Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ግራ የተጋቡ ዕቅዶችና አስደንጋጩ ድርቅ

   

  በጌታቸው አስፋው

  ኢኮኖሚክስ ፍላጎትና አቅርቦት የሚጣጣሙበትን መንገድ መፈለግ ሲሆን፣ የሸቀጥ ፍላጎት ምንጮች ምን እንደሆኑና ፍላጎቶቹን ለማርካት የምርት አቅርቦት በምን መልክ ተዋቅሮና ተደራጅቶ ከእያንዳንዱ የሸቀጥ ዓይነት ምን ያህል መመረት እንዳለበት ስለዛሬው ፍጆታና ምርት ብቻ ሳይሆን ስለወደፊቱም ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ የሚያጠና ጥበብ ነው፡፡ በአብዛኛው በቁሳዊ ሸቀጥ ምርት ላይ ያተኩራል፡፡ ኢኮኖሚክስ ማለት የገበያ ጥናት ነው ማለትም ይቻላል፡፡

  ልማት ምርት ለማምረት ሰዎች ጤናማ መሆን እንዳለባቸው፣ መማር እንዳለባቸው፣ የማኅበራዊ ኑሮ ዋስትና ማግኘት እንዳለባቸው፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘትም ሆነ እርስ በርስ ተገናኝተው ለመወያየትና ለመገበያየት መሠረተ ልማት መዘርጋት እንደሚያስፈልጋቸው የሚያጠና ጥበብ ሆኖ፣ በአብዛኛው በአገልግሎት ሸቀጥ ምርት ላይ ያተኩራል፡፡ ልማት የመንግሥት የጋራ ኢኮኖሚውን መምራት ችሎታ ጥናት ነው፡፡ በአማርታ ሴን የልማት ቋንቋ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ራሱን የሚችልበትን አቅምና ነፃነት መገንባት ማለት ነው፡፡

  ኢኮኖሚክስና ልማትን እንደማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች አድርገው ካላዩና አንዱና ሌላውን ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ አድርገው ካልተረዱ፣ አንዱ ያለሌላው ሊቆም እንደማይችል ካልተገነዘቡ ዘላቂ ዕድገት ሊመጣና ድህነት ሊወገድ አይችልም፡፡ ኢኮኖሚክስ በግል ስለማግኘት የሚወዳደሩበት፣ ልማት ደግሞ በጋራ ስለማደግ አብረው የሚሠሩበት ናቸው፡፡ ሁለቱም በጥምረት አገርን በፍጥነት ያበለፅጋሉ፡፡ ለሁለቱም እኩል ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

  የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኢኮኖሚክስና በልማት መካከል ቅንጅት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ለመጠቆም በ1987 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያን ትኩረት የሚሹ ሦስት የኢኮኖሚ ጥያቄዎች›› በሚል ርዕስ ምን እናምርት? ለማን እናምርት? እንዴት እናምርት የተሰኙ ሦስት የኢኮኖሚክስ መሠረታዊ ጥያቄዎችን የሚያስረዳ መጽሐፍ አሳትሜአለሁ፡፡

  በ2007 ዓ.ም. ‹‹ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን›› በሚል ርዕስ በኢኮኖሚያችን ውስጥ ቀሳዊ ምርትና አገልግሎት ምርት፣ ኢኮኖሚክስና ልማት፣ ፍላጎትና አቅርቦት፣ የሸማች ጣዕምና የአምራች ምርታማነት ባለመመጣጠናቸው ገቢ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት መፍጠኑ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አደጋ መሆኑን ገልጫለሁ፡፡

  ኢኮኖሚክስና ልማትን ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ ባለፉት ወራት በሪፖርተር ጋዜጣ በተለያዩ ርዕሶች አሥር ያህል ጽሑፎች ለንባብ በማቅረብ ኢኮኖሚያችን የገጠሙትን ችግሮች ጠቁሜአለሁ፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተረባርበው አገሪቱን ከአደጋ እንዲታደጓት ጥሪ አቅርቤአለሁ፡፡

  በርካታ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ባለሌላ ሙያዎች በተለይም በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ወጣቶች አበረታች ጽሑፎች በኢሜል አድራሻዬ ሲጽፉልኝ፣ የመንግሥት ባለሟል ባለሙያዎች ላቀረብኩላቸው ጥያቄዎች እንኳ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

  ለምሳሌ በ2003 ዓ.ም. በተደረገው የጥቅል አገር ውስጥ ምርት መለኪያ ዋጋ ክለሳ ምክንያት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርቱ በቅፅበት በወረቀት ላይ ሦስት እጥፍ መጨመር በነፍስ ወከፍ ገቢያችን ላይ፣ በድህነት መጠን ላይ፣ በገሃዱ የኑሮ ደረጃችን ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል? ለሚለው ጥያቂዬ መልስ ሊሰጡ አልፈለጉም፣ ወይም ምንም መልስ የላቸውም፡፡

  ባለሙያ ሲናገርና ሲጽፍ መንግሥት የመስማት፣ የማንበብና ባለሟሎቹን የመጠየቅ ግዴታ አለበት፡፡ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ኑሮን በእጁ ይዞ በዋዛ ፈዛዛ ሊያልፈው የሚገባው ጉዳይ የለም፡፡ በባለሙያ ያልተመከረ በመከራ ይመከራልና ይኸው ድርቁ ሊመክረው መጥቷል፡፡ ሽቅብ ጋላቢው ኢኮኖሚ ቁልቁል ሊጋልብ ነው፡፡ የባለሟሎቹን ለሆዴ ስል ልዋሸ በሬ ወለደ ወሬን ሰምቶና እንደ አስተማማኝ መረጃ ቆጥሮ ሕዝቡን አውላላ ሜዳ ላይ ሊተው አይገባውም፡፡

  የዕቅዶች መነሻ ፖሊሲዎች

  ሶሻሊዝም ከፈራረሰ በኋላ ካፒታሊዝም በሁለት ጎራ በመከፈል የአሜሪካና የእንግሊዝ ፈለግን የተከተሉ ወደ ሙሉ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያዘነበሉ አገሮች ኒዮ ሊበራሊስቶች ሲባሉ፣ ጃፓንና ቻይናን ጨምሮ አንዳንድ የእስያ አገሮች ከአፍሪካም ቦትስዋናና ሞሪሽየስ እንደ ምሳሌ የሚቆጠሩበት የልማታዊ መንግሥት መንገድ የግል ሀብት ይዞታንና የመንግሥት አመራርን ያዋሀደ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ይከተላሉ፡፡

  ልማታዊ መንግሥት ራዕዩን ለማስፈጸም ሥልታዊ፣ መዋቅራዊና የሙያ ቴክኒካዊ ብቃት ኖሮት በግልጽ የሚለካና በጊዜ ገደብ የታጠረ ብሔራዊ አጀንዳ ግብ ቀርፆ ወደ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በመመንዘር በሕዝብ አጋርነት መርቶ ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ ልማታዊ መንግሥት መኖር የሚል መርህ እንደምትከተል ብትገልጽም፣ የልማታዊ መንግሥት ሚና ነፃ ገበያውን የመምራት እንጂ ነፃ ገበያውን የመጥላት እንዳልሆነ በትክክል አልተረዳችም፡፡ ብሔራዊ አጀንዳና አጀንዳውን ለማስፈጸም ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ ቢኖርም፣ የብሔራዊ መንግሥቱ ሥልጣን ከክልሎች ተቆርሶ የተጠሰ በመሆኑ ባሻቸው ሰዓት እየሸራረፉ አቅመ ቢስነቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ታይቷል፡፡

  መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የንብረት ዋስትና (Property Right) ሕግ መኖርና ሕግ ማስከበር (Law Enforcemnet) አቅም መኖር አስፈላጊ ቢሆኑም፣ እነኚህ ሕጎች በክልሎች ሲጣሱ ብሔራዊ መንግሥት የዳር ተመልካች ሆኗል፡፡ የራሱን ብሔራዊ አጀንዳ ለማስፈጸም አቅም እንዳነሰውም በቅርቡ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የልማት አጀንዳው ውድቅ መደረጉ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  የሕዝብ አጋርነትን በተመለከተ የሰዎች እንቅስቃሴ በተስፋ (Expectation) የተሞላ ስለሆነ፣ ለኢኮኖሚክስ ከዛሬ መረጃ እኩል የነገ መረጃ ጠቃሚ ነው፡፡ ሕዝቦች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ወደፊት ለመኖርና ሠርተው ለማግኘት ተስፋ ሲኖራቸው ነው፡፡

  የድህነት ቅነሳና ብሔራዊ ልማት አጀንዳ አጋር የሚሆኑትም የማኅበራዊ ኑሮ ተስፋቸው የለመለመ ሲሆን ነው፡፡ አድልኦ፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሕዝብን ከመንግሥት ማራራቃቸው የአደባባይ ሚስጥር ስለሆነ፣ ለዛሬ ብቻ መኖር እየተመረጠ የነገ ተስፋ እየደበዘዘ ነው፡፡

  የሙያ ቴክኒካዊ ችሎታን በተመለከተ ለራሱ ብቻ የሚሠራ ባለሙያ ቢሰንፍ ራሱን ይበድላል፡፡ ለአገር የሚሠራ ባለሙያ ቢሰንፍ ሕግ ይበድላል፡፡ ለአገር የሚያቅድ ባለሙያ የዝንባሌ ትንታኔ (Trend Analysis) ሠርቶ የነገውን መመልከት የሚችል መሆን አለበት፡፡ የትናንቱንና የዛሬውን ብቻ የሚያይ ባለሙያ ዕቅዶቹ ህልምና ቅዠት ናቸው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅዶቹ በችግሮች የታጠሩ በመሆናቸው መንግሥት የባለሙያ ረሃብተኛ ነው፡፡

  የዕቅዶቹ ስያሜ ይዘት የግቦች አለካክና ንፅፅር

  ስምን መልዓክ ያወጣል ይባላል፡፡ ስያሜ ሁሉን ነገር እንደሚናገር ለመግለጽ፡፡ ትራንስፎርሜሽን የሚለው ቃል በዲክሽነሪ ትርጉሙ ከፍተኛ የቅርፅ ወይም የባህሪ ለውጥ ማድረግን፣ ለምሳሌ አየር ቅርፁንና ባህሪውን ሲለውጥ ወደ ጠጣር ነገርነት ይቀየራል፡፡

  ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ዕቅዶች ይህን የመሰለ የቅርፅና የባህሪ ወይም የምርት አደረጃጀት መዋቅራዊ ለውጥ ታመጣለች ተብሎ ስለማይታመን፣ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ በስያሜው ራሱ ግራ የተጋባ ነው፡፡ የስያሜው ግራ መጋባት ይዘቱን፣ ግቡንና ዓላማውንም ግራ አጋብቷል፡፡

  በግብና ዓላማ ሲገመገም የመጀመርያ ዕቅድ በሁለት አማራጮች (Two Senarios) ሲዘጋጅ፣ አንደኛው መሠረታዊ አማራጭ ግቦች በመጣኝ ቁጥሮች የተለኩ ሲሆኑ፣ የቀድሞን የተፋጠነና ዘላቂ ልማት ድህነትን ለማጥፋትና የምዕተ ዓመቱን ግቦች ማሳካት ዕቅድን (PASDEP) የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት መጣኝን ማስቀጠል ነው፡፡

  ሁለተኛውና ከፍተኛ አማራጭ ከ14 በመቶ የዕድገት መጣኝ ጋር በ2002 ዓ.ም. አንድ መቶ አርባ ቢሊዮን ብር የነበረውን የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ 2007 ዓ.ም. እጥፍ በማድረግ በመጠንም የተለካ ነበር፡፡            

  በመሠረታዊና በከፍተኛ የዕድገት አማራጮች ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ክፍለ ኢኮኖሚ (በመቶኛ)

   

  አፈጻጸም

  ዕቅድ

  አፈጻጸም

   

  ዘርፍ

   

  2002

  በመሠረታዊ አማራጭ አማካይ (2003 እስከ 2007)

  በከፍተኛ አማራጭ አማካይ (2003 እስከ 2007)

   

  አማካይ (2003 እስከ 2007)

  ግብርና

  7.6

  8.6

  14.9

  6.6

  ኢንዱስትሪ

  10.6

  20.0

  21.4

  20.2

  አገልግሎት

  13.0

  10.6

  12.8

  10.8

  ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት

  10.4

  11.2

  14.9

  10.1

  ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በመጠን

  141 ቢሊዮን ብር በ2002

   

  282 ቢሊዮን ብር 2007

  691 ቢሊዮን ብር በ2007

   

  የ1992 ዓ.ም. የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መለኪያ ዋጋ ወደ 2003 ዓ.ም. በመከለሱ ገና በ2003 ዓ.ም. የአገር ውስጥ ምርት አራት መቶ ሰባ ስድስት ቢሊዮን ብር በመድረስ፣ ከ2002 ዓ.ም. አንድ መቶ አርባ አንድ ቢሊዮን ብር ከሦስት እጥፍ በላይ ሆኖ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ስድስ መቶ ዘጠና አንድ ቢሊዮን ብር ደርሶ አምስት ጊዜ እጥፍ ሆኗል፡፡

  ሁለት የሚነፃፀሩ ነገሮች ተመሳሳይ ማነፃፀሪያ መለኪያ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የ2002 ዓ.ም. የዕቅዱ መነሻ አፈጻጸም መረጃ በ1992 ዓ.ም. መለኪያ ዋጋ ነው የተለካው፡፡ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ያሉት ዕቅዶችም በ1992 ዓ.ም. መለኪያ ዋጋ ነው ተለክተው የታቀዱት፡፡ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ያሉት አፈጻጸሞች ግን የተለኩት በተከለሰው በ2003 ዓ.ም. መለኪያ ዋጋ ነው፡፡ እነኚህን ቁጥሮች ከማነፃፀራችን በፊት የጋራ አካፋይ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

  የየዓመቱ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕቅዶችን በ2003 ዓ.ም. አጠቃላይ ዋጋ አመልካች (General Price Index) በማናር (Inflate)፣ ዘርፋዊ የምርት ዕቅዶቹን በ2003 ዓ.ም. ዘርፋዊ ዋጋ አመልካቾች (Sectoral Price Index) በማናር (Inflate) ከአፈጻጸሙ ጋር የጋራ አካፋይ እንዲኖቸው በማድረግ መለካት ይቻላል፡፡

  አለበዘሊያም የዓመቱን ጥልቅ የአገር ውስጥ ምርቶች አፈጻጸምን በ1992 ዓ.ም. አጠቃላይ ዋጋ አመልካች (General Price Index) በማርከስ (Deflate)፣ ዘርፋዊ የምርት አፈጻጸምን በ1992 ዓ.ም. ዘርፋዊ ዋጋ አመልካቾች (Sectoral Price Index)  በማርከስ (Deflate) አፈጻጸምን የዋጋ ደረጃዎችን ከዕቅዱ ጋር ተመሳሳይ በማድረግ መጣኞችን ማነፃፀር ይቻላል፡፡ ወይም ደግሞ ሥሌቱንና ትንታኔውን በሁለቱም መንገድ ሠርቶ በማሳየት ሁኔታውን ማብራራት ይቻላል፡፡ እነኚህ ሁኔታዎች ባልተደረጉበት የተሰላ ሥሌትና የተሰጠ ትንታኔ ማለት የዕድሜ ጉዳይን ከግምት ሳያስገቡ የአዋቂና የሕፃን ልጅን ቁመና ማነፃፀር እንደማለት ነው፡፡ ዕቅዱና አፈጻጸሙ በተለያዩ ዋጋዎች በመለካታቸው አፈጻጸሙ በዕቅዱ መሠረት የተከናወነ መሆኑን ልንመለከት የምንችልበት መነጽር የለም፡፡ እንደታቀደው ተከናውኗል ልንለው የምንችለው አንድም ነገር ስለሌለ፣ የሆነው ሁሉ እንዲሁ በሕዝብ ጥረትና በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ፡፡

  ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገና ከመጀመሩ በፊት አገሪቱ በድርቅ ተመታች፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ተፈጠረ፡፡ ዕቅዱ ድርቁንና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ምን ያህል ከግምት አስገብቷል? እንደ አንድ የእግር ኳስ ጨዋታ ቡድን ተጨዋቾች ቁጥር በሕግ ተደንግጎ በየዓመቱ ኑሯችንን ባልመሰለ ጥላ ኢኮኖሚ በወረቀት ላይ የልብ ወለድ አሥራ አንድ በመቶ ቁጥሮች ዕድገት በማቀድ፣ እኛ ሳናድግ የወረቀት ላይ ቁጥሩ አድጎ መካከለኛ ገቢ ውስጥ አስገብቶን ያለ ድጋፍ አንድ ስንዝር እንኳ ወደፊት መራመድ የማንችለውን ሰዎች፣ ከለጋሽ አገሮች ለልማት የምናገኘውን ድጋፍ ሊያስቀርብን ይችላል፡፡

  ሁሌም በወረቀት ላይ በአሥራ አንድ በመቶ የሚያድገው ኢኮኖሚ ወትሮም ልብ ወለድ ጥላ (Shadow) ኢኮኖሚ እንጂ፣ ኑሯችንን የማይወክል ስለሆነ እንደፈለገው ሊያድግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእኛ ኢኮኖሚ ጋር ለማመሳሰል የሚደረገው ጥረት በድርቁ ምክንያት ይበልጥ እየተጋለጠ ይመጣል፡፡

  የገንዝብ ጣኦትነት

  መሬት ያልረገጡ ልብ ወለድ ቁጥሮች ገጣጥሞ በሚመሳሰል ጥላ ኢኮኖሚ መካከለኛ ገቢ ውስጥ ለመግባት በሚደረገው ሩጫ፣ ገንዘብ እንደ ጣኦት የማምለክ ስሜት (Money Illusion) እየሰረፀብን ነው፡፡

  ቀድሞ በ15 ሳንቲም ዋጋ የምንበላውን ሽሮ ወጥ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ማደግ ምክንያት ኪሳችን በመሙላቱ 30 ብር ከፍለን መመገብ ችለናል፡፡ በገንዘብ ቁጥሩ መጠን መለወጥ እኛ የ30 ብር ጌታ የሆንን መስሎናል፡፡ ነገር ግን 30 ብር ማለት ሸቀጥ በመግዛት አቅሙ የቀድሞው የ15 ሳንቲም ሽሮ ወጥ ማለት ነው፡፡  

  ከ30 ብር የሽሮ ዋጋ ውስጥ 15 ሳንቲሙ የሽሮው የቀድሞ ዋጋ በእኛው ሠፈር የሚቆይ ሲሆን፣ የ29 ብር ከሰማንያ አምስት ሳንቲሙ ተዟዙሮ ቦሌ ሄዶ የቦሌን ሕንፃዎች ይገነባል፡፡ በእኛ ሠፈር ውስጥ የሚሽከረከረው ያው የቀድሞ የሽሮ ዋጋ 15 ሳንቲም ነው፡፡

  የ15 ሳንቲም ሹሯችንን በትንሹ ሁለት መቶ እጥፍ ዋጋ ጨምሮ በእኛው ሠፈር 30 ብር (በነቦሌ 150 ብር) መግባት አንጀታችንን በረሃብ የማሰር መስዕዋትነት ዋጋ ከፍለን ያስዋብናቸው እነቦሌ እየታዩ፣ በአንጀታችን መታሰር ሳይሆን በነቦሌ ውበት እየተለካን አደጉ እንባላለን፡፡

  ዳያስፖራው ከሩቅ አገር መጥቶ የትውልድ ሥፍራውን ሳይረግጥ በአዲስ አበባ እንኳ ከዳያስፖራነቱ በፊት በቤልቦተም ሱሪና በአፍሮ ስታይል ጎፈሬ የተንሸራሸረባትን ፒያሳ ሳያይ፣ በኑሮ ከውጭው ዓለም ጋር በሚነፃፀሩት ቦሌና ሸራተን ሰንብቶ ወደ መጣበት ሲመለስ በጠባብ ዕውቀት ጠባብ ወሬ ያወራል፡፡ ፈረንጁም እንደዚሁ ነው፡፡

  የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሃያ ዓመታት ምሳና እራት ሽሮ በሁለት መቶ እጥፍ ዋጋ አባዝተው የቆረጠሙት እነቦሌ ሁለት ሚሊዮን እጥፍ ቢዋቡስ ምን ይደንቃል?

  የአራት ኪሎና የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰብ አባላት የአኮኖሚ ዕቅድ አውራ በነበረው በጥንት ስሙ የጓዳ ሚኒስቴር በዛሬው ገንዝብ ሚኒስቴር ሕንፃ ዙሪያ ባሉት የላስቲክና ቆርቆሮ ቤቶች የ15 ሳንቲም ሽሮ ተሻምተው ሲበሉ ሳይ፣ ንጉሡ መጣፈጡን እየቀመሱልን የእንቁላል ፍርፍር፣ የዳቦ ቅቤና የማርማላት ቁርስ፣ ዶሮና ሥጋ ወጥ ምሳና እራት የምበላት ዘመን ትዝ ይለኛል፡፡

   ለሀብታሙ ሲዘንብ ለደሃውም ያካፋል፡፡ ሞኛሞኝነት ትምህርት ወይም ለሀብታሙ ሞልቶ ከሚተርፈው (Trikling Down) ሊቃርም ይችላል፡፡ ደሃን የመናቅና እኔ እጎዳለሁ አንተ አትጎዳም አመለካከት በኢትዮጵያ ነግሷል፡፡ የጥንት ባላበት እንኳ ለጪሰኛው እንጨት አስፈልጦ ወይም ጌሾ አስወቅጦ ከጉርሻም በላይ ስንቅም ይቋጥር ከነበረው ዘመን ወርደን፣ የነቦሌዎቹን ባለፀጎች ትርፍራፊ ‹ቡሌ› በሆቴል ቤት ተደራጅቶ በጉርሻ ተመዝኖ፣ ዋጋው በገንዘብ ተተምኖ ከነተጨማሪ እሴት ታክሱ (With Vat) ከፍለን የምንበላት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

  ‹ጄኔራል ድርቅ›

  በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች አርጀንቲና፣ ግሪክና ሌሎችም የአውሮፓና የአሜሪካ አገሮች ከፍተኛና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ከሀብታሟ አሜሪካ እስከ ደሃዋ ኢትዮጵያ የንግድ ሥራ መድራትና መቀዝቀዝ፣ የማሻቀብና የማቆልቆል ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረድ ፈረቃዊ ዙር ያጋጥማቸዋል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2008 አሜሪካ ከምርት ሞልቶ መትረፍረፍ በኋላ አቅርቦት ከፍላጎት ስለበለጠ ሸመታ ቀዝቅዞ ኢኮኖሚው ወደ ማቆልቆል አዘንብሎ ነበር፡፡ መንግሥት በወሰደው ተጨማሪ ገንዘብ አትሞ የሸማቾችን ገቢና የመግዛት አቅም ማሳደግ ፖሊሲ፣ ፍላጎት ጨምሮ አቅርቦትን ስላከለ ኢኮኖሚው ተቀልብሶ ወደ ማሻቀብ አቅጣጫ አመራ፡፡

  በኢትዮጵያ ባጋጠመው የድርቅ ንዝረት (Drought Shock) የንግድ ሥራ ዙሩ ወደ ማቆልቆል አቅጣጫ ማዘንበሉ በአንዳንድ ሁኔታዎች እየታየ ነው፡፡ ድርጅቶች የሸመታ ትዕዛዝ እያጡ ነው፡፡ የሸቀጦች ዋጋ እየቀነሰ ነው፡፡ ሠራተኞች ሥራ እየፈቱና ገቢም እየታጣ ነው፡፡ ምርትም እየቀነሰ ነው፡፡ ዙሩ ወደ ማቆልቆል አቅጣጫ ተቀይሮ ለስድስት ወራት ከቆየ ኢኮኖሚው ወደ መቀዛቀዝ (Recession) ደረጃ ይቀየራል፡፡ መቀዛቀዙ ከአንድ ዓመት በላይ ከቆየም ወደ ዝቅጠት (Depression) ደረጃ ይቀየራል፡፡

  ድርቁ የተደበቀውን ገሃድ የማውጣት ተልዕኮ ይዞ የመጣ ክስተት ነው፡፡ ልብ ወለዱ የወረቀት ላይ ጥላ ኢኮኖሚና ትክክለኛው ኑሯችንን በባለሙያ ትንታኔ ሳይሆን፣ በሌጣ ዓይናችን ዓይተን እንድንፈርድ ለምስክርነት የተላከ ነው፡፡

  ናፖሊዮን ከፍተኛ የጦር ኃይል በሩሲያ ምድር አፍስሶ ሩሲያን ለመግዛት ሞከረ፡፡ ሩሲያዎች መዋጋት ሳያስፈልጋቸው ክረምቱ እስከሚገባ ጠበቁ፡፡ የሩሲያው ‹ጄኔራል ክረምት› እንደገባ የክረምት ካፖርት ሳይዙ ወደ ሩሲያ የገቡትን የናፖሊዮን ወታደሮች እንደ እንጨት አደረቃቸው፡፡

  በዓለም ማኅበረሰብ መረባረብ ባይገታ ኖሮ በኢትዮጵያ የገባው ‹ጄኔራል ድርቅ› በኢኮኖሚክስ ጥበብ ያልተቃኘውን ኢኮኖሚ እንደ ናፖሊዮን ወታደሮች እንደ እንጨት ሊያደርቀው ይችል ነበር፡፡ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ጎን ለጎንም መንግሥትም ኢኮኖሚው ወደ ማሽቆልቆል እንዳይቀለበስ ተቃራኒ የፖሊሲ ዕርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ይህን የፖሊሲ ዕርምጃ አውቆ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሹም ሆነ፣ የፍጆታ ሸቀጥ ተጠቃሚ ሸማቹ ምን አንድምታ እንዳሉት መረዳት ያስፈልጋቸዋል፡፡

  አጣብቂኝ ውስጥ መግባት

  ኢኮኖሚው ከማቆልቆል አልፎ ወደ መቀዛቀዝ፣ ከመቀዛቀዝም አልፎ ወደ ዝቅጠት እንዳይገባ መንግሥት የመባባስ ሁኔታን ለመከላከል በወረቀት ላይ ያለው ጥላ ኢኮኖሚው ከኑሯችን ሁኔታ ጋር እንዲመሳሰል፣ አዲስ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ እንደሚነድፍ ይጠበቃል፡፡

  ሆኖም የማቆልቆሉ ምክንያት የአቅርቦት ማነስ እንጂ መብዛት ስላልሆነ፣ እንደ አሜሪካው አስፋፊ የጥሬ ገንዘብና የበጀት ፖሊሲ (Expansionary Monetary and Fiscal Policy) ሳይሆን የዋጋ ንረትን የሚከላከል አኮማታሪ የጥሬ ገንዘብና የበጀት ፖሊሲ (Contractionary Monetary and Fiscal Policy) መንደፍ ይገደዳል፡፡ ይኼንንም ቢሆን ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ለክቶ መመጠን ይኖርበታል፡፡ ምን ያህል አስፋፊ ወይም ምን ያህል አኮማታሪ በመጠን ከነምክንያቱ መለካት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

  ኢኮኖሚክስ መጠን በተለይም የተጨማሪውን ወይም የተቀናሹን ለውጥ መጠን የሚያጠና ጥበብ ነው፡፡ መጠንን ለማወቅ ደግሞ መለካት ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እስከዛሬ ድረስ ፍላጎትና አቅርቦትን እኩል የሚያደርግ የገቢ መጠን ተለክቶ ስለማይታወቅ፣ የፍላጎት መብዛት ወይም የአቅርቦት ማነስ የሚስተካከለው በከፍተኛ የዋጋ ውጣ ውረድ መዋዠቅ ነው፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ ኢኮኖሚውን በሚፈልገው መልክ መርቶታል ልንል የምንችልበት አጋጣሚ የለም፡፡ መንግሥትም ይህንን ድክመቱን አውቆ ተቀብሏል፡፡ ሕዝቡን ይቅርታም ጠይቋል፡፡

  በድርቁ ምክንያት አቅርቦት በከፍተኛ መጠን ስለቀነሰ የሸቀጦች ዋጋ እንዳይንር ፍላጎትን መግታት ስለሚያስፈልግ፣ ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያቀራርባቸው የገቢ መጠን አሁን ካለው ዝቅ ማለት ያለበት እንደሆነ ግን ግልጽ ነው፡፡

  መካከለኛ ገቢ ለመግባት ዓይኗን ጨፍና ለምትሮጠው ኢትዮጵያ ይህ ሊዋጥ ባይችልም የኢኮኖሚክስ ሕግ ስለሆነ መቀበል ግድ ይላታል፡፡ ያለው ዕድል ገቢን በምን ያህል መቀነስ ይገባል? የሚለውና የትኛውን የገቢ ቅነሳ ፖሊሲ የበጀት ቅነሳ ወይስ የገንዘብ አቅርቦት መጠንን መቀነስ ወይም ሁለቱንም መጠቀም ከሚሉት መምረጥ ብቻ ነው፡፡

  መንግሥት በጀትን መቀነስ የልማት ፕሮጀክቶቹን ማጠፍ ስለሚሆንበት ከሁለቱ አማራጮች የገንዘብ አቅርቦትን መቀነስ አማራጭ ሊከተል ይችላል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ሀብት ስለሚቀንስ ይህንን ለማካካስ የአገር ውስጥ ብድር መጠኑን ሊጨምር ቢያስብ የዋጋ ንረት ስለሚያስከትል፣ የእርሾ ጥሬ ገንዘብ (Reserve Money)፣ (High Powered Money) መጠን በራሱ ሒደት እንደሚቀንስ ይገመታል፡፡ የንግድ ባንኮች ብድር መጠን ከእርሾ ጥሬ ገንዘብ ቅነሳው መጠን በላይ ከቀነሰም የጥሬ ገንዘብ አርቢ (Money Multiplier) መጣኝም ስለሚቀንስ አጠቃላይ የገንዘብ አቅርቦት መጠን ይቀንሳል፡፡

  መንግሥት ፍላጎትን ከአቅርቦት ጋር ለማስተካከል ገቢን የሚያሳንስ ፖሊሲ ሲከተል፣ ሸማቹ ቀድሞ የቆጠበውን ከባንክ አውጥቶ ስለሚበላ ባንኮች በተቀማጭ ማነስ ምክንያት የቀድሞውን ያህል ማበደር ያቅታቸዋል፡፡ በንግድ ሥራ መቀዛቀዝ ምክንያት የምርት አቅርቦት ስለሚቀንስ የገንዘብ ዝውውር ፍጥነት (Money Velocity) ይቀንሳል፡፡

  ድርጅቶች በገንዘብ እጥረት የምርታቸውን መጠን ሊገድቡና ሠራተኛ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ በዚህም ኢኮኖሚው በመኮማተር ተባብሶ ከማቆልቆል ወደ መቀዛቀዝ፣ ከመቀዛቀዝ ወደ ዝቅጠት ሊያመራ ይችላል፡፡ የመባባስ ሁኔታው እንዳይከሰት የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ስለሆነ ጥንካሬውን የምንለካበት ወቅት መጥቷል፡፡

  የፖሊሲ ለውጥ አንድምታ

  የንግድ ሥራ ውጣ ውረዱንና የገበያውን መዋዠቅ ተቆጣጥረን ድርቁ ለጥቂት ጊዜ የሚያደርስብንን ጉዳት መቋቋም ከቻልን፣ የኢኮኖሚ አመለካከታችንን ቀይሮ በትክክለኛው መንገድ እንድንጓዝ ስለሚያስገድደን የሩቅ ጊዜ ጠቀሜታው ከቅርብ ጊዜ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡

  ኢኮኖሚውን በልማት ስድ ንባብ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚክስ ሥሌትም መረዳት ያስፈልግ እንደነበር ሳይረዳ የቆየው መንግሥት፣ ከእንግዲህ የልማታዊ መንግሥትን ሚና ለመጫወት ከፊት ግብ አግቢ ሳይሆን ከኋላ ግብ እንዳይገባ ተከላካይ ይሆናል፡፡ የመሪነት ሚናውን ለገበያው ያስረክባል፡፡

  መንግሥት በአስተዳደረው በልማት ኢኮኖሚ መሪነት ብዙ ሰዎች በእጃቸው ሳይሆን በአፋቸው ሠሩ፡፡ በአፋቸው ከበሩ፡፡ ገበያውን በሚመራው በኢኮኖሚክስ ብዙ ሰዎች የሚከብሩት በአፋቸው ሳይሆን በእጃቸው ሠርተው ይሆናል፡፡

  የኢኮኖሚክስ ውጤት በሆነው በማኮማተሪያ የገንዘብ ፖሊሲው ምክንያት የሰዎች ገቢ ሲቀንስ፣ የሸመታ ምርጫቸው ወደ ቁሳዊ ሸቀጦች ፍጆታ ያዘነብላል፡፡ በዚህም የአፍ ሥራ ገቢ የሚያገኙ ሰዎች ኪስ ይደርቃል፡፡ የእጅ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ኪስ ይረጥባል፡፡

  የድርቁ ንዝረት ለትምህርት የሚሆን ማስጠንቀቂያ ከመስጠት አልፎ፣ በኢኮኖሚያችን ውስጥ ቀውስ ላይፈጥር ይችላል፡፡ መንግሥት እንደ እስከዛሬ አመጣጡ ኢኮኖሚውን በኑሯችን መልክ ሳይሆን በልብ ወለዳዊ ቁጥሮች የጥላ ኢኮኖሚ አምሳያነት እመራለሁ ብሎ ቢንቀሳቀስ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ አደጋ ሁሌም እንዳንዣበበብን ይኖራል፡፡

  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን የደሃ ደሃ ከሚባሉ አገሮችም ያነሰ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህን አሳፋሪ ሁኔታ ከሥር መሠረቱ ለመለወጥ ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ግልጽ ነው፡፡ ጥያቄያችን እንዴት የሚለው ብቻ ነው፡፡

  በምርታማነት ያልተደገፈ የገቢ ዕድገት ሩጫና ከገቢ ዕድገቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሸማቹ የሸቀጥ ፍላጎት መዘመን፣ የኢምርታማነት ንዝረት ወይም የመዘመን ንዝረት (Non Productivity Shock or Modernization Shock) ፈጥረው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሥር የሰደዱ የቀውስ ምንጮች ስለሚሆኑ እንዴት ለሚለው ጥያቄያችን መልስ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]       ማግኘት ይቻላል፡፡