Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኑዌር ባህላዊ ምግቦች

የኑዌር ባህላዊ ምግቦች

ቀን:

ጋምቤላ ክልል ካለው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የተፈጥሮ ሀብትና የአየር ንብረት የተነሳ ሕዝቡ ከእርሻ ውጤቶች፣ ከዓሳ ምርት፣ ከማርና ከእንስሳት ውጤቶች ጋር ተያያዥነት ያለው ሰፊ የምግብ ባህል አለው፡፡

በክልሉ ከሚኖሩት ብሔረሰቦች አንዱ የሆነው ኑዌሮ የአመጋገብ ባህል አብዛኛው ከእርሻ ውጤቶች (በቆሎና ማሽላ) እንዲሁም ከእንስሳት ተዋጽኦ (ሥጋና ወተት) ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‹‹ጋምቤላ›› በተሰኘው መድበለ ባህል ላይ እንደተገለፀው፣ በብሔረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ማኅበራዊ ደረጃዎችን መሠረት አድርገው የሚዘጋጁ ምግቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ኛምኳር›› የሚባለው ባህላዊ ምግብ ትርጉሙ ‹‹የንጉሥ ምግብ›› ማለት ነው፡፡ በኑዌር ከላይ ከተጠቀሱት የምግብ ምንጮች በተጨማሪ ዓሳ ማስገር፣ አደንና ወንዝ ዳር የሚበቅሉ የጎመን ዝርያዎች ሌላ የምግብ ምንጮች ናቸው፡፡ ኑዌር ብሔረሰብ የሰፈረው ቆላማ ቦታ ላይ ስለሆነ የሕዝቡ አኗኗር ከአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር የተዛመደ ነው፡፡ በብሔረሰብ ያሉ ባህላዊ ምግቦች የሚከተሉት መሆናቸውን መድበሉ ይገልፀዋል፡፡

ኮንዳክ፡- ይህን ምግብ ለማዘጋጀት ‹‹ኮው›› (የእንጨት ሙቀጫ) እና ‹‹ለቅ›› (የእንጨት ዘነዘና) ተግባር ላይ ይውላሉ፡፡ አዘገጃጀቱም የሚጀምረው በቆሎ ውኃ ውስጥ ነክሮ በማውጣትና በመውቀጥ ሲሆን፣ ገለባው ከተለየ በኋላ ፀሐይ ላይ ተሰጥቶ እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም የደረቀው በቆሎ ከተወቀጠ በኋላ ሸካራው ከደቃቁ ይለያል፡፡ ይህን ሒደት ተከትሎም ውኃ በ‹‹ቡል›› (ድስት) ይጣዳል፤ ውኃው ሲፈላ መጀመርያ ሸካራው በቆሎ ተጨምሮ ይበስልና በተከታይነት ዱቄቱ ጋር ተቀላቅሎ በ‹‹ፒች›› (ማማሰያ) እየተማሰለ ይገነፋል፤ ከዚያም ሲበስል ወጥቶ በ‹‹ሊየር›› (ከቅል የተሠራ ማንኪያ) እየተዛቀ በ‹‹ቱኦክ›› (ከቅል በተዘጋጀ ማቅረቢያ) ይቀርባል፡፡ ይህ ምግብ ቀለል ያለ የዘወትር ምግብ ነው፡፡

ሌላው ምግብ ኮፕ ሲሆን፣ የዱቄት ዝግጅት ሒደቱ ከኮንዳክ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የተዘጋጀው የበቆሎ/ማሽላ ዱቄት በውኃ ተቦክቶና ተፈርፍሮ እንደ ቅንጨ ከሆነ በኋላ በባዶ ቡል ውስጥ ተጥዶ አነስተኛ ውኃ እየተጨመረ በ‹‹ፒች›› እየተማሰለ በእንፋሎት ይበስላል፡፡ ከእሳት ወርዶ በሊየር እየተዛቀ በቱኦክ ይቀርባል፡፡ ይህ ምግብ በካዬና ሙላክ (ከሥጋ ወይም ዓሳ) የሚበላ ሲሆን፣ ለእንግዳ ብቻ የሚዘጋጅ ምግብ ነው፡፡

ቶዎብ፡- የበቆሎ ዱቄት ሳይበስል በውኃ ደረቅ ብሎ ይቦካል፤ የለሰለሰ መሬት ላይ ወይም ማዳሪያ ላይ ተደርጎ በፀሐይ ይደርቃል፡፡ ለአደን ወይም ባሮ ዳር ለእርሻ ለሚሄድ ሰው እንደ ስንቅ ይያዛል፡፡ በኋላ ሲደርሱ እሳት ላይ ቱኦክ ይጣድና ውኃ ይፈላል፤ ቶዎብ በቀዝቃዛ ውኃ ተበጥብጦ ይጨመራል፤ በፒች እየተማሰለ በምድብ ከበሰለ በኋላ ዱቄት ጋር አብሮ እንዲበስልና እንዲያያዝ ይደረግና ወጥቶ በሊየር እየተዛቀ በቱኦክ ይቀርባል፡፡ ይህም የገንፎ ዓይነት ‹‹ኮን›› ይባላል፡፡ ይህን ምግብ ለአደን የሚሄዱ ክሪንግ በተሠራ ሙላክ፣ ባሮ ዳር ያሉት ደግሞ ከረች በተሠራ ሙላክ ይበሉታል፡፡

ዋጅ፡- ሲሠራ ዱቄት በቀዝቃዛ ውኃ ተቦክቶ በሩዝ መጠን ይፈረፈራል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ በቡል ውኃ ተጥዶ ከፈላ በኋላ በትንሽ በትንሹ እየተጨመረና በፒች እየተማሰለ ሲበስል እሳት ወርዶ በሊየር እየተዛቀ ‹‹ሊየት›› (ቅቤ) ተጨምሮበት ከ‹‹ቻክ›› (ወተት) ጋር ተቀላቅሎ በቱኦክ ይቀርባል፡፡ ይህ ምግብ በአብዛኛው ከብቶች እንደታለቡ ጠዋት ላይ ይበላል፡፡

ኛምኳር፡- የዝግጅት ሒደቱ የበቆሎ ግርድፍ በማጠብ የፈላ ውኃ ውስጥ ከዓሳ ቋንጣ ጋር ማብሰልና በደምብ አማስሎ ጨው መጨመርን ያካትታል፡፡ በመጨረሻም ምግቡ በዚህ ደረጃ በስሎ ከምድጃ ሲወርድ በሊየር እየተዛቀ ሊየት ተጨምሮበት ከቻክ ጋር ተቀላቅሎ በቱኦክ ይቀርባል፡፡ ይህ የምግብ ዓይነት በአብዛኛው ለባለሥልጣናት፣ ለኃላፊዎችና ለሙሽሮች የሚቀርብ ነው፡፡

የምግብ ማባያዎች

‹‹ሙላክ›› (ወጥ)፣ ‹‹ከረች›› (ዓሳ) ወይም ከሪንግ (ሥጋ) ይዘጋጃል፡፡ ከሪንግ የሚዘጋጀው ወጥ መጀመርያ ውኃ በ‹‹አለ›› (የሸክላ ድስት) ይጣድና ሥጋው ተቆራርጦ ይገባል፤ በደንብ ሲበስል ሊየት ‹‹ዋየ›› እና ጨው ተጨምሮበት ወርዶ በታአክ ይቀርባል፡፡

ከረች የሚዘጋጀው ወጥ፣ ዓሳው በደንብ ታጥቦ ከተዘጋጀ በኋላ በአለ ይጣዳል፤ ሲበስል አጥንቱ ተለቅሞ ይወጣል፤ ከዛ ሊየት፣ ‹‹ዋየ›› (ባህላዊ ጨው) እና ጨው ተጨምሮበት ወርዶ በታአክ ይቀርባል፡፡

‹‹ካዬ›› (የጎመን ወጥ) ሥጋ/ዓሳ በአለ ይጣዳል፤ ሲበስል ታጥቦ የተዘጋጀው ‹‹ማረ›› (ጎመን) ይገባል፤ ከዛ በኋላ ዋየ ይጨመርበታል ሲበስል ሊየት እና ጨው ተጨምሮ ይወርዳል፡፡ በመጨረሻም በታአክ ይቀርባል፡፡

የመጠጥ ዓይነቶች

ኮዋንምቦር (ቦርዴ) ከበቆሎ/ማሽላ ዱቄት እንዲሁም ከበቆሎ/ከማሽላ ብቅል ይዘጋጃል፡፡ ይህን መጠጥ ለማዘጋጀት በመጀመርያ የበቆሎው ገለባ እንዲለቅ በውኃ ነክሮ መፈተግና ከደረቀ በኋላ መፍጨትን የሚጠይቅ ሲሆን በደንብ ከደቀቀ በኋላ በ‹‹ቡል›› (ድስት) ይገነፋል፡፡ ከዚህ ሒደት በኋላ የበቆሎ ብቅል ተፈጭቶ ይገባበታል፡፡ ይህን ተከትሎም መጠኑ ታይቶ ውኃ ይጨመርበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ቦርዴው እንዲብላላ ለሁለት ቀን ይቆይና ለመጠጥነት ይውላል፡፡ ይህን ባህላዊ መጠጥ የማዘጋጀት አጠቃላይ ሒደቱ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ይወስዳል፡፡ በዚህ መልክ የሚዘጋጀው ይህ ባህላዊ መጠጥ እንግዳ ሲኖር፣ ለግብዣ፣ ለሠርግ፣ በበጋ ወቅት ደግሞ የብሔረሰቡ አባላት ወደ ባሮ ዳር በሚሄዱበት ሰዓት ይጠጣል፡፡ ኑዌሮች በክረምት ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ይህንኑ መጠጥ ያዘጋጃሉ፡፡ በመጨረሻም ቦርዴው በቡል ከቀረበ በኋላ ከቀጫጭን ‹‹ሮር›› በሚሠራ ‹‹ዱፈር›› (ውስጡ ክፍት የሆነ ቀሰም) እየተመጠጠ ይጠጣል፡፡

‹‹ኮዋንማቻር›› (አረቄ) ከበቆሎ/ከማሽላ ገለባና ከበቆሎ/ከማሽላ ብቅል የሚሠራ ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡ አሠራሩም የበቆሎ/ማሽላ ገለባ ፈጭሮ/ወቅጦ በማቡካትና በእንኩሮ መልክ በማብሰል እንዲሁም እንስራ ውስጥ ከብቅል ጋር በውኃ በመበጥበጥ የሚከናወን ሲሆን በመጨረሻም እንኩሮው ገብቶ በአርኮንግ (በእንስራ) ውስጥ ይበስልና በቀርቀሃ ቀፎ ኮደ (ኮዳ) ላይ እንዲጠራቀም ይደረጋል፡፡ መጠጡን ለማዘጋጀትም ከሰባት እስከ ስምንት ቀን ሲወስድ በሊየር (ትንንሽ ቅል) ይጠጣል፡፡

በኑዌር ብሔረሰብ የዘወትር ምግቦች ‹‹ኮንዳክ›› እና ‹‹ዋጅ›› ሲሆኑ የአመጋገብ ሥርዓቱ በጾታና በዕድሜ የተለየ ነው፡፡ እንደ ብሔረሰቡ ልማድ ሴቶች ለባሎቻቸው ምግብ የሚያቀርቡት ተንበርክከው ነው፡፡

እንደ መድበሉ አገላለጽ፣ በጋምቤላ ሕዝቦች ዘንድ የሚዘወተሩት በርካታ የምግብ ሥርዓቶችና የምግብ ዓይነቶች ትኩረት ተሰጥቷቸውና ተጠንተው ወደ ዘመናዊው የአመጋገብ ዘይቤ ቢቀየሩ፣ የአገራችንን ሕዝቦች የአመጋገብ ባህል ከመቀየር አልፈው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሊሰጣቸው የሚችሉ ናቸው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...