 4.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 1.933 ቢሊዮን ብር ያህሉን ከተለያዩ ምንጮች አግኝቶ ለባንኩ ካፒታል እንዲውል አድርጓል፡፡ ቀሪውን 2.57 ቢሊዮን ብር በልዩ የመንግሥት ቦንድ (የዕዳ ሰነድ) በመሰብሰብ ለባንኩ ካፒታል እንዲያውል በአዋጅ እንዲፈቀድለት ነው የጠየቀው፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነዶች ከወጡበት ጊዜ አንስቶ ከአምስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በአሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት የሚወጣው ልዩ የመንግሥት ቦንድ (የዕዳ ሰነድ) ወለድ እንደማይከፈልባቸውም ተገልጿል፡፡

የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት የቦንድ ሽያጩ ከመፈቀዱ በፊት ሽያጩ የሚከናወነው አገር ውስጥ ይሁን ወይስ ከአገር ውጭ እንዲጣራላቸው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሒሳብ እንዲመረመርላቸው ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥመው የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ በመጠነኛ ወለድ ለፋይናንስ ተቋማት የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የሚገኝን ገንዘብ ግፋ ቢል በ365 ቀናት ውስጥ እንዲመልስ ይገደዳል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት የገንዘብ ፍላጐቱን ለማሟላት በተለምዶ የህዳሴ ግድብ ቦንድ ተብሎ የሚታወቀው (የመንግሥት ቦንድ) ሲሆን፣ በዚህ መንገድ የሚሰበሰብ ገንዘብ በአምስት ዓመት ውስጥ መከፈል አለበት፡፡ ለፓርላማው የቀረበው ልዩ የመንግሥት የዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ በ15 ዓመት ዕዳው እንዲከፈል የሚያደርግ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች