Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ፈርጀ ብዙው አጭበርባሪነት የዜጎችን ህልውና እየተፈታተነ ነው!

  በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው በኃላፊነት ግዴታቸውን የሚወጡ ያሉትን ያህል፣ የተከበረውን የንግድ ሥራ ከለላ በማድረግ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመበራከት ላይ ናቸው፡፡ ዜጎች በሕይወት ዘመናቸው ያፈሩትን ቅርስ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በተሽከርካሪና ማሽነሪዎች አቅርቦት፣ በምርቶችና በአገልግሎቶች አቅርቦት፣ በተለያዩ የሥራ ውሎችና በመሳሰሉት የዜጎችን አንጡራ ሀብት የሚዘርፉ ማፍያዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ውስጥ በሚዲያ በሚተላለፉ ማስታወቂያዎችና በአፈ ጮሌ አግባቢዎች ቅስቀሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት እየተዘረፈ ነው፡፡

  ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአጭበርባሪዎች ወርቅ ተብለው በቀረቡለት የባሌስትራ ብረቶች ምክንያት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መጭበርበሩ ይታወሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የንግድ ፈቃድ አውጥተው በሬዲዮና በቴሌቪዥን ማስታወቂያ እያስነገሩ ከዜጎች ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮችን የዘረፉም ታይተዋል፡፡ ዜጎች በሚዲያ በሚቀርቡ ማስታወቂያዎች በመተማመንና በሽያጭ ሠራተኞች ጉትጎታ አንጡራ ሀብታቸውን ለዘራፊዎች አስረክበው ባዶአቸውን ሲቀሩ፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅ አካል መኖር አለበት፡፡ በተለይ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም አማላይ የሆኑ ማስታወቂያዎች በሚዲያ እየተዥጎደጎዱ ሕዝቡ ለፍቶ ያገኘውን ገንዘብ እንዲከፍል ሲጠየቅ፣ እንደ ቀልድ እየተመለከተ ወይም ዓይቶ እንዳላየ ከሆነ የሕዝቡ መተማመኛ ምንድነው? ሕገወጦች ሲፈነጩ የሕዝብ ህልውና አደጋ ይጋረጥበታል፡፡

  ዜጎች ጥረው ግረው ያገኙትን ገንዘብ ለመኖሪያ ቤት፣ ለተሽከርካሪ፣ ለትምህርት፣ ለምርቶችና ለአገልግሎቶች አቅርቦት እንዲከፍሉ ሲደረጉ ከተዘጋጁ የውል ስምምነቶች በተጨማሪ አስገዳጅ የሆኑ ማዕቀፎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ አንድ የተሽከርካሪ አስመጪ ድርጅት በግማሽ ክፍያም ሆነ በሙሉ ከሰዎች ላይ ገንዘብ ከመሰብሰቡ በፊት፣ በቂ የሆነ ዋስትና ሊኖረው ይገባል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ ከሥራው ጋር ተመጣጣኝ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በስመ አስመጪነትና ሪል ስቴት ኩባንያነት በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ውንብድና በመንግሥት አስገዳጅ ሕግ ልጓም ካልተበጀለት፣ የዜጎች ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ በተለይ ዕድሜ ልካቸውን ለፍተው ያጠራቀሙትን ገንዘብ እየተዘረፉ ያሉ ዜጎች የሚታደጋቸው አንዳችም አሠራር ባለመኖሩ፣ ለእንግልትና ለሰቆቃ እየተዳረጉ ናቸው፡፡ ለአዕምሮ ሁከት የተዳረጉም አሉ፡፡

  ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ በተለያዩ ጊዜያት የተደራጁ ብዙዎቹ አክሲዮን ማኅበራት ውጤታማ መሆን ያልቻሉት፣ ጠንካራ ተቆጣጣሪ ተቋምና ማስፈጸሚያ ሕጎች ባለመኖራቸው ነው፡፡ የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገባቸውና በርካታ መመርያዎች እየወጡላቸው ባይመሩ ኖሮ፣ በአሁኑ ጊዜ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ቀርቶ ብዙዎቹ ብትንትናቸው ይወጣ ነበር፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ማንሳት የሚቻለው በተለያዩ ባንኮች ውስጥ ተከስተው የነበሩ ውዝግቦች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በሪል ስቴት፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉት ዘርፎች የተቋቋሙ በርካታ አክሲዮን ማኅበራት ከስመዋል፡፡ አሉ ከሚባሉትም ብዙዎቹ እንደሌሉ ይቆጠራሉ፡፡ መንግሥት ትኩረት በመስጠት ጠንካራ ቁጥጥር የሚያደርግባቸው በዕድገት ግስጋሴ ላይ ሲሆኑ፣ ተቆጣጣሪ የሌላቸው ደግሞ የአገርና የሕዝብ ሀብት በልተው ወድመዋል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ችግር በየአክሲዮን ማኅበራቱ ተደራጅተው የሚገቡ ደፋር አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡

  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚታዩት የአጭበርባሪነት ተግባራት የጠንካራ ተቆጣጣሪ አካልን አስፈላጊነት ያመላክታሉ፡፡ ለዓመታት በመተማመን በባህላዊ መንገድ ንግድ በሰላም ይካሄድባት የነበረች አገር በዚያው መንገድ መቀጠል የሌለባት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ክፍተቶችንና ድክመቶችን እያነፈነፉ ዜጎችን የሚያራቁቱ አደገኛ ማፍያዎች የንግድ ሥራውን እየወረሩት ናቸው፡፡ ንግድ በተፈጥሮው በብልኃትና ንቁ በሆነ አዕምሮ የሚከናወን ቢሆንም፣ አሁን ግን ከብልኃትና ከንቁነት በላይ አደገኛ የሆኑ ማጭበርበሮች እየተፈበረኩ ነው፡፡ ከሕዝብ ላይ ከተሰበሰበ ገንዘብ በሚከፈል በሚዲያ የሚተላለፉ አማላይ ማስታወቂያዎች በመተማመን ገንዘባቸው የሚዘረፍ ዜጎች ሲበዙ፣ መንግሥት የሚመለከተውን አካሉን ምን እየሠራህ ነው ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ዜጎች እየተዘረፉ ስለ የሕግ የበላይነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ዘራፊዎች በቡድን ሆነው ሕዝቡን ዘርፈው ከአገር ወጥተው ተይዘው ቢመለሱ እንኳ፣ የዜጎች ህልውና ግን ለአደጋ ይዳረጋል፡፡ ያለ የሌለ ቅርሱን ሰጥቶ ሙልጩን የወጣ ዜጋ የመጨረሻው መውደቂያው ልመና ብቻ ነው፡፡

  በተለያዩ ክልሎች ሳይቀር በመሰማራት የረባ የተከፈለ ካፒታል ሳይኖራቸው የንግድ ፈቃድ ብቻ በመያዛቸው፣ ከሕዝብ ላይ ሚሊዮኖችን የሚዘርፉ ማፍያዎች እየታዩ ነው፡፡ በአልባሌ የውል ስምምነቶች በአደባባይ ሕዝብን የሚዘርፉት እነዚህ አጭበርባሪዎች ሕግን በመናቅ ሕዝብ እያስለቀሱ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በግልጽ ወጥተው ዜጎችን እያሳሳቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲሰበስቡ ከበስተጀርባቸው የተማመኑበት ኃይል የላቸውም? በሕግ ሽፋን ሕገወጥ ተግባር ሲያከናውኑ ለምን ብሎ የሚጠይቅ አካል እንዴት ይጠፋል? በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተዟዟሩ ከዜጎች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲሰበስቡ የንግድ ፈቃዳቸውን፣ የካፒታል መጠናቸውን፣ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የሥራ ልምድና ተዓማኒነት፣ ለሚሰበስቡት ገንዘብ ዋስትና፣ ወዘተ. መጠየቅ የነበረበት ማን ነው? የጥቅም ተጋሪ በመሆን ከለላ የሚሰጡትስ እነማን ናቸው? ማጣራቱም ሆነ ምርመራው ሲከናወን ይህንን ሁሉ ማካተት አለበት፡፡ በሕዝብ ህልውና ላይ የተቃጣ ውንብድና ነውና፡፡

  አጭበርባሪዎችንና ዘራፊዎችን መከላከል የሚቻለው በሕግ ብቻ ነው፡፡ ከዜጎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ገንዘብ ሲሰበሰብ፣ በዚያው ልክ ሰብሳቢው ዋስትና ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት አስመጪም ይሁን አምራች፣ አገልግሎት ሰጪም ይሁን ሌላ የሕዝብ ገንዘብ ሲበስብ ከኢንሹራንስ ድርጅትም ሆነ ዋስትና ከሚሰጥ ተቋም ለወሰደው ገንዘብ የዋስትና ማረጋገጫ ማግኘት አለበት፡፡ ይህንን ተግባር የመቆጣጠር ኃላፊነት ደግሞ በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው የንግድ ሚኒስቴር ወይም ውክልና የሰጠው ኤጀንሲ ወይም ባለሥልጣን ነው፡፡ ዜጎች በጠራራ ፀሐይ ጥረው ግረው ያገኙትን ጥሪታቸውን የሚዘርፉ አካላትን ማስቆም የሚቻለው በዚህ ዓይነት ሕጋዊ አሠራር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ሆነ በቅርቡ ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ወገኖች መንግሥት እንዲታደጋቸው ይፈልጋሉ፡፡ መንግሥት ከካዝናው አውጥቶ የሚሰጠው ዳረጎት ባይኖር እንኳ፣ የተጎዱ ዜጎችን ለመታደግ የሚያስችሉ የመፍትሔ አማራጮች መታየት አለባቸው፡፡ አጥፊዎችን በሕግ ከመፋረድ በተጨማሪ የተበደሉት የሚካሱበትን ዘዴ ማፈላለግ የግድ ይላል፡፡ በአጭበርባሪዎች ምክንያት የዜጎች ህልውና ለአደጋ በመጋለጡ የሚመለከተው ሁሉ ልብ ይበል! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...

  ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ቃል ሲከበር ብቻ ነው!

  እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን...